Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከመንቀል መትከል ያፀድቃል!

እነሆ መንገድ ከጀሞ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። በተወላገደ ነገረኛነት፣ በግፋኝ ወይ ልግፋህ አጉል ትዕቢት ተወጥረን ዛሬም እንራመዳለን። ዓመታት ይነጉዳሉ፡፡ ዘመናት በቁጥር ስልቻ ውስጥ እየታጎሩ፣ ትውልድ ከቁጥር ጎሎ ትውልድ በቁጥር ይሞላል። በድካም ያንቀላፋው በጣፋጭና በመራር ትዝታ እየተምታታ ያልፋል። የዛሬ ብርቱ ተጓዥ ለይምሰል ያህል በመንገዱ ላይ ይናኛል። መውጣትና መውረድ በእንባና በሳቅ በኩል ገጻቸውን እየለዋወጡ፣ ተረኛውን ተራማጅ ያባብላሉ። በዚህ መሀል የማይጎል ተስፋ የማይነጥፍ የለውጥ ሕልም ጉልበተኛ ሆኖ ጡንቻውን ያፈረጥማል። መንገድ ዓይኑ አይፈስ ነገር የወሰደውን እያመጣ፣ ያመጣውን እየወሰደ ዝንት ዓለም እንደ ጅረት ዳገት ቁልቁለቱን ያራምደናል። ብርቱው የሰው ልጅ አጭር በሆነው የሕይወት ዘመኑ በመፈጠር ዕዳ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ከእምነት ወደ ክህደት፣ ከተስፋ ወደ ሥጋት፣ ከደግነት ወደ ክፋት እንደ እስስት እየተቀያየረ ዕድሜውን ይገፋል።

ስለሆነም ዛሬም መንገዱ የዛሉ ጉልበቶቹን በጥበብ አድሶ በሚታገል የሰው ልጆች ሠልፍ ተጨናንቋል። የታክሲያችን ወያላው ይጣራል። “ሜክሲኮ! ሜክሲኮ! ለቆንጆ በቅናሽ ለፉንጋ በእጥፍ፤” ይላል። ከወያላው አንደበት ተንደርድረው እንደ ቀልድ የሚወጡት እነዚህ ደስ የማይሉ ቃላት የብዙዎችን ልብ ያደማሉ፣ አጉል ቀልደኞችንና ተረበኞችን በዓይን ያጠቃቅሳሉ፡፡ አንዳንዶች ከተፈጥሯቸው ጋር እየተጋጩ፣ “ያጠፋነው ጥፋት ምንድነው?” ብለው ወደ ሰማይ ቀና ይላሉ። አስተዋይ ይኼን ልብ ይላል። አንዳንዶች በበቀሉባት በዚች መሬት፣ በተወለዱባት በዚች አገር የሆኑትን ሆነው ማንነታቸውን ተቀብለው በሥርዓት ላይ ሳያምፁና ከፈጣሪ ጋር ሳይጣሉ ተመሥገን እያሉ ይኖራሉ፡፡ ‹‹ተኖረና ተሞተ›› አሉ አለቃ ገብረ ሃና፡፡ በግልጽ በሚስተዋለው ትዕይንት ጎዳናው ላይ የሕይወት ትርጓሜ በጥያቄ መሳይ እሳቤዎች እየተባዘተ ይፈተላል። እንዳሰቡት ሳይሆን ባላሰቡት ውለው በዘመን የሚያጉረመርሙት፣ በለስ ቀንታቸው ነገን በተስፋ ከሚጠብቁት እኩል ታክሲ ይጠብቃሉ። ሕይወት በዚህኛውና በዚያኛው መስመር በተወከሉ የሰው ልጆች ሠልፍ ደምቃለች። ጉዞ ጀምረናል።

ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ ሁለት ጎልማሶች ቀደም ብለው የጀመሩትን ወግ በምሳሌ ሲያበረቱት ምሳሌው ጆሯችን ይደርሳል። “ሁለት ወፍራም ሰዎች መንገድ ይሄዳሉ፤” ይላል አንደኛው ጎልማሳ። “መሀላቸው አንድ ቀጭን ሰው ይገባና አንደኛውን ወፍራም ‘ለመሆኑ እንዲህ የወፈርከው በምን ምክንያት ነው?’ ይለዋል፤” ጎልማሳው ጨዋታውን አቋርጦ ብዙ ዓይተዋል የሚላቸውን ዓይኖቹን አቡዞ ወዳጁን ያስተውለዋል። ወዳጁ ቀጥል በሚል ስሜት ያዳምጣል። “የተጠየቀው ወፍራም ሰው ‘በጣም ስለምበሳጭ ነው’ ብሎ ይመልስለታል። ‘አንተኛውስ?’ ብሎ ከወዳጁ ይበልጥ ሰውነቱ የሚወፍረውን ሲጠይቀው፣ ‘እኔማ እንዲህ የሰማይ ስባሪ እስካክል የወፈርኩት በጣም ስለምደሰት ነው’ ብሎ ይመልሳል። እንግዲህ ቀጭኑ ሰውዬ ከሁለቱ እንደማንኛቸው መሆን እንደሚፈልግ እያሰበ መንገዱን ቀጠለ እልሃለሁ። የእኛም ነገር እንደዚሁ ነው፤” ብሎ ምሳሌውን ያመጣው ጎልማሳ ቀልዱን ጨረሰ።

ወግ በምሳሌ በሚደምቅበት እንደ እኛ ባለ ማኅበረሰብ አንዱ ያቦካውን አንዱ መጨረሱ ልማድ ስለሆነ፣ መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ ተሳፋሪዎች መነጋገር ይዘዋል። “አይ ሰው ምስኪኑ! ደስታውም ሐዘኑም የማይታወቅበት ፍጡር፤” ስትል አንዷ አጠገቧ የተቀመጠው ተቀብሎ፣ “እኔ ደግሞ ብስጭት ሲያደልብ ዛሬ መስማቴ ነው። አስቢው እስኪ? እውነት የልብ ሐዘን የውፍረት ምንጭ ቢሆን በአገራችን በሚታየው እንጭጭ አክቲቪስትነት፣ አዙረው ማሰብ በተሳናቸው ጨካኞችና በጥቂቶች ጥጋብ አንጀቱ የሚነፍረው ሕዝብ በ‘ሃምበርገር’ ውፍረት ከሚሰቃየው የአሜሪካ ሕዝብ በላይ አይሰቃይም ነበር? ይቀልዳሉ እንዴ ሰውዬው?” ይላታል። ጎልማሶቹ በራሳቸው ጨዋታ ታጥረው የቆሰቆሱት እሳት የት እንደ ደረሰ መታዘብ ተስኗቸዋል። ወዲያው ልጅት ተቀበለችውና፣ “ያው ነው እባክህ! ሲያዩን በሥጋ የደላን እንመስላለን እንጂ ውስጣችን ጉፋያ ነው። እንዲያማ ባይሆን የገዛ ወገናችንን እየገደልንና እያፈናቀልን በሰላም እንተኛ ነበር?” አለችው። አንዱ በመስማማት አንገቱን አወዛወዘላት። የሚስማማንን ብቻ ሳይሆን የሚጎረብጠንን ጭምር ለምን እንደማንደግፍ ትዝ ሊለን የሚገባው በዚህ ጊዜ ነው፡፡

ጉዟችን ቀጥሏል። ወዲያው ግን ሾፌራችንና ወያላው ምክንያቱን ሳይረዱ ትራፊክ ፖሊስ አስቆመን። “ትርፍ ይዘሃል እንዴ?” ሾፌሩ ወደ ኋላ ዘወር ብሎ እየቆጠረን ወያላውን ጠየቀው። “ጊዜው እንደሆነ የጥቂቶች ነው፡፡ ሌሎቻችን እኮ ትርፍ ነን። ምን ትርፍ ጭነሃል ይላል ይኼ?” መሀል መቀመጫ ላይ ከአንዲት እናት ወይዘሮ ጋር የተሰየመ ወፈፍ የሚያደርገው ወጣት ጮኸ። ወያላው ሰምቶ እንዳልሰማ አለፈውና እንዳልጫነ ተናገረ። ትራፊክ ፖሊሱ በወያላው በኩል ሲሮጥ መጥቶ፣ “ክፈተው!” አለው። ወያላው ከፈተለት። ገብቶ ሞተሩ ላይ ፊቱን እንደ ዕድር ሰብሳቢ ወደ ተሳፋሪው አዙሮ ተቀምጦ “ንዳው!” አለው። “ወይ ቀጭን ትዕዛዝ!” ትላለች ጎኔ ያለች ወጣት። “ይቅርታ ትርፍ አልጭንም፤” አለ ወያላው የቀልዱን በዕፎይታ ተንፍሶ ነፍሱን እያረጋጋ። “ግድ የለም እኔ አለሁ!” አለው ትራፊኩ ቀልዱን እንደ ቀልድ ሳይቆጥር በሥልጣኑ እየተኩራራ። ሥልጣን ሳይኖራቸው የሰው ነፍስና ሥጋ የሚለዩ ሰይጣኖች በበዙበት ጊዜ ይህ ምን መኩራት ይባላል፡፡

“አቤት አንቺ አገር! ሁሉም መቼ አግኝቶ መቼ እንደሚያጣው በማያውቀው ሥልጣኑ የሚመካብሽ መሬት፤” አለ ያ ወፈፌ። የትራፊክ ፖሊሱ ደነገጠ። ወያላው ወደ ጆሮው ዝቅ ብሎ የሆነ ነገር ሲለው ከድንጋጤው መለስ አለ። ልጁን ግን እንደ አብዛኞቻችን ወደ ልቦናው የሚመልሰው ሰው እንዳጣ ቀረ። “አለመፈጠር አይቀልም ጎበዝ? ሥልጣን፣ ሀብትና ዝና ዕውቀትን በልጠው እኩልነት ይሻር? ሕግ የጥቂቶች መደበቂያና መደላደያ ምሽግ ሆኖ ሲቀር አያሳፍርም?” ይላል ወፈፌው። በከፊል ድንጋጤ በከፊል መገረም ውስጥ ያሉት የታክሲያችን ተሳፋሪዎች እርስ በእርስ እየተያዩ፣ ‘ይኼ ጉደኛ ዛሬ ሳያስጨርሰን አይቀርም’ የሚባባሉ ይመስላሉ። ወፈፌው ግን፣ ‹‹ችግኝ እንትከል ተብላችሁ ስትጠሩ ሐሜታችሁ መከራ፣ በሥርዓት ተመሩ ስትባሉ ነገራችሁ አስመራሪ፣ እንሠልጥን ስትባሉ እንደ አውሬ ካልተባላን ትላላችሁ፣ ትንሽ ሹመት ያለው ጉልቤ ቢጤ ሲመጣባችሁ ደግሞ ትደነብራላችሁ፣ ደንባራ ሁሉ . . .›› ሲል በድንጋጤ ፀጥታው በረታ፡፡

በወፈፌው የተዘጋው ልሳናችን መከፈት የጀመረው ወያላው ሒሳብ ተቀብሎ መልስ ሲሰጥ ነው። “እኔ እምለው ጊዜንና ገንዘብን ቻይናዎች በኮንትራት ያዙት እንዴ? ምነው ቶሎ ቶሎ ያልቃል?” ይላል አንዱ ተራቢ። ወያላው፣ “ኧረ ከቻይና ራስ እንውረድ። እኛ ሦስት ሺሕ ዘመን ኖረን ከሠራንላት እነሱ በጥቂት ዓመታት የሠሩት ሥራ ቀልድ ነው እንዴ?” ብሎ ለእኩያው እንደሚመለስ ሁሉ ለወጣቱ ተሳፋሪ መለሰ። “ለወሬ ጊዜማ ወገብህ ይጠብቃል፣ ምነው የሥራው ጊዜ ሀሞትህ ይፈሳል? አለ የድሮ ሰው? ምናለበት ወሬውን ትተህ መልሴን ብትሰጠኝ?” ብለው ሴትዮዋ ሲጮሁበት ወያላው ደነገጠ። ይኼን ጊዜ ደግሞ ሦስተኛው ረድፍ ላይ አጠገቤ የተቀመጠችው ወጣት ሞባይል የጽሑፍ መልዕክት ደረሰኝ ብሎ ተንጣጣ። “እኔ መቼ አፍቃሪ አጣሁ ዕድል እንጂ፤” አለች የፍቅር ጥቅስ ተልኮላት ነው፡፡ መጨረሻ ወንበር ላይም ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ጐረምሳ ስልኩ እንዲሁ የምሥጋና መልዕክት አስተላልፎ ሲንጣጣ  ሰምቶ፣ “ፍቅር ምን ችግር ነበረው እኛ ተባልተን አለቅን እንጂ!” ይላል። “በረከትና ረድኤት ያጣው ሰላማችን መሀል ክፋት ገብቶ አረፈው። እንዲህ ብለሽ ብለሽ የወለድሽ እንደሆን፣ እናቱስ አንቺ ነሽ አባቱ ማን ይሆን?’ ተብሎ ነገር መጀመሩ አይቀርም . . .” የሚለው ደግሞ ከጎልማሶቹ አንዱ ነው። በሥርዓት የተጀመረው የጨዋታ ዓረፍተ ነገር ሳያልቅ በቅንፍ ሽሙጥ አዝሎ የሚደመጠውን የነገር አንቀልባ፣ አዘውትሮ የሕዝብ ትራንስፖርት የሚጠቀመው ሕዝብ የለመደው ክስተት ነው። ይብላኝ ከሕዝብ ልብ ለራቀው ልብ የለሽ እንጂ!

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ሜክሲኮ ልንደርስ ጥቂት ሲቀረን ልማት ተኮር ወግ ተቀጣጥሏል። ጋቢና ከተቀመጡ ወጣቶች አንዱ፣ “የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም፤” ብሎ ሲተርት እንሰማዋለን። አገርን ሥራ እንጂ ውኃ የማይቋጥር ወሬ አይገነባም ለማለት ይመስላል። ወዲህ እኛ መንደር፣ “ተረቱ መቼ ጠፋን በቃል ተገማጁ፣ ማጣት ይዞን እንጂ የእጁን ይስጠው የእጁ፤” ይላሉ በምሳሌያዊ አባባል ጥርስ የነቀሉ የሚመስሉ አዛውንት። በቃላቸው ቁጥብ የነበሩት ወይዘሮ ይኼን ቀበል አድርገው፣ “ባላለቀ መንገድ ይኼ ሁሉ እሮሮ ምንድነው ነገሩ?” ሲሉ ጠየቁ። መጨረሻ ወንበር ላይ ካሉት ወጣቶች አንዷ ቀበል አድርጋ፣ “እንጃ! መንገዱስ ማለቁ አይቀርም! የጀመርነውም ቢሆን ከእነ እንከኑም ቢሆን ተስተካክሎ ይጠናቀቃል እንጂ ወደኃላ መመለስ የለም። ይብላኝ እንጂ ተኝቶ ኖሮ ሲቀሰቅሱት ህልሜን አቋረጣችሁኝ እያለ ለሚነጫነጨው?” አለች። ነገሩ ተጋግሎ አረፈው።

ታክሲያችን በሁለት ጎራ ተከፍሎ የነገር ምትሮሽ መጫወት ከመጀመሩ ወያላው፣ “መጨረሻ!” ብሎ ባያሰናብተን ኑሮ ለድብድብ የሚጋበዝ ሁሉ ነበር። “ልማት፣ ዴሞክራሲ፣ እኩልነት፣ ፍትሕና ነፃነት ሲሏቸው ለስም ይቀላሉ። አሁን ባለው አያያዛችን ፈጣሪ ራሱ ቢመጣ የምንመቸው አይመስለኝም፡፡ ገና ብዙ መንገድ ይቀረናል ጎበዝ!” ብላ ወጣቷ ብሩህ ዘመን አይታየንም ባዮችን ገረመመቻቸው። እነሱ ደግሞ የተሳለ ምላሳቸውን ከአፎቱ ማውጣት ሲጀምሩ፣ ሳይታሰብ የተነሳው ግብግብ መቋጫው የወያላው የውረዱልኝ ቁጣ ሆነ። ግብግቡ ያስገረመው የሚመስል አንድ ጐልማሳ ከጐኔ እየተራመደ፣ ‹‹በነገር እየተተነኳኰስን አንገት ለአንገት ለመያያዝ ግብግብ ከመግጠም ይልቅ፣ እየተደማመጥን ለምን የሐሳብ ፍልሚያ አናደርግም? የቸገረ ነገር . . .›› እያለ ሲብከነከን ሰማሁት፡፡ የሚሸሸው በዛ እንጂ ከዱላ ይልቅ የሐሳብ ፍልሚያ ምንኛ ደግ ነገር ነው እባካችሁ? ይህንን ጊዜ ነው እኚያ አዛውንት፣ ‹‹ሐሳብ መለዋወጥዋ ሥልጣኔ ነው፡፡ ያስቸገረን እኮ መረን የወጣው ብልግና ነው፡፡ ችግኝ እንትከል ተብሎ አገር ተነቅንቆ ሲወጣ ዓይኑ ደም የሚለብስ ባለጌ በብልግና አፉ ስንት ይላል መሰላችሁ? ለማንኛውም እኛ ችግኛችንን ተክለን አገራችንን አረንጓዴ እናደርጋለን . . . ልብ በሉ ከመንቀል መትከል ያፀድቃል . . . የተከልነው ነው ሕይወት የሚዘራልን . . .›› እያሉ ሲወርዱ እኛም አጅበናቸው ወረድን፡፡ መልካም ጉዞ!                     

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት