Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለዕረፍት ተበትኖ የነበረው ፓርላማ ለአስቸኳይ ስብስባ ተጠራ

ለዕረፍት ተበትኖ የነበረው ፓርላማ ለአስቸኳይ ስብስባ ተጠራ

ቀን:

የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ምክር ቤቶችንና የአካባቢ ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ ይወስናል

የባንክ ማሻሻያ፣ የጉምሩክና የመሬት ይዞታና ካሳ አከፋፈል አዋጆች ይፀድቃሉ

የሥራ ዘመኑን ሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ጨርሶ ለዕረፍት ተበትኖ የነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአስቸኳይ ስብሰባ ተጠራ፡፡ አስቸኳይ ስብሰባውንም ረቡዕ ሐምሌ 24 ቀን እንደሚያካሂድ ከምክር ቤቱ የወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

 ምክር ቤቱ በመጀመሪያ የሚመለከተው አጀንዳ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ ምክር ቤቶች እንዲሁም የአካባቢ ምርጫን በተመለከተ የሚቀርብለትን የውሳኔ ሐሳብ ነው፡፡ የውሳኔ ሐሳቡንም መርምሮ እንደሚያፀደቅ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

 በሕግ በተደነገገው መሠረት በአገሪቱ የሚካሄዱ ሁሉም ምርጫዎች በየአምስት ዓመቱ መከናወን ይገባቸው ነበር፡፡ በ2010 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበት የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች ምክር ቤቶችና የአካባቢ ምርጫን በወቅቱ በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው የፖለቲካ ቀውስና ይህንን ተከትሎ በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ለማካሄድ እንደማይችል በመግለጽ ምርጫው እንዲራዘምለት፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሐሳብ በ2010 ሚያዚያ ወር አቅርቦ ምርጫው ወደ 2011 ዓ.ም. እንዲተላለፍ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ምክር ቤቱ ምርጫዎቹ ተላልፈው በ2011 ዓ.ም. እንዲካሄዱ ቢወስንም፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ከተጠናቀቀ በኋላ በኃላፊነት ላይ ለመቆየት የማይችሉ በመሆኑ፣ በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ላይ ሊፈጠር የሚችለውን የአስተዳደር ሥልጣን ክፍተት ለመሸፈን የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ በከተማ አስተዳደሮቹ ማቋቋሚያ ቻርተሮች ላይ ተደርጎ በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በምክር ቤቱ ፀድቋል፡፡

በቻርተሮቹ ላይ የተደረገው ማሻሻያ የሁለቱም የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫ በየአምስቱ ዓመቱ እንደሚካሄድ፣ ነገር ግን ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ገጥሞ ምርጫውን ለማካሄድ ካልተቻለ ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ፓርላማው ሊወስን እንደሚችል፣ ይህ በሚሆንበት ወቅትም በሥራ ላይ ያለው የከተማ አስተዳደር ምክር ቤትና ካቢኔ ምርጫው ተካሂዶ እስኪተካ ድረስ በሥልጣን ላይ እንዲቆይ የሚደነግግ ነው፡፡

 ይሁን እንጂ በ2011 ዓ.ም. እንደ አዲስ የተደራጀውና አዳዲስ የቦርድ አመራሮች የተሾሙለት ምርጫ ቦርድ የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ እንዲሁም የአካባቢ ምርጫን በ2011 ዓ.ም. ለማካሄድ እንደማይችል ጠቅሶ ፓርላማው ተገቢ ነው የሚለውን ውሳኔ እንዲሰጥበት ከሳምንት በፊት ጠይቋል፡፡

 ለአስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው ፓርላማም በዚሁ ጉዳይ ላይ የሚቀርብለትን የውሳኔ ሐሳብ መክሮ እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም የባንክ ሥራ አዋጅን ለማሻሻል ቀርቦለት የነበረ ረቂቅ አዋጅን ሲመረምር የቆየው የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀርበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል፡፡

ይህ አዋጅ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ዝግ ሆኖ የቆውን የባንክ ዘርፍ ክፍት በማድረግ በባንክ የሥራ ዘርፍ ሀብታቸውን የማዋልና የመሰማራትን ዕድል የሚሰጥ ድንጋጌን በዋናነት የያዘ ነው፡፡

ከባንክ ሥራ አዋጅ ማሻሻያ በተጨማሪ የጉምሩክ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ፓርላማው እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል፡፡ ይህ ረቂቅ አዋጅ ከያዛቸው ጉዳዮች አንዱ ጭነት አመላላሽ ተሽከርካሪዎች የአቅጣጫ መጠቆሚያ ቴክኖሎጂ በተሽከርካሪዎቻቸው ላይ እንዲገጥሙ የሚያስገድድ ነው፡፡ በዚህም መሠረት መሣሪያውን ያልገጠመ የማጓጓዣ ባለንብረት የወጭና ገቢ ዕቃ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደማይችል አዋጁ ይደነግጋል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት አዋጆች በተጨማሪ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጅ ላይም ፓርላማው ተወያቶ እንደሚወስን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...