Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮከብ ደረጃ ያገኙ ሆቴሎች ብዛት 250 ደረሰ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዳግም ምደባው አዲስ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል አልተካተተም  

የሁለተኛ ዙር የሆቴሎችን የኮከብ ምደባ ውጤት ይፋ ያደረገው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር 250 ሆቴሎች ከአንድ እስከ አምስት ያለውን የኮከብ ደረጃ ማግኘታቸውን አስታወቀ፡፡

ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ይፋ የተደረገው የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ፣ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን ጨምሮ የምደባ ሥራው በአምስት ዙር መካሄዱን ያስታወሱት፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሒሩት ካሳ (ዶ/ር)፣ መሥርያ ቤቱ ሁሉንም ክልሎችና ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮች በራሱ ባለሙያዎች በተካሄደ ምዘና ደረጃ መስጠቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመት እንደ አዲስ ለደረጃ ምደባው የተለዩት ሆቴሎች ቁጥር 159 ሲሆን፣ የደረጃ ምደባ የተደረገላቸው ሆቴሎች ብዛት 88፣ እንዲሁም በደረጃ የተካተቱም 83 መሆናቸው ታውቋል፡፡

በደረጃ ምደባ አማካይነት የምደባ ሥርዓቱን ማሟላት ያልቻሉና ከደረጃ በታች የሆኑ ሆቴሎች አምስት ሲሆኑ፣ ያልተመዘኑ ሆቴሎችም 71 እንደሆኑ ተብራርቷል፡፡

ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ ከገቡት አዳዲስ ሆቴሎች ውስጥ በአዲስ አበባ 51 ሆቴሎች ተመዝነው 30ው ደረጃ ውስጥ መግባት ችለዋል፡፡ በአማራ ክልል 26 ሆቴሎች ምዘና ውስጥ ተካተው 13ቱ የኮከብነት ደረጃ ወጥቶላቸዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል 15 ሆቴሎች ውስጥ 12ቱ፣ በደቡብ ክልል 17 ውስጥ አሥር ሆቴሎችና በትግራይ ክልል ከ15 ሆቴሎች ስምንቱ ከአንድ እስከ አምስት ደረጃን ይዘዋል፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው የሆቴሎች የደረጃ ምደባ መሠረት ባለ አራት ኮኮብ ያላቸው ሆቴሎች ቁጥር 12 ባለ ሦስት ኮከብ 13 ባለ ሁለት ኮከብ 31 ባለ አንድ 27 እንዲሁም አምስት ከደረጃ በታች የሆኑ ሆቴሎች ተመዝግበዋል፡፡ ስድስት ወራት በፈጀው የሆቴል የምደባ ሥርዓት መሠረት እያንዳንዱ የሆቴሎች አገልግሎት መስጫ ክፍሎች ውጫዊና ውስጣዊ ገጽታዎች ላይ የአካል ምልከታን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በደረጃ ምደባ ሥርዓት ውስጥ በርከት ያሉ ትልልቅ ሆቴሎች የሥራ አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸውን ተከትሎ በሚቀጥለው መርሐ ግብር ውስጥ መመዘን እንደሚፈልጉ ማስረዳታቸውን መዛኙ አካል አብራርተዋል፡፡

በምዘናው ወቅት ለደረጃ ምደባ ሥራ ብቁ ሆነው ያልተገኙ ሆቴሎች ወደፊት  ደረጃ ውስጥ እንዲገቡ ሙያዊ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሲሆን፣ በአንፃሩ ፈቃደኛ ያለመሆን፣ ለጉዳዩ ትኩረት ያለመስጠት፣ የንጽህናና የፈሳሽ አወጋገድ ሥርዓት ጉድለት፣ ለምዘናው ያላቸው ግንዛቤ እጥረት እንዲሁም የደረጃ መዳቢው አካል ለምዘና ሲመጣ ተሽቀዳድሞ እንደ አዲስ ዕቃዎችን ማሟላት የመሳሰሉ ችግሮች መታየታቸው ተጠቅሷል፡፡

ባለሀብቱ የቀረጥ ነፃ አገልግሎት የኃይል ዕጥረት ብሎም ለማስፋፊያ ግንባታ የሚያውለው ተጨማሪ መሬት ከማግኘት አንፃር ከፍተኛ ችግር እንዳለበት አንስተዋል፡፡ በሆቴሉ ባለንብረቶች ዘንድ የሆቴሎችን ዲዛይን ጀምሮ ተገንብተው እስኪጠናቀቁና አገልግሎት መስጠት እስኪጀምሩ ድረስ የተጠናከረ የሥነ ሕንፃና ምህንድስና ማድረግ እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡ በተለይ በርካታ ሆቴሎች የእሳት አደጋን መከላከል የሚያስችልና ሙቀትን መቆጣጠሪያ መሣሪያ ከማስገጠም አንፃር ክፍተቶች እንዳሉ እንዲሁም የንጽህና ችግሮች ማስተካከል ይሻሉ ተብሏል፡፡

በ2007 ዓ.ም. የጀመረው የሆቴሎች የኮከብ የደረጃ የምደባ ከአንድ እስከ አምስት የኮኮብ ደረጃ የተሰጣቸው ሆቴሎች ዝርዝር ይታወሳል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዝቅተኛ የኮኮብ ደረጃ ያገኙት ሆቴሎች ራሳቸውን አሻሽለው ለዳግም ምዘና ይቀርባሉ ከተባሉት ውስጥ ሒልተን አዲስ ሆቴል ከዚህ ቀደም በአምስት ኮከብነት ከሚታወቅበት ደረጃው ወደ ሦስት ኮከብ ደረጃ ዝቅ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ በመጪው ምዘናም እንዲህ ያለውን ደረጃ ከሚያሻሽሉ ሆቴሎች መካከል አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደረገው የኮኮብ ደረጃ ምደባ መሠረት ሸራተን ሆቴል፣ ኢሊሌ ሆቴል፣ ራዲሰን ብሉ ሆቴልና ካፒታል ሆቴልና ስፓ የአምስት ኮኮብ ደረጃ ካገኙት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

በሌላ በኩል በአገር አቀፍ የኮከብ ምደባ ሥርዓት ውስጥ ከሚካተቱ ሆቴሎች ባሻገር የቱሪስት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች፣ ሎጅና ሬስቶራንቶች የኮከብ ምዘና እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ የሆቴሎችን የኮከብ ደረጃ ይፋ ያደረገው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በቀጣይ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ሥፍራዎችና ሌሎችም የቱሪስት አገልግሎት ሰጪዎች ደረጃ እንደሚያወጣላቸው አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች