Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየደቡብ ክልል በውይይትና በምሁራን ተሳትፎ መዋቀሩ በጥናት መረጋገጡ ተገለጸ

  የደቡብ ክልል በውይይትና በምሁራን ተሳትፎ መዋቀሩ በጥናት መረጋገጡ ተገለጸ

  ቀን:

  የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚል መጠርያ አምስት የቀድሞ ክልሎችን በአንድ በማጠፍ የተመሠረተው የደቡብ ክልል ‹‹ኢሕአዴግ የጠፈጠፈው ነው›› እየተባለ የሚነገረው ስህተት እንደሆነ፣ የክልሉ የወቅቱ ባለሙያዎችና ምሁራን ተሳትፈው ይበጃል በማለት ያዋቀሩት እንደሆነ ባደረጉት ጥናት ማረጋገጣቸውን 20 አባላት ያለው የጥናት ቡድን አባላት ተናገሩ፡፡

  በደቡብ ክልል በተለይም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በስፋት እየተነሱ ያሉ የክልልነት ጥያቄዎችን ‹‹ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ›› ለመመለስ ያስችል ዘንድ ጥናት እንዲካሄድ በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራስያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) በ10ኛ ጉባዔ በተወሰነው መሠረት ጥናት ያደረጉት ተመራማሪዎቹ፣ የክልሉን አመሠራረት በተመለከተ የደረሱበት ግኝት እንዲያውም ‹‹አስደናቂ›› ሆኖ እንዳገኙት አስታውቀዋል፡፡

  ‹‹ደቡብ ክልል በኢሕአዴግ የተጠፈጠፈ ነው የሚባለው ልክ ነው ወይ?›› በሚል ጥያቄ መነሻነት ጉዳዩን ለመዳሰስ እንደተሞከረ ያስታወቁት አንደኛው የጥናት ቡድኑ አባልና የጥናቱ ውጤት አቅራቢ ፊሊሞን ሃደሮ (ዶ/ር)፣ ‹‹በጣም የሚያስገርሙ ውጤቶች ናቸው የተገኙት፡፡ ይኼ ክልል ሲመሠረት መንግሥት ሰብስቦ ያሰረው አይደለም፡፡ በዚሁ በክልሉ አሉ የሚባሉ በርካታ ምሁራን ተሰብስበው የተወያዩበት ነው፡፡ በተለይ በገዥው መንግሥት የሌሉና በተቃራኒው የቆሙ ሁሉ መሠረታዊ ጉዳዮችን በማንሳት ነበር ክልሉን  የመሠረቱት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

  አመሠራረቱም በክልሉ የሰው ኃይል እጥረት በመኖሩ ያለውን ውስን የሰው ኃይል የመጠቀም ዓላማን ያነገበና የክልሉን የተፈጥሮ ሀብት በጋራ መጠቀምን ያገናዘበ መሆኑን የጠቆሙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገር ልማት ጥናት የማስተርስ ፕሮግራም አስተባባሪ ፊሊሞን (ዶ/ር)፣ በክልሉ ያሉ ሕዝቦች ያላቸው ግንኙነት በሚገርም ሁኔታ የተሳሰረና ከሚታሰበው በላይ በመሆኑ ክልሉ ወደ አንድ ክልልነት ቢዋቀር ይችላል በሚል መነሻ የተመሠረተ ነው ብለዋል፡፡

  በክልሉ የሚኖሩ 56 ብሔር ብሔረሰቦች ላለፉት ዓመታት በጋራ በአንድ ክልል ሥር በመቆየታቸው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትፉፋቶችን ማግኘታቸውን የጠቆሙት ፊሊሞን (ዶ/ር)፣ አዲስ ደቡባዊ ማንነትን መፍጠር መጀመሩን፣ በርካታ የኢኮኖሚ መነቃቃትና የሀብትና የጉልበት እንቅስቃሴ እያደገ መምጣቱን፣ እንዲሁም ክልሉ በአገሪቱ ተደማጭና የውሳኔ ሰጪ አንዱ አካል እየሆነ መምጣቱ የእነዚህ ትሩፋቶች መገለጫ እንደሆኑ አውስተዋል፡፡

  ሆኖም በአሁኑ ወቅት የሚነሱ ጥያቄዎች በደቡባዊ ማንነት የብሔር ማንነታችን ተውጧል የሚል ስሜት በመምጣቱና የሕዝቦችን ማንነት ከክልሉ  አዲስ ማንነት ጋር አብሮ ለማስኬድ ያስቻለ አሠራር ባለመኖሩ፣ በአገር እንደሚታየው ሁሉ በክልሉ የነገሠው ኢፍትሐዊነት መታየቱና ይኼንን ለመፍታት አቅዶ የሚሠራ ሥርዓት ባለመፈጠሩ ምክንያት አሁን ለመፈራረስ ምክንያት ሆነዋል ብለዋል፡፡

  ይኼ ቢሆንም ግን በክልሉ ለተደረገው ጥናት የተጠየቁ መልስ ሰጪዎች እነዚህ ችግሮች እንዲቀረፉና ክልሉ ባለበት እንዲቀጥል እንደሚመርጡ የተናገሩት ፊሊሞን (ዶ/ር)፣ ምላሻቸው ይኼ ከተስተካከለ ለመከፋፈል አያበቃንም የሚል አንድምታ አለው ብለዋል፡፡

  ከ17,600 በላይ መላሾችን ያሳተፈውና ከሦስት እስከ አራት ሚሊዮን ብር ያህል ወጪ እንደተደረገበት የተገለጸው ይኼ ጥናት ጥናቱን ላስጠኑት ደኢሕዴንና የክልሉ መንግሥት መቅረቡን፣ ከመረጃ ሰብሳቢዎች የመጓጓዣና አበል ወጪዎች በስተቀር አጥኚዎች ያለ ክፍያ ያከናወኑት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

  አሁን ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው የክልልነት ስሜት ሰከን ተብሎ ሊታይ እንደሚገባና ከስሜት ይልቅ አማራጮችን በማየት ለውሳኔ መዘጋጀትን፣ ሕጋዊ ሆነውም ቢሆን የከፋ ውጤት ያስከተሉ ውሳኔዎች ስላሉም ታሪካዊ ስህተት እንዳይሠራ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባና በጥድፊያ የሚደረግ ውሳኔ ላለማስተላለፍና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲኖር መሥራት እንደሚያስፈልግ ጥናቱ አሳስቧል፡፡

  ጥናቱ ሰባት ወራት እንደፈጀና በአገር ደረጃ የመጀመርያ በመሆኑ ሁሉም ሊማርበትና አገራዊ ተሞክሮ ሊወሰድበት ይገባል ያሉት የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የጥናት ቡድኑ አባል ገብሬ ይንቲሶ (ፕሮፌሰር)፣ አስቀድሞ ጥናቱ በደኢሕዴንና በመንግሥት ይከናወን ሲባል ከአሁን ቀደም በሳይንሳዊ መንገድ ውሳኔ ልወስን ሲል ተደምጦ ከማያውቀው መንግሥት የመጣ ጥያቄ መሆኑ እንዳስደነቃቸው አስረድተዋል፡፡ በጥናቱ ሒደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ጣልቃ ገብነቶችና ውጤቱን የመቀበል ችግር ያጋጥማል የሚል ሥጋት እንደበራቸውም አክለዋል፡፡ ሆኖም ሒደቱም  ሆነ የውጤቱ አቀባበል የነበረውን ጥርጣሬ ያስወገደ ነበር ብለዋል፡፡

  ጥናቱ በአገሪቱ አሉታዊ አስተሳሰብ በነገሠበት ወቅት የተካሄደ በመሆኑ ፈተና አንደነበር ያስታወቁት ገብሬ (ፕሮፌሰር)፣ ይኼ አስተሳሰብ አስተውሎት ላይ ችግር ስለሚጋርጥና ለስህተት ስለሚዳርግ በአዎንታዊ አስተሳሰብ መቀየር እንዳለበት አሳስበው፣ ጥናቱም ይኼንን ይመክራል ብለዋል፡፡

  በቀዳሚነት ክልሉን አሁን ባለበት ቅርፅ ማስቀጠል፣ በሁለተኛነት ክልሉን በሁለት ወይም ከአምስት በማይበልጡ የተለያዩ ክልሎች መልሶ ማዋቀር፣ ይኼ ካልሆነም የክልልነት ጥያቄዎችን ላልተወሰነ ጊዜ ማቆየት የሚሉ ምክረ ሐሳቦችን ያቀረበው ጥናቱ፣ ይኼ ምክረ ሐሳብ የቀረበው ተጠያቂዎችን መሠረት አድርጎና በደረጃ በአብዛኛው የሰጡትን ምላሽ ይዞ ነው ብለዋል፡፡

  ‹‹የትኛውም ቢመረጥ ከአሁን በኋላ ሳይቀየሩ የማይሄዱ ጉዳዮች አሉ፤›› ብለዋል፡፡ እነዚህም የሕዝቡን የፍትሐዊነት ጥያቄዎች መመለስና በአንድ ማዕከል ብቻ የታጠረ ሳይሆን፣ በርካታ ማዕከላት (ከተሞች) ያሉት አደረጃጀት ማስፈለጉ ለወደፊት ሳይመለስ መቅረት የሌለበት ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡

  ሌላው የጥናቱ ተሳታፊና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር ካይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) የአማራጮቹን የተለያዩ ጉዳትና ጥቅሞች ከተናገሩ በኋላ፣ ውሳኔ የሚሰጥ ከሆነ ‹‹ከሕዝብ ጋር በጥልቀት ውይይት ተደርጎ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለው አደረጃጀት ሰፊውን ሕዝብ አላወያየም በሚል ስለሚተች፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

  የጥናቱን ተሳታፊዎች ወካይነት አስመልክቶ ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የአመራርና አስተዳደር ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በላይነህ (ዶ/ር)፣ ጥናቱ ከ17,600 በላይ መላሾችን ማካተቱ ብዙ የሚባል ተሳታፊዎችን እንዳሳተፈ እንደሚያመለክት በመግለጽ፣ በአገር ደረጃ እንኳን የሚደረጉ ጥናቶች ግፋ ቢል ከ10,000 ተሳታፊዎች በላይ አያካትቱም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

  ነገር ግን ወካይነት በቁጥር ብቻ ሳይሆን ማን ተሳተፈ? ትንታኔውስ እንዴት ተሠራ? የሚለውን ያገናዘበ መሆን አለበት ያሉት ብርሃኑ (ዶ/ር) በዕድሜ፣ በፆታ፣ በመኖርያ አካባቢ (ከተማና ገጠር)፣ በሥራና በመሳሰሉት መንገዶች መላሾችን ለማሳተፍ ተሞክሯል ብለዋል፡፡

  በሐዋሳና በሲዳማ ዞን መረጃዎች አለመሰብሰባቸውንና በሁለተኛ የመረጃ ምንጭ ለማሟላት መሞከሩን የገለጹት ካይረዲን (ዶ/ር)፣ የተለየና ተዓማኒ ያልሆነ መረጃ አለመኖሩን ለማረጋገጥ ከተለያዩ ምንጮችና በሌላ መንገድ ፈትሸናል ብለዋል፡፡ ከ94 በመቶ በላይ ዞኖችንና  ልዩ ወረዳዎችን ሸፍኖ የመላሾችን ምላሽ ከ94 በመቶ በላይ በሆነ ምጣኔ መሰብሰብ መቻሉን የገለጹት ካይረዲን (ዶ/ር)፣ የሲዳማና የሐዋሳ መረጃ አለመሰብሰብ የተጠቀሰው ከሥነ ምግባር አንፃር በማስፈለጉ እንጂ የመረጃውን ጉድለት ስለሚያመለክት አይደለም ብለዋል፡፡

  በሕገ መንግሥት የተሰጠን የብሔር፣ የብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ክልል የመመሥረት መብትን ማጥናት አስፈላጊነት በተመለከተ ሪፖርተር ላነሳው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የጥናቱ ዓላማ የመብትን አስፈላጊነትና አላስፈላጊነት ማጥናት ሳይሆን፣ አሁን እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች መነሻ ምን እንደሆነና እንዴት ምላሽ ሊያገኙ እንደሚችሉ የመፍትሔ አቅጣጫ ለማመልከት ነው፤›› በማለት፣ የጥናት ቡድኑ አባልና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ተሾመ ታፈሰ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

  አሁን ባለው አደረጃጀት የተገኙ ትሩፋቶች ቢኖሩም ተግዳሮቶችም ታይተዋል ያሉት የጥናት ቡድኑ አባል፣ የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ  ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) አሁን ከለውጡ ጋር  ተያይዘው እየተነሱ ያሉ የመልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች እየጎሉ ነው ብለዋል፡፡ ይኼንን ለመመለስ የተጠናው ጥናት ለደኢሕዴን እንደቀረበ አረጋግጠው፣ በቀጣይ ከሕዝብ ጋር በሚደረግ ውይይት ወደ ውሳኔ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...