Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያ እግር ኳስና የግል ተጠቃሚዎች ተፅዕኖ

የኢትዮጵያ እግር ኳስና የግል ተጠቃሚዎች ተፅዕኖ

ቀን:

የውድድር ዓመቱ በተለይም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስቸጋሪና ፈታኝ ሆኖ ተጠናቋል፡፡ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እምነት በሚቀጥለው ዓመት ኢትዮጵያን በአህጉራዊ መድረክ የሚወክሉ ቡድኖች ተለይተው የታወቁ መሆኑ የውድድሩን መጠናቀቅ እንደ ማብሰሪያ ቢወስደውም፣ በሌላ በኩል በተለይ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጠናቋል ማለት የሚቻለው፣ ሁሉም ቡድኖች በውድድር ዓመቱ ማከናወን የሚጠበቅባቸውን 30 የጨዋታ ፕሮግራም ያላሟሉ በመሆናቸው በፌዴሬሽኑ እንደተጠናቀቀ ተደርጎ የሚነገረውን እንደማይቀበሉት አንድ ቀሪ ጨዋታ ያላቸውን የቅዱስ ጊዮርጊስንና የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለቦችን መነሻ በማድረግ ውድድሩ አልተጠናቀቀም የሚሉ አሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ በሚናገረው መልኩ ተጠናቋል ተብሎ የሚነገርለት የጨዋታ መርሐ ግብር እንዲያውም አንዳንዶቹ በተለይም የአዲስ አበባ ክለቦች በቀጣዩ ዓመት ሊከውኑት ስለሚገባው የውድድር ሥርዓት እንዴትና በምን አግባብ ሊሆን እንደሚገባ ከውሳኔ እንዲደርሱ ምክንያት እንደሆናቸው ጭምር እየተነገረ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ፣ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተለየ ሁኔታ የሚታይ ካልሆነ በስተቀር ምንም እንኳን አስቸጋሪና እልህ አስጨራሽ ሁኔታዎች ቢገጥሙትም የፌዴሬሽኑና የብዙዎቹ ክለቦች ይሁንታ ታክሎበት በየደረጃው የሚገኙ የሁሉም ሊጎች የጨዋታ ፕሮግራም በተያዘለት ጊዜ ሰሌዳ መሠረት ተጠናቋል ይላል፡፡ ቀጣዩ እንዴት ይሁን የሚለውን በተመለከተ ደግሞ ውሳኔው የፌዴሬሽኑ ጉዳይ እንዳልሆነ፣ ባለቤቶቹ ራሳቸው ክለቦች እንደመሆናቸው መጠን በጉዳዩ ተነጋግረው በሚወስኑት መሠረት ቢቀጥል በፌዴሬሽኑ ላይ አንዳችም ጉዳት እንደሌለው የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ይናገራሉ፡፡

የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ኃላፊነት ከተረከበ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የአቶ ኢሳያስ ጅራ አመራር ተቋሙን ማዘመን ያስችላል ያላቸውን የተለያዩ ጥናቶች አስጠንቻለሁ ቢልም፣ እስከ አሁን ባለው ግን የጥናቱ ውጤት እየታየ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ስፖርቱ በፖለቲካው መጠለፉ ለዘርፉም ሆነ ለተቋሙ አለመረጋጋት አሉታዊ አስተዋጽኦ ማድረጉ አልቀረም፡፡ ይህ ነገር በተለይም የአዲስ አበባ ክለቦች ወደ ክልል ወጥተው ከክልል ክለቦች ጋር እኩል ተፎካክረው ውጤት ማግኘት እንዳይችሉ ትልቅ መሰናክል እንደሆነባቸው ይነገራል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ተግዳሮቶች፣ ‹‹ተቸግረናል›› የሚሉት የአዲስ አበባ ክለቦች በሚቀጥለው ዓመት የራሳቸውን ሊግ መስርተው መወዳደር ይችሉ ዘንድ ነገሮችን ለማመቻቸት እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይሰማል፡፡ ፌዴሬሽኑ ምን ይላል? ኮሎኔል አወል አብዱራሂም የሚሉት ይኖራቸዋል፤ ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2011 የውድድር ዓመት መጠናቀቁን ይፋ አድርጎ በ2012 አገሪቱን በአህጉራዊ መድረክ የሚወክሉ ቡድኖችን ለካፍ አሳውቋል፡፡ በተለይ ፕሪሚየር ሊጉ ዕውን ተጠናቋል ማለት ይቻላል?

ኮሎኔል አወል፡- በልዩ ሁኔታ ታይቶ እንዲቆይ የተደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስና የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለቦች የ28ኛ ሳምንት ጨዋታ ካልሆነ ተጠናቋል ማለት ይቻላል፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው ሁለቱ በካፍ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና በካፍ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊዎች ተለይተው ታውቀዋል፡፡ ከሁሉም በፊት ሁሉም ሰው ማወቅ የሚገባው ቢኖር፣ የዘንድሮ የፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ ሌሎችም በየደረጃው የሚገኙ ውድድሮች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፈዴሬሽን የሚመራው ለዚህ ዓመት ብቻ እንደነበር የ2011 የውድድር ዓመት ከመጀመሩ ሁሉም በፊት ክለቦችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በመስከረም ወር ውይይት ተደርጎ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ፌዴሬሽኑና ክለቦች ከውድድር ጋር ተያይዞ ሊኖራቸው የሚገባው አጀንዳ ከ2011 በኋላ በፌዴሬሽኑ የሚመራ ሊግ ኮሚቴ የሚባል እንደማይኖር ነው፡፡ ይህም የሆነው ውድድሩ መቆም ስለሌለበትና ክለቦችም ተወካዮቻቸውን በደንብ ተመካክረው እንዲያዘጋጁ ለማድረግ ሲባል ነው፡፡ ሌላው ሊጉ የሚመራበት መነሻ ሐሳብ በፌዴሬሽኑ ተዘጋጅቶና ክለቦች ተወያይተውበት ባመኑበት ሊጋቸውን እንዲያስተዳድሩ ከስምምነት መደረሱ ሊወሰድ ይገባዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋሙ በስሩ የሚመራቸውን ክለቦች በትክክል አስተዳድሬያለሁ ብሎ ያምናል? ምክንያቱም የፕረሚየር ሊጉ ጉዳይ እንደተጠበቀ፣ የኢትዮጵያ ዋንጫ በአብዛኛው በፎርፌ የተከናወነ ከመሆኑ አንጻር ጠንካራ ትችቶች ይሰነዘራሉ፣ ይህ በአመራሩ እምነት ከማጣት የሚመነጭ አይመስልዎትም?

