Thursday, March 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሙስና ወንጀል ተከሰው በነበሩ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተሰጠ

በሙስና ወንጀል ተከሰው በነበሩ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተሰጠ

ቀን:

በእስር ላይ እያሉ ሕይወታቸው ባለፈው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የአገዳ ተከላና ፋብሪካ ግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በነበሩት አበበ ተስፋዬ (ኢንጂነር) የክስ መዝገብ፣ በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩ አምስት የኮርፖሬሽኑ የተለያዩ ክፍሎች ኃላፊ የነበሩ ግለሰቦች ላይ የእስራትና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ ተሰጠ፡፡

ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ)፣ 33፣ 407 (1ሀ እና ለ)፣ (3) እና የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 (1ሀ) እና (3) በመተላለፍ፣ ለየማነ ግርማይ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ኩባንያ ጥቅም ለማስገኘት፣ ለራሳቸውም ጥቅም ለማግኘትና በመንግሥት ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ፣ እንዲሁም የተሰጣቸውን ኃላፊነትና ሥልጣን ያላግባብ በመገልገል፣ ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ መስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ክስ መሥርቶባቸው የነበሩ ናቸው፡፡

ላለፉት 20 ወራት ሲከራከሩ ቆይተው ሐምሌ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት የቅጣት ውሳኔ ያስተላለፈባቸው ተከሳሾች፣ በኮርፖሬሽኑ የመስኖና ቤቶች ግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ኪሮስ ደስታ (ኢንጂነር)፣ የአገዳ ተክል ልማትና ፋብሪካ ፕሮጀክት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ደረጀ ጉተማ፣ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ዮሴፍ በጋሻው፣ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ጊዜያዊ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አታክልቲ ተስፋዬና የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ፈለቀ ታደሰ ናቸው፡፡

ተከሳሾች ከአርማታ፣ ከጠጠር፣ ከብረት፣ ከሲሚንቶና ከአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ሥራ ግዥና ብድር ጋር በተያያዘ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ የሰነድና የሰው ምስክሮች በማቅረቡ ተከራክረዋል፡፡ ተከሳሾቹም ድርጊቱን እንዳልፈጸሙ ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት የተከራከሩ ቢሆንም፣ የዓቃቤ ሕግን ክርክር ማሸነፍ ባለመቻላቸው እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ መከላከያ ምስክሮቻቸውንና የሰነድ ማስረጃዎቻቸውን አቅርበው ነበር፡፡ ነገር ግን የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችንና የሰነድ ማስረጃዎችን ማስተባበል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ ሁለቱም ወገኖች የቅጣት ማክበጃና የቅጣት ማቅለያ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር፣ ማስረጃ፣ የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ ከሕጉ ጋር በመመርመርና በማገናዘብ የቅጣት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም ኪሮስ ደስታ (ኢንጂነር) በአንድ ዓመት ከአምስት ወራት እስራትና በ6,000 ብር የገንዘብ ቅጣት፣ አቶ ደረጀ ጉተማ (በሌሉበት) በስድስት ዓመታት ከስድስት ወራት ፅኑ እስራትና 15,000 ብር የገንዘብ ቅጣት፣ አቶ ዮሴፍ በጋሻው በሁለት የክስ መዝገቦች የተቀጡትን በመደመር በአራት ዓመት ፅኑ እስራትና በ6,000 ብር የገንዘብ ቅጣት፣ አቶ አታክልቲ ተስፋዬ ሁለት ዓመት ከስድስት ወራትና በ3,000 ብር የገንዘብ ቅጣት፣ እንዲሁም አቶ ፈለቀ ታደሰ በሁለት የክስ መዝገቦች የተቀጡትን በመደመር በአምስት ዓመታት ፅኑ እስራትና በ10,500 ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...

የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ለወቅታዊው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 16...