ኦሞቲክ ጠቅላላ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥር የሚተዳደረው ፓራዳይዝ ሎጅ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ለቱሪስት መዳረሻ በሆኑ አካባቢዎች 15 ሎጆችን እንደሚገነባ አስታወቀ፡፡
ረቡዕ ሐምሌ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢያሱ ወሰን እንዳስታወቁት፣ ፓራዳይዝ ሎጅ ሆቴልና ሪዞርት፣ ሞናኮ አውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግ፣ ኦሞቲክ አስመጪና ላኪ፣ ፓራዳይዝ ሎጅ/ቱርሚ፣ ኦሞቲክ የቆርቆሮ ማምረቻ ፋብሪካንና ሌሎችንም በሥሩ ያጠቃለለው ማኅበር ከ15 ሎጆች ግንባታ በተጨማሪ ጂንካና ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ ሆቴሎችን ለመገንባት አቅዷል፡፡ ኩባንያው በ2012 ዓ.ም. በርካታ የማስፋፊያ ግንባታዎችን እንደሚካሂድም አስታውቀዋል፡፡
የማስፋፊያ ሥራዎች ከሚከናወንባቸው መካከልም ፓራዳዝድ ሎጅ አንዱ ነው፡፡ ፓራዳይዝ ሎጅን ከነባር ይዞታውና አሠራሩ ለማሻሻል በአምስት ሺሕ ዶላር የሚከራዩ በፕሬዚደንሻል ደረጃ አገልግሎት የሚሰጡ የመኝታ ክፍሎችን በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ኃላፊው ጠቅሰው፣ የስፓ አገልግሎቱም አነስተኛ በመሆኑ ወደ ዓለም አቀፋዊ ይዘት በመቀየር ሁሉን ያሟላ ሰፊ ስፖ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ለማስፋፊያው 100 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግ የገለጹት አቶ ኢያሱ፣ ገንዘቡ 30 በመቶ በድርጅቱ የሚሸፈን እንደሆነና 70 በመቶ ደግሞ ከባንክ ብድር እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በ1999 ዓ.ም. የተመሠረተው ኩባንያው 340 ቋሚና 500 ጊዜያዊ ሠራተኞች ሲኖሩት፣ የ20 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘቱንም አቶ ኢያሱ ገልጸዋል፡፡ አሁን ካለው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ‹‹ከምንም ነገር በላይ የሰላም ነገር ድርድር የለውም፡፡ ስለዚህ ሰላምን ማምጣት የመሪዎቻችን ብቻ ግዴታ ሳይሆን፣ የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው፤›› ያሉት አቶ ኢያሱ፣ ‹‹ባለሀብት የሚመጣው ሊጠቅመን ነው፡፡ ስለዚህ አለመረጋጋቱን ለማጥፋት ሕዝቡም፣ የሃይማኖት አባቶችም፣ ተማሪዎችም፣ ወጣቶችም፣ ፖለቲከኞችም አንድም ብርጭቆ እንዳትሰበር የሁሉም ጥረት ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