በኪሩቤል ፍሬሰንበት
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ዕድሜው ለሥራ የደረሰና ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስ ወይም የማንቀሳቀስ ድርሻውን መወጣት የሚችለውን ኃይል እንዳየ የኢኮኖሚ አቅሙ በሦስት መክፈል ይቻላል፡፡ የመጀመርያው በአንፃራዊነት በከፍተኛ የገንዘብ አቅም የሚንቀሳቀስ ባለሀብት፣ ሁለተኛው በመካከለኛ የገንዘብ አቅም በግል የሥራ ፈጠራ ተሠማርቶ ወይም በራሱ ጥረት ከዝቅተኛው የማኅበረሰቡ ክፍል በተሻለ ብቃት ላይ የሚገኝ መጠነኛ ገቢ ያለውን ሲሆን፣ ሦስተኛውና የመጨረሻው ክፍል ደግሞ በዝቅተኛ የገንዘብ አቅም የሚሠራ ወይም በሥራ አጥነት የሚገኝ ያህል ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከንጉሣዊ ሥርዓት ወደ ወታደራዊ ሥርዓት ስትሸጋገር በወቅቱ የነበረው መንግሥት ከላይ የሚገኘውንና በአንፃራዊነት በከፍተኛ የገንዘብ አቅም የሚንቀሳቀሰውን ኃይል በኢምፔሪያሊስት፣ በበዝባዥነትና በፊውዳልነት በመፈረጅ የመደምሰስ መንገድ መከተሉ አጠቃላይ ከነበረው የማያባራ ጦርነት ጋር ተደማምሮ ኢኮኖሚውን ወደ ማንቀላፋት አሸጋግሮት ነበር፡፡ ይህ በራሱ ጥረት ሀብት ያፈራውንና የሚያፈራውን ሁሉ በጅምላ (Categorically) በበዝባዥነት የመፈረጅ አስተሳሰብ አሁንም ተፅዕኖው በሥልጣን ላይ ባለው ትውልድ ይታያል፡፡ ከወታደራዊው መንግሥት መውደቅ በኋላ የተተካው ሥርዓት ወደመጀመርያው የሥልጣን ዘመን አካባቢ፣ ከሶሻሊስትነት በፈጣን አክሮባት ወደ ካፒታሊስትነት ተገልብጦ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ያለው ኢንቨስተር ከውጭ የመሳብ ፍላጎት ላይ ተጠምዶ የቆየ ቢሆንም፣ በሥልጣን ዘመኑ እየገፋ ሲሄድ በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ለሥልጣኑ ፈተና ሲሆንበት ሥራ አጡንና ዝቅተኛውን የማኅበረሰብ ክፍል ላይ ለማተኮር ሞክሯል፡፡ አሁንም ሲሞክር ይታያል፡፡ ከሶሻሊስትነት ወደ ካፒታሊስትነት ያደረገው ለውጥም ለውጭ ኢንቨስተሮችና ለፖለቲካው ታማኝ ለሆኑ የራሱ የፖለቲካ ደጋፊ መደብ እንጂ፣ ለሌላው ሲተርፍ አልታየም፡፡ ይህ በውጭ ባለሀብቶችና በፖለቲካ ታማኞች ላይ የተንጠለጠለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አሁን ላለንበት ውስብስብ ችግር ዳርጎናል፡፡
ባልተጠናከረ የመሀል መደብ ኢኮኖሚ ያለበት አገር ላይ በጥቂት ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስተሮችና የፖለቲካ ታማኞች ብቻ የአገርን ኢኮኖሚ ለማንቀሳቀስ ማሰብ ‘ተኩላን ዶሮ ጠባቂ’ ለማድረግ እንደ መሞከር ያለ የቂል ተግባር ነበር፡፡ በተግባርም ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነው ይኼ ነው፡፡ “ኢንቨስተሮቹ” እና የፖለቲካ “ታማኞቹ” ያለ ርህራሔ ለነገ እንኳን ሳይሉ ያገኙትን የዘረፉት የተኩላነት ባህሪ ስላላቸው ነው፡፤
በዚህ ወቅት ካለው የፖለቲካ ትኩሳት አንፃር የጽሑፉ ዓላማ ለተንኮል ፖለቲካ እንዳይውል የፖለቲካ “ታማኞቹን” ለጊዜው እንተውና ለዚህ የተኩላነት ባህሪህ እንደ ማሳያ ሊሆን የሚችሉት የካሬቱሪ ኩባንያ ዓይነት ኢንቨስተሮች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ የውጭ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያውያን የማይሰጥ ዕድልና እንክብካቤ ተደርጎላቸው የፕሮጀክት ዋጋን እንዳሻቸው በተጋነነ ዋጋ በማስገመትና 30 በመቶ የኢንቨስትመንት ድርሻ ከውጭ ይዘው የመጡ በማስመሰል (ለእዚህ የማጭበርበር ድርጊት በተዘዋዋሪ መንገድ የመጡበት አገሮች ኤክዚም ባንኮች ድጋፍ ያደርጋሉ) ፕሮጀክቱን ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የ”ሰባ በመቶ” ፋይናንስ ብድር ተብሎ በሚወጣ ገንዘብ ፕሮጅክቱን መቶ ከመቶ ከመሥራት አልፎ ፕሮጀክቱ ሥራ ሳይጀምር ይዘው መጡ የተባለውን የ30 በመቶ ድርሻ በካፒታል ዕቃዎች ግዥ በውጭ ምንዛሪ ወደ አገራቸው ወስደው ፕሮጀክቱ ሳይጀመር በትክክል ካወጡት ገንዘብ 233 በመቶ ወይም የተጣራ 133 በመቶ የሚደርስ ትርፍ ከባንኩ ካዝና ከመመዝበር፣ ይህ ምዝበራ ተመልካችና ጠያቂ እንዳይኖረው ከኢትዮጵያ ባንክ የወጣ ገንዘብ ተመልሶ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ኪስ መሙላቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው (የ133 በመቶ ቅድሚያ ትርፍ ቸር ሆነው ፕሮጀክቱን በእጥፍ ብቻ በተጋነነ ዋጋ ካስገመቱት ነው፡፡ አራት አምስት እጥፍ ካስገመቱ ፕሮጅከቱ ሳይጀመር ያላቸው ትርፍ ከ700 እስከ 800 በመቶ ሊደርስ ይችላል)፡፡ ካሩቱሪ የኢትዮጵያን ደን በኢትዮጵያውያን አስመንጥሮ ከሰል አክስሎ ለኢትዮጵያውያን ከሸጠ በኋላ፣ የአገርን መሬት ለራሱ ለባለ አገሩ ባንኮች አስይዞ ተበድሮ መጥፋቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ እዚህ ላይ ከሰል አከሰልክ፣ ደን መነጠርክ ተብሎ የታሰረውንና የተቀጣውን ኢትዮጵያዊ ማሰብ ነገሩን የበለጠ አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡
በዚህ መንገድ የሚመጣ ኢንቨስተር ከራሱ ኪስ ያወጣው መዋጮ ባለመኖሩና ሥራው ሳይጀመር ከበቂ በላይ ትርፍ ስለሚያገኝ ነው “ኢንቨስተሩ“ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጨርቄን ማቄን ሳይል ያለ ማቅማማት አገር ለቀው ውልቅ የሚለው፡፡ ባለቤቱ ‹‹የውጭ ኢንቨስተር ነበር የተበደረውን ዕዳ ሳይከፍል ከአገር ኮበለለ፤›› የሚባለውም ዜናም የሚበዛው ለዚህም ነው፡፡ ከልማት ባንክ ሃራጅ እንደሚወጣበት እየተነገረ ተጨማሪ ኢንቨስት አደርጋለው የሚል ኢንቨስተርም የምንሰማው ለእዚህ ነው፡፡ በአጠቃላይ የውጭ ኢንቨስተሮች ሥራ የለበሰውን ሸሚዝ አስወልቆ መልሶ ለባለ ሸሚዙ መልሶ የመሸጥና በባለ ሸሚዙ እንደ ባለውለታ የመቆጠር ዓይነት ከፍተኛ የማጭበርበር ሥራ ነው፡፡ በተለይም በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሠማሩ የውጭ ባለሀብቶች የኢትዮጵያን መሬት አስይዘው ከኢትዮጵያ ባንኮች በተበደሩት ገንዘብ የኢትዮጵያን መሬት በኢትዮጵያውያን በማሳረስ መልሰው ያመረቱትን ሰብል ለኢትዮጵያውያን በመሸጥ፣ በአገር ውስጥ የተገኘን ትርፍ በውጭ ምንዛሪ በጥቁር ገበያ ከማሸሽ የተለይ ሥራ ሲሠሩ አልታዩም፡፡ በአርባ ምንጭ አካባቢ የሙዝ እርሻ እንዳላቸው በሥራ አጋጣሚ ያጫወተኝ የህንድ ኢንቨስተር ወኪል ወደ ውጭ አገር የተመረተውን ሙዝ ኤክስፖርት ማድረግ አለማድረጉን ስጠይቀው፣ ውጭ አገር አንድ ኪሎ ሙዝ ብዙ የጥራት መሥፈርት እንዲያሟላ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት በ20 ብር ሲሸጥ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አሰስ ገሰሱን ጭምር ያለ ብዙ ድካም በኪሎ 22 ብር ስለምንሸጥ ለምን ኤክስፖርት እንዳደርጋለን ብሎ የመለሰልኝ ሳስበው፣ እንደ አገር ምንኛ በከፍተኛ ማንቀላፋት ውስጥ እንደምንገኝ ያስታውሰኛል፡፡
ቀድሞ ኢትዮጵያን ሊወር የመጣው ጣሊያን በፋሽስትነትና የቀለም የበላይነት እሳቤ መደብደቡንና ማሰሩ በራሱ ለመሥራት ስለሞከረ ወራሪ ብለን አባረርነው፡፡ አሁን ግን ዘመናዊው ኢንቨስተር የመደብደቡን ሥራ ለራሳችን ለኢትዮጵያውያን ሰጥቶ፣ ከካዝናችን ብር ውስዶ፣ በራሳችን ጉልበት አምርቶ፣ መልሶ ለራሳችን ሸጦ ኢንቨስተር እየተባለ በመሪዎቻችን ደጃፍ ላይ ቅድሚያ እያገኝ ተከብሮ ይኖራል፡፡ ከላይ ለመጥቀስ በሞከርኳቸው መንገዶችና በተለያዩ መንገዶች ከራሳችን ኪስ የተገኘውን ሀብትም በውጭ አገሮች ጥሪት ለመቋጠር ከሚንከራተቱ ኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሪ ከብሔራዊ ባንክ የምንዛሪ ተመን ላይ ዋጋ እየጨመረ በመግዛት ወደ አገሩ ያሸሻል፡፡
አንድ የአሜሪካ ዶላር 13 ብር በነበረበት ጊዜ የጥቁር ገበያው 16 ብር፣ በሕጋዊ ምንዛሪ ዶላር 16 ብር ሲገባ ጥቁር ገበያ 18 ብር፣ ቆይቶ ቆይቶም ብሔራዊ ባንክ የምንዛሪ ዋጋውን 28 ብር ሲያደርስ የጥቁር ገበያው 30 ብር እያለ የሚጓዘው በዋነኝነት በዚሁ ምክንት ነው፡፡ እንደ ሰሞነኛው ደግሞ የአገር ውስጥ የፖለቲካ መረጋጋት ሲጠፋ ልዩነቱን እስከ አሥር ብር በማድረስ ሀብትን ለማሸሽ ስለሚሞከር፣ እንዲህ ዓይነት የውጭ ኢንቨስተሮች ተመልካች እስካላገኙ ድረስ ብሔራዊ ባንክ አንድ የአሜሪካ ዶላር መግዣን አንድ ሺሕ ብር ቢያደርስም የጥቁር ገበያው ዋጋ በላዩ ላይ ጭማሪ በማድረግ እንደናረ ይቀጥላል እንጂ፣ ብሔራዊ ባንክ ከጥቁር ገበያ ጋር ተወዳድሮ የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን ሊያስተካክል አይችልም፡፡ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ውስጥ በብሔራዊ ባንክ በኩል ብቻ የሚላከውን የገንዘብ መጠን የአገሪቱ ቀንደኛ ኤክስፖርት ከሆነው፣ ቡና በላይ የውጭ ምንዛሪ የሚያመነጭ መሆኑንና ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሚላከው ገንዘብ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አንድ አምስተኛ እንኳን እንደማይሞላ ማስታወስ፣ በእነዚህ የውጭ ኢንቨስተሮች ምክንያት እየደረሰ ያለውን ጉዳት መገንዘብ ያስችላል፡፡
በእዚህ ምክንያት ያጋጠመውን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመፍተታት ብሔራዊ ባንክ ትርፉን በአገሩ ላይ የሚያፈሰውን የአገር ውስጥ አስመጪ ላይ ብቻ ትኩረቱን በማድረግ የውጭ ምንዛሪ መፍቀድን አቁሞ የኢምፖርት ሥራን በማዳከም የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን ለማሻሻል ቢሞክርም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የኑሮ ውድነት ከመፍጠርና የማኅበረሰቡን የመግዛት አቅም ከማመንመን ውጪ የተሻለ ውጤት ሊያመጣ ያልቻለውም ለእዚህ ነው፡፡ በአጠቃላይ ተኩላን የዶሮ ጠባቂ ማድረግ ማለት ይኼ ነው፡፡ በዚህ በውጭ ኢንቨስተር የአገርን ኢኮኖሚ ለማስተዳደር በሚደረግ ሙከራ በሚመጣ ችግር ምክንያት በዝቅተኛው የኢኮኖሚ ዕርከን ውስጥ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የመኖር ዋስትናቸው ጥያቄ ውስጥ ስለሚገባ የመንግሥት ራስ ምታት ይሆናሉ፡፡ ዝቅተኛውን የማኅበረሰብ ክፍል ወይም ሥራ አጡ በኢኮኖሚው ውስጥ በበቂ ሁኔታ ስለማይካተት አመፅ ለማንሳት ወደ ኋላ አይልም፡፡ የዚህ የኅብረተሰብ ክፍል ጥያቄም በቀላሉ ወደ ፖለቲካ ጥያቄ ማደግ ስለሚችል፣ መንግሥትንም ሆነ አገርን ለማጥቃት ለሚዘጋጁ ኃይሎች ጥሩ መሣሪያ ይሆናል፡፡ ጥያቄው በአንድ ጀንበር የሚፈታለት ስለሚመስለውም ይኼው የማኅበረሰብ ክፍል አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል አያመነታም፡፡
መንግሥትም ይህን ስለሚያውቅ እነዚህን የማኅበረሰብ ክፍሎች አነስተኛና ጥቃቅን በመሳሰሉ በበቂ ጥናት ላይ ያልተመሠረቱ ፕሮግራሞች መሥርቶ ተጠቃሚ በማድረግ የራሱ የፖለቲካ ደጋፊ እንዲሆኑ ብዙ ገንዘብ በጅቶ እላይ እታች ሲል ይታያል፡፡ ዕድሜው ላልደረሰ ልጅ ከአቅሙ በላይ የሆነ ሥራ ማሠራት ሕፃኑን እንደሚገድልና የነበረውን ዕድልና ተስፋ እንደሚያባክን ሁሉ ያልጠነከረ የማኅበረሰብ ክፍል ላይ በጀት ማፍሰስም እንዲሁ ትውልድ ገዳይ መሆኑ አይቀርም፡፡ ለችግር መውጫ እየተባለ ለሥራ ፈጣሪነት ከመንግሥት የሚለቀቀው ገንዘብ ሥራ ፈጠራን ሳይሆን፣ ሕገወጥ ስደትን ስፖንሰር እንዳደረገ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ከስደትና ከመባከን ውጪ ጥቃቅንና አነስተኛ ተብለው ለተደራጁ ወጣቶች በፈሰሰው ገንዘብ ወጣቶቹ እንዲሠማሩበት የተደረገው የሥራ መስክ በአብዛኛው ተጨማሪ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መፍጠሩ ለከተሜ ኑሮ የሚሆኑ ያለቁ የመገልገያ ዕቃዎችን ማምረት ስለሆነ፣ በዚህ መንገድ ወደ ገበያው የሚገባው ገንዘብ የኑሮ ውድነትን ሲፈጥር ይታያል እንጂ ኢኮኖሚውን በዘላቂነት ሲቀየር አይታይም፡፡
መንግሥት በሌብነት፣ በዘረኝነትና በሌሎች ችግሮች ቢኖሩበትም የጽሑፉ ዓላማ ኢኮኖሚ ላይ ስለሆነ፣ ለጊዜው እነሱን ትተን ያለ ዕውቀትና ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ፖለቲካን ብቻ ታሳቢ አድርጎ በሚመራው ኢኮኖሚ ምክንያት ወጣቱ ላይ ገንዘብ ቢያፈስም፣ የሕዝቡን ችግር ሊፈታ ስለማይችል ሥራ አጡንና ዝቅተኛው የማኅበረሰብ ክፍል ዘረፉህ፣ ሰፋሪዎች መሬትህን ወሰዱብህ፣ በሚል ተፃራሪ ያህሎች በእጃቸው ያደርጉታል፡፡ የሚያጣው ነገር ትንሽ ስለሆነ ፣በአፋጣኝ ችግሩ የሚፈታለት ስለሚመስለውና ስለማይፈራም ይህ የማኅበረሰብ ክፍል አመፅ ያነሳል፡፡ ተፃራሪም ይህን ኃይል ተጠቅሞ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ራሱ የቀሰቀሰው ኃይል ለራሱ ሥልጣንም ስለሚያሠጋ፣ ይህን አካል ለማስተንፈስ ባልተጠናና አዋጭ ባልሆነ መንገድ ገንዘብ ያፈስለታል፡፡ ለዓላማው መሳካት ላገዘው ሁሉ ችሎታ ለሌለውም ቢሆን፣ ሥልጣን ለመስጠት ይገደዳል፡፡ ይህም አገራዊ ኢኮኖሚውን ኪሳራ ላይ እንዲወድቅ ያደርግና የሁሉን ነገር ፈተና ወደ ጥያቄ ቁጥር አንድ ይመልሰዋል፡፡ በዚህ ዓይነት የፖለቲካ ትኩሳትን ለማብረድ እየተባለ በሚሠራ ሥራ ምክንያት የመካከለኛው የማኅበረሰብ ክፍል ለኢፍትሐዊ የኢኮኖሚ አስተዳደር ይጋለጣል፡፡ የተሳሳተ የኢኮኖሚ አመራር ሄዶ ሄዶ አገር ለማፍረስ ዳር ሲደርስ ከሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት እንደታየው ለኢትዮጵያዊው ባለሀብት የለም ወይም በከፍተኛ ዋጋ በጨረታ ውሰድ የሚባለው መሬት ለአመፅ ለተዘጋጀው ወጣት በነፃ ይከፋፈላል፡፡ በስንት ልፋት መሬት አግኝቶም በባንክ ዕዳ ሥራ የጀመረውም ቢሆን፣ የፖለቲካ ትኩሳቱ ሲያይል ሀብትና ንብረቱን አንሳ ተብሎ ያለማው የማዕድን ቦታ ተቀምቶ ለወጣቶች ተሰጥቷል ይባላል፡፡ ለመካከለኛው የኅብረተሰብ ክፍል የተነፈገው የባንክ ብድርም በጥቃቅንና በአነስተኛ ለተደራጀ ወጣት ይከፋፈላል፡፡
በዚህ የእሳት ማጥፋት ሥራም ኢትዮጵያ ውስጥ ከጓደኞቹ በርትቶ በትምህርቱ የገፋው ወጣት የትምህርት ዘመኑን በዋዛ ፈዛዛ ሲያሳልፍ ከነበረ ወጣት ያነሰ የኢኮኖሚ አቅም እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ በርትቶ የግል ሥራ ፈጠራ ላይ ያለው ወጣት እየተተወ በሥራ አጥነት አገር ሲያስቸግር የነበረ ወጣት የመሥሪያ ሼድና የገንዘብ ብድር ይሰጠዋል፣ መንግሥታዊ ኮንትራት በቀጥታ ያገኛል፣ ወዘተ.፡፡ በትምህርት ዓለም ውስጥ ሲታትር የነበረው ወጣት ሥራ አጥ ሆኖ ሲንከራተት ወይም በአነስተኛ ደመወዝ ሥራ ተሻምቶ እንዲያገኝ ሲሆን፣ ለመማር ፈቃደኝነት ያልነበረው ወጣት በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅ እየተባለ “ሚሊየነር” የሚሆንበት፣ በርትቶ ነግዶና ሥራ ፈጥሮ ሥራውን ለማሳደግ የሚሞክረው ወጣት እያለ ሥራ ከመሥራት ይልቅ አመፅ የሚያነሳው ወጣት ብቻ ድጋፍ የሚያገኝበት ሁኔታ፣ በአጠቃላይ በጠንካራው የወጣት ክፍል ተስፋ መቁረጥን አስከትሏል፡፡
አሁን በዚህ ወቅት በወጣቱ ላይ እየታየ ያለው ከምትለፋና ከምትጣጣር ወይ አመፅ አንሳ ወይም ወደ ውጭ አገሮች ተሰደድ የሚለው አስተሳሰብ መበራከትና ባለ ምጡቅ አዕምሮ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ሳይሆን፣ ለባዕድ አገር ዕውቀታቸውን ለመገበር የሚሽቀዳደሙበት ዋነኛ ምክንያት በአገር ውስጥ ያለው ይህ ሀቅ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ የሚመራውን ማኅበረሰብ በሚጠበቅበት ደረጃ መምራት የተሳነውና ስንፍና ሆነ ተንኮል የተጠናወተው መሪ ጥያቄ ሲበዛበት ሌብነት ሥራ ነው ብሎ ያውጅና ‘የራበው ውሻ ጆሮውን ቆርጠው ቢሰጡት ምግብ የሰጡት ይመስለዋል’ እንደሚባለው፣ ከራሱ ኪስ እየሰረቀ የሚኖር ማኅበረሰብ ይፈጥራል፡፡ ቀጥሎም የሚፈጠረውን የኢኮኖሚ ውጥንቅጥ በስግብግብ ነጋዴዎች እያሳበበ በወንበሩ ለመቆየት ይጥራል፡፡ በርትቶ መሥራት መልካም ነው ሳይሆን፣ ሌብነት ሥራ ነው የሚል መሪ የሚያይ ማኅበረሰብ በጤናማ ኢኮኖሚ ራሱን ሊያሳድግ አይችልም፡፡ አብዛኛው ሥራ ፈጣሪ የሚሆነው ወጣታችን ጊዜውን በአምራች በሆነ መንገድ ሳይሆን፣ ኢመደበኛ የኢኮኖሚ መስኮች ላይ በማፍሰስ እንዲጠመድ ያደረገውም ይህ ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ከጠዋት እስከ ማታ መንገዶች የሚጨናነቁትም በመደበኛ ኢኮኖሚ የሚያመርት ሳይሆን፣ በኢመደበኛ ኢኮኖሚ ከላይ ታች ሲዋትት የሚኖር ማኅበረሰብ ስለበዛ ነው፡፡ ይህ ውጤታማ ሊሆን የሚችል መካከለኛው የኅብረተሰብ ክፍል ለአፍታም ቢሆን ከሚኖርበት የባለሀብት እርገጥ ጉዞ ደከም ቢል ወደ ዝቅተኛው ማኅበረሰብ እንደሚወርድ ስለሚያስብ የሆዱን በሆዱ አድርጎ ሲፍጨረጨር ያኖራል፡፡ ለመንግሥት ቀጥተኛ ሥጋት ስለማይሆነውም መንግሥትም ዞር ብሎ አያየውም፡፡
በራሱ ጥረት በርትቶ በኢኮኖሚና በዕውቀት የጎለመሰውን መካከለኛው የማኅበረሰብ ክፍል ወደ ላይ እንዳያድግ በፋይናንስ፣ በመሥሪያ ቦታና በቢሮክራሲ ማነቅ ለአገር አደጋ የሆነ፣ በሌብነትና በሌብነት ብቻ ማደግ ይቻላል ብሎ የሚያምን፣ በአየር በአየር የአጭር ጊዜ ሥራ ላይ ብቻ የሚንጠለጠል ኢኮኖሚ ውስጥ የሚሳተፍ የመካከለኛ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ይፈጥራል፡፡ ድለላ፣ አስመጪነት፣ ቤት ሠርቶ ማከራየት፣ አንድ ሱቅ ላይ ችርቻሮ የመሥራት የመሳሰሉ ሥራዎችን በመሥራት መኪና በሞዴል መቀየር እንጂ ሌላ የማይመኝ፣ ሀብትን ጥቅም በማይሰጥ ብልጭልጭ ነገር የሚያጠፋና ያገኘውን ገንዘብ ምን እንደሚያደርግበት ግራ ገብቶት ለሱስና ለመጤ ባህል የሚጋለጥ ትንሽ ገንዘብ ሲያገኝ ዱባይና ሌሎች አገሮች ኼዶ ሆቴል ማደርን እንደ ዕድገት መለኪያ የሚቆጥር የማኅበረሰብ ክፍል ይፈጥራል፡፡ አንድ ወጣት እንደ ዕድሜው እንዲሠራ እንዲታትር ቢያበረታቱት ያለውን ትኩስ ኃይል እንዲጠቀም ቢደረግ፣ ከፍተኛ ለውጥ እንዲያመጣ ማድረግ እንደሚቻል ሁሉ በተቃራኒው እንዳይሮጥና እንዳይታትር ታስሮ እንዲቀመጥ ማድረግ ሰነፍና ለቤተሰቡ አደጋ የሆነ ወጣትን ይፈጥራል፡፡ ከሥር የሚያየውም ታዳጊም በላብና ወዝ ማደግን እንዳይመኝ ያደርጋል፡፡ በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ዕድገት የሚገኘው ሥራ ሲከበር ሁሉም እንደ ጥረቱ ውጤቱን ሲያገኝና ማበረታቻ ሲደረግለት ነው፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ግን የሚታየው የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ አምራችና ጥረት የሚያደርግ የማኅበረሰብ ክፍልን የሚያበረታታ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነውና ከኢትዮጵያውያን አንፃር ከፍተኛ ገቢ አለው የሚባለው የማኅበረሰብ ክፍልም ደግሞ መንግሥት በተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት ለውጭ ባለሀብቶች ብቻ ትኩረት የሰጠ በመሆኑ፣ የአምራችነት (ባለ ኢንዱስትሪ የመሆን) ሞራሉ ሞቷል፡፡ አምራች እንዲሆን የሚያደርገው መንገድ በአብዛኛው ለአገር ውስጥ ባለሀብት ሁሉ እንደ ዳገት እንዲከብደው ተደርጓል፡፡ ውኃ ዳገት ከገጠመው የመሬቱን አቀማመጥ እያየ ወደ ቀለለው እንደሚፈስ ሁሉ፣ ይህ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ኃይልም ወደ ቀለለው ይሄዳል፡፡ ማምረቻ ቦታ ለማግኘት ያለው የቢሮክራሲው ውጣ ውረድና የተቀመጠው የሊዝ ዋጋ ልምዱንና የሥራ ባህሉን ተጠቅሞ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪያሊስትነት እንዳያድግ ሲያቅተውና ችግሩን ለመፍታት አንድ ሚኒስትር ለማግኘት ለወራት ሲንከራተት፣ እንደ አክጉን ግሩፕ ያሉ የቱርክ “ባለ ሀብቶች” በባዶ እጅ ቤተ መንግሥት ገብተው በሺዎች የሚቆጠር ሔክታር ሲቀበሉና ያለ ሥራ ለዓመታት አጥረው ሲያስቀምጡ ይታያል፡፡ ይህ የማኅበረሰብ ክፍል በጽሑፉ መግቢያ ላይ በተገለጸው ምክንያት በውጭ ባለሀብቶችና በሌሎች ምክንያቶች በሚመጣው የውጭ ምንዛሪ ችግር በእጁ ያለው ገንዘብ የመግዛት አቅም ከማጣቱ በፊት፣ በአገር ውስጥ ያፈራውን ሀብት በሥራ ፈጣሪ ኢንቨስትመንቶች ላይ ከማዋል ይልቅ ለመገንባት የውጭ አገር ግብዓቶችን የሚጠቀም፣ ከተገነባም በኋላ ምንም ዓይነት ተዘዋዋሪ አገራዊ ኢኮኖሚ ፋይዳ የሌለው የመኖሪያ ቤትና ሕንፃ ሠርቶ ማከራየት ላይ ሀብቱን እንዲያውል ይገደዳል፡፡ ከአገር ውስጥ ባንክ ተበድሮ የሚገዛውን የግብርና ምርት በኪሳራ ለውጭ አገሮች በመሸጥ በሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ የባዕድ አገር ፋብሪካ ምርት አምጥቶ ለአገር ውስጥ በማቅረብ ትርፍ ለማግኘት ይሞከራል፡፡ ኑግ ልኮ ዘይት ይገዛል፡፡ ዘይት እዚሁ የመጭመቁ መንገድ ዳገት ተደርጎበታል፡፡ ‹‹ድብ ሲያባርርህ የሚጠበቅብህ ከጓደኛህ መቅደም ብቻ ነው›› እንደሚባለው፣ ይኼኛው የማኅበረሰብ ክፍል ከሌላው በተሻለ ስለሚኖር ከተቀረው የኅብረተስብ ክፍል ትርፍ በመሰብሰብ ኑሮውን በአንፃራዊ “ምቾት” ነገር ግን ዘላቂነት በሌለው መንገድ ይመራል፡፡
‘አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ ለምን ይሆን የራበው ሆዴ?’ ለሚለው የዘመናት ጥያቄ መልስም ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች ከበዙት ችግሮቻችንና መልሶቻቸው ውስጥ አንዱ፣ ከላይ የተዘረዘረው ዓይነት የተሳሳተ የኢኮኖሚ አስተዳደር ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህ የተሳሳተ የኢኮኖሚ አስተዳደር የፖለቲካ ቀውስ ለመፍጠር ዳር ዳር ሲለው ‘ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ’ በሆነ መንገድ የሚከናወነው ሥራ ችግር አባባሽ ሲሆን እንጂ መፍትሔ ሲሆን አልታየም፡፡ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ድህነትን በመፍጠር ድህነት የፖለቲካ አለመረጋጋትን፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት የኢኮኖሚ ድቀትን፣ የኢኮኖሚ ድቀት የኑሮ ውድነትን፣ የኑሮ ውድነት ተመልሶ የፖለቲካ አለመረጋጋት እየወለደ ጨካኝና አውዳሚ የሆነ እሽክርክሪት (ቪሸስ ሰርክል) ውስጥ አገር እንድትሽከረከር ያደርጋል፡፡
ይህን ውስብስብ የችግር ቋጠሮ ለመፍታት በችኮላ ያገኙትን ጫፍ ይዞ ከመጎተት እንደ ኢትዮጵያ ያለ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያቀፈን፣ አብዛኛው ወጣት የሆነ ማኅበረሰብ ያለውን፣ ለምና ለሥራ ምቹ የሆነ መሬትና የአየር ፀባይ ያለው አገር ይዞ የውጭ አገሮች ላይ ለዕድገት ከማተኮር ይልቅ ማኅበረሰባችን ለምን ማደግ አልቻለም ብሎ ቆም ብሎ ማሰብ ያስልፈልጋል፡፡
የአገር ኢኮኖሚን አሳድጎ በዘላቂነት ለማስቀጠልና ለትውልድ እንዲተርፍ ለማደረግ ከሥር ወደ ላይ የሆነ ተፈጥሯዊ የዕድገት መስመርን ተከትሎ የራስን አቅም መገንባት ይበጃል፡፡ አንድ ልጅ ተወልዶ በሚያስፈልገው ጊዜ የሚያስፈልገውን ምግብ እያገኘና በዕድሜ መጠኑ ልክ የሆነ ሥራ እየሠራ እንዲያድግ ቢደረግ ለራሱም ለማኅበረሰቡም የሚጠቅም እንደሚሆን፣ ዜጎችም በዚሁ የኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሰላል ውስጥ ተገቢውን ሥፍራ እየተሰጣቸው እንደ መጠናቸው አስፈላጊ የሆነ ድጋፍ እየተደረገላቸው በኢኮኖሚ ካደጉ፣ ኢትዮጵያውያን ላለው ትውልድ የተመቸች ለቀጣዩም ትውልድ የምትተርፍ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከታችኛው ወጣት ጀምሮ እስከ ላይኛው የአገር ውስጥ ኢንቨስተር ድረስ ያለው ሰንሰለት እንደ አስፈላጊነቱና በጥረቱ እንደ ደረሰበት ደረጃ ማበረታቻና ድጋፍ እያገኘ፣ በሥሩ ከእሱ ያነሱትን እያቀፈ እንዲሄድ ማድረግ ለዘለቄታዊ የአገር ዕድገትና ህልውና ወሳኝ ነው፡፡ በራሳችን ስህተት ባመጣነው የደን መራቆትን ለመፍታት ከባህር ማዶ ያስመጣነው ባህር ዛፍ መሬቱን ሁሉ፣ አድርቆ አገር በቀል ዛፎችን እንዳያድጉ እንዳደረገው ሁሉ ዜጋን ችላ ብሎ ትልልቅና ጠንካራ የሆኑ የውጭ ኢንቨስተሮችን ወደ አገር ውስጥ እንዲመጡ ቢደረግ የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾችን በመጨፍለቅ ማኅበረሰቡን እንደ አንድ አንድ የአፍሪካ አገሮች ተቀጣሪ ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የተደራጀ መካከለኛ ክፍል ማኅበረሰብ በሌለበት አገር የሚመጡ የውጭ ኢንቨስተሮች በአገር ውስጥ የተዘጋጀ ገበያ ስለማይኖራቸው፣ በተቻላቸው መጠን መላው አገሩን እንደ ወርክ ሾፕ ብቻ በመቁጠር የሚቻላቸውን ያህል ገብዘብ ወደ መጡበት አገር ያሻግራሉ እንጂ፣ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት በአገር ውስጥ ለማፍሰስ ፍላጎት የላቸውም፡፡ እዚህ ላይ እንደ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) ማብዛት ያሉ በዓለም ባንክና በሌሎች ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊነት የሚቀነቀኑ የኢኮኖሚ ምክሮችን እንደ እውነተኛ ምክር በመቁጠር፣ የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ ትክክለኛ መንገድ ነው ብለው የሚሟገቱ ወገኖች ይኖራሉ፡፡ ለእነዚህ ወገኖች የዓለም አቀፍ ተቋማትና ያደጉ አገሮች መንግሥታት ለእኛ ሳትገብሩ ብቻችሁን ዕደጉ ብለው እንዲመክሩን እየጠበቃችሁ ነው ወይ? የገዘፈ ኢኮኖሚ ባለቤት በሆኑ አገሮች የተቋቋሙ የፋንናንስ ተቋማት እንጂ ለፅድቅ የተቋቋሙ ተቋማት እንዳልሆነ ዘንግታችሁታል ወይ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡
ባራክ ኦባማን ጨምሮ የተለያዩ አገር መሪዎች መካከለኛውን የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ መደብ በማንቀሳቀስና በማበረታታት ዜጎቻቸው በኢኮኖሚ እንዲያድጉ ማድረግ፣ ለአገራቸው ኢኮኖሚ እንደሚበጅ ሲሟገቱና ትልልቅ ተቋማቶቻቸውን በሚገባ ሲደግፉ ይታያሉ እንጂ፣ የውጭ ኢንቨስተር እንዲመጣላቸው ወይም ሥራ አጥ ወጣቶቻቸው ተደራጅተው ጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ላይ እንዲሠማሩ ሲሞግቱ አይታይም፡፡ ያደጉት አገሮች ከውጭ የመጡ ኢንቨስተሮች የማይፈልጉት በቴክኖሎጂ ከራሳቸው አገሮች ድርጅቶች ስለማይበልጡ አይደለም፡፡ የውጭ ኢንቨስተር የኢኮኖሚ ጥቅሙ ለመጣበት አገር ስለሆነ እንጂ፡፡
ሁዋዌ የተባለው ግዙፉ የቻይና የቴሌኮም ኩባንያና በአሜሪካ የገጠመው ችግር ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ሁዋዌ የደረሰበት 5G ቴክኖሎጂ የአውሮፓና የአሜሪካ ካምፓኒዎች የደረሱበት ቴክኖሎጂ አይደለም፡፡ በቅርቡም የሚደርሱበት አይመስልም፡፡ ሁዋዌ በአሜሪካ ኢንቨስት በማድረጉና የቴሌኮም መስመር ዝርጋታዎችን በመሳተፉም በሺዎች ለሚቆጠሩ አሜሪካውያን ሥራ ይፈጥራል፡፡ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንቅስቃሴም በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጓል፡፡ ይኼ ሁሉ ጥቅም እያለው ሁዋዌ ከአሜሪካና ከምዕራባዊያን ኢኮኖሚ እንዲወጣ ጫና ውስጥ የገባው በአደባባይ እንደሚባለው ለቻይና መንግሥት መሰለያነት እንደሚውል ስለተሠጋ ብቻ አይደለም፡፡ የ5G ቴክኖሎጂ በአውሮፓና በአሜሪካ በሥራ ላይ በመዋሉ ለቻይናና ለሁዋዌ ከ500 ቢሊዮን ዶላር በላይ ጥቅም የሚያስገኝ ስለሆነና የምዕራባዊያን የቴሌኮም ኩባኛዎችን ከሥራ ውጪ ስለሚያደርግ ነው፡፡ ይህም ዞሮ ዞሮ በአጭር ጊዜ ለምዕራባውያን የሚሰጠውን የኢኮኖሚ ጥቅም በረጅም ጊዜ ውስጥ አጥፍቶ፣ የኢኮኖሚውንም ሆነ የፖለቲካ ኃይሉን ወደ ቻይና ስለሚያዞረው ነው፡፡
ምዕራባውያን የሚፈልጉት የውጭ ኢንቨስትመንት (FDI) የሌሎች አገር ዜጎች በምዕራባውያኑ ኩባንያዎች አክሲዮን እንዲገዙ፣ ገንዘባቸውን ከአገራቸው አውጥተው በምዕራባውያን ባንኮች እንዲያስቀምጡ፣ የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት ስላላቸው ለመጠባበቂያ ቤት እንዲገዙ በማድረግ ላይ የተመሠረት እንጂ፣ መሠረታዊ የሆነ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾቻቸውን የሚወዳደሩ የውጭ ኢንቨስተሮች እንዲመጡ አይፈቅዱም፡፡ ይህ ሀቅ ከእኛ አገር “ኢኮኖሚስቶች” እና “ምሁራን” ለምን እንደተሰወረ መረዳት ይቸግራል፡፡ በውጭ አገሮች የኢኮኖሚ ቱሪስቶች ትምህርትን በመሸምደድ ብቻ ኢኮኖሚስት ስለተባሉ ወይም በግላቸው ለውጭ ባለሀብቶች ተቀጥረው በመሥራት የሚያገኙትን ጥቅም ታሳቢ በማድረጋቸው፣ ወይም ደግሞ የባዕድ ቋንቋንና ቃላትን ብቻ እንደ ዕውቀት ወስደው ዋናውን ዕውቀት ባለመውሰዳቸው ይሁን በሌላ ምክንያት አልታይ ያላቸው መገመት ይከብዳል፡፡
በምዕራብ አገሮች የኢኮኖሚ ቱሪስቶች ሐሳብ በሥራ ሰዎች (የኢኮኖሚው አንቀሳቃሾች) ተመዝኖና ተመርጦ ኢኮኖሚው ሲመራ፣ በእኛ አገር ግን “ኢኮኖሚስቶች” የመንግሥት አማካሪ በመሆን ያለ ሥራቸው የኢኮኖሚው መሪ ስለሚሆኑ ይሆናል የኢኮኖሚ ችግራችን ሊፈታ ያልቻለው የሚል ግምት አለኝ፡፡ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግርና የኢትዮጵያ ዜጎች የኢኮኖሚ ድቀት በውጭ አገር ኢንቨስትሮች ሊፈታ አይችልም፡፡ አንድ ሺሕ የውጭ ከፍተኛ ኢንቨስተሮች መጥተው በኢንዱስትሪ ፓርኮች እያንዳንዳቸው ለአምስት ሺሕ ሠራተኞች (እስካሁን አምስት ሺሕ የፈጠረ ፋብሪካም መኖሩ ያጠራጥራል) ሥራ ፈጥረው ደመወዝ ቢከፍሉ እንኳን፣ በየዓመቱ እስከ ሦስት ሚሊዮን ሥራ አጥ በሚጨመርበት አገር ውስጥ አምስት ሚሊዮን ሥራ በመፍጠር የኢትዮጵያ ችግር ሊፈታ አይችልም፡፡ የውጭ ኢንቨስተር ላይ ማተኮር ከችግር ወደ ችግር እንድንኳትን ከማድረግ ውጪ መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ የሚያስፈልገን የውጭ ኢንቨስተር ዓይነት የእኛን ምርት ሊገዛ የሚችል ኢንቨስተር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ ቤት የሚገዛ፣ እንደ ዱባይ በራሱ አገር ያመረተውን ምርት ለሌላ አገር ለመሸጥ በአገራችን ወደብና ደረቅ ወደብ ውስጥ የሚሠራ ኢንቨስተር ነው የሚያስፈልገን፡፡
የትኛውም አገር ከውጭ መጥቶ የአገር ውስጥ ባለተስፋ አምራቾችን በሚያቀጭጭ ኢንቨስተር አላደገም፡፡ የውጭ ኢንቨስተር ጥቅም፣ የተወረወረበት ደርሶ ሳያርፍ ወደ ወርዋሪው የሚመለስውን ተሽከርካሪ መጫወቻ ዓይነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ውጥንቅጥ ወጥታ እርስ በርሱ በደንብ የተሳሰረ፣ ከስደት ይልቅ በአገር ውስጥ መኖርን ህልሙ ያደረገ፣ በቀላሉ በጠላት የማይፈታ ሆኖ የተሳሰረ ማኅበረሰብ እንዲኖራት ሁሉም በሥራው መጠን ልክ የሚከበርበትና የሚበረታታበት ሥርዓት መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ተፈጥሯዋዊ ዕድገት ተከትለን ነገር ግን ፈጣን በሆነ መንገድ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር ወጥታ ካደጉት አገሮች ተርታ እንድትሠለፍ፣ የተጠናቀረ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት ትኩረት ሊሰጠውና ከፍተኛ ድጋፍ ሊደረግለት የሚገባው የውጭ ኢንቨስተር ወይም በኪራይ ሰብሳቢነት ኑሮውን ማጣጣም የለመደውን የአገር ውስጥ ከፍተኛ ባለሀብትንና በተቃራኒው አቅጣጫ ያለውን ለሥራ ዝግጁ ያልሆነን የታችኛው ማኅበረሰብ ሳይሆን፣ ገና ሮጦ ያልጠገበው ለመሥራት ከፍተኛ አቅምና ለማደግ ከፍተኛ ጉጉት ያለውን የመካከለኛውን የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ክፍል ነው፡፡
ይህ የማኅበረሰብ ክፍል ባለው ዕምቅ ችሎታና ከፍተኛ የማደግ ፍላጎት አንድም ያንቀላፋውን የላይኛውን ማኅበረሰብ በኢንቨስተርነት በመሳብ ያለውን ፋይናንስ የሚጠቀምበት መንገድ በመፍጠር ለኢኮኖሚው ግብዓት ያደርገዋል፡፡ ካልሆነም በተደረሰብኝ ስሜት እንዲሮጥ ያስገድደዋል፡፡ በሌላም መንገድ ለታችኛውም ማኅበረሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ በየዓመቱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚመረቁ ተማሪዎች አሁን በውጭ ባለሀብቶች እንደሚታየው የዓመታት የሥራ ልምድ ሳይጠይቅ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ መንግሥትም ከመንግሥታዊ ሥራው ወጥቶ የነጋዴና የከፍተኛ ኢንቨስትመንት ሥራ ውስጥ ገብቶ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የአገር ሀብት ከሚባክን፣ የመሥራት አቅም ላላቸው የአገር ውስጥ ዜጎች የጥቅምም የኪሳራም ባለቤት በማድረግ ጀምሮ በኪሳራ ያቋረጣቸውን ፕሮጀክቶቹን ቢያስተዳድር፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መንግሥት በመሥራት ለማከራየት ከሚሯሯጥ ለግል ባለሀብቱ እንደ አቅሙና በአክሲዮን እየተደራጀ በመሥራት እንዲያከራዩ የረጅም ጊዜ የፋይናንስ ድጋፊ ቢያደረግ፣ ፋብሪካዎችን በባለቤትነት እንዲያስተዳድሩ የአክሲዮን ማኅበራትን ቢያጠናክር የተሻለ ይሆናል፡፡ አገር በቀል በሀቅ የሚሠሩ መካከለኛ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ባንኮችን ከዜሮ ተነስተው በመመሥረት በታጠረና በማይመች ፖሊሲ ውስጥ የት እንዳደረሱ መመልከት በራስ መለወጥ የሚችል ኃይል እንዳለን በቂ ማሳያ ነው፡፡
በመንግሥት ውስጥ ያሉ ስታሊኒስትና ያልገባቸውን ሶሻሊዝም እንደ ሃይማኖት የያዙ ባለሥልጣናትም፣ የራስ አገር ዜጋ አሥር ብር ያለአግባብ ከሚጠቀም ቻይና ትውልድን ባለ ዕዳ ብታደርግ ይሻላል ከሚል አመለካከት ቢወጡ ይሻላል፡፡ ቢያንስ በራስ አገር ያላግባብ የተገኘ ገንዘብ ተመልሶ የሚገላበጠው አገር ውስጥ ነው፡፡ በረጅም ጊዜም በሕጋዊ መንገድ ለማስመለስም ዕድልም አለው፡፡ የራስ ዜጋ ላይ ጦር ሰብቆ ቆሞ ለቻይናና ለህንድ ዜጎች ሥራና እንጀራ የሚፈጥር ከራስ ስው ጋር የመጠማመድ አስተሳሰብ ሊወገድ ይገባዋል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት መፍትሔው የራስን ችግር መመልከትና የተንሰራፋውን ኢፍትሐዊ የኢኮኖሚ ሞዴል ማስተካከል ነው፡፡ ሁሉም እንደ የአቅሙ እንደ ሥራ ድርሻው እንዲወጣ ከማድረግ ውጪ አሁን እንደሚታየው ሥራ መፍጠር ያልቻለ ሥራ አጥ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ እንዲሆን የሚጣርበት፣ መንግሥት ነጋዴ ለመሆን ሞክሮ በአሳፋሪ ሁኔታ የሚወድቅበት ነገር ግን ተጠያቂ የማይሆንበት፣ አቅም ያለውና ለሥራ የሚታትር ሰው እንደ በዝባዥ የሚታይበትን የተሳከረ አስተሳሰብ ማስተካከልና ከሁሉም በላይ በራስ አቅም ማመን ለዘላቂ ልማት ወሳኝ ነው፡፡ ራስ ማለት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንጂ ሜቴክና የፖለቲካ ደጋፊ ማለቴ አለመሆኑን ይያዝልኝ፡፡ አዎ ያለ ውጭ ኢንቨስተር የኢኮኖሚ ፖሊሲያችንን ብቻ በማስተካከል አገራችንን የበለፀገች ማድረግ እኛው እንችላለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