Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኢትዮጵያን ከገባችበት ቀውስ እናውጣ!

ኢትዮጵያን ከገባችበት ቀውስ እናውጣ!

ቀን:

በጌታቸው አስፋው  

የኢሕአዴግ መሪዎች ‹መሬት የግል ንብረት የሚሆነው በእኛ መቃብር ላይ ነው›

የሚለው አመለካከታቸውን አልቀይርም ብለው 30 ዓመታት ሙሉ እንደ ፈርኦን ልብ ታብየው በአገሪቱ ላይ መቅሰፍት አመጡባት፡፡ ጥቂቶች ብቻ ቢሆኑም ምሁራን ለ30 ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን፣ ዕድገትና ብልፅግና እንዲመጣ በታወጀው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ሕግ መሠረት መሬትና ሌሎች ንብረት ማፍሪያ የማምረቻ መሣሪያዎች ወይም የምርት ግብረ ኃይሎች (Factors of Production) የግል ንብረት ሆነው አገልግሎታቸው በገበያ የሚከራይ ወይም የሚሸጥ የሚለወጥ ይሁን ብለው፣ በሙያቸውና ከሌሎች በተቀሰመ ልምድ ዘመኑን በሚመጥን የኢኮኖሚ አስተዳደር ሥርዓት ዕውቀታቸው መክረዋል ዘክረዋል፡፡

እኔም በበኩሌ እንደ ሌሎች ባለሙያዎችና ምሁራን ላለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ደጋግሜ ይህንኑ ስወተውት ኖሬአለሁ፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በ2009 ዓ.ም. ከአንድ የፌዴራሊዝም ፕሮፌሰር ጋር የብሔር ፌዴራሊዝሙና መሬትን የመንግሥት ንብረት ያደረገው ልማታዊ መንግሥት የአቶ መለስ ፍልስፍና የማይታረቁ ሆነው እንደሚቃረኑ፣ በሪፖርተር ጋዜጣ ሁለት ሦስት ጊዜ የክርክር ምልልስ አድርገናል፡፡ ሌሎች ምሁራንም በተለይ የማኅበራዊ ሳይንስና የሥነ ልቦና ምሁራን እንዲሳተፉ ጋብዤ ነበር፣ ፈቃደኛ ሆኖ የቀረበ አልነበረም፡፡ የተከራከርኩበትን ነጥብ ክፋይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወዴት በተሰኘው መጽሐፌ አሥፍሬያለሁ፡፡

ተቃዋሚና ደጋፊ የሚባሉ የእኛ ፖለቲከኞች ስለምርጫ ቦርድ አደረጃጀትና ፓርላማ ስለሚገቡበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሁኔታ ብቻ እንጂ፣ ሕዝቡ አብሮ በሰላም ስለሚኖርበት ሁኔታ ግድ አልሰጣቸውም፣ አልተመካከሩምም፡፡ ሕዝቡ ስለሚበላው፣ ስለሚጠጣው፣ ስለሚለብሰው፣ ስለሚኖርበት፣ ስለወጣቱ ሥራ ማጣት፣ ስለዋጋ ንረት፣ ስለመሬትና ከመሬት መፈናቀል በአጠቃላይ ስለኢኮኖሚው እንዳያስቡ እንደ የግብፅ ፈርኦኖች እግዚአብሔር ልባቸውን አደነደነው፡፡ ዛሬ ሁኔታዎች ተለውጠው ፓርላማ ለመግባት ያሰበ ሁሉ በጠማማ መንገድ ስለተጓዘ ሲኦል ላለመግባት ጭንቀት ይዞታል፣ መፍትሔውን ግን አጥቷል፣ ውሳኔው የሌሎች ሆኗል፡፡ በእጄቶዎች፣ በፋኖዎችና በቄሮዎች ጉያ ውስጥ ለመሸሸግ ይሯሯጣል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከመጡ በኋላም በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የነበረውን የመሬት ባለቤትነት ካርኒ ያለውን ሰው ማንም እንዳይነጥቀው በሕግ የተከለከለ እንደነበረ ጠቅሼ፣ በዕድሜዬ ባካበትኩት ልምድ መክሬአለሁ፡፡ ባለፉት አምስት ስድስት ዓመታት  በሪፖርተር ጋዜጣ ባወጠኋቸው ወደ ዘጠና የሚጠጉ ጽሑፎቼ የነፃ ገበያ መሠረት ስለሆኑት መሬትን ጨምሮ፣ የምርት ግብረ ኃይሎች የግል ንብረት መሆን ለዕድገት ብቻ ሳይሆን ለሰላምም አስፈላጊነት ደጋግሜ ጽፌያለሁ፡፡

ኮሎኔል መንግሥቱ ሥልጣን በያዙ በጥቂት ወራት መሬትን፣ ትርፍ ቤትንና የግል ማምረቻ ድርጅቶችን ወደ የመንግሥት ይዞታነት ሲያዞሩ በአገሪቱ የነበረውን ድባብም በጊዜው ኖሬ ያየሁትን በምስክርነት ጠቅሼያለሁ፡፡ ምናልባት በጊዜው ያልነበሩ ሰዎች ኮሎኔሉ ይህን ማድረግ የቻሉት አምባገነን መሪ ስለሆኑ ነው ሊሉ ይችሉ ይሆናል፡፡ ግን አይደለም፡፡ በጊዜው የኮሎኔል መንግሥቱ አምባገነንነት አልታየም፣ ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብርም ገና አልመጡም፡፡ ኮሎኔሉ ብዙ ተቃውሞ ያልገጠማቸው አገር እንደ ዛሬው ያልተሸበረችው፣ ተማሪውን ጨምሮ መላው ወጣትና ከዘጠና አምስት በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ በአንድ ልብ የሚደግፈውን አዋጅ ስላወጁ ነው፡፡

ማንም ጤነኛ ሰው እንደሚረዳው መቀማት ከመስጠት ይከብዳል፡፡ መቀማት ብጥብጥንም ያመጣል መስጠት ግን ፍቅርን ያመጣል፡፡ ዶ/ር ዓብይንም የምመክራቸው ቀሙ ብዬ ሳይሆን ስጡ ብዬ ነው፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ሲቀሙ ያልገጠማቸው ችግር እርሳቸው ሲሰጡ እንደማይገጥማቸው ነው፡፡ መሬት የግል ይሁን ሲባል የግል የሚሆነው፣ አሁን የመንግሥት ጪሰኛ ከሆኑት ተነጥቆ ሀብት ላለው ይሰጥ ማለት ሳይሆን፣ እዚያው ባሉበት ባለቤትነታቸው ይፅደቅላቸው ማለት ስለሆነ የገባንበትን የአካባቢያዊነት ስሜት አምክኖ ሰላምን ያመጣል፡፡ ለመለካትና ለማከፋፈል የሚወስደው ጊዜና ሀብት የለውም፡፡ ባለቤት እንዲረጋጋ ለባለ ይዞታው፣ በባለቤት ቤት እንዲፀናለት አዋጅ ማወጅ ብቻ ነው፡፡

ኮሎኔል መንግሥቱ በሥልጣናቸው ጥቂት ወራት ውስጥ መቀማት የቻሉት ጥቂት ፊውዳሎችና ባላባቶችን አስቀይመው ነውና የዕደገት በኅብረት ዘማች በነበሩት ተማሪዎች ላይ አደጋ ለማድረስም ሞክረዋል ዶ/ር ዓብይም ጥቂት የኢሕአዴግ ባለሥልጣናትን አስቀድመው የሕዝብ የሆነውን ለሕዝብ መቀማት ሳይሆን፣ መስጠት የራሱ የነበረውን ለራሱ መመለስ ይችላሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱና አንቀጾቹን አገር ሳያፈርሱና ሕዝብ ሳይበትኑ በፊት ማፍረስ የግድ ይሆናል፡፡ የሰው ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የነፃ ገበያ ጠበቃ የሆኑ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና ምዕራባውያን የሚደግፉት ጉዳይ ስለሆነም ከጎናቸው ይቆማሉ፣ በጥበብ ለማከናወን ድጋፍም ያደርጉላቸዋል፡፡

እጄቶዎችን፣ ፋኖዎችንና ቄሮዎችን ምን አስተባበራቸው? ምን አሳመፃቸው? መሬታችን የእኛ በብሔር የተሰባሰብን ቡድኖች የጋራ ሀብት ነው የሚል በልማድ የመጣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ኮንትራታዊ ውል አይደለምን? የሥነ ልቦና ጠቢቦች እንደሚያስተምሩት ሰው ሀብትን ከእናቱም ጋር መጋራት አይፈልግም፡፡ የራሱ የብቻው እንዲሆን ነው የሚፈልገው፡፡ በብሔረሰብ ተደራጅቶ ንብረት የመሻማት ቡድናዊ ስሜትን ማርከስ የሚቻለው፣ ቡድናዊ ባለቤትነት ስሜት የተሰማውን የግል ባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው በማድረግ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከእንግዲህ ከሰሜን ወደ ደቡብ ከደቡብ ወደ ሰሜን ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ተጉዞ የመሬትና የንብረት ባለቤት መሆን የሚቻለው፣ አገራዊ ስሜት ሊሰማ የሚችለው ገበያው ሲፈቅድ ብቻ ነው፡፡ ያለው ለመሸጥና የሌለውም ለመግዛት ሲስማሙ ብቻ ነው፡፡ የብሔር ፖለቲካ ተሟጋቾች የብሔረሰባቸው ሰው መሬት እንዳይሸጥ ሕዝባቸውን ማስተማር ይችላሉ? ወይ እነርሱ ወይ ገበያው ከሁለት አንደኛቸው ያሸንፋል፡፡ ትግላቸው ከሰው ጋር ሳይሆን፣ መጤ ነው ከሚሉት ሰው ጋር ሳይሆን፣ ከገበያው ጋርና ከብሔረሰባቸው አባል ግለሰብ የጥቅሙን ምርጫ ለእነርሱ አሳልፎ መስጠት ወይስ ራሱ ከመወሰን ጋር ይሆናል፡፡

ሌላው በዚህ ጉዳይ ላይ ደጋግሜ የወተወትኩበት ጉዳይ ትራንስፎርሜሽን ለምንለው ቃል የእኛውንና የሌሎችን ትርጉም በማነፃፀር ነው፡፡ የእኛው ትራንስፎርሜሽን በቁሳዊ ነገሮች ላይ ብቻ አትኩሮ የምርት ዕድገት የምርት ዓይነት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መቀየር፣ ወይም በምርት ዕድገት ላይ የሚመረኮዘው የነፍስ ወከፍ ገቢ ዕድገት ላይ ሲያተኩር የሌሎች ትራንስፎርሜሽን ግን ከምርት ዕድገት ባሻገር የምርት አደረጃጀትና አጠቃቀም አመለካከት እንደሆነ፣ የእንግሊዝ ታላቁ ትራንስፎርሜሽን ትርጉምም ኢኮኖሚን ከማኅበራዊና ፖለቲካዊ ኮንትራታዊ ውሎች ነፃ አድርጎ የገበያ ማኅበረሰብ መፍጠር እንደሆነ አመልክቼአለሁ፡፡

ሥነ ጽሑፎች የእንግሊዝን ታላቁ ትራንስፎርሜሽን አመለካከትና አስተሳሰብ ለዋጭነት ሲገልጹ የምዕራባውያን ሴቶች ጀልፋፋ ቀሚሶቻቸውን አውልቀው ሚኒስከርት መልበስ የጀመሩት፣ ብስክሌት በአደባባይ መንዳት የጀመሩት ያኔ ነው ይላሉ፡፡ በእርግጥ ሲጋራ፣ መጠጥና ጭፈራዎችን የመሳሰሉ አጉል ልማዶችም ያቆጠቆጡት ያኔ ነው፡፡ ሆኖም ሰው የሚኖረው በመጀመርያ ለራሱ እንደሆነና ራሱን መቻል የራሱ ኃላፊነት እንደሆነም ተምረዋል፡፡ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ልማዳዊ ኮንትራታዊ ውሎችን በልክ እንዲሆኑ አድርገው ቀንሰዋል፡፡

በ1975 ዓ.ም. የሶሻሊዝም ትምህርታዊ ጽንሰ ሐሳብና ከመኖር የተገኘ ተግባራዊ ዕውቀቴን ከካፒታሊዝም ተግባራዊ ዕውቀት ጋር ለማመሳከር፣ በሶቭየት ኅብረት እከታተለው የነበረውን ትምህርቴን ለአንድ ዓመት ያህል አቋርጬ አሜሪካ ኖሬ ነበር፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የማልረሳው የቀሰምኩት ዕውቀት በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት የፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬጋን ወንድ ልጅ የሥራ አጥነት ድጎማ ከማኅበራዊ ዋስትና እንደተቀበለ በታተመ ጋዜጣ ላይ ያነበብኩት ነው፡፡ የእኛ አነስተኛ ሱቅ ነጋዴዎች ልጆቻቸውን በውድ የውጭ መኪኖች ያንቆጠቁጧቸዋል፡፡ 

ምዕራባውያን ሀብታቸው የተትረፈረፈ ቢሊየነሮችም ቢሆኑ፣ ልጆቻቸው አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላቸው ወይ የቤት ኪራይ ክፈለኝ ወይም ቤቴን ልቀቅልኝ እንደሚሏቸው ዘወትር እንሰማው የነበረ ጉዳይ ቢሆንም፣ የአንድ አገር መሪ ልጅ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል ብዬ ግን አልጠበቅሁም ነበር፡፡ ንፉግ ሆነው ሳይሆን አገር የምታድገው ልጆቹ ሲሠሩ እንደሆነ ለማስተማር ብለው ነው፡፡

