Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአራቱ የዜማ ቅኝቶች

አራቱ የዜማ ቅኝቶች

ቀን:

‹‹እኛም አለን ሙዚቃ መንፈስ የሚያነቃ . . .›› እያለ የሀገረሰብ የሙዚቃ መሣርያዎችን ክራራችን፣ ማሲንቋችን፣ ዋሽንታችን፣ እምቢልታችን፣ ከበሮአችን ወዘተ እያለ የሚሰማ ዘመን ተሻጋሪ ዜማ ከብዙዎች አዕምሮ አይጠፋም፡፡ ከዚህ ሙዚቃው ቃና ጋር በተሰሚነት ስሙ የሚተሳሰረው ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ነው፡፡

በእነዚህ የሙዚቃ መሣሪያዎች አማካይነት ድምፃውያኑ፣ የመሣርያ ተጫዋቾቹ በተለያዩ የሙዚቃ ቅኝቶች ይጫወታሉ፣ ያቀነቅናሉ፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ የሙዚቃ ቅኝቶች ህልው እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህም መካከል በአምስት ድምፆች የሚደራጁትና ‹‹ፔንታቶኒክ እስኬል›› ተብለው የሚጠሩት ገዝፈው ይታያሉ፡፡ በበርካታ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባለሙያዎችና የባህልና የዘመናዊ ሙዚቀኞች ይበልታ የተሰጣቸው አራት ቅኝቶች ትዝታ፣ ባቲ፣ አምባሰልና አንቺ ሆዬ ናቸው፡፡

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በሰሜንና ደቡብ ወሎ ባደረገው የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ምዝገባ ኅትመቱ ላይ ከዳሰሳቸው ውስጥ አንዱ የሙዚቃ ቅኝቶች ናቸው፡፡ ቅኝቶቹ በርካታ የሙዚቃ ሰዎች እንደሚስማሙበት ዜማዎቹ በተደጋጋሚ ከሚያነሷቸው ቦታዎች፣ ብዙ ጊዜም በወሎ አካባቢ ከመቃኘታቸውና አገልግሎት ከመስጠታቸው የተነሳ መገኛቸው ወሎ እንደሆነ መረጃ ሰጪ የሙዚቃ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

እነዚህ ቅኝቶች በአምስት የድምፅ ምቶች ወይም ድምፆች የተዋቀሩ ከመሆናቸው የተነሳ ብዙ ጊዜ ተመሳሳይነት ያላቸውና ስያሜያቸውንም በተደጋጋሚ ተዘውትረው ከሚነሱ ቃላትና ከሚከናወኑባቸው ቦታዎች አንፃር ሊሆን እንደሚችል የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ መምህሩን ቴዎድሮስ አርጋውን ጠቅሶ ሰነዱ ያስረዳል፡፡ ቅኝቶቹ መሠረታዊ ልዩነታቸው ከአንዱ የድምፅ ምት ወደ ሌላው የድምፅ ምት ለመሸጋገር በሌላኛው የድምፅ ምት መካከል ያለው የጊዜ ልዩነት በሰከንድ ወይም በማይክሮ ሰከንድ መሆኑን በዚህ ከመገለጫ ባህርያቱ ጋር እንዲህ ተዘርዝሯል፡፡

አንቺ ሆዬ ቅኝት፡- ብዙ ጊዜ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ዜማዎች ላይ ማለትም በቅዳሴና በመዝሙሮች ላይ አገልግሎት ላይ የሚውል ከመሆኑ የተነሳ፣ ብዙ ጊዜ በዓለማዊ ዘፈኖች ላይ አይስተዋልም፡፡ በዚህ ቅኝት ከሚዜሙ ዜማዎች መካከል መዲናና ዘለሰኛ ተብለው የሚጠሩት መንፈሳዊ ይዘት ያላቸውና ዓለማዊም መንፈሳዊም የሆኑ ዜማዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አስቴር ሙሉ (ዶ/ር) ‹‹ተከታታይነትና ለውጥ በወሎ አዝማሪዎች የኑሮና የዘፈን ልምድ›› በተሰኘው ጥናታቸው ስለ አንቺ ሆዬ (ለእኔ)፣ የትመጣ በአፈ ታሪክ የሚነገረውን እንዲህ ገልጸውታል፡፡

‹‹አፈታሪኩ እንደሚለው አንቺ ሆዬ ዜማ የተፈጠረው በአንድ ወታደር አማካይነት ነው፡፡ በአንድ ወቅት በተደረገ ዘመቻ ከሚሴ ውስጥ ርቄ በምትባል ቦታ ወታደር ሰፍሮ ነበር፡፡ በዚህ ቦታ ከሰፈሩ ወታደሮች አንዱ ከአካባቢው ነዋሪ ከሆነች ሴት ጋር ፍቅር ይይዘዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ እያለ ጦሩ እንዲነሳ ይታዘዛል፡፡ ይህንን ጊዜ ወታደሩ በጣም ተጨንቆ ፍቅሩን ለመግለፅ ይሆነው ዘንድ መገን አንቺ ሆዬየሚለውን ዜማ አንጎራጎረላት፡፡ ከዚያ በኋላም ዜማውን ፍቅር የያዘው ሰው ሁሉ፣ የፍቅሩን መጠንና የፍቅረኛውን ውበት ለመግለፅ እየተቀባበለ የሚያንጎራጉረው ሆነ፡፡ በድግግሞሹ የተነሳ አንድ ቅኝት ለመሆን በቃ፡፡››

አንቺ ሆዬ ቅኝት ከሌሎች ቅኝቶች ለየት ያለ ፀባይ አለው ይላሉ መረጃ ሰጪዎች፤ በጀመረበት የማይጨርስ በጨረሰበት የማይጀምር ‹‹አወናባጅ›› ቅኝት ነው ይሉታል፡፡ ሌሎች ቅኝቶች ግን በጀመሩበት ድምፅ የሚጨርሱ፣ በጨረሱበት የሚጀምሩ ናቸው፡፡

በአንቺ ሆዬ ቅኝት ከሚባሉ ግጥሞች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

ወድጄሽ ብቆጣ ፍቅርሽ ቢጠናብኝ

ቀናተኛ ብለሽ ምነው የላክሽብኝ፤

በሰቆጣ መንገድ በመንበረ ጣይ

ሸጌ ጥላ ይዤ ልከተለሽ ወይ፤

ባቲ ቅኝት፡- ይህ ቅኝት ሁለት ዓይነት የዜማ ስልት ያሉት ሲሆን፣ ብዙ ጊዜ በወሎ የሚገኘውን ባቲን በማውሳት የሚዜም ከመሆኑ አንፃር ባቲ እንደተባለና ማኅበረሰቡ ፍቅርንና ጥላቻውን፣ እንዲሁም ደስታና ሐዘኑን የሚገልጹበት የቅኝት ዓይነት ነው፡፡

በባቴ() ቅኝት የሚባሉ ግጥሞችን የአስቴር ጥናት እንዲህ ይገልጸዋል፡፡

ኧረ ባቲ ባቲ ባቲ ገንደ ላዩ

ሃድራው የሚገባው ደራርበው ሲተኙ

የሰው ሁሉ ህመም ራስ ወገቡን ነው

የእኔ በሽታዬ ባቴ ነው ባቴን ነው፡፡

ትዝታ ቅኝት፡- በአምስት ድምፆች የሚዋቀር ዜማ ሲሆን፣ ብዙ ጊዜ ለስለስ ያሉ ዜማዎችን ለማዜም የሚጠቅምና ሁለት ዓይነት የአዚያዜም ሥልቶች ያሉት ቅኝት ነው፡፡ ይህን ዜማ ማኅበረሰቡ ብዙ ጊዜ ለሐዘን፣ ለትካዜና ብሶት መሰል የሕይወት ገጠመኞቹን ለመግለጽ የሚገለገልበት ቅኝት ነው፡፡

በትዝታ ቅኝት የሚባሉ ግጥሞች

ትዝታሽ ዘወትር ወደእኔ እየመጣ

እፎይ የምልበት ሕይወቴ ጊዜ አጣ፤

ተይኝ ትቼሻለሁ ረሳሁሽ እርሽኝ

እንደደረቀ ጠጅ እየጣልሽ አታንሽኚ፤

አምባሰል ቅኝት፡- ይህ የቅኝት ዓይነት በተደጋጋሚ የአምባሰልን ተራራማ ሥፍራዎች የሚያነሳና ብዙ ጊዜ ብሶትን፣ ፍቅርንና ቅሬታን መግለጫ ዜማዎች የሚዜሙበት ነው፡፡ በዚህ ቅኝት የሚጫወቱ ባለሙያዎችም ትልቅ የተፈጥሮ ተሰጥኦንና ብዙ ጊዜ የማዜም ልምድን የሚጠይቁ፣ እንዲሁም ብዙ ጊዜ ለማዜም ከፍተኛ የሆነ የድምፅ ብቃትን የሚጠይቁ እንደሆነና በማሲንቆ፣ በክራርና በዋሽንት ሊታጀቡም እንደሚችሉ መረጃ ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡

በአምባሰል ቅኝት የሚባሉ ግጥሞች

እኒህ አምባሰሎች አበላል ያውቃሉ

ከገብስ እንጀራ ላይ ሳማ አርጉ ይላሉ፤

እንዴትነሽ አምባሰል እንደምንነሽ ጢሳ

የተቋደስንብሽ ፍቅር ራት ምሳ፤

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባሳተመው መዝገቡ፣ ቅርሱ አሁን የሚገኝበት ሁኔታን አስመልክቶ እንደገለጸው፣ በአሁኑ ሰዓት አራቱ ቅኝቶች በማኅበረሰብ ዘንድ የሚከበሩ ቢሆንም ቅርሶቹ ብዙ ጊዜ ተመሳሳይነት ያላቸው ከመሆኑ የተነሳ ለአብዛኛው የአዳዲስ የሙዚቃ ዜማዎች ጨዋታ የሚያመቹ አይደሉም፡፡ በተጨማሪም ምንም እንኳን በአራቱ ቅኝቶች ዙሪያ በዘመናዊ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በጥናት የተደገፈና ምሉዕ የሆነ ትምህርት ባይሰጥም፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙ የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች ትምህርቱ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ያም ሆኖ ክዋኔያቸው በአካባቢው አሁንም ድረስ እንደሚተገበር አንዳንድ መረጃ ሰጪዎች ገልጸዋል ይላል፡፡

ቅርሱን በተገቢው መልኩ ባህላዊ ይዘቱንና ቅርጹን ጠብቆ መተግበር ቅርሱን ከትውልድ ወደ ትውልድ ማሸጋገርያ ዋነኛ መንገድ ነው የሚለው የባለሥልጣኑ ጥናት፣ ከዚያም ባለፈ ቅኝቶቹን በሰፊው በማጥናት ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ የአገርኛ ሙዚቃ ሥርዓተ ትምህርትን በመቅረፅ ለሕፃናት፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች በትምህርት መልክ ቢሰጥ፣ እንዲሁም በድምፅና በምስል በመቅረፅ ወደ ዲቪዲና ቪሲዲ ካሴቶች በመቀየር ለገበያ ማዋልና ዶክመንት ማድረግ ቅርሱን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር ለሚደረገው ጥረት ወሳኝ መሆኑን ያመለክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...