ኮሎኔል አወል፡- በግሌ ሊጉን የሚመራው ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደመሆኔ፣ በአገሪቱ ከመጣው ለውጥ ጋር ተያይዞ ከታዩት የፀጥታ ችግሮች በስተቀር ፌዴሬሽኑ ባሰበው ልክ  እቅዱን አሳክቷል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስና የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለቦች ቀሪ ጨዋታ በፍትሕ አካሉ ወደፊት የሚያየው ጉዳይ ነው፡፡ በተረፈ ግን ምክንያቱ አሁን ያለው አመራር ሥራውን ሲረከብ በተቋሙ የነበሩ ተገቢ ሙያተኞች አንድና ሁለት ሰዎች ካልሆኑ ከሊግ ኮሚቴ ጀምሮ የተሟላ ነገር አልነበረም፡፡ ችግሩ እንዳለ ሆኖ ነገሮችን በማቻቻል ውሳኔዎችን ስናሳልፍ የነበረው ሕግና ደንብን መሠረት በማድረግ የተሟላ ቃለ ጉባዔ በመያዝ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ተቋሙ የፍትሕ አካላትን ውሳኔ በጣልቃ ገብነት እንደሚሽር ሲነገር እንሰማለን፣ ውሳኔ ማስቀየር ቀርቶ ሙከራ እንኳ አልነበረም፡፡ በውድድር ዓመቱ አከራካሪ ጉዳይ የነበረው በሐዋሳና በፋሲል መካከል የተደረገው የሁለተኛ ዙር ጨዋታ የመሐል ዳኛው ለሐዋሳ ያጸደቀለት ግብ ፈርቼ እንጂ ጎሉ ትክክል አልነበረም ብሎ የተናገረበት አጋጣሚ ነው፡፡ እሱንም ቢሆን ውጤቱን ብናፀድቀው ችግር እንደሌለው ተማምነን ግን ደግሞ ደንቡን መሠረት በማድረግ ነው አመራሩ በዳኛው ላይ የእገዳ ውሳኔ ያሳለፈው፡፡ የክለብ አመራር በነበሩኩበት ወቅት የምጠረጥራቸው ፌዴሬሽኑ ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮችን ለፍትሕ አካላት አያደርስም የሚሉ ነገሮች ስለነበሩ እነዚያን ሐሜቶች ላለማስተናገድ ጭምር ውሳኔ የሚፈልጉ ነገሮችን ያለአንዳች ማመንታት ነው ለፍትሕ አካላት ሲተላለፉ የቆዩት፡፡ ይህ በፖለቲካው ሽፋን ውጪያዊ የሆኑ ችግሮች ባሉበት ማለት ነው፡፡ ተስተካካይ ጨዋታዎችን በሚመለከት የተወሰኑ መፋለሶች ቢኖሩም ፌዴሬሽኑ በነበረው ቁርጠኝነት ያለምንም ችግር በተለዋጭ ፕሮግራም እንዲከናወኑ አድርጓል፤ መርሐ ግብሩም በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. እንዲጠናቀቅ ተደርጓል፡፡ በዚህም ብዙዎቹ ክለቦች ደስተኛ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ ይህ ለስፖርት አመቺ ባልሆነው ከፖለቲካው ጋር ተያይዞ የተከሰተውን ሳያካትት ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በችግሩ ውድድሮች ላይካሄዱ ይችላል የሚል አንድምታ እንደነበርም ሊዘነጋ አይገባውም፡፡

ሪፖርተር፡- አመራሩ በሙያተኞች ደረጃ በሚከናወን ስራ ላይ ጊዜው እንደሚያጠፋ፣ ይህ ደግሞ ጣልቃ ገብነቱ እንዲባባስ ማድረጉ ይነገራል፤

ኮሎኔል አወል፡- ተቋሙ ከዲሲፕሊን ደንቡ ጀምሮ በርካታ ክፍተቶች ያሉበት ነው፡፡ አመራሩ እነዚህን ክፍተቶች ለመድፈን የተለያዩ ጥናቶች አድርጓል፣ ደንቦችና መመሪያዎች እንዲሻሻሉና ለጠቅላላ ጉባዔ እንዲቀርቡ ለማድረግ እየሠራ ነው፡፡ በዋናነት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የማስፈጸም አቅም ውስንነት ስላለ ያንን የተሟላ ለማድረግ ተጨማሪ አንቀጾች እንዲካተቱ ተደርጓል፣ የሚቀረው የጉባኤ ውሳኔ ነው፡፡ ይህን ማድረግ እንደ ጣልቃ ገብነት ተቆጥሮ ካልሆነ የሚወራው ውሸት ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር የቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዳይ በደንቡ መሰረት ቢታይ የቅጣት ሰለባ እንደሚሆን የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ እንዲያውም አመራሩ ነው ውሳኔዎችን ተቻኩሎ ከመወሰን በፊት ጉዳዩን ሰከን ብሎ መመልከቱ የተሻለ እንደሚሆን በአማራጭነት ያየው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሊጉ በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት እንዳይካሄድና ችግሩ ይበልጥ ተወሳስቦ ወደ ሚቀጥለው ዓመት እንዲሸጋገር ፍላጎት የነበራቸው አካሎች እንደነበሩ መረጃው እንዳለን ሊታወቅ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ ውድድር መምራት ካልሆነ ሌሎቹን የልማት ሥራዎች ዘንግቷቸዋል የሚሉ አሉ፤

