ከ3.5 ቢሊዮን ብር እስከ 490 ሺሕ ብር ባለው ደረጃ ለ165 ግብር ከፋዮች በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ዕውቅና ባገኙት ምሽት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግዴታ እንዲወጡና መንግሥትም የሕዝቡን ገንዘብ እንደማይሰርቅ በመግለጽ፣ ‹‹ገንዘባችሁን አንሰርቅም ገንዘባችንን አትስረቁ›› የሚል ጥሪ አቀረቡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ለግብር ከፋዮቹ የማበረታቻ ዕውቅና ሽልማት ከሰጡ በኋላ እንደተናገሩት፣ ዘንድሮ በዝቅተኛ የደመወዝ እርከን ላይ ለሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ሠራተኞች የተወሰነ የደመወዝ ማስተካከያ ተደርጓል፡፡ ይህም የሆነው ዘንድሮ መጠነኛ የገቢ መሻሻል በመኖሩ እንደሆነ ሲያብራሩም፣ ከ‹‹ለሸገር ገበታ›› 2.2 ቢሊዮን ብር ገቢ በአንድ ምሽት መገኘቱን ጨምሮ ከቀረጥና ከአገር ውስጥ ገቢ ግብር የተገኘው 198 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሆነ አክለዋል፡፡ እንዲህ ያሉ አኃዞችን በመንተራስ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ከሞትና ከግብር የሚቀር ማንም የለም፤›› በማለት፣ ከ2,000 ዓመታት በፊት ከነበረው የሮማ ሥርዓት ጋር በማገናኘት ስለግብር ግዴታ አብራርተዋል፡፡
በሮማ መንግሥታት አስተዳደር ወቅት የታክስ አስተዳደርና የዜጋ አስተዳደር ሥርዓት መሥርተው ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሮማውያን ‹‹የቄሳርን ለቄሳር›› የሚለውን ብሒል እስከማስረፅ በመድረሳቸው እንደሚታወሱ ገልጸው፣ አሜሪካዊው ቤንጃሚን ፍራንክሊን ከሚታወቁባቸው ንግግሮች መካከል ስለታክስና ስለሞት የተናገሩትን አጣቅሰዋል፡፡ ‹አዲሱ ሕገ መንግሥታችን ታውጇል፡፡ ለዘለቄታው የሚቆይም ይመስላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ዓለም ከሞትና ከታክስ በቀር በምንም ነገር እርግጠኛ መሆን አይቻልም› በማለት እ.ኤ.አ. በ1789 የተናገሩትን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም ግብር ከፋዮች በአግባቡ እንዲከፍሉ፣ መንግሥትም የሰበሰበውን ግብር በአግባቡ እንደሚያስተዳድር በመግለጽ፣ ‹‹ገንዘባችሁን አንሰርቅም ገንዘባችንን አትስረቁ›› በማለት ነጋዴዎችን አሳስበዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ይፋ እንዳደረጉት፣ በ2011 ዓ.ም. 198.2 ቢሊዮን ብር ታክስ ተሰብስቧል፡፡ ከዚህ ቀደም ከሚሰበሰበሰው የ13 በመቶ ጭማሪ የታየበት ግብር በመሰብሰብ በጀት ዓመቱን ተጠናቋል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የሚኒስቴሩ የ2011 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምን በሚመለከት ሲገልጹ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ213 ቢሊዮን ብር የታክስ ገቢ እንዲሰበስብ ቢያውጅም፣ ተቋሙ ግን የታቀደውን ገቢ ወደ 241 ቢሊዮን ብር ከፍ በማድረግ ለማሳካት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ 198.1 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረው ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ከ2007 እስከ 2009 ዓ.ም. ከነበሩት የዕቅድ ዓመታት ጋር ሲነፃፀር የ70፣ የ54 እና የ38 ቢሊዮን ብር ዕድገት ማሳየቱንም ጠቁመዋል፡፡
በ2011 በጀት ዓመት ዕቅድን በተሳካ ሁኔታ መፈጸም መቻሉን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በአሠራር ሥርዓትና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግና የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ሥርዓት በመዘርጋት ውጤት እንደተመዘገበ ተናግረዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ በተካሄዱ የግብር ንቅናቄ ኩነቶች ከግብር ከፋዩ ጋር ተቀራርቦ መሥራት በመቻሉ፣ በኅቡዕ ይንቀሳቀሱ የነበሩ 12 ሺሕ ነጋዴዎችን ወደ ግብር ሥርዓቱ ማስገባት መቻሉንም አስረድተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከፍተኛ ታክስ ከፋይ ሆነው ነገር ግን በተጭበረበረ ሰነድና በሐሰተኛ ማስረጃ ግብር የሰወሩትን በስም በማጋለጥ፣ በኮንትሮባንድ ላይ በተካሄደ ዘመቻ ጭምር ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ዕቃዎች መያዛቸውንም አስታውሰዋል፡፡ ገቢዎች ሚኒስቴር በ2012 በጀት ዓመት 224 ቢሊዮን ብር ገቢ እንዲሰበሰብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢፀድቅለትም፣ ዕቅዱን በመለጠጥ 248.3 ቢሊዮን ብር ለመሰብስብ ማቀዱን ወ/ሮ አዳነች መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በ2011 ዓ.ም. ለተመዘገበው የታክስ ገቢ በቀረጥና በአገር ውስጥ ገቢ ምድብ 165 ድርጅቶች ለሀቀኛና ለመልካም ግብር ከፋይነታቸው የፕላቲኒየም፣ የወርቅና የብር ደረጃ ያለውን የዕውቅና ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ በመክፈል የፕላቲንየም ተሸላሚ ከሆኑት ድርጅቶች ቀዳሚው ነበር፡፡ ሞኤንኮ በ1.51 ቢሊዮን ብር ሲከተል፣ ሳሊኒ በ1.4 ቢሊዮን ብር ሦስተኛ፣ ሐይኒከን በ885 ሚሊዮን ብር አራተኛ፣ ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ (ኖክ) በ757 ሚሊዮን ብር አምስተኛ ደረጃ ያገኙበትን የከፍተኛ ግብር ከፋይነት ሽልማት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀብለዋል፡፡ ብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት በ616 ሚሊዮን ብር፣ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ወይም ኮካ ኮላ በ508 ሚሊዮን ብር ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡
በጉምሩክ ገቢ የፕላቲንየም ተሸላሚ ከሆኑት መካከል ትራኮን ትሬዲንግ በ431 ሚሊዮን ብር ቀዳሚው ሆኗል፡፡ ትራንስ ኢትዮጵያ በ417 ሚሊዮን ብር ሁለተኛው ከፍተኛ ተሸላሚ ነበር፡፡ በወርቅ ደረጃ ከተሸለሙ ትልልቅ ኩባንያዎች መካከል በአገር ውስጥ ገቢ ሞሐ ለስላሳ 492 ሚሊዮን ብር ታክስ በመክፈል ሲሸለም፣ አዋሽ ባንክ በ491 ሚሊዮን ብር፣ ዳሞት ኢንዱስትሪያል ማይኒንግና ሚድሮክ ወርቅ በ319 ሚሊዮን ብር ተሸልመዋል፡፡
በብር ደረጃ ከተሸለሙት ውስጥ የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ በ124 ሚሊዮን ብር ቀዳሚው ሲሆን፣ የሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ኩባንያ የሆነው ማራቶን ሞተርስ ከቀረጥ የ155 ሚሊዮን ብር ገቢ በማስገኘት ሲሸለም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ኃይሌ የለመደብህ ወርቅ እንጂ ብር አይደለም›› በማለት በቀልድ መድረኩን አዋዝተውታል፡፡ የሪፖርተር ጋዜጣ አሳታሚ ድርጅት ሚዲያ ኤንድ ኮሙዩኒኬሽንስ ሴንተርና ሽመልስ በቀለ ሚዲያ፣ ከሚዲያ ዘርፍ በግብር ከፋይነታቸው በብር ደረጃ ከተሸለሙ ድርጅቶች ውስጥ ተካተዋል፡፡