Sunday, October 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለትራንዚት መንገደኞች ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት በአዲሱ ስያሜው ‹‹ቱሪዝም ኢትዮጵያ›› ከዓለም ባንኩ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር አዲስ አበባን አቋርጠው ለሚጓዙ የትራንዚት መንገደኞች በቆይታቸው ወቅት ከተማዋንና አካባቢዋን መጎብኘትና ማወቅ የሚችሉባቸውን አሠራሮች የሚመራ አካሄድ መቅረፁን አስታወቀ፡፡

የመጀመርያው ረቂቅ የአሠራር መመርያ ተዘጋጅቶ ምክክር ተደርጎበታል፡፡ ስለዚሁ እንቅስቃሴም የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሌንሳ መኮንን ገልጸዋል፡፡ የተዘጋጀው ረቂቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትራንዚት ወቅት በአዲስ አበባ የሚቆዩ መንገደኞች ጉብኝት (Stop Over Tourism) ምንነትን በተመለከተ ውይይት ተደርጎበትና ተፅዕኖው ምን ሊሆን እንደሚችል በአግባቡ ከታየ በኋላ ወደ ሥራ እንደሚገባበት ወ/ሮ ሌንሳ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ረቂቁን ወደ መሬት ለማውረድ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ለየብቻ ስናደርግ የነበረውን ውይይት ሁሉም አካላት በአንድነት የተገኙበትን መድረክ በማዘጋጀት አንድ ዓይነት አስተሳሰብ አለን ወይ? ሁላችንም አንድ ደረጃ ላይ ነን ወይ? ትክክለኛ ዕይታ ይዘን ነው ወይ የምንሄደው? የሚለውን አንድ ላይ ሆነን ተነጋግረናል፤›› በማለት፣ አገልግሎቱ የሚጀመርበት የአሠራር ሒደት በምን መልኩ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው ውይይት በቱሪዝም መስክ የተሠማሩ ባለድርሻዎች በተገኙበት የትራንዚት ቱሪዝምን በማስመልከት በርካቶች ከየተሰማሩባቸው ዘርፎች አንፃር ሲገልጹት ተደምጠዋል፡፡ ራዕዩንም አስቀምጠዋል፡፡ ብሔራዊ ሙዚየም፣ የአዲስ አበባ አስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር፣ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የንግድ ትርዒት አዘጋጆች፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ የተፋሰስና አረንጓዴ ልማት ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች የዘርፍ ማኅበር፣ እንዲሁም የቱሪዝም ባለሙያዎች በውይይቱ ከተሳተፉ ተቋማት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ይህ ዓይነቱ የቱሪዝም መስክ በምን አግባብ መመራት እንዳለበት የየዘርፉ ተዋንያን ካሉበት ዘርፍ አንፃር ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡ ይህ የቱሪዝም መስክ የሥራ ዕድል ከመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪን ከማመንጨት፣ ባህልን ከማስተዋወቅ፣ የአዲስ አበባንና አካባቢዋን ገፅታ ከመቀየር፣ አዲስ አበባንና ኢትዮጵያን ከማስተዋወቅ፣ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ፣ የመንገደኛውን ምቾት ከመጠበቅ እንዲሁም ለተቀረው ዓለም ኢትዮጵያን ከማስተዋወቅ አኳያ በምን አግባብ መሥራት እንደሚገባ ውይይት አድርገዋል፡፡

 በትራንዚት አዲስ አበባ በሚቆዩ መንገዶች ዙሪያ ላለፉት ሦስት ወራት ጥናት መካሄዱ የተገለጸ ሲሆን፣ አብዛኞቹ መንገደኞችም መዳረሻዎችን የመጎብኘት ፍላጎት እንዳሳዩ ወ/ሮ ሌንሳ ገልጸዋል፡፡ ጎብኚዎች በትራንዚት ሲጓዙ በሚኖራቸው ቆይታ መሠረት፣ በሦስት የተከፈለ የጉብኝት መርሐ ግብር እንደተዘጋጀም አብራርተዋል፡፡ የመጀመርያው አዲስ አበባን ብቻ ለመጎብኘት የሚያስችል አጭር ቆይታ ላላቸው የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህም በአብዛኛው እስከ ሁለት ቀናት ቆይታ ለሚኖራቸው መንገደኞች የተሰናዳ ነው፡፡

ሁለተኛው እስከ አራት ቀናት ለሚቆዩ መንገደኞች የሚሆን ሲሆን፣ በዚሁ ጊዜም አዲስ አበባንና አካባቢዋን የመጎብኘት ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ ሦስተኛው ለረጅም ጊዜ ማለትም ከአምስት እስከ ስድስት ቀናት ለሚቆዩ መንገደኞች የተዘጋጀ ጉብኝት ነው፡፡ ለእነዚህ መንገደኞች የአገር ውስጥ በረራዎችን በመጠቀም ኢትዮጵያን በጨረፍታ  ማየት የሚችሉበት መርሐ ግብር ተመቻችቷል፡፡

‹‹Stop Over Tourism››ን እንደ አንድ የቱሪስት ምንጭነት በመያዝ የሚንቀሳቀስ እንደሌለ የገለጹት ወ/ሮ ሌንሳ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን እየተንቀሳቀሰ እንደቆየ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ምንም እንኳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተቀናጀ ቢንቀሳቀስም፣ የአንድ ተቋም ተነሳሽነት ብቻውን ውስን ስለሚሆን ሁላችንም ተቀናጅተን ብንሠራ ጥሩ ውጤት ማምጣት እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡

የታቀደው የትራንዚት መንገደኞች የቱሪዝም መርሐ ግብር ሲመጣ አብረውት ከሚነሱት መካከል፣ ሸገርን የማስዋብ ሥራ መጀመሩ፣ የታላቁ ቤተ መንግሥት ለሕዝብ ክፍት የማድረግ ጅማሮ እየተጠናቀቀ መሆኑ፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና መሆኗ፣ የቪዛ አሰጣጥ ፖሊሲ መቀየሩ፣ የአገር ውስጥ በረራዎች መስፋፋታቸው፣ መንገዶች መሻሻላቸው እንዲሁም አዲስ አበባ ላይ ሊተገበሩ የታቀዱ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ለታቀደው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ እንደ ችግር ከሚጠቀሱት መካከልም አዲስ አበባ እንደሌሎች የዓለም ከተሞች ታዋቂነት አለማትረፏ፣ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ለመጓጓዝ ምቹ ከተማ አለመሆኗ፣ የግልና የአካባቢ ንፅህና ጉድለት በሰፊው የሚታይባት መሆኗ፣ በጠቅላላውም በኢትዮጵያ ላይ የምዕራቡ ሕዝብ ያለው አሉታዊ ዕይታና ምቹነትም ደረጃም የጎደለው የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ በቱሪዝም ዘርፉ ከሚጠቀሱ ሥጋቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያስተናግዳቸው የትራንዚት መንገደኞች ቁጥር ከአሥር ሚሊዮን እንደሚበልጥም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች