Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናምክትል ከንቲባው የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ኃላፊን ማገዳቸው ተሰማ

ምክትል ከንቲባው የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ኃላፊን ማገዳቸው ተሰማ

ቀን:

የዕግዱ መንስዔ ከወጣቶች ፈንድ ብድር አሰጣጥ ጋር ተያይዟል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አሸብር ብርሃኑን ከሥራ ማገዳቸው ተሰማ፡፡ ዳይሬክተሩ የታገዱት ከወጣቶች የብድር ፈንድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ምክንያት እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ከሰሞኑ በሥራ ዕድል ፈጠራና በወጣቶች ፈንድ አማካይነት በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የሥራ መጀመርያ ብድር ለማግኘት፣ በየክፍለ ከተማውና በየወረዳው ተሠልፈው ታይተዋል፡፡ ይህም ሆኖ የብድር አሰጣጡ በተናጠልም ሆነ በቡድን ተደራጅተው የሚመጡትን እያስተናገደ ቢቆይም፣ ከሰሞኑ ግን በቡድን ጥያቄ ለሚያቀርቡ እንጂ በተናጠል ለሚቀርቡ ወጣቶች መሰጠት አልነበረበትም የሚል ክርክር ተነስቷል፡፡ ይህንን ተከትሎም ብድሩን ለወጣቶቹ የሚያቀርበው የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ኃላፊ እንዲታገዱ ምክንያት ሊሆን እንደቻለ፣ ክፍላተ ከተሞችና ወረዳዎችም በተናጠል የሚቀርቡ ወጣቶችን እንዳያስተናገዱ መመርያ እንደተላለፈላቸው የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ለሳምንታት የሥራ ዕድል ለመፍጠር መነሻ የሚሆነውን ፈንድ በብድር ለማግኘት፣ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን የሰነድ ማስረጃ፣ የብድር መድን ዋስትና ክፍያ፣ የሥራ ቦታ ኪራይና የመሳሰሉትን ወጪዎች በማውጣት ብሎም በአስተዳደሩ እንደ ግዴታ የተቀመጠውን የሥልጠና መርሐ ግብር አጠናቀው ብድሩ የሚለቀቅበትን አግባብ ሲጠባበቁ በተናጠል ጥያቄ ለሚያቀርቡ አይሰጥም መባሉ፣ ፈርጀ ብዙ ጉዳትና ኪሳራ እንዳስከተለባቸውና የሥራ ተነሳሽነት ሞራላቸውን እንደነካው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የወጣቶች ሥራ ፈጠራ ላይ ያተኮረው ፈንድ በከተማው አስተዳደር በመገናኛ ብዙኃን ሲተዋወቅ በመቆየቱ በርካቶች በዕድሉ ለመጠቀም ቢካሄዱም፣ ከላይ የተጠቀሰውን ጨምሮ በርካታ ውጣ ውረዶች መከሰታቸው ቀድሞውኑ ለተወሰኑ ተጠቃሚዎች ከተለቀቀ በኋላ በተናጠል የሚጠይቁት ላይ ሲደርስ ሆን ተብሎ እንዲቆም ተደርጓል በማለት ሪፖርተር ያነጋገራቸው ወጣቶች ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያለውን የወጣቶቹን ቅሬታና የብድርና ቁጠባ ተቋሙ ኃላፊ ስንብትን በማስመልከት ሪፖርተር ለማጣራት ባደረገው ጥረት የከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ወ/ሪት ፌቨን ተሾመ በወጣቶች የሥራ ፈጠራ ፈንድ ላይ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ግምገማዎች በርካታ ቅሬታዎች ከወጣቶች ሲቀርቡ እንደነበር ጠቁመው፣ የዳይሬክተሩ መታገድ በተመለከተ መረጃው እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ ሪፖርተር የአቶ አሸብርን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ሙከራ ባይሳካም፣ ለቀናት ያህል በሥራ ገበታቸው ላይ እንዳልተገኙ፣ የእሳቸውን ሥራም ምክትላቸው ደርበው በመሥራት ላይ እንሚገኙ ከጽሕፈት ቤታቸው ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ሌሎች ምንጮችም ዳይሬክተሩ ስለመታገዳቸው አረጋግጠዋል፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ‹‹ከሊፋ ፈንድ ፎር ኢንተርፕራይዝ ዴቨሎፕመንት›› የተሰኘው ተቋም ከጥቂት ቀናት በፊት የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዓለም ባንክ፣ የጃፓን መንግሥትና ሌሎችም ተቋማት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ አጋዥ ፈንድ በማቅረብ ለመንግሥት ድጋፍ አድርገዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ በመጪው ዓመት ለሦስት ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ዕድል እንድሚፈጥር፣ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥም 14 ሚሊዮን ወጣቶችን የሚያሳትፉ የሥራ ዕድሎች እንደሚፈጠሩ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ የአዲስ አበባ ወጣቶችም በቢሊዮን የሚቆጠር የብድር ድጋፍ እንደሚያገኙ ታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...