[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር ቢሯቸው እያወሩ ነው]
- ይገርማል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ ነው የሚገርመው?
- በቃ ተተኮስን፡፡
- ማን ነው የተተኮሰው?
- በአንድ ጀንበር እኮ ነው የተተኮስነው፡፡
- ምንድነው የምታወራው?
- ተቸበቸበ እኮ፡፡
- ምኑ?
- ችግኙ ነዋ፡፡
- ምን ጥያቄ አለው?
- እኔ እንደዚህ ይሆናል ብዬ አልጠበኩም፡፡
- እንዴት?
- ያው ሕዝቡ አልተደመረም ብዬ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሕዝቡ እኮ በልቡ ተደምሯል፡፡
- እሱንማ አሁን በሚገባ አረጋግጫለሁ፡፡
- እንዴት?
- ይኼን ያህል ሕዝብ በችግኝ ተከላው ይሳተፋል ብዬ አልጠበኩማ፡፡
- ሕዝቡ እኮ ለውጥ የተራበ ነው፡፡
- አዎን ግን አሁን አሁን እኮ ለውጡን እየተጠራጠረው ነበር፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- በቃ አብዛኛው ሰው ለውጡ አቅጣጫውን ስቷል እያለ ነበራ፡፡
- እንዴት አድርጎ ነው ለውጡ አቅጣጫውን የሳተው?
- ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ እኮ ከነበረችበት ችግር የባሰ እየገጠማት ነው የሄደችው፡፡
- ይህ የፀረ ለውጡ አራማጆች ሐሳብ ነው፡፡
- በመሬት ላይ ያለውም ሀቅ ግን እንደዚያው ነው፡፡
- እንዴት?
- ማለቴ ኢኮኖሚው አይሉ ፖለቲካው ሁሉም ነገር ተቃውሶ ነበር፡፡
- ያው ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል አይደል የሚባለው?
- ቢሆንም ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ እኮ የመፍረስ ጫፍ ላይ ናት፡፡
- እ…
- ይኸው በየጊዜው የሚፈናቀለው ሕዝብ ብዛት ከዓለም ራሱ አንደኛ አድርጎናል እኮ፡፡
- ምን ይደረግ ታዲያ?
- በዚህ ሁሉ ቀውስ ውስጥ ታዲያ እንዲህ ዓይነት የሕዝብ ንቅናቄ በጣም ያስገርማል፡፡
- ሕዝቡማ ለአገሩ ያለውን ፍቅር በሚገባ አስመስክሯል፡፡
- ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር እኛ በግርግሩ አምልጠናል፡፡
- ጥሩ ተሸቀለ?
- ምን ጥያቄ አለው፡፡
- ለነገሩ በችግኝ ተከላው እኮ የራሳችንንም ሪከርድ ሰብረነዋል፡፡
- ሰሞኑን ምን ያልተሰበረ ሪከርድ አለ?
- ደግሞ ሌላ የምን ሪከርድ ተሰበረ?
- እርስዎም ሪከርድ ሰብረዋል፡፡
- የምን ሪከርድ?
- የኮሚሽን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የፖለቲካ ተመራማሪ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- በጣም ደስ ይላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ?
- የሰሞኑ የችግኝ ተከላ እንቅስቃሴ ነዋ፡፡
- እኛ እኮ የተግባር ሰዎች ነን፡፡
- እርሱን እንኳን ተውት፡፡
- ምነው?
- አሁን የፖለቲካ ዲስኩርዎትን እንዲያሰሙኝ አልፈልግማ፡፡
- ይኼ እኮ ዲስኩር ሳይሆን ሀቅ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እናንተ እኮ የምትተቹት እንዲያውም በዚህ ነው፡፡
- በምን?
- የተግባር ሰዎች አይደሉም ተብላችሁ ነዋ፡፡
- ይኸው አረጋገጥን አይደል እንዴ?
- በእርግጥ በችግኝ ተከላው ጥሩ ሥራ ነው የተሠራው፡፡
- ገና ሌላ ብዙ እንሠራለን፡፡
- ለጊዜው ጉራውን ተውትና ሕዝቡን ማመስገን አለባችሁ፡፡
- እሱማ ግዴታ ነው፡፡
- ሕዝቡ የፖለቲካ ልዩነቱን ወደጎን ትቶ እንዲህ በነቂስ ወጥቶ በችግኝ ተከላው በመሳተፉ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡
- እውነት ብለሃል፡፡
- ግን ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ ምን ያህል አገሩን እንደሚወድ አላያችሁም፡፡
- በደንብ ነው እንጂ ያየነው፡፡
- ታዲያ ለምን ታባሉታላችሁ?
- እ…
- አሁን ይኼን ታሪክ የሠራ ሕዝብ በብሔር ከፋፍላችሁ ማባላቱ ጠቃሚ ነው ትላላችሁ?
- ኧረ እኛ መቼ አባላነው?
- ተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምነው?
- ሰው መቼ ከቦታ ቦታ እንደፈለገው ተንቀሳቅሶ ይኖራል፡፡
- ይኼ እኮ የአንዳንድ ጠባቦች ሴራ ነው፡፡
- ይኸው በቅርቡ እንኳን በክልልነት ጥያቄ ቀውስ ስንቶች አይደል እንዴ የተጎዱት?
- ልክ ነህ፡፡
- አሁን ደግሞ ሕዝቡ አገራዊ ጥሪ ሲቀርብለት መቼ አሳፈራችሁ?
