Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉየኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ፖለቲከኞች ስለፈለጉ ሊዳከም ይችላል?

የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ፖለቲከኞች ስለፈለጉ ሊዳከም ይችላል?

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

አንዳንድ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ውጤቶች በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረው የፖለቲካ ግንኙነት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ሲጋጋል እንደነበረ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ጊዜ ግን እየቀዘቀዘ እንደመጣ ይገልጻሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱ በምሥራቅ አፍሪካና በደቡብ የኮመንወልዝ ጥናት ተቋም ነባር ተመራማሪ የሆኑት ማርቲን ፕላውት የተባሉ ሰው፣ ሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ለንባብ ባቀረቡት ኳርቲዝ አፍሪካ በተሰኘ ሚዲያ በሰፊው ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ይገኝበታል፡፡ እኚህ ተመራማሪ ለቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ ኤዲተር ሆነው ያገለገሉ ከመሆናቸውም በላይ፣ ‹‹አንደርስታንዲንግ ኤሪትሪያ›› በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ መጽሐፉም በአዲስ አበባ መጻሕፍት መደብሮች እንደ ልብ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለይም የፕሬዚዳንት ኢሳያስና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ፣ ብሎም በኢትዮጵያ ላይ መሠረተ ቢስ የሆነ ጅምላ ጥላቻ ያላቸው ተቃዋሚ የሆኑ ጸሐፊዎችና የማኅበራዊ ሚዲያው ተጠቃሚዎች ከግንኙነቱ በፊት የነበረውን ፖለቲካዊ ሁኔታ ሲያወግዙ እንደነበረው ሁሉ፣ ከግንኙነቱ ወዲህ የነበረውንም ግንኙነት እንዳልተቀበሉት ይታወቃል፡፡

ለሚስተር ፕላውትና እርሳቸውን ለመሳሰሉ አድርባይ የፖለቲካ ተንታኞች በህልም ዓለም የተመሠረተችው ኤርትራ፣ ‹‹ከኢትዮጵያ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላት›› ህያው ናት፡፡ ለእነርሱ የኢትዮጵያ ሕዝብና የኤርትራ ሕዝብ ወንድማማች አይደለም፡፡ ለእነርሱ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ምንም ዓይነት ታሪካዊ ትስስር የላትም፡፡ ለእነርሱ የኢትዮጵያውያንና የኤርትራ ሕዝብ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በደምና በኢኮኖሚ የተሳሰረ አይደለም፡፡ ለእነርሱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኤርትራ ሕዝብ ተነጥሎ ቢኖር ምንም ጉዳት ሊደርስበት እንደማይችለው ሁሉ፣ የኤርትራም ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ለዘለዓለም ሳይገናኝ ቢቀር የሚጎድልበት ነገር አይኖርም፡፡

- Advertisement -

የእነርሱን አስተያየት ለሚያቀነቅኑ አንዳንድ ኤርትራውያንም አገራቸው የኢትዮጵያ መተንፈሻ ጉሮሮ ስለሆነች፣ እርሷ ከሌለች ሲል እንደምትልና ሕይወቷን የምታጣ አድርገው ይገምታሉ፡፡ ይህንን አመለካከት የሚጋሩ አንዳንድ ኢትዮጵያውያንም ኤርትራ ያለ ኢትዮጵያ በቁሟ የሞተች አገር አድርገው ይገምቷታል፡፡ ሌሎች ጉዳዩን በሽምግልናና በአዘኔታ የሚከታተሉ ሰዎች ደግሞ ለሁለቱም ሕዝቦች መስማማት እንደሚበጃቸው ይመክራሉ፡፡ ሦስቱም የሚስቱት ዋና ነገር ምንም እንኳን በሁለት አገሮች የሚኖሩ ቢሆኑም፣ ሊነጣጠሉ የማይችሉ አንድ ሕዝብ መሆናቸውን ነው፡፡ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ከ139 ዓመታት በፊት በነበሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ዘመናትም፣ ኢጣሊያ ለ60 ዓመታት በቅኝ ገዥነት በያዘቻት ወቅትም፣ የእንግሊዝ የሞግዚት አስተዳደር በያዛት ጊዜም ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን አልተለያዩም፡፡ በማንኛውም መንግሥት ሥር ይተዳደሩ የአንድነታቸው ቀለም አልደበዘዘም፡፡ ነገሩን ከሥሩ በደንብ እንዳሰው፡፡ የጥንቱን ትተን ከኢጣሊያ ወዲህ ያለውን ታሪክ እንመልከት፡፡

ኤርትራ በኢጣሊያ ተይዛ በነበረችበት ጊዜ አልተለያዩምና አሁን አይለያዩም

እንደሚታወቀው ኤርትራ በኢጣሊያ ተይዛ በነበረችበት ጊዜ በፍጥነት ወደ ዘመናዊ ግዛት እየተለወጠች ነበር፡፡ አንፃራዊ በሆነ መንገድ ስንመለከተውም በርካታ ፋብሪካዎች ነበሯት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ እንደ ምግብ (ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ድልህ፣ የከብት፣ የዶሮ፣ የበግ፣ የፍየልና የዓሳ ሥጋ)፣ የሲሚንቶ፣ የቆርቆሮ፣ የቤት ቁሳቁስ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የጫማ፣ የመጠጥ፣ የቆዳ፣ የሚስማር፣ ምየሳሙና፣ የኦሞ፣ ፋብሪካዎች፣ የመኪና መገጣጠሚያዎች ነበሯት፡፡ ኢጣሊያ በቃል ኪዳን አገሮች ተሸንፋ እንግሊዝ ኤርትራን ስታስተዳድር ከሁለት ሺሕ በላይ ፋብሪካዎች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ የመኪና መንገዶች በመላው አውራጃዎቿ የተዘረጉ ሲሆን፣ በተለይም ከረን፣ ምፅዋ፣ ሰንዓፈና ዓዲዃላ ዘመናዊ ሕንፃዎች ተገንብተውባቸዋል፡፡

አስመራ ቀጥ ባሉ ሰፋፊና በየቀኑ በውኃ እየታጠቡ የሚፀዱ መንገዶች የተሸነሸነች፣ በመንገዶቿ መሀል ወይም ዳር ዘንባባዎች፣ ሺባኻ የተባሉ ተክሎች የተተከሉባት፣ ትልልቅ ሱቆቿ፣ ወዘተ. ተደምረው ፒኮሎ ሮማ (ትንሽቱ ሮማ) እየተባለች የምትጠራ እንድትሆን አብቅተዋት ነበር፡፡ አንዳንዶቹም ከአፍሪካ ውስጥ የሚወዳደራት ከተማ እንዳልነበረ ይገልጻሉ፡፡ በእርግጥም ጸሐፊው በ1958 ዓ.ም. እና ከዚያም በኋላ አስመራን እንዳያት መንገዶቹ የሚመቹ ነበሩ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሁሉም ዘመናዊና ያማሩ ሕንፃዎች አስቀድሞ (በ1990/91) የተገነባው የአስመራ ገዥ ቤተ መንግሥት፣ ሲኒማ ኢምፔሮ፣ የኦርቶዶክስና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት፣ ታላቁ መስጊድ፣ በዋና ዋና መንገዶች የተገነቡ ባለ አራት ፎቆች ኢጣሊያ በመጀመርያዋ ቅኝ ግዛት፣ እነርሱ ‹‹ኮሎኒያ ፕሪሞጀንታ›› (እንደ ልጅ ከሚቆጠሩት ቅኝ ግዛቶች አንጋፋዋ) እንድትባል አድርገዋት ነበር፡፡ ጸሐፊው እ.ኤ.አ. በ1980 ወደ ኢጣሊያ (ሮም፣ ፍሎሬንስ፣ ሞቴካቲኒ፣ ኮሎዲ) ሄዶ በነበረበት ጊዜ የአስመራና የእነዚህ ከተሞች በተለይም የሞንቴካቲኒ ቴርሚ ከተማ መመሳሰል አስደንቆት ለጋዜጠኞች አስተያየቱን ሰጥቶ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

የአስመራ ከተማ ውብ ሆና ስትገነባ ፈርዲናንዶ ማርቲኒ የተባለው የመጀመርያው ገዥ (ከ1928 እስከ 1934 ባሉት ስድስት ዓመታት ውስጥ የገዛት) እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህንንም ያደረገችው ኢጣሊያ በቅኝ ግዛቶቿ ዘመናዊ ዕድገት በማምጣት ላይ መሆኑን ዓለም እንዲመሰክርለት ስትል መሆኑ ይታወሳል፡፡ አስመራ ያኔ ከነበራት 98 ሺሕ ነዋሪ ውስጥ 53 ሺሕ ኢጣሊያውያን፣ ሌሎቹ ኤርትራውያን፣ ኢትዮጵያውያን፣ ዓረቦች፣ ሱዳናውያን፣ ወዘተ. ነበሩ፡፡ ያኔ በመላው ኤርትራ የነበሩ ኤርትራውያን ከ75 ሺሕ እንደማይበልጡ እ.ኤ.አ. በ1928 የወጣው የኢጣሊያ የሕዝብ ቆጠራ ያመለክታል፡፡

የአስመራ ከተማና፣ የምፅዋ ወደብ እጅግ ዘመናዊ ሆነው የተቀየሱ ከመሆናቸውም በላይ የባቡር ሐዲድም ከምፅዋ እስከ አስመራ፣ ከአስመራ እስከ ከረንና አቆርዳት ድረስ ተዘርግቶ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከተራራ ወደ ተራራ የሚያሸጋግሩ በ71 ኪሎ ሜትር ርቀት የተዘረጉ የሽቦ መጓጓዣዎች ኬብል ባስ (ባጃጅ የሚመስሉ ሰዎች የሚሳፈሩባቸው ከተራራ ወደ ተራራ በተዘረጋና በሞተር በሚጠመለል ሽቦ አማካይነት የሚጓዙ) የመጓጓዣ አገልግሎቶች በቀን ከሰባት ሺሕ ኩንታል በላይ የሆነ ጭነት ከምፅዋ ወደ አስመራ፣ ከአስመራ ወደ ምፅዋ ያጓጉዙ ነበር፡፡

የስልክ፣ የፖስታና የቴሌግራፍ አገልግሎት በሁሉም አውራጃዎችና ወረዳዎች ተስፋፍቷል፡፡ አብዛኛው የከተማ ነዋሪ የሚጠቀመው በኤሌክትሪክ ነው፡፡ የዘመናዊ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ኑሮ አውታሩ፣ የዘመናዊ እርሻውና የኢንዱስትሪው መስፋፋትም በርካታ የጉልበት ሠራተኛ ከኤርትራና ከአጎራባቾቿ እንዲጎርፉ አድርጓቸዋል፡፡ የኢንዱስትሪው ዕድገት እንደ ተሰነይና ባረንቱ፣ አዲዑግሪ፣ አቆርዳት፣ ሰንአፈ ያሉ የገጠር ከተሞች ወደ ከተማነት ለመቀየር አብቅቷቸዋል፡፡

በእርሻ ረገድም ዘመናዊ እርሻ ልማት ተጀምሮ ነበር፡፡ በተለይም በአብዛኛው በኢትዮጵያ ግዛት ታይተውና ተሰምተው የማይታወቁ ሰፋፊ የጥጥና የአዝርእት፣ ሰፋፊ የአትክልትና ፍራፍሬ እርሻዎች፣ ዘመናዊ የከት ማደለቢያ ሥፍራዎች፣ ዘመናዊ ዶሮ ዕርባታ፣ መስፋፋት ጀምረው ነበር፡፡ የእርሻ መሬቶች አንድም እየተነጠቁ፣ ያለበለዚያም በርካሽ ዋጋ እየተገዙ በዘመናዊ ዘዴ ይታረሱ ስለነበር፣ ኤርትራውያንና ሌሎች በኤርትራ የሚኖሩ ጥቁሮች በከተማና በገጠር ወደ ላብ አደርነት መቀየር ጀምረው ነበር፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ በኢጣሊያ የተገነባው ሥራ ሁሉ ከመሀል አገር የሄዱ ሠራተኞች የተሳተፉበት፣ ላባቸውን ጠብ ያደረጉበት እንደሆነ ማንም ምንጊዜም ሊክደው የሚችል አይደለም፡፡ ዛሬ ኤርትራውያን ተብለው የሚጠሩትም በአብዛኛው ኤርትራን የገነቡት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡

የኢጣሊያ ቅኝ አገዛዝ ተወግዶ የእንግሊዝ ሞግዚት አስተዳደር በተተካ ጊዜም፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ኤርትራ ሄደው ኖረዋል፡፡ ኤርትራውያንም ሆነዋል፡፡ የእንግሊዝ ሞግዚት አስተዳደር ቀርቶ ከኢትዮጵያ ጋር በተዋሀደችበት ጊዜም በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ኤርትራ ሄደው ኤርትራውያን ሆነዋል፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ ብቻ ሳይሆን፣ በደርግ ጊዜም በርካታ ሲቪልና ወታደር ኢትዮጵያውያን ወደ ኤርትራ ሄደው በዝተው ተባዝተው ምድርን ሞልተዋታል፡፡ ይህንን እውነት የትኛውም ፖለቲካ ሊፍቅ የማይችለው ነው፡፡ ለምን? እንደገና ወደ ጋራ ታሪካችን እንመለስ፡፡

የጋራ ታሪካችን በፖለቲካ ምክንያት አይደበዝዝም

የጋራ ታሪካችን ከሲሚንቶ የበለጠ አጣብቆናልና ግንኙነታችን በፖለቲካ ምክንያት አይደበዝዝም ስንል ከቶ ያለ ምክንያት ከቶ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ አብዛኛው ግብፅ ከኢትዮጵያ ቀድሞ ትልቅ መንግሥት የነበረ ይመስለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግብፅን ታስገብር እንደነበረ የሚያውቀውም በጣም ጥቂቱ ነው፡፡ ዛሬ በግብፅ ከሚገኙ ጥንታዊ ኮረብታዎች ቅርሶች በኢትዮጵያውያን የተሠሩ መሆናቸው ሲነገረው ማመን የሚከብደው ይኖራል፡፡ ኤርትራን የምትጨምረዋ ኢትዮጵያ ከግብፅም ባሻገር እስከ ጥንታዊት ፐርሺያ ግዛቷን አስፋፍታ እንደነበር ለማወቅ ሲመራመር ልቡን የሚጠራጠርም ሊኖር ይችላል፡፡

ነገር ግን ኤርትራን የምትጨምረው ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በመላው ዓለም ስመ ገናና ሰፊ ግዛት የነበራት መሆኗን ጥንታውያኑ የግሪክ፣ የሮማ፣ የባይዛንታይን፣ የፊንቅ፣ የቻይና፣ የዓረብ ታሪክ ጸሐፊዎች በሰፊው ጽፈውላታል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ የሥልጣኔ ጮራን የፈነጠቀች አገር መሆኗን አሁንም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ (በተለይም በአክሱም፣ በአዱሊስ፣ በመጠራ፣ በቋሐይቶ፣ በይሓ፣ በእንደርታ፣ በውቅሮ፣ በላስታ፣ በጎንደር፣ ወዘተ.) ያሉ ቅርሶቿ ያረጋግጣሉ፡፡ ወደፊት ተቆፍረው የሚወጡና ታላቅነቷን የሚመሰክሩ መረጃዎችም ሩቅ ባልሆነ ጊዜ እንደሚወጡ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር የአንዳቸው ታሪክ ያለ አንዳቸው ታሪክ የተሟላ ሊሆን አይችልም፡፡ ለዚህም የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች አንድነት ጥቅል የማንነት ጥያቄን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ በመሠረቱ ማንነት ከእናት ማህፀን፣ በቤተሰብ፣ በጎረቤት፣ በአካባቢ፣ በቀበሌ. . . በአገር የሚዳብር ሲሆን፣ በአገር ደረጃ የሚገኘው አገራዊ ባህሪ ይባላል፡፡ በአገራዊ ደረጃ ከሚከሰቱት የማንነት መገለጫ ባህሪያት አንዱ ብሔራዊ ኩራት ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ 1985 እስከ 1988 ዓ.ም. ባለው ጊዜ በሰሜን ትግራይ ተዘዋውሮ እንደተመለከተው፣ ለብዙ ዓመታት በጦርነት እየታመሰ ፍዳውን ያይ የነበረ ሕዝብ ዕፎይታ አግኝቶ ነበር፡፡ ከዛላ አምበሳ ወደ ሰነዓፈ፣ ከዓድዋ ወደ ዓድቀይህ፣ ከሽሬ ወደ ሰራዬ፣ ከሌሎች ሥፍራዎች እየተነሳ ይንቀሳቀስ የነበረው ሕዝብ ጦርነት ያስከተለውን ችግር በአጭር ጊዜ ረሳ፡፡ በጣሊያን ጊዜ እንደሆነው ሁሉ ተለያይተው የነበሩ ወንድማማቾችና እህትማማቾች፣ አባትና ልጆች፣ ባልና ሚስቶች እየተገናኙ ደስታቸውን ገለጹ፡፡ ለመንግሥታቱም ምሥጋና አቀረቡ፡፡ ድሮውንም የነበረው የጋብቻ ትስስር ቀጠለ፡፡ አንድ ሆነ፡፡ ድንበር እየተሻገረ አንድ ቤተ ክርስቲያን መሳለም፣ በአንድ መስጊድ መስገድ ቀጠለ፡፡ ጸሐፊው ይህን መሠረታዊ የማንነት ጥያቄ ግን በሚገባ ተንትኖ ማየት ያስፈልጋል ብሎ ያምናል፡፡ ስለሆነም እንደሚከተለው ሐሳቡን ያቀርባል፡፡

ራሱን የሚያውቅ ሕዝብ አንድነቱ አይደበዝዝም

በመሠረቱ አንድ ሰው በማንነቱ ላይ ቁጥጥር ሊያደርግ አይችልም፡፡ ሌላ ለመሆን ቢፈልግ እንኳን በውስጡ ያለው ማንነቱ ‹‹አለሁ›› ብሎ ሳያውቀው አፈትልኮ ይመሰክርበታል፡፡ ሌላ የሆንን ቢመስለንም ማንነታችን ይከተለናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊ በግል አመለካከታቸው ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ‹‹እኔ እንደዚህ ነኝ›› ‹‹አይደለህም›› ሊባባሉም ይችላሉ፡፡ ሁለቱ በተናጠል ወይም በጋራ ከሌላ ሰው ጋር ሲወያዩ ሌላ ሰው በሁለቱ መካከል በሐሳብ አቀራረብ፣አገላለጽ፣ በሥነ ምግባር፣ በእንቅስቃሴ ልዩነት ላያይ ይችላል፡፡ ከእነዚህ ሁለት ሰዎች ጋር አንድ ምዕራብ አፍሪካዊ ወይም ደቡብ አፍሪካዊ ዘግይቶ ቢመጣና ቢቀላቀል ግን የተለየ መሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይታወቃል፡፡  ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች የሱዳን፣ የግብፅ፣ የጂቡቲ፣ የሱማሌ ተወላጆች ቢኖሩ የሱማሌና የጂቡቲዎቹ ሰዎች ከሱዳኖቹና ከግብፆቹ ይበልጥ ተመሳሳይ ባህሪ ይኖራቸዋል፡፡

