Monday, May 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የነበረበት 3.1 ቢሊዮን ብር የግብር ዕዳ በድርድር ወደ 549 ሚሊዮን ብር ዝቅ ተደረገለት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ታግዶበት የነበረው የባንክ ሒሳብ ተለቀቀለት

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በተለያዩ ጊዜያት ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲከፍል፣ በቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን (ገቢዎች ሚኒስቴር) ሲጠየቅ የነበረውን ውዝፍ የንግድ ትርፍ ግብር 3.1 ቢሊዮን ብር ዕዳ፣ ከረጅም ጊዜ ድርድር በኋላ 549 ሚሊዮን ብር ለመክፈል ሰሞኑን መስማማቱ ታወቀ፡፡

ኮርፖሬሽኑ ላለፉት 13 ዓመታት እንዲከፍል ሲጠየቅ የነበረውን የንግድ ትርፍ ግብር ሳይከፍል የከረመ ቢሆንም፣ ግብር አስከፋዩ ገቢዎች ሚኒስቴር በቅርቡ የኮርፖሬሽኑን የባንክ ሒሳብ አግዶ ነበር፡፡

በባንኮች ያሉት ሒሳቦች የተዘጉበት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከረዥም የድርድር ሒደቶች በኋላ ለመክፈል ከተስማማበት 549 ሚሊዮን ብር ውስጥ፣ የመጀመርያውን 50 ሚሊዮን ብር በመክፈል ተጥሎበት የነበረውን የባንክ ዕግድ ማስነሳቱም ተረጋግጧል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ሁለቱም ተቋማት የመንግሥት ናቸው፡፡ በኮርፖሬሽኑም ሆነ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መካከል ክፍያውን በሚመለከት አሁንም መተማመን የለም ብለዋል፡፡ ነገር ግን ሚኒስቴሩ በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን ተጠቅሞ የኮርፖሬሽኑን ሒሳብ በማገዱ፣ ያለው አማራጭ በድርድር ስምምነት ላይ የተደረሰበትን የገንዘብ መጠን በረዥም ጊዜም ቢሆን መክፈል ስለሚቻል፣ የጀመርያውን ክፍያ 50 ሚሊዮን ብር በመክፈል የታገደውን ሒሳብ ማስለቀቁን ተናግረዋል፡፡

የገንዘቡ መጠን ከፍተኛ ሊሆን የቻለው፣ የቀድሞው የውኃ ሀብት ሚኒስቴር በራሱ የሚያሠራቸውን የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በመስጠት እንዲሠራ ማድረጉ፣ ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ በኮንትራት እንደሰጠ ተገልጾ፣ የንግድ ትርፍ ግብር እንዲከፍል በመጠየቁና ክርክር ሲያደርግ በመቆየቱ መሆኑን ኃላፊዎቹ አብራርተዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ለትርፍ ተብለው የሚሠሩ ሳይሆን የራስ ፕሮጀክቶች ስለነበሩ፣ በወቅቱ ለሦስተኛ ወገን ሲተላለፉ እንደ ትርፍ እንዳልተያዘ በመግለጽ ሲከራከሩ ቢከርሙም፣ ስምምነት ላይ ሳይደረስ መቅረቱንም አክለዋል፡፡

ገቢዎች ሚኒስቴር ባቀረበው መከራከሪያ ሐሳብ የመንግሥት ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት የሚባለው ራሱ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ባለቤት በሆነባቸው ፕሮጀክቶች ላይ እንጂ፣ ከሌላ ሚኒስቴር መሥርያ ቤትም ሆነ ሌላ ተቋም ጋር ውል ፈጽሞ የሚሠራቸው ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት  ፕሮጀክቶች ሊባሉ እንደማይችሉ ሲገልጽ መክረሙም ታውቋል፡፡ በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ ሲሠራቸው የነበሩ ፕሮጀክቶች ለትርፍ የሚሠሩ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን በማስታወቅ፣ ካገኘው ትርፍ ላይ ደግሞ የንግድ ትርፍ ግብር በሕጉ መሠረት ሊከፍል እንደሚገባ ሲከራከር መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡

በመሆኑም ከእነ ወለዱና ቅጣቱ 3.1 ቢሊዮን ብር እንዲከፈለው መጠየቁም ታውቋል፡፡ የሁለቱ ተቋማትን ክርክር ምክንያት በማድረግ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ከፍተኛ ኃላፊዎችና ሚኒስትሮች ሳይቀሩ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ ኮርፖሬሽኑ ይኼንን ያህል ዕዳ መሸከም እንደሌለበትና ሚኒስቴሩም ዕዳው መክፈል እንዳለበት መተማመን ላይ በመድረስ፣ ቅጣቱ ቀሪ ተደርጎለት ኮርፖሬሽኑ 549 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል የመጨረሻ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተረጋግጧል፡፡

የተስማሙበት ክፍያ በምን ያህል ጊዜ መጠናቀቅ እንዳለበት የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎች በቀጣይ ተነጋግረው የሚስማሙ ቢሆንም፣ የተዘጋውን የኮርፖሬሽኑን የባንክ ሒሳብ ለማስከፈት 50 ሚሊዮን ብር እንደከፈለና እንዳስከፈተም ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች