በውብሸት ሙላት
የሚዲያ ቴክኖሎጂዎች በዓይነትም በጥራትም እየጨመሩ መምጣታቸው ሐሳብንና መረጃን ለሌላው የማጋራትም ከሌላው የማግኘትም ዕድሉ እየሰፋም እየጨመረም መጥቷል፡፡ ሐሳብን የመግለጫና የመቀበያ ሚዲያ መስፋፋትና መጨመር የግለሰቦችን መብት ዕውን በማድረግ ረገድ ፋይዳው እየጎላ የመሄዱን ያህል በተቃራኒው ለግላዊነት፣ ለአገር ደኅንነት፣ ለሕዝብ ፀጥታ፣ ለመልካም ሥነ ምግባር ተፃራሪ የሆኑ መረጃዎችና መልዕክቶች በመበራከት የአንዱ ብልጽግና ለሌላው መኮሰስ የምክንያትና ውጤት ትስስር እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ መገፋፋታቸውን ለማስቆም የሚያስችል ድንበር መወሰን በበርካታ አገሮች ዘንድ ፈተናነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡
ማንኛውም ሰው ወደ አደባባይ ይዞ መምጣት የሌለበትን ሐሳብና መረጃ ይዘቱ ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት ቀድሞ በሕግ በመወሰን በግል እንጂ በሚዲያ የማይነገረውን፣ የማይጻፈውንና የማይተላለፈውን ይወስናሉ፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ይህ ሁኔታ ሐሳብንና አመለካከትን የመግለጽን መብት ወሰኑን ለይቶ ገደብ ማበጀት ሲሆን፣ ለብሮድካስት ሚዲያና ለበይነ መረብ (ኢንተርኔት) አገልግሎት ደግሞ ተጨማሪ ገደቦች በመጣል ‹‹ይዘትን መወሰን›› (Content Regulation) እየተባለ ይጠራል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓብይ ጭብጥ በኢትዮጵያ ያለውን የይዘት አወሳስን ሕግና ሥርዓት መዳሰስ ነው፡፡ ያሉትን ሕግና ሥርዓት አሳይቶ፣ የጎደሉትን አጉልቶ የሚስተዋሉትን ተቋማዊ ውዥንብሮች አጥርቶ የመፍትሔ ሐሳብ መጠቋቆም ደቂቅ ጭብጮቹ ናቸው፡፡
የይዘት ቁጥጥር ለምን?
በኅትመት ሚዲያ ላይ የይዘት ወሰን ማድረግ፣ ከመታተሙ አስቀድሞ ሳንሱር በማድረግ ካልሆነ በስተቀር ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ በሚደረጉ ገደቦች የሚገዛ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ አገሮች ልክ በኢትዮጵያ በተለያዩ አዋጆች ውስጥ ከሕገ መንግሥቱ ባፈነገጠ ሁኔታ ተጨማሪ ገደብ ብሎም የወንጀል ድንጋጌዎችን ሊያስቀምጡ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ የኅትመት ሚዲያ ላይ ይዘቱ ‹እንዲህ ይሁን›፣ ወይም ‹እንደዚያ ይሁን› የሚለው አጀንዳ ሲሆን አይስተዋልም፡፡ ሕግን የጣሱ ይዘቶች ከታተሙ ግን ተጠያቂነት አይኖርም ማለት አይደለም፡፡
በብሮድካስት ሚዲያ የሚተላለፉ ፕሮግራሞች ይዘታቸው ምን መምሰል እንዳለበት መወሰን በየትም አገሮች ያለ ነው፡፡ ቢያንስ ምን ምን ይዘት ያላቸው መተላለፍ እንደሌለባቸው በአሉታ መሥፈርት በሕግ ቀድሞ ይወሰናል፡፡ ከኅትመት ሚዲያ በተለየ ሁኔታ ብሮድካስትን በሚመለከት ስለምን ይዘትን መወሰን አስፈለገ? ሊባል ይችላል፡፡ በበይነ መረብ አማካይነት የሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግሞችን ማሠራጨት ከመቻሉ አስቀድሞ በቴሌ ኮሙዩኒኬሽን በኩል በሚመደብ ፍሪኩዌንሲ አማካይነት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በኤሌክትሮ ማግኔቲክ ሞገድ መልክ ይተላለፍ ነበር፡፡ ከመሬት ወደ አየር በሚለቀቅ ሞገድ (Terrestrial)፣ በሳተላይት፣ በኬብል አማካይነት ሲሠራጭም አገልግሎቱንም ማግኘትም ነባሩና የተለመደው ነው፡፡