ዊልያም ጀምስ የተባሉ የሥነ ባህሪ ሊቅ (1892) እኔነት ሁለት ደረጃዎች ሲኖሩት አንደኛው ራስን የማወቅ ሒደት ሲሆን፣ ሁለተኛው ራስን በሒደት ማወቅ ነው፡፡ ራስን ማወቅም ቁሳዊ እኔነት፣ ማኅበራዊ እኔነትና መንፈሳዊ እኔነት እንደሆኑ ይተነትናሉ፡፡ ማኅበራዊ እኔነት (ማንነት) ሌሎች ስለእርሱ የሚረዱት ሲሆን፣ ቁሳዊ ማንነት ደግሞ የእኔ ባዩ አካልና የእርሱ ንብረት ይሆናል፡፡ መንፈሳዊ ማንነት ደግሞ በውስጡ የሚሰማው የእኔነት ስሜቱ ነው፡፡ እውነተኛ ማንነት በውጭ ከሚንፀባቀው ጋር ይወዳደራል (ይመሳሰላል) ማለት አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልጹት ሮይ ኤፍ ባውመስተርና ማርክ ሙራቬን፣ ‹‹ማንነትን ከማኅበራዊ፣ባህላዊና ከታሪካዊ ዓውድ ጋር ማዋሀድ (ማስማማት) በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት ግለሰብ ሊመርጥ፣ ሊለውጥ፣ እንደሚመቸው አድርጎ ለማሻሻል ይችላል፣ ነገር ግን የእዚያ የግለሰብ ማንነት ህልውና እንዲኖረው ታሪክ፣ ባህል፣ ተቀራራቢ ማኅበራዊ ግንኙነት ሊኖር ይገባል፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

ስለማንነት ጉዳይ በርካታ ሊቃውንት ከጥንት ጀምሮ አስተያየታቸውን፣ ምክራቸውን፣ ፍልስፍናቸውን፣ አመለካከታቸውን ሰጥተውናል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ግርሃም ግሪን የተባለው ዕውቅ ደራሲ ሲሆን፣ እርሱም ‹‹የጉዳዩ ማለቂያ›› (The End of the Affair) በሚል ርዕስ በጻፈው መጽሐፉ፣ ‹‹እኔ የሚያሰኝህን ሁሉ ብትጥል ምን ትሆን ይሆን?›› ማለቱ ይጠቀሳል፡፡ መልሱምከሁለት ያጣ ጎመን’ የሚል ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያዊ የኢጣሊያ ቅኝ ገዥ መንግሥት ከኢትዮጵያዊነት ማንነት ውጪ የሆነ ሰው ሠራሽ ማንነት ቢሰጠው፣ ማንነት ላይ ላዩን ሊገልጽ በሚችል ባህሪው ሊያንፀባርቅ ቢችል እንጂ በውስጡ ሌላ ሊሆን አይችልም እንደ ማለት ነው፡፡ ወይም በተለምዶ ተዋናይ ቋሚ የሆነ ማንነቱን የማወቅ ችግር አለበት እንደሚባለው ነው፡፡ በእርግጥም አንድ ተዋናይ እንደተላበሰው ገጸ ባህሪ ላዕላዊ ማንነቱ ሊለዋወጥ እንደሚችለው ሁሉ፣ አንዳንድ የፖለቲካ ሰዎችም ያልሆኑትን ልሁን ቢሉ የራሳቸው ማንነት ሊጠፋባቸው ይችላል፡፡ ግሬይ ፉል የተባሉ የሥነ ባህሪ ሊቅም ይህን በሚለከት ‹‹የትናንቱ እኔ ከዛሬው እኔ ጋር ሥነ ባህሪያዊ ግንኙነት አላቸው›› በማለት ይገልጻሉ፡፡

የማንነት ምንነትን በተጨባጭ ለማሳየት እንዲቻል ቀደም ሲል የቀረቡት ሐሳቦች በምሳሌነት ቀረቡ እንጂ፣ ከዚህ ሰፋ ባለ መንገድም ማቅረብ ይቻላል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ማንነት በረጅም የታሪክ ሒደት የሚዳብርና ይህም በተለያዩ ባህሎችና አስተሳሰቦች የሚገለጽ መሆኑ ነው፡፡ ጆን ሎክ የተባሉ ታዋቂ እንግሊዛዊ ፈላስፋ ማንነትን ከንቃተ ህሊና ጋር አያይዘው ያቀርቡታል፡፡ ንቃተ ህሊና ደግሞ በደመ ነፍስ ከሚደረግ፣ ከሚኮንንና ከሚንፀባረቅ ባህሪ የተለየ ነው፡፡ ከኅብረተሰብ የረጅም ጊዜ ታሪክ፣ ባህል፣ እምነት ወዘተ. ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያውያንና የኤርትራውያን አንድነት በፖለቲካ ምክንያት ሊጠፋ አይችልም፡፡ የማንነት ጥያቄን እንዲህ በሰፊው ከተመለከትን ኤርትራን የማልማት ኃላፊነት የማን ነው? ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡

ኤርትራን እንደገና የማልማት ኃላፊነት የኢትዮጵያውያንም ጭምር ነው

እንደ እውነቱ ከሆነ ኤርትራ ከ30 እና ከ40 ዓመታት በፊት ታላቅ ነበረች፡፡ ጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የኤርትራን ክፍለ ሀገር ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሰኔ ወር 1970 ዓ.ም. በጠራው ጉባዔ እንደቀረበው ሁሉ፣ ከፌዴሬሽኑ በኋላ በአምስተኛው ዓመት (1957) ላይ በኤርትራ ክፍለ ሀገር የነበረው የኢንዱስትሪ ካፒታል ክምችት 16,739,000 ብር ነበር፡፡ በተቀሩት የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገሮች 44,000,000 ብር ነበር፡፡ ከአሥራ ሁለት ዓመታት በኋላ ግን (በ1969) በኤርትራ የነበረው የኢንዱስትሪ ካፒታል 153,597,000 ብር ሲገመት በተቀሩት ክፍለ ሀገሮች 188,768,000 ብር ብቻ ነበር፡፡ ምንጭ (statistical Abstract & Commercial Bank of Ethiopia Economy 1970)፡፡ ይህም ማለት በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ በኤርትራ ክፍለ ሀገር የኢንዱስትሪ ካፒታል ክምችት ዘጠኝ እጥፍ ሲያድግ በተቀሩት ክፍለ ሀገሮች ያደገው 4.5 ጊዜ ብቻ ነበር፡፡ ይህም ማለት 45 በመቶ የመላ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ካፒታል ክምችት በዚች 2,000,000 ሕዝብ ገደማ በሚኖርባት ክፍለ ሀገር ተጠራቅሞ ነበር፡፡

በዚህ ጉባዔ እንደቀረበው ሁሉ ኤርትራ ከኢትጵዮያ ጋር ከተዋሀደች በኋላ፣ የኢንዱስትሪዎች ምርት ሰፊ የኢትዮጵያ ገበያ አግኝቶ ስለነበር አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችም በተለይ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በየጊዜው ይከፈቱ ጀመር፡፡ በእንግሊዝ ጊዜ ወድቆ የነበረው የኤርትራ ኢኮኖሚ የመላ ኢትዮጵያ ቀላል ኢንዱስትሪ እምብርት ሆነ፡፡ ከፌዴሬሽን ጀምሮ በኢትዮጵያ አብዮት እስከ ፈነዳበት የመጀመርያው ዓመት ድረስ በኢኮኖሚ ደረጃ ተጠናከረ፡፡ ይህንን በአጠቃላይ የኤርትራ ቡርዣ አመጣጥ ብንለውም፣ ቡርዣውም ሆነ ወዝአደሩ ይበልጡኑ ከትግራይ ትግሪኛው ክፍል የመነጨ ነበር፡፡ የቆላው ሕዝብ በፊውዳሎቹ ነፃ አውጭ ነን ባይ ግንባሮች ታፍኖ እንዲያውም ከካፒታሊስት ግንኙነት ውጪ ተገለሉ፡፡ ለግንባሮቹ ያመረታትን ሁሉ ይተፋ ነበር፡፡ ነፃ አውጪ ነኝ ባዮች በተለይም የቆላውን ሕዝብ ጋጡት፡፡ ከልጁ አፍ ድረስ እየነጠቁ ይመዘብሩት ነበር፡፡ በሌላ በኩል ሽፍታ ተብሎ በሚሊታሪ ቢሮክራሲ የተፈረጀው ሥፍር ቁጥር አልነበረውም የሚል እውነታ እናገኛለን፡፡

ይህም እውነታ ኤርትራ ለ30 ዓመታት በተደረገው ጦርነት መውደሟን ያረጋግጣል፡፡ ጸሐፊው ባለፈው ዓመት በነሐሴ ወር  የበፊቷን ደማቋ አስመራ ሲጎበኝ በድንጋጤ ፀጥ ያለች ትመስላለች፡፡ ፋብሪካዎቿ በዝምታ ተውጠዋል፡፡ ወይም ሞተዋል፡፡ የፈራረሱና ወና የሆኑም አሉ፡፡ ውቧ ምፅዋ በቀላሉ በማታገግምበት ምክንያት ወደ ባድማነት ተቀይራለች፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ከአስመራ እስከ ምፅዋ በመኪና ሲጓዝ ያየው አንድ የጭነት መኪና ያውም የማዕድን ኮንቴይነር የተጫነ መሆኑ ነው፡፡ ከአስመራ ወደ ከረን ሲጓዝም ያየው ተመሳሳይ መሆኑ ነው፡፡ የአሰብም ወደብ ተመሳሳይ እንደሚሆን አይጠራጠርም፡፡ በምፅዋ ወደብ የተመለከታትም አንዲት አነስተኛ መርከብ ስትሆን፣ እርሷም የወርቅ ማዕድን የያዘ አፈር ጭና ወደ ቻይና የምትሄድ መሆኗን የአካባቢው ሰዎችን ጠይቆ ተረድቷል፡፡ ስለሆነም ይህች አገር እንድትነሳ፣ ከድሮ በበለጠም እንድታደግ መርዳት ያስፈልጋል፡፡ ሁለቱ እህትማማች አገሮች ሲያድጉ ሕዝባቸው ይበለፅጋል፡፡ ለመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጥረት በአንድ ዓመት ውስጥ ምን አፈራ?

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የኤርትራ ጉብኝት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ካከናወኗቸው ተግባራት አንዱ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረውን የተበላሸ ግንኙነት ወደ ተሻለ አቅጣጫ ለመለወጥ ያደረጉት ጥረት ነው፡፡ ይኸው ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. የተካሄደ ጉብኝት በኢትዮጵያና በኤርትራ ከ20 ዓመታት በላይ ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ለመቀጠል ያስቻለ ሲሆን፣ በዚህ ጉብኝታቸው በመላው ኤርትራ የነበረው ሕዝብ በደስታ ተቀብሎታል፡፡ አንዳንድ የኤርትራ ሱቆችና የገበያ መደብሮች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት ምክንያት በማድረግ የዋጋ ቅናሽ ያደረጉ ሲሆን፣ ጸሐፊው በዚህ ወር አጋማሽ በአስመራ፣ በምፅዋና በከረን ተዘዋውሮ ሲጎበኝም ይህንን እውነታ ጠይቆ ተረድቷል፡፡ አንዳንዶቹ ፎቶ ግራፍ ቤቶችና ሱቆችም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ፎቶ ግራፍ በትልቁ በማተም ‹‹አንዳርጋቸው›› የሚል ጽሑፍ ጽፈው በየመስኮቶቻቸው አድርገውበት ተመልክቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የአሰብና የምፅዋ ወደቦች ለኢትዮጵያ ፈጣን ልማት አስፈላጊ መሆናቸውን አምነው እምነታቸውን ይፋ ያደረጉት፣ ሥልጣን በያዙ በሦስት ወራት ውስጥ ነው፡፡ እጅግ በጣም ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ አሰብንና ምፅዋን ላለመጠቀም በእልህ የሄድንበት መንገድ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን ታሪክ በሰፊው በዝርዝር ያቀርበዋል፡፡ ምን ያህል እንዳንከራተተንም እንደዚሁ፡፡ ዋናው ቁምነገር ባለፈው መኖር አይደለም፡፡ አዲስ ተስፋ ሰንቆ መጓዝ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ ዓመት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኤርትራ ተጉዘው የሁለት ቀን ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ ይህም በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በማኅበራዊ ኑሮ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ለማስተሳሰር እንደሚሆን ጥልቅ የፖለቲካ ትንተና አያስፈልገውም፡፡ አንድ ጉብኝታቸውን በሚመለከት የተሠራጨ ፊልም እንደሚያሳየው፣ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኤርትራ የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ኢምባሲ ጽሕፈት ቤት መርቀው ከፍተዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች ከቤተ መንግሥት እስከ ኤምባሲው ጽሕፈት ቤት የተጓዙት በእግራቸው ሲሆን፣ እስከዚያ ድረስ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከአቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ጋር ያልተቋረጠ ውይይት በማድረግ ነበር የተጓዙት፡፡ ይህም የሚያመለክተው ኢትዮጵያ የኤርትራን አየር መንገድ በትልቁ ለመገንባት ዕቅድ እንዳላት ነው፡፡ ሁለቱ መሪዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሽከርካሪነት ወደ ነፋሲት፣ ከዚያም ወደ ደቀመሓረ መጓዛቸውን የሚያመለክተው ትዕይንት ሲሆን፣ በዚህም ጉዞ ከበለስ ግብዣው ባሻገር ከአስመራ እስከ ምፅዋ የተዘረጋ መንገድ እየሰፋ መሆኑ ተስተውሏል፡፡ ከአስመራ እስከ ምፅዋ የተዘረጋው መንገድ በጣሊያ ጊዜ የተሠራ ሲሆን፣ በደርግ ጊዜና ከነፃነት ወዲህ መጠነኛ ስፋት እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ ሆኖም ወደፊት ከምፅዋ ወደብ ተጭነው ወደ መሀል ኢትዮጵያ የሚገቡ ግዙፍ የጭነት መኪናዎችን እንደ ልብ ሊያስተናግድ ስለማይችል፣ በአስቸኳይ የማስፋት ሥራው መከናወን እንደሚኖርበት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ከአስመራ ደቀመሓረና ከአስመራ ዛላ አምበሳ የተዘረጋው መንገድም እንደዚሁ ወደ መሀል አገር የሚያገናኝ ስለሆነና ከፍተኛ ጭነት የሚያስተላልፍ በመሆኑ፣ በስፋትና በጥራት መታደስ እንዳለበት አያጠያይቅም፡፡ ይህም የሚያረጋግጠው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ነው፡፡

እንደ ማርቲን ፕላውት ያሉ ተንታኞች የፈለጉትን ቢሉም ጸሐፊው ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ኤርትራ ሄዶ በነበረበት ጊዜ ጸሐፍቱም ሆኑ ተቃዋሚዎቹ ከሚሉት የተለየ ሁኔታ እንዳለ በአስመራ፣ በምፅዋ፣ በከረን ባደረገው ጉብኝት ለመገንዘብ ችሏል፡፡ ዳሩ ግን የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ ግንኙነት እንዲህ በቀላሉ የሚናድ አይደለም፡፡ በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እምነት በሁለቱም አገሮች ሕዝብ መካከል እጅግ በጣም ኃያል የፖለቲካ ማዕበል ሊነሳ ይችላል፡፡ በሚነሳው ማዕበልም ብዙ ጥፋት ሊከሰት ይችላል፡፡ ተከስቷልም፡፡ ዳሩ ግን ማዕበሉ ፀጥ እንዳለ ብዙም ሳይቆይ የሕዝቡ አንድነት በፍጥነት ይቀጥላል፡፡ በቁስል ምክንያት ተጎድተው እንደነበሩ ሴሎች ሁሉ ወዲያውኑ ድነው የመጀመርያ መልካቸውን ይይዛሉ፡፡ ይህ ጠንካራ ግንኙነት በምን ላይ የተመሠረተ እንደሆነ በብዙ መንገዶች በኢትዮጵያ ታሪክ ተገልጿል፡፡ በተለይም በትውልድ፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህል ያለው ግንኙነት በሰፊው እየተገለጸ ቢኖር ተዝቆ አያልቅም፡፡ አዎን፣ በአዲስ ተስፋ ስንጓዝ ኢትዮጵያና ኤርትራ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ፡፡ መደምደሚያ

ያለፈው አለፈ፡፡ ወደፊት ግን በምፅዋና በአሰብ ወደቦች የኢትዮጵያንና የኤርትራን ወደቦች የሚያጨናንቁ በርካታ ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ የኤርትራ ወደቦችም እንደ ሌሎቹ አገሮች በወረፋ የሚገባባቸው ይሆናሉ፡፡ ከምፅዋና ከአሰብ እንዲሁም በሁለቱ አገሮች ስምምነት ወደፊት በቀይ ባህር ድንበር በሚሠሩ ወደቦች ምክንያት  በአቋራጭ መንገዶች በርካታ የጭነት መኪኖች ይርመሰመሳሉ፡፡ አሰብና ምፅዋ ካሸለቡበት ይነቃሉ፡፡ መላው የኤርትራ መንገዶች እንደ ኢትዮጵያ መንገዶች ሁሉ በጭነትና በሕዝብ መጓጓዣ መኪኖች ይጨናነቃሉ፡፡ መኪናውም ስለማይበቃ የባቡር መስመሮች በቅርቡ ይዘረጋሉ፡፡ መንገዶች የባቡር መንገድ ስለማይበቁ በየወደቦቹ ያሉ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ሥራ ይበዛባቸዋል፡፡

ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ትልቅ አገርና በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ያላት  በመሆኗ አሰብና ምፅዋ ብቻ አይበቋትም፡፡ ጂቡቲም፣ በርበራም፣ ኪሲማዮም፣ ሞቃዲሾም፣ ሞምባሳም፣ ፖርት ሱዳንም ያስፈልጓታል፡፡ ትክክለኛ ራዕይ ካለን በሁሉም ወደቦች እየተጠቀምን ኢኮኖሚያችንን ለማፋጠን እንችላለን፡፡ ባለፈው ዓመት የዶ/ር ዓብይ ከቻይና በቀጥታ ወደ አሰብና ምፅዋ የተደረገ ጉዞም ከዚህ የመነጨ መሆኑን መገንዘብ አይከብድም፡፡ ሆኖም ሁሉም የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንደዚህ ያለ ቅን ሐሳብና ጉጉት በውስጣቸው ሊያድግ፣ ሊያብብና ሊያፈራ ይገባል፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ አንድ ታሪክ የሚጋራና በባህልም በቋንቋም በእምነትም፣ አንድ ላይ የተዋሀደ ነው፣ ተዋህዷል፡፡ ከዚህም ውህደት የሚለያየው የለም፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ እስካሁን ድረስ ያከናወኑት አንስደናቂ ተግባራት ሁሉ ከታሪካቸው፣ ከእምነታቸው፣ ከባህላቸው፣ ከኢኮኖሚያቸው ጋር ተያይዘው የተመዘገቡ ናቸው፡፡ እነዚህ አስደናቂ ድሎች እንደ ፖለቲካ ድባቡ ብቅ ጥልቅ እያሉ ቢኖሩ፣ አንዳንድ ጊዜም ብሩህ ሰማይ ውልብ ብሎ በሚያልፍ ደመና እንደሚሸፈነው ሁሉ የተደበቁ ቢመስልም ከምድረ ገጽ በማንኛውም ኃይል ተፍቀው አይጠፉም፡፡ እንዲህ እንዳሁኑ ሁኔታው ሲመቻችና ሰላሙ ሲሰፍን ያብባሉ፣ ይጎመራሉ፡፡ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚታየው በምሥራቅ አገሮች አፍሪካ የሚታየው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለሪካዊ መነቃቃት ቀጣይነት የሚኖረውና ሁለተናዊ ትስስሩ ወደ ዘላቂ አቅጣጫ የሚጓዝ ከሆነ፣ ከሌላው የበለጠ የኢትዮጵያንና የኤርትራን ሕዝብ የሚጠቅም በመሆኑ የሚሻለን አንድ መሆኑ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...