ኮሎኔል አወል፡- በፍጹም፣ እንዲያውም የእኛ ፍላጎት ክለቦች ውድድራቸውን ራሳቸው ይዘው ተቋሙ ለትልልቅ የልማት ሥራዎች ትኩረት እንዲሰጥ ፍላጎት አለው፡፡ ይህን የሚያወሩት የሚያውቁ እንዳለወቁ በመምሰል ትርምስ እንዲፈጠር የሚፈልጉ ወገኖች የሚያስወሩት ነው፡፡ የሚገርመው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለቦች ሊጉን እንዲያስተዳድሩ ለማድረግ ከሁለት ጊዜ በላይ ጥሪ ተደርጎላቸው በመጀመሪያ ከ16 ክለቦች የተገኙት ሁለት ብቻ ነበሩ፤ በሁለተኛው ደግሞ የተሻለ ቁጥር ያላቸው ተገኝተው ውይይት ቢደረግም ሊጉን ለመረከብ ፍላጎት የላቸውም፡፡ አሁንም ሊጉ ቀጣይ ዕጣ ምን ይሁን የሚለውን ፌዴሬሽኑ በጥናት ላይ በመመሥረት ዝግጅት እያደረገበት ነው፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ከመገናኛ ብዙኃኑ ጭምር ጉዳዩ ምንድነው ብሎ ተቋሙን ከመጠየቅ ይልቅ በስማ በለው የሚወራው ነገር ትዝብት ካልሆነ ለእግር ኳሱ የሚያተርፈው አንዳች ሊኖር እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ አመራሩ በአንድ ልብ እግር ኳሱን ለመለወጥ እየሠራ ስለመሆኑ ይነግሩናል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተቋሙ ውስጥ ያለው አመራር ለሁለት መሰንጠቁ ነው የሚነገረው፣ የሚሉት ይኖርዎታል?

ኮሎኔል አወል፡- በግሌ የሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደመሆኔ የሚመለከተኝንና የሚመለከተኝን ብቻ ነው መሥራት የሚኖርብኝ፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ፡፡ በዚሁ መሰረት የዳኞች ኮሚቴ፣ የቴክኒክና ልማት ኮሚቴ፣ የስፖንሰርሺፕ ኮሚቴ፣ የፀጥታ ኮሚቴና በሌሎች የሥራ ዘርፎች አመራሮቹ በሰብሳቢነት ተመድበው ሥራቸውን እያከናወኑ ስለመሆኑ አውቃለሁ፡፡ ማን ምን ዓይነት ሥራ አከናወነ የሚለውን ለማወቅ የውስጥ ግምገማ ስላለን ውጤቱ ይፋ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ይህ የሥራ ድርሻን ማወቅ እንጂ ክፍፍል ሊባል አይገባም፡፡ ሌላውም እንደዚያው ነው፡፡ ከዚህ ውጪ እንደሚነገረው ሌሎችን አግለን በእኔና በአቶ ኢሳያስ የተወሰነ አሰራር ካለ መነጋገር ይቻላል፡፡ ምናልባት ውድድር ከሌሎቹ የሥራ ድርሻዎች ጎልቶ ስለሚታይ እንዳይሆን ሥጋት አለኝ፡፡ በተረፈ የሥራ ድርሻ ያልተሰጠው አመራር የለም፡፡ በእርግጥ የሚወሩ አሉባልታዎች እንዳሉ በግሌ እሰማለሁ፣ የእኔ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለማንኛውም ሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. አመታዊ ግምገማ ስለሚኖረን ሁሉም ነገር ግልጽ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ክለቦች በፌዴሬሽኑ እምነት እያጡ ለመሆኑ ብዙ ማሳያዎች ይስተዋላሉ፣ በተለይ የአዲስ አበባ ክለቦች ከውድድር ሥርዓት ጋር እየደረሰብን ነው በሚሉት ጫና አሁን ሁኔታ አንቀጥልም የሚል አቋም ላይ ደርሰዋል፣ ምን ይላሉ?

ኮሎኔል አወል፡- በግሌ እንዲታወቅ የምፈልገው ቢኖር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከፎርማት ጋር በተያያዘ የሚያገናኘው አንዳች የለም፡፡ የክለቦች ፍላጎት ከሆነ በወረዳ ይሁን በቀበሌ፣ ፍላጎታቸው ከሆነም በየወረዳው፣ ካልሆነም በየክልሉ የሚያገባው ምንም የለም፡፡ ውሳኔው የራሳቸው የክለቦቹ ነው፡፡ የሚገርመው ጉዳዩን ከፌዴሬሽኑ ጋር እያገናኙ የሚናገሩ ወገኖች ፍላጎት ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ እስከአሁን በዚህ ጉዳይ ለፌዴሬሽኑ ጥያቄ አቅርቦ አይሆንም የተባለ ክለብ ካለ ግልጽ ይደረግና እንነጋገርበት፤ እኔ እስከማውቀው ድረስ ጥያቄውን ያቀረበ ክለብ የለም፡፡ ወሬውን የሚያወሩት ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ከሆነ ካዛንቺስ ተቋሙ ጽሕፈት ቤት ሄዶ ማጣራት ችግሩ ምንድነው? ክለቦች ፍላጎታቸው ከሆነ በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በክልል ብቻ ራሳቸው በመረጡት ተስማምተው ውሳኔያቸውን ማቅረብ መብታቸው ነው፡፡ በተረፈ ባልቀረበ ጥያቄ የተቋሙን አመራሮች ስም ማጥፋት ጥቅም ያለው አይመስለኝም፡፡ ክለቦች ይበጀናል የሚሉትን የመምረጥ ኃላፊነት እጃቸው ላይ ነው፡፡ የፌዴሬሽኑ ድርሻ ከሚመለከታቸው ማለትም መንግሥት ካስቀመጠው ስፖርት ኮሚሽን ጋር ጭምር ሁሉም አካላት በተስማሙበት መንገድ ማስኬድ፣ ማስተባበር፣ ማልማትና የአገሪቱን እግር ኳስ ማሳደግ ከዚያም ብሔራዊ ቡድኑን ማጠናከር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፎርማቱ ጉዳይ በፌዴሬሽኑ እንዴት ይታያል፣ ምክንያቱም አሁን ያለው ፎርማት እያስከተለ ያለው ጥፋት ግልጽ ነው፤

ኮሎኔል አወል፡- ፎርማት ሕገ መንግሥት አይደለም፣ ባለው ነገር ሕገ መንግሥቱ እንኳ መሻሻል እንዳለበት አስተያየት እየቀረበበት ነው፡፡ ለአገሪቱ እግር ኳስ ሲባል ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ ተወያይተውበት የሚበጀውን መምረጥ ያስፈልጋል፡፡ የእኔ ክርክር በዚህ ጉዳይ ጥያቄ ያቀረበ የለም ነው፡፡ ከቀረበ መነጋገርና የሚበጀውን መምረጥ ችግሩ ምንድነው? የሚገርመው ክለብ ይዤ በነበሩኩበት ወቅት በፌዴሬሽኑ ውስጥ የሚነገረው መጓተት ምክንያቱ ምንድነው? የሚል ጥያቄ ነበረኝ፤ አሁን የተረዳሁት ቢኖር ለአገሪቱ እግር ኳስ በሚል ሳይሆን ለግል ጥቅም መጓተቱ በግልጽ እንዳለ ነው ማረጋገጥ የቻልኩት፡፡ የሚገርመው በስፖርቱ ያሳለፍኩትን በሚመለከት መጽሐፍ እያዘጋጀሁ ነው፣ ለምን አይወጣም የሚሉኝ ነበሩ፣ አሁን ሲገባኝ እንኳን አላወጣሁት፤ ምክንያቱም ይህን መጓተት የማካትትበትን አጋጣሚ ፈጥሮልኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ እንደ ፌዴሬሽን አመራር ሳይሆን የግሌ አስተያየት፣ ፕሪሚየር ሊግና ከፍተኛ ሊግ እያልን በየደረጃው የምናወዳድራቸው ቡድኖች ለአገሪቱ እግር ኳስ አንዳች የፈየዱት ነገር የለም፤ በመሆኑም አካሄዱን በሙያተኞች አስጠንቼ እላይ ያሉት ክለቦቻችንን ለአንድ አምስትና ከዚያም በላይ ዓመት እንዲቋረጥና ከታች ታዳጊ ወጣቶች ላይ እንዲሠራ ማድረግ ነው ፍላጎቴ፡፡ ዕድሜያቸው ከአሥር ዓመት ጀምሮ በየደረጃው እስከ ሃያ ዓመት ባሉት ላይ ትክክለኛውን ሥራ ሠርቶ እግር ኳሱ በጠንካራ መሰረት ላይ ማስቀመጥ ምርጫዬ ነው፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...