በዚህ መንገድ ለሚተላለፉት ለእያንዳንዱ አገርና ለእያንዳንዱ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ የተለያና የማይደራረብ ስፔክትረም ይኖራቸዋል፡፡ የአንዱ ጣቢያ ፍሪኩዌንሲ ከሌላው ጋር ሳይጋጭ፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፉ የቴሌ ኮሙዩኒኬሽን ኅብረት ለአንድ አገር ተወስኖ የተሰጠው ፍሪኩዌንሲ መጠኑ ውስን ስለሆነ በቁጠባ ሊተዳደር ይገባዋል፡፡ ውስን የሕዝብ ሀብት መሆኑ የተመረጠ መልዕክት ማስተላለፍ ስፔክትረምን ውጤታማና ፍትሐዊ ጥቅም እንዲሰጥ አድርጎ ማስተደዳር አስፈላጊ ያደርገዋል፡፡ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅምና ጉዳትን አስልቶና መዝኖ ለክቶ የተሻለ ጥቅም ሊሰጥ በሚችልበት አገልግሎት መመደብ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሳቢያ ማንም ሰው ገንዘብ ስላለው ብቻ የፈለገውን ፕሮግራም ለማሠራጭት የብሮድካስት አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ ሊያገኝ አይችልም፡፡ ለዚህም ነው የብሮድካስት አገልግሎት ለመስጠት የሚፈልግ ሰው እንደ መብት ቆጥሮ በምዝገባ ብቻ ሥርጭት መጀመር የማይችለው፡፡ ይልቁንም አስቀድሞ ፈቃድ ማግኘት ግድ ነው፡፡ በርካታ አገሮች የኅትመት ሚዲያ ለመጀመር መመዝገብ ብቻ ሲያስፈልግ፣ የብሮድካስትን በሚመለከት ግን ከምዝገባ በፊት የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ ፈቃድ ማግኘት አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም ይዘትን መወሰን የተገባ አሠራር ነው ማለት ነው፡፡
በዲጂታል ሚዲያ አማካይነት የሚሠራጩትን በሚመለከት የይዘት ገደብ ያስፈለገው ከላይ ስለብሮድካስት ከቀረበው በተለየ ምክንያት ነው፡፡ የኅትመትና ዲጂታል ሚዲያው ውስን ሀብት አይደለም፡፡ ገበያ ወይም የኅትመት ወጪው እንቅፋት እስካልሆነ ድረስ በአንድ አገር ይህን ያህል ጋዜጣ ወይም መጽሔት ብቻ እንጂ ከዚህ በላይ ማሳተም አይቻልም ሊያስብል የሚችል የሀብት አጠቃቀም ውስንነት የለም፡፡ ዲጂታል ሚዲያውም ቢሆን ያው ነው፡፡ በዲጂታል ሚዲያ ሲሆን ይዘት ላይ ወሰን አብጅቶ ቁጥጥር የማድረግ አስፈላጊነቱ በራሱ አጠያያቂ ነው፣ ምክንያቱ ደግሞ ውስን ሀብት ባለመሆኑ ነው፡፡ በዲጂታል ሚዲያ የሚተላለፈው ፀያፍና ሕገወጥ ይዘት ያለውን ሥርጭት ቁጥጥር ይደረግበት ቢባል ተግባራዊ ማድረግ የመቻሉ ጉዳይም በራሱ አጠያያቂ ነው የሚል ተደራቢ ምክንያት ይቀርባል፡፡ ‹‹ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም›› እንዲሉ ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር ማድረግ ስለማይቻልም ምንም ዓይነት ቁጥጥር መኖር የለበትም የሚሉትን በመቀበል ከቁጥጥር ነፃ የሆነ ዲጂታል ቀጣና መፍቀድን መምረጥ አስቸጋሪ ነው፡፡ በዲጂታል ሚዲያ እስካሁን ድረስ አከራካሪ ሆነው ከቀጠሉት ጭብጦቹ መካከል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በይዘት ቁጥጥርና ሐሳብን በመግለጽ መካከል የሚፈጠር ውጥረት በምን ሁኔታ አስታርቆ ማስማማት ይቻላል? በይነመረብን ሳይጠቀሙ (Offline) የሚተላለፉና በበይነ መረብ አማካይነት (Online) የሚሠራጩት ላይ የሚኖረው ክልከላ (ቁጥጥር) መለያየትን መሠረት ያደረገ ክርክር አለ፡፡ በይዘት ተመሳሳይ ነገር ግን በይነ መረብን በመጠቀም ወይም ባለመጠቀም ብቻ ተለያይተው ሕገወጥ የሚባሉ/የማይባሉ ሊኖር ይገባል ወይስ አይገባም? ቁጥጥር የማድረግ ውጤታማነት ላይ ጥርጣሬ በማሳደር የቁጥጥር ሥርዓቱ ወጥና በሁሉም ላይ እኩል ተፈጻሚ ማድረግ ይቻላል ወይስ አይቻልም? በተጨማሪም ይዘትን የመቆጣጠር ኃላፊነቱ የማን ይሁን? የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እነዚህ አከራካሪ ጭብጦች ቢኖሩም ይዘትን ለመቆጣጠር በርካታ ገፊ ምክንያቶች እንዳሉ የሚነሳ ጥያቄ የለም፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ትክክለኛና ገልለተኛ ዜና የማቅረብ የሞራልና የዴሞክራሲ መርሆች፣ የምርጫ ሥነ ምግባር መመርያዎችን የመተግበር አስፈላጊነት፣ ለሕፃናትና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ወጣቶችን መልካም አስተዳደግ ሲባል፣ የሰብዓዊ ክብርን ለመጠበቅ ብሎም ፀያፍና አስነዋሪ ነገሮችን ከአደባባይ ለማራቅና ለመቆጣጠር፣ የግለሰቦችን ግላዊነትና ምላሽ የመስጠት መብት ለማስጠበቅ፣ ወንጀልንና የሥርዓት መፍረስን ለመከላከል፣ ብሔርን፣ ዘርንና ሃይማኖትን ወዘተ. መሠረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮችን ለመከላከል የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ምክንያቶች በተለያዩ ሕግጋት ጥበቃ ተድርጎላቸዋል፡፡ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
የይዘት ቁጥጥርና የሚዲያ ውህደት
በበይነ መረብ አማካይነት ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ወዘተ. መተላለፍ ከጀመሩ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በወረቀት የሚታተሙትም ፍሪኩዌንሲ ተመድቦላቸው የሚሠራጩትም በበይነ መረብም ይነበባሉ፣ ይሰማሉ፣ ይታያሉ፡፡ ሚዲያዎቹ አንድም ሁለትም ይሆናሉ፡፡ ሁለትነታቸው በወረቀትና በስፔክትረም አማካይነት በመሠራጨት ኅትመትና ብሮድካስት መሆናቸው ነው፡፡ አንድነታቸው በበይነ መረብ አማካይነት የኅትመቱም የብሮድካስቱም በአንድ ቅርፅ መተላለፋቸው ነው፡፡ በአንድ ዓይነት ሚዲያ ሁለቱም ይስተናገዳሉ፡፡ ይህን ተከትሎ ሚዲያዎቹን ለማስተዳደር ጥቅም ላይ ይውል የነበረው ሥልት እየተለወጠ መጥቷል፡፡ ኅትመትን የብቻ ነጥሎ በማስተዳደር፣ የብሮድካስት አገልግሎትን በአንዳንድ አገሮች ከቴሌኮሙዩኒኬሽን ጋር በማዳበል በሌሎች ዘንድ ደግሞ በየፊናቸው ማስተዳደር የተለመደ ነበር፡፡
የቴሌኮሙዩኒኬሽን መሠረተ ልማትን በመጠቀም በበይነ መረብ አማካይነት የብሮድካስት አገልግሎት መስጠት እየተስፋፋ ሲመጣ የብሮድካስት አገልግሎትን፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽንንና በይነ መረብን በአንድነት ማስተዳደር የበርካታ አገሮች ምርጫ ሆኗል፡፡ ፍሪኩዌንሲ ተመድቦላቸው በሳተላይት፣ በአንቴናና በገመድ ወዘተ. የሚሠራጩት የብሮድካስት አገልግሎቶች እንዳሉ ሆነው በበይነ መረብ የሚተላለፉትን ደርቦ በአንድነት ማስተዳደርን በርካታ አገሮች ከመረጡ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ውስን የሆነውን የሕዝብ ሀብት ውስንነት ከሌለበት ጋር በጋራ ይተዳደራል፡፡ የድምፅ ወይም ምስል የሚዲያ አገልግሎትን አጠቃሎ በአንድ ሕግ የማስተዳደር አካሄድ በነባሩ የብሮድካስት አገልግሎትም ይሁኑ በዲጂታል ሚዲያ የሚተላለፉትን ዝግጅቶች በሚመለከት በምን ዓይነት ሚዲያ ተሠራጩ? የሚለውን በመተው በአንድ የሕግ ሚዛን ላይ ማስቀመጥ የአውሮፓ ኅብረትም ለአባል አገሮች የመረጠው ፈለግ ነው፡፡ ለተግባራዊነቱም ሕግ አውጥቷል፡፡
ምን ዓይነት ይዘትን?
የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ፕሮግራሞች በተመደበላቸው ፍሪኩየንሲም በበይነ መረብም በተለያዩ ዲጂታል ሚዲያዎች በተመሳሳይ ወይም በተለያየ ጊዜ ያሠራጫሉ፡፡ ዲጂታል ሚዲያው ውስንነት ኖሮበት በቁጠባ ጥቅም ላይ ለማዋል ባይሆንም በሕግ የተከለከሉ ይዘቶች እንዳይተላለፉ ሲባል የይዘት ወሰን ይደረጋል፡፡ በመሆኑም፣ በዲጂታል ሚዲያ የሚተላለፉት ገደብ የሚኖረው በይዘት ረገድ ሕገወጥ ወይም ጎጂ ሲሆኑ ነው፡፡
‹ሕገወጥ› የሚባሉት በሕግ ክልከላ ሲኖር ነው፡፡ ‹ጎጂ› የሚባሉት ግን ሕገወጥ ባይሆኑም ማኅበራዊ ጉዳታቸው የሚያመዝኑ ይዘት ያላቸው ሲሆኑ ነው፡፡ የትኛው ጎጂ፣ የቱ የማይጎዳ ነው የሚለውን አገሮች በፖሊሲያቸው ላይ ሊወስኑ የሚወስኑት ነው የሚሆነው፡፡ በብሮድካስት አገልግሎት የሚሠራጩ ፕሮግራሞች ይዘታቸውን ለመቆጣጠር ሲባል የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነትን በብሮድካስተሮች ላይ ከመጣል ይልቅ አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲሆን የሚሟገቱ አሉ፡፡ ራስን በራስ የመቆጣጠር ባህሉ በጠነከረበትና ውጤታማ በሆነበት አካባቢ (አገር) አስተዳደራዊ ቅጣትም ቢሆን አስፈላጊ አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ የቁጥጥር ዓይነቶች መብዛት አንዱን ውጤታማ እንዳይሆን ስለሚያውክ፡፡ ስለሆነም የቁጥጥር ሥልቶቹም አስፈጻሚ ተቋማትም ቁጥራቸው በርካታ ሆኖ ከመረባረብ ይልቅ አንዱን መርጦ ትኩረት ማድረግ ተመራጭ ስለመሆኑ በዘርፉ የተጻፉ ድርሳናት ምስክር ናቸው፡፡ በአገሮች ደረጃ ባይወሰን እንኳን የበይነ መረብ አገልግሎት አቅራቢዎች ወይም ወላጆች ለልጆቻቸው፣ ዩኒቨርሲቲና ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎቻቸው ጎጂ የሚሉትን ፕሮግራም (ይዘት) የተለያዩ አሠራሮችን ወይም ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው ሊገድቡ/ሊወስኑ ይችላሉ፡፡
የይዘት ቁጥጥር እንዴትና በማን?
በዓለም አቀፍ ደረጃ (በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶችና ልማዳዊ ሕጎች) ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ስምምነት ሊባል በሚችል ደረጃ የተደረሰባቸው እንደ ፖርኖግራፊና የጥላቻ ንግግር ወዘተ. አሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በተወሰነ አገሮች ነባራዊ የፖለቲካና ማኅበራዊ ሁኔታን የሚመለከቱ ይዘት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሦስተኛ ደግሞ ፖለቲካዊ ሳንሱር (ማዕቀብ) ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከሦስቱ በአንዱ ሊካተቱ የሚችሉ ዕቀባዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
የይዘት ቁጥጥር በባህሪው ወደ ሳንሱር የተጠጋጋ ወይም የሚመሳሰል ነው፡፡ በብሮድካስትና በኢንተርኔት አማካይነት ለሚሠራጩት የተለመደው ይዘት ቁጥጥር ማድረግ ነው፡፡ ይኼ ቅድመ ኅትመት ሳንሱር ማድረግ ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም የይዘት ማጣሪያ በማድረግ ማለትም በመዝጋትም ወይም ክልክል ይዘት ያለውን ወይም የሐሰት ዜናውን ከአውታር (ኔትወርክ) ላይ በማስወገድ ወደ ሕዝብ እንዳይደርስ ማድረግን ይይዛል፡፡ በፓኪስታን የኤሌክትሮኒክስ ወንጀልን ለመከላከል ሲባል በወጣው ሕግ አስነዋሪና ክልክል ይዘት ያለውን ንግግር (ጽሑፍ፣ ምስልና ቪዲዮ ወዘተ.) የያዙ ገጾችን መዝጋት፣ ሕገወጥ ይዘትን (Unlawful Content) ቀድሞ መዝጋትን መርጠዋል፡፡ ፌስቡክ፣ ቲውተር፣ ማይክሮሶፍትና ዩቲዩብ በአውሮፓ ኅብረት ደረጃ በ2016 የተስማሙት በበይነ መረብ የሚሠራጩ የጥላቻን ይዘት ያላቸው ንግግሮች ተሠራጭተው ሪፖርት ሲደረግላቸው በ24 ሰዓት ውስጥ መልሰው ለመከለስና ለመመርመርና እንደ ሁኔታው ለማስወገድ ነው፡፡
በጀርመን ባለፈው ዓመት በወጣው የአውታር ጥበቃ ሕግ (Network Enforcement Law) መሠረት ደግሞ የበይነ መረብ ማሠራጫ እንዲሁም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የጥላቻ ይዘት ያለውን ንግግር እንዲያስወግዱ መረጃ በደረሳቸው በ24 ሰዓት ካላስወገዱ ወይም ውስብስብ የሕግ ጉዳይ ካለው ደግሞ በሰባት ቀናት በማስወገድ በሕግ የተደነገገውን ሳያከብሩ ከቀሩ እስከ 60 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ሊከተላቸው እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም ጥቆማ እንደደረሳቸው ብዙም ማጣራት ሳያደርጉ ማስወገድን የመምረጥ አዝማሚያ እየተከተሉ ነው፡፡ ምክንያቱም ቅጣቱ ከፍተኛ ስለሆነ፡፡ የሚወገደውን ይዘትም በሚመለከት የሚወስነው ፍርድ ቤት ሳይሆን የግል ተቋም ነው፡፡ ከዚህ ሌላም እነ ቲውተር፣ ጉግል፣ ፌስቡክና ማይክሮሶፍት በራሳቸው የሽብርና የኃይል ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያነሳሳ መልዕክት ያላቸውን ቴክኒካሊ በተለያዩ ዘዴዎች (የቴክኖሎጂ ውጤቶች) ለማስወገድ ስምምነት አድርገዋል፡፡ ምን ይዘት ያለው ላይ እንዴት ቁጥጥር ይደረግ የሚለውን የሚወስነው በዋናነት መንግሥት ነው ብለናል፡፡ የበይነ መረብ አገልግሎት አቅራቢዎች ኃላፊነትም ከፍ እንዲል የማድረግ አዝማሚያው የላቀ ነው፡፡ አቅራቢዎቹም ይዘትን እያጠለሉ አንድም በመንግሥት ሕግና ሥርዓት ትዕዛዝ ኖሮባቸው፣ አንድም በራሳቸው አነሳሽነት ቢያንስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙትን ይዘቶችን በሚመለከት ቁጥጥር ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ወላጆችን ለልጆቻቸው፣ የትምህርት ተቋማት ለተማሪዎቻቸው የሚሆኑትን ይዘቶች መምረጥ ሌላውና ተጨማሪ አካሄድ ነው፡፡
