Friday, December 8, 2023

በጀመረበት ፍጥነት መጓዝ ያልቻለው የኢትዮ ኤርትራ ዳግም ግንኙነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በ2010 ዓ.ም. ወርኃ መጋቢት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ሲከናወኑ የነበሩ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ባስከተለው ግፊት በገዥው ግንባር የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የአመራር ለውጥ ተደርጎ ወደ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ካከናወኗቸው ዓበይት ተግባራት መካከል፣ ለሁለት አሥርት ዓመታት ያህል ተቋርጦ የነበረውን የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት እንደገና ማስጀመራቸው አንዱ ነው፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ካካሄዱት ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት ምንም እንኳን በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቅቆ የአልጀርስ ስምምነት ቢፈረምም፣ ስምምነቱን ተፈጻሚ ማድረግ ላይ በተፈጠረ አለመግባባት ሁለቱ አገሮች ጦርነትም ሰላምም በሌለበት መፋጠጥ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ፡፡

ይህ ፍጥጫ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ መሠረት የዛሬ ዓመት ገደማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ባቀረቡት የሰላም ጥሪ አማካይነት የተቋጨ ሲሆን፣ የሰላሙን ጥሪን ተከትሎ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ምላሽ ታክሎበት ሁለቱ አገሮች ግንኙነታቸውን ዳግም ማደሳቸው እንደ ስኬት ተቆጥሮ የበርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም የተለያዩ መንግሥታት መሪዎች አድናቆታቸውን ቸረውት ነበር፡፡

ይህ የግንኙነት ማደስ፣ እንዲሁም ጠላትነትን የማስወገድ ስምምነት በርካታ ተቋርጠው የነበሩ እንቅስቃሴዎች ዳግም እንዲጀመሩ ያደረገ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ የስልክ አገልግሎት መጀመር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀን ሁለቴ በረራ ማድረግ፣ የድንበር መከፈትና ድንበር አካባቢ ከተሞች በሚኖሩ የሁለቱም አገሮች ዜጎች ገበያ መጀመር ዋነኛዎቹ ናቸው፡፡

ምንም እንኳን ተከፍቶ የነበረው ድንበር በቂና ተገቢ ማብራሪያ ባልተሰጠበት ሁኔታ መልሶ ቢዘጋም፣ የድንበሩ መከፈት በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረውን መለያየት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን እንዲሻሻልና ለውጥ እንዲያሳይ ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡ ነገር ግን የድንበሩ መከፈትም ሆነ ግንኙነቱን በማደስ ተፈጥሮ የነበረው ደስታና ፈንጠዝያ ለመትነን የወራት ዕድሜ በቂው ነበር፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ሁለቱ አገሮች ፈጣን የሚባል የወዳጅነት ስሜት ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ በሳዑዲ ዓረቢያ የሁለቱ አገሮች መሪዎች የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ንጉሥ ለሁለቱ አገሮች መሪዎች ላሳዩት ‹የሰላም ወዳድነት› በሚል የአገሪቱን የክብር ሜዳልያ ሸልመዋቸው ነበር፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ የተደረገው የሰላም ስምምነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝና የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት በእማኝነት የተገኙ ሲሆን፣ ስምምነቱም በቅጡ ያልተብራሩ አምስት ነጥቦችን ያካተተ እንደሆነ ተዘግቦ ነበር፡፡ ከስምምነቱ መፈረም ጀምሮ በርካቶች የስምምነቱ ነጥቦች በዝርዝር  ለሕዝብ ይፋ ይሁን በማለት ሲወተውቱ የነበረ ቢሆንም፣ የስምምነቱ ዝርዝር ነጥቦች ምን ምን ሐሳቦችን እንዳካተቱ ሳይታወቅ በተስፋና በደስታ ተሞልቶ የነበረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በጀመሩበት ፍጥነት መጓዙ አጠራጣሪ መሆኑን የሚያወሱ በርካቶች ነበሩ፡፡

