በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚገለጹባት አዲስ አበባ፣ በመሠረተ ልማቷ የተሻለ ዕድገት ብታሳይም፣ ዛሬም ለነዋሪዎቿ ምቹ ያልሆኑ በርካታ ችግሮች አሉባት፡፡
ከተማዋ በሚያስፈልጋት ልክ ፅዱና አረንጓዴ አለመሆኗ፣ የነዋሪው መተፋፈግ፣ የትራንስፖርት አለመሳለጥ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የነዋሪው ቁጥር እየጨመረ መሄድና ከክልል ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት የከተዋማ ችግሮች ናቸው፡፡
ጎዳና ተዳዳሪነት እየተበራከተ፣ ኮሌራና ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ላይ የጠፉ በሽታዎች ዳግም እየታዩ መምጣታቸውም ሌላው የከተማዋ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም የከተማ ነዋሪ በየቀኑ ንፁህ የመጠጥ ውኃ ማግኘት አለመቻል፣ የመኖሪያ ቤት እጥረትና ሥራ አጥነትም ከከተማዋ ቁልፍ ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነበር ቢባልም፣ ዛሬም ችግሮቹ አፍጠው ይታያሉ፡፡ አዲስ አበባ የተጋረጡባትን ውስብስብ ችግሮች ለመቅረፍና የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር በተለይ በመንገድ፣ በመኖሪያ ቤት፣ በጤና ጣቢያዎችና ክፍለ ከተሞች ግንባታ ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶች በመንግሥት ሲከናወኑ ከከረሙት ይገኙባቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ባለፈው አንድ ዓመት በሦስት ወር፣ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ከሆኑ ከአንድ ዓመት ወዲህ የአዲስ አበባን ገጽታ ይቀይራሉ፣ የሕዝቡን አኗኗር ይቀይራሉ፣ ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ ያስችላሉ የተባሉ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ተዋውቀዋል፡፡
የዕድሜዋን ያህል ያልለማችውን አዲስ አበባን ገጽታ ይቀይራሉ የተባሉት ፕሮጀክቶችም በከተማዋ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ይፋ ከሆኑ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡
ሥልጣን ከያዙ አንድ ዓመት ያስቆጠሩት ኢንጅነር ታከለ፣ ከተማዋን ያስውባሉ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ይቀርፋሉ የተባሉ ሐሳቦችን በማመንጨትም፣ ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለቱሪስት መስህብና መልካም ገጽታ እንዲኖራት ያስችላሉ የተባሉ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የግንባታ ስምምነቶችን ሰሞኑን ተፈራርመዋል፡፡
የአዲስ አበባን ውበት ለመቀየር ያስችላል፣ በከተማዋ በቀጣይ ለሚሠሩ ፕሮጀክቶች አርዓያ ይሆናል የተባለው የለገሀሩ ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይፋ ከሆነና የመሠረት ድንጋይ ከተጣለ ስምንት ወራት ካስቆጠረው የለገሀር ዘመናዊ የተቀናጀ የልማት ፕሮጀክት ቀጥሎ፤ ከተማዋን ይቀይራሉ የተባሉ የስድስት ትላልቅ ፕሮጀክቶች የግንባታ ስምምነትም ሰሞኑን ተፈርሟል፡፡
ከተማዋን ውብ፣ ፅዱና ለነዋሪዎቹ ምቹ ለማድረግ ከተረቀቁ ፕሮጀክቶች መካከል በሁለት ዓመታት ውስጥ ግንባታቸው ይጠናቀቃሉ የተባሉ ስድስት ፕሮጀክቶችን ግንባታ ከሚያከናውኑ ኩባንያዎች ጋር መፈራረማቸውን አስመልክተው ኢንጂነር ታከለ፣ እንደተናገሩት፣ ከ10.7 ቢሊዮን ብር በላይ ከተያዘላቸው ስድስት ፕሮጀክቶች አንዱ የዓደዋ 0.00 ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት ነው፡፡
የዓደዋ ማዕከል ግንባታ ባለመልማቱ ምክንያት ከሚድሮክ ተመላሽ በተደረገውና ፒያሳ እምብርት በሚገኘው አካባቢ የሚገነባ ሲሆን፣ ለግንባታውም 4.6 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን ኢንጂነሩ ተናግረዋል፡፡
በ1888 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ጣልያንን ድል በመምታት የተጎናፀፈችውን ማንነት ለማጠናከር፣ የዓደዋ ጀግኖችን ለመዘከርና ዓደዋን በሥነ ሕንፃ ከትቦ ከትውልድ ወደ ትውልድ ታሪኩን ለማስተላለፍ ያስችላል የተባለው ፕሮጀክት በ30,300 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ይሆናል፡፡
በቻይና ዢንጁ ኢንተርናሽናል ኢቲሲ ዓለም አቀፍ ኩባንያ የሚከናወነው የዓደዋ ማዕከል፣ በውስጡ ከሚይዛቸው አገልግሎቶች መካከል የዓደዋ ሙዚየም፣ ከ2,000 በላይ ሰው የማስተናገድ አቅም ያለው የዓደዋ አዳራሽ፣ እያንዳንዳቸው ከ400 በላይ ሰው የሚያስተናግዱ ሦስት አዳራሾች ይገኙበታል፡፡
የሲኒማ አዳራሽ፣ ቤተ መጻሕፍት፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የሕፃናት መጫወቻና ማቆያ ሥፍራ፣ የጌጣጌጥ መደብሮች፣ የቤተ ሥዕል ማዕከላት፣ ዘመናዊ የአውቶቡስና ታክሲ ማቆሚያ፣ ከ600 በላይ መኪናዎችን በአንዴ የሚይዝ የመኪና ማቆሚያ ተርሚናል፣ ካፌዎች እንዲሁም ለንባብ አገልግሎት የሚውሉ አረንጓዴ ሥፍራዎች በማዕከሉ የሚገነቡ ናቸው፡፡
በሁለት ዓመት ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት ይሆናል የተባለው ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ‹‹ሁሉ ከዚህ ይጀምራል›› የሚል የአዲስ አበባ ከተማ ዜሮ (0፡00) ኪሎ ሜትር ምልክት የሚያርፍበት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ሕዝብ የሚገለገልበት ቤተ መጻሕፍት በአዲስ አበባ መዘጋጃ ቤት የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ቤተ መጻሕፍት ለነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት ካቆመ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
በከተማዋ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለወጣቶች ማዘውተሪያ የሚሆኑ ጥቂት ቤተ መጻሕፍት ቢኖሩም፣ ከተማዋ ‹‹የእኔ ነው›› የምትለው፣ የተሟላና ደረጃውን የጠበቀ ቤተ መጻሕፍት የላትም፡፡
ይህንን ችግር ይቀርፋል፣ ወጣቱ በንባብ ራሱን እንዲያዳብር ያስችላል የተባለው የአዲስ አበባ ቤተ መጻሕፍት ግንባታም ሌላው ፕሮጀክት ነው፡፡
በአራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት አካባቢ የሚገነባውና በ19 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፈው ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት በቀን እስከ 20 ሺሕ ሰው ሊያስተናግድ እንደሚችልም ተነግሯል፡፡
አዲስ አበባ የምትገለጥበት ግን እርጅና የተጫጫነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤትን ሕንፃ ማደስም አዲስ አበባን የማስዋብ አንዱ አካል ነው፡፡ ከተገነባ ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ማዘጋጃ ቤቱና አርቲስት ፍቃዱ ተክለ ማርያም፣ አርቲስት ፋንቱ ማንዶዬንና ሌሎች አንጋፋ አርቲስቶችን ያፈራው የቴአትር አዳራሽ ሙሉ በሙሉ ዕድሳት የሚደረግለት ሲሆን፣ ውስጡን ሙሉ ለሙሉ የማሳመርና ቁሳቁስ የማሟላት ሥራው በስድስት ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ ነው፡፡
በአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለውና 1,000 መኪኖችን በአንዴ የሚያስተናግድ የመኪና ማቆሚያ መገንባትም አስተዳደሩ ለመተግበር ካቀዳቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ነው፡፡
የታላቁ ቤተ መንግሥት መኪና ማቆሚያ ፕሮጀክት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቤተ መንግሥትን ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ የተጀመረውን ሥራ የሚደግፍ፣ ቤተ መንግሥቱን ለሚጎበኙ እንግዶችና ሌሎች ተጠቃሚዎች የሚያገለግል ይሆናል፡፡
በአሥር ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያርፋል የተባለው የመኪና ማቆሚያ ባለ አራት ቤዝመንት እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡
የፑሽኪን አደባባይ ቄራ መንገድ ግንባታና የቦሌ መድኃኔዓለም እንግሊዝ ኤምባሲ መንገድ ግንባታም በቀጣዮቹ ሁለት ዓመት ከግማሽ ተጠናቀው ለአገልግሎት ይበቃሉ ተብሏል፡፡
የፑሽኪን አደባባይ ጎተራ መንገድ 2.3 ኪሎ ሜትር እንዲሁም የቦሌ መድኃኔዓለም እንግሊዝ ኤምባሲ መንገድ ግንባታ 3.133 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ይሆናል፡፡
የፕሮጀክቶቹ ግንባታና ከተገነቡ በኋላ የሚፈጥሩት የሥራ ዕድል፣ በከተማዋ የሚታየውን ሥራ አጥነት ለመቅረፍ የሚያግዝ ሲሆን፣ እንደ ለገሐሩ ፕሮጀክትም ለአዲስ አበባ ውበት የሚያጎናፅፍ ይሆናል፡፡
2.5 ቢሊዮን ብር ይፈጃል የተባለው የአዲስ አበባ ወንዞች የመናፈሻ ሥራ ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ ይፋ የተደረገውና ሌሎችም ሞዴል ግንባታዎች የአዲስ አበባን ገጽታ ይቀይራሉ ተብለው ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡
በ50 ቢሊዮን ብር የሚገነባው የለገሀር መንደር 25 ሺሕ ወጣቶች በግንባታው እንዲሳተፉ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፣ ግንባታውም ከአምስት እስከ ሰባት ዓመታት እንደሚፈጅ መገለጹ ይታወሳል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ችግሮች ለመፍታት ለጀመራቸው ፕሮጀክቶች ብሔራዊ ባንክ ውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እንደሚያደርግ፣ ከዚህ ባለፈም የልማት ሥራዎችን እንደሚደግፍ ማስታወቁን አስተዳደሩ በማኅበራዊ ገጹ አስፍሯል፡፡