የመንግሥትን የተቆጣጣሪነት ሚና እንመልከት፡፡ አንዱና የተለመደው ሥልት ‹መገደብ፣ ግዴታ መጣልና መቅጣት› (Restrictions, Obligations and Sanction) ነው፡፡ ለሕዝብ ይፋ ከመሆናቸው አስቀድሞ በአውታር ላይ እያለ አነፍንፍ ነጥሎ ማወቂያም እንዳይሠራጭ መገደቢያም ቴክኖሎጂዎች ተፈጥረዋል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ምርመራና ክልከላ በዲጂታል ሚዲያም ላይ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል ማለት ነው፡፡ ከአንድ ተቋም ሰርቨር (የትምህርት ቤትና የመንግሥት መሥሪያ ቤት. . .) ውስጥ ሳይገቡ በእሳተ ኬላ (Firewall) መመለስ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በአገር አቀፍ ደረጃም ሊፈጸም ይችላል፡፡ የበይነ መረብ አገልግሎት ሰጪው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ ከሆነ በቀላሉ አንዳች ውጣ ውረድ ሳይኖር፣ ብዙና የግል ከሆኑም በተለያዩ ስምምነቶች አማካይነት፣ ቢያንስ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነቶቹና በርካታ ፕሮግራሞች ከውጭ እንጂ ከአገር ውስጥ በማይለቀቅባቸው፣ በእሳተ ኬላ እያጠነፈፉ ወይም እያጠለሉ የማይፈለጉትን መመለስ፣ ክልከላ የሌለበትን ማስገባት ነው፡፡
‹መመርመር፣ ማጥፋትና መክሰስ› (Investigation, Deletion and Prosecution)፣ ሕግን የሚቃረኑ ይዘት ያላቸው ጉዳዮች ሲሠራጩ ፖሊስ ምርመራ በማድረግ፣ እንደደረሰበት በማጥፋት ወይም በማስጠፋት ብሎም ፈጻሚውን ወደ ፍትሕ ሥርዓቱ ማቅረብ (መክሰስ) ነው፡፡ ተግዳሮቱ የሳይበር ዓለም ወሰን አልባ በመሆኑ ከአገሮች ጋር ትብብር ከሌለ በስተቀር የአንድ አገር የፍትሕ ሥርዓት የሳይበር ወንጀለኞችን በፍትሕ ሥርዓቱ ሥር ለማስገባት አዳጋች መሆኑ ነው፡፡ ትብብር (Cooperation) በበይነ መረብ አገልግሎት አቅራቢዎች፣ የመንግሥት ተቆጣጣሪዎችና ዜጎች መካከል በማድረግ የሳይበር ዓለሙን የመጠበቅ አካሄድም ሌላውና ተጨማሪ አማራጭ ነው፡፡
የይዘት ቁጥጥር ለማደረግ የተፈቀደውን ከተከለከለው መለየት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ መኖር አስፈላጊ ነው፡፡ እነዚህ ሕግጋትም ለሁሉም ሚዲያዎች ተፈጻሚ የሚሆኑ በኢትዮጵያ እንደ የወንጀል ሕጉ፣ የፀረ ሽብርና የምርጫ ሕጉ ዓይነት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እንደየሚዲያው ዓይነት የተዘጋጁ ሕግጋት ይኖራሉ፡፡ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አዋጅና ደንቦች፣ የብሮድካስትና የማስታወቂያ አዋጆቹ፣ የብዙኃን መገናኛና የመረጃ ነፃነት አዋጁን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በቀጥታ በይነ መረብን በሚመለከት ደግሞ የኮምፒውተር ወንጀልና የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጆቹ አሉ፡፡ እነዚህ አዋጆች በአንድም በሌላም መልኩ ተፅዕኖ/ግንኙነት አላቸው፡፡
በአገራችን ያለው የሕግ ማዕቀፍ አንዱ ችግር እዚህም እዚያም ተበጣጠሰ መልኩ በተለያዩ አዋጆች ውስጥ ተሸጉጠው ተሸጉጠው እንጂ ተጠቃለው አለመገኘታቸው ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በይነ መረብን በሚመለከት፡፡ በተለያዩ አዋጆች ውስጥ መሸጎጣቸው ለተለያዩ ተቋማት ተመሳሳይ ኃላፊነቶችን ተደርቦ እንዲሰጥ አድርጓል፡፡ አንድን ኃላፊነት ለሁለትን ከእዚያ በላይ መሥሪያ ቤት መስጠትን አስከትሏል፡፡ በዚህ ረገድ ማስታወቂያን በሚመለከት የብሮድካስት አዋጁንና የማስታወቂያ አዋጁን ብንመለከት በሁለቱም አዋጆች ላይ ተመሳሳይ ክልከላዎች ተደጋግመው የምናገኝ ሲሆን፣ በማስታወቂያ አዋጁና በሸማቾች ጥበቃ አዋጆቹ ደግሞ የተገለጹት ተመሳሳይ ኃላፊነቶችን ለብሮድካስትና ለሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ይሰጣል፡፡ አንድ ሥራ ለሁለት መሥሪያ ቤት ይሰጣል፡፡ መተላለፍ የሌለበትን የማስታወቂያ ይዘት በሚመለከት ነው ሁለቱም፡፡
ሌላው ችግር ደግሞ የሕግ ሥርዓቱ ሚዲያው ራሱን በራሱ በትብብር የሚቆጣጠርበትን (Self-regulation and Co-regulation) ሥርዓት ከዕቁብ ባለመቁጠር መንግሥታዊ ቁጥጥርን ብቻ መምረጡ ነው፡፡ በእርግጥ በረቂቁ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ይህንን እንከን በመረዳት እነዚህን የቁጥጥር ሥርዓቶች ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችለው የኢትዮጵያ ሕግጋት እንከን በተለይ ደግሞ በይነ መረብን በሚመለከት ሕግጋቱ ከሌሎች አገሮች ሕግ ጋር የተሰናሰለሉ አለመሆናቸው ነው፡፡ በመሆኑም በተለይ ዲጂታል ሚዲያውን በሚመለከት አሁን ሥራ ላይ ያሉትን ሕግጋት እርስ በርሳቸው ማጣጣም፣ ያረጁትን ማደስና ማሻሻል፣ የተደጋገሙትን ድግግሞሹን ማስቀረት (ያልተገባ ቁጥጥርም ወይም የፉክክር ደጃፍ ሳይዘጋ ያድራል እንዲሉ ቁጥጥሩም ሊቀር ይችላል) አስፈላጊ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የሕግ ማዕቀፍ፣ በተለይ ዲጂታል ሚዲያውን በሚመለከት የተዝረከረከ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዝርክርክነቱ በተለያዩ ሕግጋት ተበጣጥሶም ተደጋግገሞም መገኘቱ ብቻ ሳይሆን የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እንዲሠሩ ኃላፊነት የተጣለባቸው ተቋማት ቁጥር መብዛቱ ውጤታማ የሆነ ሥርዓት መዘርጋት እንዳይችሉ ሰበብ ሆኗል፡፡ የብሮድካስት ባለሥልጣን፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ የቀድሞው የኮሙዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን (የአሁኑ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ) ሚኒስቴርና የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ወዘተ. በበይነ መረብ አማካይነት የሚሠራጩትን በአንድም በሌላ መልኩ ሥልጣን አላቸው፡፡
አሁን ላይ ደግሞ የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባለሥልጣን ተጨምሯል፡፡ የማርቀቅ ሥራው ወደ መጠናቀቁ የደረሰው የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ረቂቅ አዋጅም ቢሆን አዲስ እንደሚቋቋም ታሳቢ ለተደረገው የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ተደርበው የተሰጡ አሉ፡፡ ሁለተኛው ተቋም ገና ያልፀደቀና የብሮድካስት ባለሥልጣኑን እንደሚተካ የታሰበ ስለሆነ ከመፅደቁና ኋላ ላይ በኃላፊነት መደራረብ ሚዲያው ላይ ያልተገባ የጣምራ ቁጥጥር እንዳይኖር ወይም ‹‹የፉክክር ደጃፍ ሳይዘጋ ያድራል›› እንዲሉ የሥራ መገፋፋት እንዳይኖር ከወዲሁ እልባት መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ሚዲያው ወደ አንድ ቅርፅ መምጣት (Media Convergence) ሀቅ ሆኖ ሳለ፣ ከነባራዊ ሀቅ ባፈነገጠ ሁኔታ ለያይቶና በተናጠል የማስተዳደር ልማድን ማስቀጠል ውሎ ሳያድር ችግር መፍጠሩ አይቀርም፡፡
አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