ነገሮች በጀመሩበት ፍጥነት መጓዛቸውን ከማቀዝቀዛቸው በፊት በሁለቱ አገሮች መሪዎች አማካይነት የተጀመረው ጉብኝትና የአብሮነት መንፈስ ተስፋፍቶ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ የሕዝብ ለሕዝብ ልዑካን ቡድኖች ወደ አስመራና አዲስ አበባ ግንኙነቱን ማጠናከር ዓላማው ያደረገ ጉዞ አድርገውም ነበር፡፡

ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጣ 55 የልዑካን ቡድንን ያካተተ የኤርትራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት መጥቶ ነበር፡፡ በወቅቱም በአዲስ አበባ፣ በሐዋሳ፣ በባህር ዳር ጉብኝቶችን ከማድረጉ ባለፈ የሁለቱን አገሮች አንጋፋ ከያኒያንን ያካተተ የሙዚቃ ድግስም ተዘጋጅቶ ነበር፡፡

የበርካቶች ሙገሳና አድናቆት ተችሮት የነበረው የሁለቱ አገሮች አዲስ የሰላም ስምምነት መጀመርያ ላይ ከነበረው የወዳጅነት መንፈስ መዝለቅ የቻለው ለጥቂት ወራት ያህል ብቻ ነበር፡፡ ግንኙነት ተቀዛቅዟል እየተባለ በሚገለጽበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከሳምንት በፊት ወደ አስመራ አቅንተው የሁለቱ አገሮች ግንኙነትን የበለጠ ማጠናከርን፣ እንዲሁም የስምምነቱን ነጥቦች መተግበር ስለሚቻልባቸው ሁኔታዎች መወያየታቸውን አስታውቀዋል፡፡

አንድ ዓመት ያስቆጠረው የሁለቱ አገሮች አዲስ ግንኙነት በአንዳንዶች ዘንድ በጀመረው ፍጥነት አለመጓዙ እየተነቀሰ ዋነኛ ምክንያቱ ግንኙነቱ ተቋማዊ አለመሆኑ፣ እንዲሁም በመሪዎች ደረጃ ብቻ የተደረገ በመሆኑ ነው በማለት ትችት የሚቀርቡበት አጀንዳ ሆኗል፡፡

ሌሎች ደግሞ የሁለቱን አገሮች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶችን እንዴት ማረቅ ይቻላል የሚል ወጥ የሆነ ፍኖተ ካርታ በሌለበት ሁኔታ የተፈረመው የሰላም ስምምነትና የተጀመረው ዳግም ግንኙነት፣ ከዚህ በላይ ሊጓዝ አይችልም በማለት ከመጀመርያው የስምምነቱ ነጥቦች ተለይተው ባለመቀመጣቸው የተፈጠረ እክል ነው የሚል አስተያት ይሰነዝራሉ፡፡

ባለበት የቆመው ስምምነት

የዛሬ ዓመት ገደማ የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ዳግም ሲጀመር ያስተዋለ ሰው በዓመቱ ግንኙነቱ የሚደርስበትን ደረጃ ሲገምት በርካታ መላምቶችን በመሰንዘር ግንኙነቱ ምሳሌ ሊሆን የሚችል፣ ወዘተ በማለት የሚገለጽ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዓመት በኋላ በስምምነቱና ግንኙነቱ ዙሪያ የሚሰጡ አስተያየቶች ግን ስምምነቱ ባለበት መቆሙን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡

ከዚህ አንፃር ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፖለቲካና የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኝ፣ ‹‹ከድሮም ጀምሮ ቢሆን በአገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ትኩሳት ሲኖር የኤርትራን ካርድ የመምዘዝ ነገር ነው የነበረው፡፡ በመሪዎች ደረጃ ሲደረጉ የነበሩ ስምምነቶች የሁለቱን አገሮች ጥቅምን መሠረት በማድረግ የሚቃኙ አይደሉም፤›› በማለት፣ የዛሬ ዓመት የተደረገው ስምምነት በዚህ ጥላ ውስጥ የተደረገ በመሆኑ አሁን ያለበትን ቅርፅና ሁኔታ ለመያዝ መገደዱን ይገልጻሉ፡፡

በተመሳሳይ የጂኦ ፖለቲካ ተንታኝና በሁለቱ አገሮች ግንኙነትና በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ዙሪያ ጽሑፎችን በማቅረብ የሚታወቁት አቶ ልዑልሰገድ ግርማ በበኩላቸው ስምምነቱ በጀመረበት ፍጥነት ያልተጓዘበት ምክንያት፣ ‹‹በሁለቱም አገሮች እኩል ዝግጁነት ባለመኖሩ ነው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

በማከልም፣ ‹‹የሁለቱም አገሮች መሪዎች ሰላም ማምጣት መልካም እንደሆነ ከማሰብ አሊያም ከመመኘት ውጪ ስምምነቱን ተከትሎ በዘላቂ በሰላም፣ በኢኮኖሚ፣ በባህላዊ ትስስር፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ እንዴት እንተባበራለን የሚሉ ጉዳዮችን የሚቃኝ ፍኖተ ካርታ በሌለበት ሁኔታ የተከናወነ ነው፤›› ብለው፣ የሁለቱ አገሮች ስምምነት ወደሚፈገለው ደረጃ ይደርስ ዘንድ በቅጡ የተደራጀና የተቃኘ ፍኖታ ካርታ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ይሰጣሉ፡፡

የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በቅርበት የሚከታተሉ የፖለቲካ ተንታኞችና ምሁራን ስምምነቱ ከተፈረመበትና ግንኙነቱ ከታደሰበት ጊዜ አንስቶ ከሚጠይቋቸውና ከሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች መካከል ግልጽ የሆነ ፍኖተ ካርታ አስፈላጊነትን፣ በልሂቃንና በፖለቲከኞች ደረጃ የተጀመረው ግንኙነት ወደ ሕዝብ ለሕዝብ ደረጃ እንዲወርድ፣ ስምምነቱም ሆነ እርሱን ተከትሎ የሚደረገው ግንኙነት ተቋማዊና ሕጋዊ ማዕቀፍ ይበጅለት የሚሉ ናቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሁሉንም በሚያስማማ ሁኔታ የሁለቱ አገሮች መሪዎች የሚያደርጓቸው ድርድሮችና ስምምነቶች ለሕዝብ በወቅቱ ይፋ እንዲሆኑ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የተጀመሩት ግንኙነቶች የአልጀርስ ስምምነትን ከመተግበር አንፃር የሚኖራቸው ሚና ምንድነው የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ መመለስ መቻል አለበት የሚል ነው፡፡

በዚህ መሠረት አቶ ልዑልሰገድ፣ ‹‹የአልጀርስ ስምምነት እንዴት ነው ተግባራዊ የሚሆነው? በግልጽ አልተቀመጠም፤›› በማለት ሙግቱን ያጠናክሩታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ‹‹በትግራይ ክልልና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለው ጨዋታ ፈር መያዝ አለበት፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው ጨዋታ ካልጠራ ስለአልጀርስ ስምምነትም ሆነ በአጠቃላይ ስለተጀመረው የሰላም ግንኙነት መናገር የሚቻል አይመስለኝም፤› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በተመሳሳይ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የፖለቲካና የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኝ፣ ‹‹የአልጀርስ ስምምነት የኢትዮጵያን መሠረታዊ ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ነው፤›› በማለት የገለጹት ሲሆን፣ የዛሬ ዓመት የተደረሰው የሁለቱ አገሮች ስምምነት አጠቃላይ ግብ ምንድነው? በባህር በር ጉዳይ ምን ተባለ? የሚለው ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ ምላሽም ሆነ ማብራሪያ የለም፤›› በማለት፣ ከሁሉም በላይ ሁለቱ አገሮች የሚያደርጓቸው ግንኙነቶችም ሆነ ስምምነቶች ግልጽ መሆን እንዳለባቸው አጽንኦት በመስጠት፣ ‹‹እስካሁን የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ተጠያቂነትና ግልጽነት ባለው መንገድ እየሄደ አይደለም፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከስምምነቶች ግልጽ አለመሆን በተጨማሪ ተቋማዊ አለመሆን እንዲሁ በስምምነቱ ላይ ጥላ ያጠላበት በመሆኑ፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚፈለገውን ያህል አልሄደም ብቻ ሳይሆን ፈቀቅ አላለም ሲሉም ያክላሉ፡፡