የእኛውን በአርባ አምስት ዓመቱ ‹እማዬ ሽሮ አልፈላም እንዴ?› የሚል ጎልማሳ ይዞ፣ ልጁን ‹በቶሎ አግቢና ደግሶ ያበላኝን ደግሼ ላብላ› የሚል አባት ይዞ፣ ‹የእኔ አካባቢ መሬት የእኔ ብቻ ነው› የሚል ሰው ይዞ፣ የዶሮና የበግ ቆዳ ራሱ ካልገፈፈ ወይም ደም ካላፈሰሰ የዶሮና የበግ ሥጋ የበላ የማይመስለው ሰው ይዞ፣ በሬው ራሱ ሉካንዳ ቤት ተሰቅሎ ከታናሹ፣ ከታላቁ፣ ከፍርምባው፣ ከሽንጡ፣ ከዚህና ከዚያ ቁረጥልኝ የሚል ሥጋ መራጭ ይዞ ትራንስፎርሜሽንን ማሰብ ዘበት ነው፡፡

ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ እያጋጠመኝ ያለው ነገር በጣም አስፈርቶኛል፡፡ መንገድ ዳር መኪና አቁሜ ለአሥር ደቂቃ ሱቅ ስገባም አንድ ወይም ሁለትና ሦስት የሆኑ ጎረምሶች ከመጠጥ ቤትና ከሌላም ሥፍራ ሩጠው መጥተው፣ ለረጅም ሰዓት መኪናህን ስንጠብቅልህ ነው የቆየነው ክፈለን ማለት ጀምረዋል፡፡ ካልሰጠሃቸው ትልቅ ፀብ ይፈጠራል፡፡ ለዚህ ተጠያቂው ማን ነው? እኔም፣ አንተም፣ እርሱም፣ ሁላችንም ነን፡፡ አንዱ መኪና ሲነዳ ሌላው የሚበላው የሚያጣበት ምክንያት አንዱ ስለሠራና ሌላው ስላልሠራ አይደለም፡፡ በመጠጥና በሱስ ናላው ዞሮ ነው ብንልም እንኳ ወደዚያ ሁኔታ ውስጥ የከተትነው እኛው ነን ተጠያቂዎቹ እርሱ ብቻ ሳይሆን፣ እኛው በግልና በማኅበረሰብ ደረጃም ነን፡፡

የሲዳማው ‹‹11/11/11›› ለጊዜውም ቢሆን በቀላል ጥፋት ታልፏል፡፡ የአካበባቢውን መሬት የአካባቢው ሰው ንብረት ብቻ ለማድረግ የፈለገ ክልል ካልሆንኩ ባይ በመንግሥት ላይ ያመፀ፣ በጉዳዩ ውስጥ የሌሉ የሌሎች አካባቢ ንፁኃን ሰዎችን ንብረት አጋይቷል፡፡ አምስትና ስድስት የሚሆኑ የደቡብ ብሔረሰቦችም ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸም አሰፍስፈዋል፡፡ በመላው ዓለም የሚያሳፍረንን ሠርቶ መብላት አቅቶን በመሬት የመሻማት ተግባር እየፈጸምን ነው፡፡

የራስን በራስ ማስተዳደር የብሔረሰብ ፖለቲከኞችንና የኢትዮጵያዊ ዜግነት ፖለቲከኞችንም ያግባባቸዋል ብዬ የማምነው መፍትሔው አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ በመንግሥት ንብረትነት ስም የብሔረሰቦች የጋራ ንብረት የሆነው መሬት የግል ንብረት ተደርጎ፣ አሁን መሬቱን በመጠቀም ላይ ላሉት ሰዎች በባለቤትነት መስጠትና መሬት ለሌላቸውም በመንግሥት በጋራ ከተያዘው መሬት በስጦታም ሆነ በግዥ አግኝተው ሠርተው እንዲያድሩ ማድረግ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ከገባችበት ቀውስ ውስጥ እናውጣት፡፡ ፖለቲከኞች ፓርላማ የመግባትና የምርጫ ቦርድ ጉዳያችሁን ለጊዜው ትታችሁ አገር የማዳን ሥራ ሥሩ፡፡ ሰሞኑን በአሜሪካ ትውውቅ ለማድረግ የተጓዙ የኢዜማ ልዑካን ለኢሳት በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፕሮግራማችንን ለምርጫ ስንቀርብ ነው ይፋ የምናደርገው በማለታቸው ቅር ተሰኝቼያለሁ፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጋር ተቀራርበው እንደ መሥራታቸው አገር ከጥፋት የምትድንበትን የመሬት ይዞታ ሥሪትና የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸውን እስከ ምርጫ ወቅት ሊደብቁት አይገባም፡፡ ዛሬውኑ የሚተገበርበትን መንገድ ቀይሰው ከሌሎች የብሔርም ሆነ የዜግነት ፖለቲከኞች ጋር ተመካክረው፣ አገር ከቀውስ ትዳን ብዬ ነው የማምነው፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቃት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውንበኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...