- እኛም ከጠበቅነው በላይ ነው የሆነብን፡፡
- ታዲያ እናንተ ለፖለቲካ ቁማራችሁ እያላችሁ ሕዝቡን ማለያየቱ አይቀርባችሁም?
- ምን እያልክ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እያመራት ያለችው በእናንተ ፖለቲከኞች ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት እንጂ ሕዝቡ መቼም ቢሆን ለአገሩ ቅድሚያ እንደሰጠ ነው፡፡
- እሱንማ አሁን በሚገባ ተረድተናል፡፡
- ለማንኛውም ሕዝቡን በብሔር እየከፋፈሉ ማባላት ለማንም አይጠቅምም፡፡
- እ…
- ስለዚህ ልዩነታችንን ለጊዜው ወደጎን ትተን መተባበሩ ይጠቅመናል፡፡
- እውነት ነው፡፡
- አገሪቱ ላለችበት ችግርም መፍትሔው ተገኝቷል፡፡
- ምንድነው?
- አንድነት!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- ለመሆኑ ተሳተፍክ?
- በምኑ?
- በችግኝ ተከላው ነዋ፡፡
- ምን ዓይነት ጥያቄ ነው?
- ምኑ ነው ያልገባህ?
- ጥያቄው ነዋ፡፡
- እንዴት?
- ችግኝ መትከል እኮ አገራችንን ነው የሚጠቅመው፡፡
- እኔም እኮ ለዚያ ነው የጠየቅኩህ?
- ተክያለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ያው የፖለቲካ ልዩነት ስላለን ምናልባት ላትተክል ትችላለህ ብዬ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ችግኝ እኮ ፓርቲ የለውም፡፡
- ቀልደኛ ነህ መቼም?
- መቼ ነው ግን የሚለወጠው ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑ?
- የፖለቲካ ሥርዓታችን ነዋ፡፡
- እንዴት?
- አገራዊ አጀንዳ ላይ እኮ አንድ ላይ እንተባበራለን ብለን ማሰብ ካልቻልን ያሳዝናል፡፡
- ያው የፖለቲካ ሥርዓታችን እኮ ሴራ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው፡፡
- ለነገሩ በብቃትና በአቅም ላይ ቢመሠረት ኖሮ አገራችን አሁን ያለችበት ችግር ውስጥ ባልተዘፈቀች ነበር፡፡
- የምን ችግር ነው?
- ምን ችግር ውስጥ ያልተዘፈቀ ነገር አለ፡፡
- እ…
- ፖለቲካው ቢሉ ኢኮኖሚው፣ ሁሉ ነገር መላ ቅጡ ጠፍቶታል አይደል እንዴ?
- ያው ለውጥ ላይ ስለሆንን ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ለሁሉም ችግር እኮ ለውጡ ሰበብ መሆን አይችልም፡፡
- ምን?
- የሆነ ችግር ሲመጣ ለውጥ ላይ ስለሆንን እየተባለ መድበስበስ የለበትም፡፡
- ለውጡን አትደግፈውም ማለት ነው?
- ለውጡን ሳይሆን በአገሪቱ ያለውን ቀውስ ነው የማልደግፈው፡፡
- እ…
- እናንተ አሁን አሁን ለውጡን እንደ ማርያም መቀነት እያደረጋችሁት ነው፡፡
- ምን?
- ለሁሉም ችግር ለውጡ ላይ ነው የምታላክኩት፡፡
- የለውጡ ተቃዋሚ መሆንህን በሚገባ ተረድቻለሁ፡፡
- እንዳይመስልዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ በቅርቡ ተደራጅታችሁ መንቀላችሁ አይቀርም፡፡
- ምንድነው የምንነቅለው?
- የተተከሉትን ችግኞች ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በአገሪቱ ከችግኝ ነቀላ በላይ የሚያሳስብ ነገር አለ፡፡
- ምን?
- የሕዝብ ነቀላ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]
- እንኳን ደስ አለዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምኑ?
- ለሪከርዱ፡፡
- እኛ እኮ ሪከርድ መስበር የለመደብን ነን፡፡
- ለነገሩ 100 ፐርሰንት ምርጫ በማሸነፍ ሪከርድ የያዝን ፓርቲ ስለሆንን ይኼኛው ብዙም ላያስደንቅ ይችላል፡፡
- ምን?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- አሁን የእኛን ስም ለማጠልሸት ነው ከማይነፃፀር ነገር ጋር ይኼን የችግኝ ተከላ የምታነፃፅረው?
- ምን ችግር አለው ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት ችግር የለውም?
- 100 ፐርሰንት ፓርላማ ማሸነፋችንን ያፍሩበታል ማለት ነው?
- እ…
- እናንተ ቀጣዩ ምርጫ በተያዘለት ፕሮግራም ላይካሄድ ይችላል እያላችሁ አይደል እንዴ?
- ማን አለ?
- እሱን እንኳን ተውት፡፡
- ምን?
- ለማንኛውም እንኳን ደስ አለዎት፡፡
- ለመሆኑ አንተ ችግኝ ተክለሃል?
- እኔማ ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ነበር የምተክለው፡፡
- የምቆርጠው ማለትህ ነው?
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እናንተ አይደላችሁም እንዴ አገሪቱን ባዶ ያስቀራችኋት፡፡
- ምን?
- የአገሪቱን ደን እየጨፈጨፋችሁ ስትሸጡ ነበር እኮ፡፡
- ማን ነው ያለው?
- እናንተ መቁረጥ እንጂ መትከል አትችሉም፡፡
- እ…
- ባይሆን በመትከል የታወቃችሁበት ነገር አለ፡፡
- ምን በመትከል ነው የታወቅነው?
- ችግር!