ከዚህ አንፃር የፖለቲካና የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኙ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ይሸጋገር ዘንድ፣ ሦስት መሠረታዊ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣሉ፡፡ 

የመጀመርያው በፖለቲከኞችና በልሂቃን ደረጃ ሚገኘውን የሁለቱ አገሮች ግንኙነቱን መሠረት በማስያዝ ቀጣይነት ወዳለው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማሸጋገር የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የሁለቱ አገሮች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን እንዴት ማስታረቅ ይቻላል የሚለው ላይ መሥራት ነው፡፡

በዚህ ረገድ ሁለቱ አገሮችን የሚያስማሙ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሠሩ በሚያለያዩዋቸው ጉዳዮች ላይ ደግሞ ወደ ግጭት ሳይገባ እንዴት ይፈታ የሚለውን መንገድ በመከተል የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ሰላማዊና ዘለቄታዊ ማድረግ እንደሚቻል ያሳስባሉ፡፡

በሦስተኛነት ደግሞ ከባህር በር ጋራ የተያያዙ ጉዳዮችን እንዴት መፍታት ይቻላል የሚለውን የሚመለከት ነው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙያዎችን በማካተት በዓለም አቀፍ ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ የባህር በር የማግኘት መብት አለን ወይ የሚለውን ማስጠናት፣ በዚህ መሠረትም የባህር በር ጉዳይን በዘለቄታው መፍታት፤›› በማለት ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች አዲስ ግንኙነት የታሰበውን ያህል መጓዝ ያልቻለው ከኤርትራ በኩል ሙሉ ቁርጠኝነት ባለመኖሩ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ልዑልሰገድ፣ በዚህም ምክንያት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ይደርስ ዘንድ፣ ‹‹ከኤርትራ በኩል ሙሉ ቁርጠኝነት እስኪመጣ መጠበቅ ያለብን ይመስለኛል፤›› በማለት፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ የኤርትራ መንግሥት ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በመጨረሻም ዓምና የተፈረመው የሰላም ስምምነት ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ወጥ የሆነ ፍኖተ ካርታ ሲዘጋጅ እንደሆነ በመግለጽ፣ ከዚህ በተጨማሪም በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያና በሱዳን እየነፈሰ ያለው የለውጥ ንፋስ ወደ ኤርትራም ሊዛመት እንደሚገባ በመግለጽ፣ ‹‹ይህ ካልሆነ ግን ውኃ መውቀጥ እንዳይሆን ያሠጋኛል፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ከዓመት በፊት በነበረበት የደስታና ፌሽታ ድባብ ወጥቶ ወደ ፊት ምን ሊፈጠር ችላል? በሚል ባልተረጋገጠ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል፡፡ ተስፋው፣ ደስታውና ፌሽታው ይቀጥል ዘንድ የሁለቱን አገሮች ብሔራዊ ጥቅም ባስከበረ መንገድ የሚደረጉ ስምምነቶችና ስምምነቶቹን ተቋማዊ ማድረግ የሚለው ጉዳይ በአጽንኦት ይታይ የሚለው የብዙዎች ጥያቄና ሐሳብ ምላሽና ማብራሪያ ይሻል፡፡

ይህ ጥያቄና ሐሳብ እየተብላላ ባለበት ወቅት ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሒሩት ዘመነ፣ የሁለቱን አገሮች ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የንግድ ስምምነቶች እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የንግድ ልውውጡን ሕጋዊ ማድረግ ሰላማዊ ግንኙነቱን ከማጠናከር በላይ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣሉ ብለዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -