ክፍል አንድ
በፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
መግቢያ
በየጊዜው የተለያዩ ጸሐፊዎች አዳዲስ ጽሑፎችን በመጻፍ ለሰፊው ሕዝብ ለንባብ ያቀርባሉ፡፡ እንደምገምተው ከሆነ በዚህ መልክ የታሪክን አደራ ለመወጣት በማሰብና አገራቸውም እንዳትበታተን ለማሳሰብ ነው፡፡ ይሁንና ግን አንደኛ የአብዛኛዎች የአጻጻፍ ሥልት ግልጽ አይደለም፡፡ ሁለተኛ አብዛኛዎች ጽሑፎች በተወሰነ ሐሳብ ላይ ያተኮሩና በዚያው ላይ የሚሽከረከሩ አይደሉም፡፡ በሌላ አነጋገር እንድንወያይበትና እንድንከራከርበት በር የሚከፍቱ አይደሉም፡፡ ሁሉም እንደፈለገውና እንደመሰለው የሚጽፍ እንጂ ከተጨባጭ ሁኔታዎችና ከህሊና ሁኔታ በመነሳት ችግራችንን የሚተነትን አይደለም፡፡ በሦስተኛ ደረጃ በአንዳንድ ድረ ገጾች ላይ የሚወጡት ጽሑፎች በአንድ ግለሰብ ሐሳብና ራዕይ ላይ ያተኮሩ ሳይሆኑ የግለሰብን ስም የሚያጎድፉ ወይም ሞራሉ እንዲወድቅ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ አሁንም በሌላ አነጋገር ሳይንሳዊ ትንተና መሆናቸው ቀርቶ ተራ እንካ ስላንቲያ ወይም ስድብ ናቸው፡፡ ስለሆነም የሚያሰተላልፉት መልዕክት ይህንን ያህልም የሚጨበጥና እንድናስፋፋው ወይም ትችታዊ በሆነ መልክ እንድንገመግመው የሚጋብዘን አይደለም፡፡
እንደሚታወቀው አንድን ኅብረተሰብ የሚመለከት ጽሑፍ ተጽፎ በሚቀርብበት ጊዜ የራስን ስሜት ለመግለጽ ተብሎ አይደለም፡፡ እንደሚገባኝ ከሆነ ለኅብረተሰቤ ያገባኛል የሚል፣ ስለዚህም የራሴን አስተዋጽኦ ማበርከት አለብኝ ብሎ ብዕሩን የሚሰነዝር ስለሚጽፈው ነገር ማወቅ አለበት፣ ለምን እንደሚጽፍ መረዳት አለበት፡፡ በሌላ አነጋገር ምን መልዕክትና ትምህርት ለማስተላለፍ እንደሚፈልግ ማውጣትና ማውረድ አለበት፡፡ ምን ዓይነት የአሠራር ሥልት እንደሚጠቀም መገንዘብ አለበት፡፡ ዝም ብሎ በጥሩ አማርኛም ሆነ እንግሊዝኛ አቀነባብሮ ለመጻፍ ብቻ ወይስ ሳይንሳዊ የአሠራር ሥልትን በመጠቀም በተለይም ታዳጊውን ትውልድ ለማስተማር እችላለሁ ብሎ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ከመጀመርያውኑ መረዳት አለበት፡፡ ይህም ማለት አንድን ኅብረተሰብም ሆነ አንድን ሁኔታ የሚመለከት ነገር ለመጻፍ ስንነሳ የተወሰነ ስልትንና ሳይንሳዊ የአተናተን ዘዴን መከተል አለብን፡፡ አንድን የአሠራር ዘዴና ሳይንሳዊ አተናተንን ያልተከተለ አጻጻፍ የሰውን ጭንቅላት ለማደስና ለማስተማር አይችልም፡፡ እውነተኛውንም የነፃነት መንገድ ይዘን እንድንጓዝ መመርያ ሊሆነን አይችልም፡፡ ከተጨባጭ ሁኔታዎችና ከአገዛዝ አወቃቀር፣ እንዲሁም ከአጠቃላዩ የሕዝብ አስተሳሰብ ተነስቶ የማይጻፍና የችግሮችንም አመጣጥ በተቻለ መጠን ተቀራራቢ በሆነ መንገድ ለማመልክት የማይችል ጽሑፍ የሰውን አስተሳሰብ በታኝ ብቻ ሳይሆን፣ የአንድን ኅብረተሰብም ችግር እንዳይፈታ እንቅፋት ይሆናል፡፡ በየጊዜው በኢትዮጵያውያን ድረ ገጾች ላይ በእንግሊዝኛም ሆነ በአማርኛ የሚወጡትንና ለንባብ የሚቀርቡትን ጽሑፎች ስመለከትና ሳገላብጥ ግራ የሚያጋቡኝ ነገሮች አሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለአገራችን ተቆርቋሪ ነን ብለውና አጥብቀው የሚሟገቱትን ሰዎች ጽሑፍ ሳነብ ለምን እንደሚጽፉ፣ ምን ዓይነት ሥልትና ሳይንሳዊ ዘዴን እንዲሁም የትኛውን ፍልስፍና መሠረት በማድረግ እንደሚጽፉ ለማወቅ ግራ ከተጋባሁ ዘመናት አልፈዋል፡፡ የአገራችንም የተወሳሰበ ችግር እንዴት እንደሚፈታና እንደ ኅብረ ብሔር ወይም እንደ አገር በጠንካራ መሠረት ላይ በየአቅጣጫው እንዴት መገንባት እንዳለባት የሚጠቁም አጻጻፍ አይደለም፡፡
ስለሆነም አገራችንና ሕዝባችንን ነፃ እናወጣለን፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በማድረግ የተከበረችና የተፈራች አገር እንዲገነባ እናደርጋለን፣ ሺሕ በሺሕ የሚቆጠሩ ሳይንቲስቶች፣ የቴክኖሎጂ ሰዎች፣ ፈላስፋዎችና የጥበብ ሰዎች ለማፍራት የሚያስችል መሠረት መጣል አለብን የምንል ከሆነ ከሳይንሳዊ ጥናትና ትንተና ማለፍ አንችልም፡፡ የፍልስፍና መሠረትና እምነትም ያስፈልገናል፡፡ ማንኛውም ነገር ምግብ እንኳ ሳይቀር ከሳይንስ አኳያ እየታየ የሚተከልና ለምግብም የሚቀርብ ካልሆነ በሽታን ነው የሚያስከትለው፡፡ በተጨማሪም ከሳይንስ አንፃር እየታየና እየተመጠነ የማይቀቀል ምግብ የመጨረሻ መጨረሻ ጤንነትን ያቃውሳል፡፡ አንድ ጽሑፍም እንዲሁ ከሳይንስ አኳያ የማይጻፍና የተወሰነ የአሠራር ዘዴን የማይከተል ከሆነ የታዳጊን ትውልድ ጭንቅላት ከማደንዘዝ በስተቀር የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ አይኖርም፡፡ ጭንቅላቱ እንዲሾልና ተጨባጩን ሁኔታ በደንብ እየተመለከተ ትንተና ለመስጠት የማይችል ወጣት ትውልድ በሚፈለፈልበት ኅብረተሰብ ውስጥ ደግሞ ትግል ከስሜታዊነት ሊዘልቅ በፍፁም አይችልም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ትውልድ ደግሞ በራሱ ላይ እንዳይተማመንና ጥቂት ግለሰቦችን እያመለከ እንዲኖር ይገደዳል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ የግዴታ ወደ እርስ በርስ መነታረክና ወደ መጨራረስ እንድናመራ ያስገድደናል፡፡ በየካቲቱ አብዮት ወቅት የደረሰው የወንድማማቾች መተላለቅና እስከ ዛሬም ደርሶ እንዳንግባባ ያደረገን ነገር ከዚህ ከሳይንስና ከፍልስፍና ውጭ የተደረገና የሚደረግ ትግል መመርያችን በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም ከሳይንስ፣ ከፍልስፍና፣ ከዲያሌክቲክና ከሶስዮሎጂ ውጭ ትግል ማድረግ በመጀመራችን ስንትና ስንት መቶ ሺሕ ሕዝብ እንዲያልቅ ማድረጋችን ብቻ ሳይሆን፣ ትግሉ ሁለት ትውልድ አልፎ እስከ ዛሬ ድረስ ሲያፋልመንና ሲያነታርከን ቆይቷል፡፡ በዚህም ከቀጠለ በቀላሉ መቋጠሪያ የሚገኝለት አይመስለኝም፡፡ ይህ ጸሐፊ ይህንን ችግር ተረድቶ የአመለካከታችንን ሁኔታዎች የማንበብ ጉዳይና ከዚያ በመነሳት እንዴት ትንተና ማድረግ እንዳለብን ከአሥር ዓመታት በላይ የፈጀ ትግል ቢያደርግም ተደማጭነት ሊያገኝ አልቻለም፡፡ በዚህም የተነሳ ሀቀኛውን የትግል ዘዴ ከአሳሳቹና የሰውን ጭንቅላት ከሚያበላሸው የትግል ዘዴ ለመለያየት የቱን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ከተገነዘብኩኝ ዘመናት አልፈዋል። ይሁንና ግን ደግሞ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ እንደ ተሸናፊነት መቆጠሩ ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ወንጀልም እንደ መሥራት ይቆጠራል፡፡ የድህነቱ ዘመን እንዲራዘምና ሕዝባችን ውርደትን ተከናንቦ በውጭ ኃይሎች ዘለዓለሙን እየተናቀ እንዲኖር አስተዋጽኦ እንደማበርከት ይቆጠራል።
ያም ሆነ ይህ እኔም ሆነ ሌሎችም ጻፉ በአጠቃላይ ሲታይ የአስተሳሰብ ለውጥ (Mindset) ማድረግ እስካልቻልን ድረስ ምንም ዓይነት ለውጥ ልናመጣ አንችልም፡፡ ዛሬ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሰፈነባቸው የሚባሉትን የምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮችን ሁኔታ ስንመለከትና ስንመረምር በየአገሮች ውስጥ የአስተሳሰብ ለውጥ ሳይደረግ ዝም ብሎ በጭፍን ትግል የተካሄደበት ቦታ የለም፡፡ በሌላ ወገን ግን የአስተሳሰብ ለውጥ አንድ ቦታ ላይ በመጫን የሚመጣ ሳይሆን በየጊዜው ራስን በመጠየቅና የጭንቅላት ጂምናስቲክ በማድረግ የሚመጣ ነው፡፡ የታሪክን ሒደት መረዳት የሚቻለውና የአንድን ኅብረተሰብ አስቸጋሪ ሁኔታ መገንዘብ የሚቻለው ከሳይንስ አንፃር ትግል ለማድረግ ሲሞከርና ጥረት ሲደረግ ብቻ ነው፡፡ በየጊዜው ጥያቄን ማቅረብ ሲቻል ብቻ ነው ተቀራራቢ መልስ ማግኘት የሚቻለው፡፡ ከዚህ ስንነሳ የተወሳሰበውን የአገራችንን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህልና የሥነ ልቦና ችግሮችን ለመረዳት የግዴታ የአዕምሮን መሠረታዊ ወይም ቁልፍ ቦታ መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ቆንጆም ሆነ መጥፎን ነገር ማድረግ የምንችለው በአዕምሮአችን እየታገዝን በመሆኑ የአዕምሮን ቁልፍ ሚና መረዳቱ በተለያየ መልክ የሚታየውንና የሚገለጸውን ችግር ለመረዳት ያግዘናል።
ዋናው ችግራችን የአዕምሮን ወይም የመንፈስን ትርጉም ያለመረዳት ነው!
እንደሚታወቀውና ሁላችንም የምንቀበለው ሀቅ ማንኛውም ሰው በግልጽ የምናየውና የምንዳስሰው አካል ብቻ ሳይሆን መንፈስም ሆነ አዕምሮ እንዳለው ነው። እኛም ራሳችን አለን። እንደ አስተዳደጋችን፣ እንደ ትምህርት አቀሳሰማችንና ንቃተ ህሊናችን የማሰብ ኃይላችን፣ አንድን ነገር መረዳትና መተንተን፣ ወይም ያለመረዳትና ለመተንተን ያለመቻል፣ ማውጣትና ማውረድ፣ ግንዛቤን ማሳደር፣ ወይም ግንዛቤ ማሳደር ያለመቻል፣ አርቆ የማሰብ ኃይላችንም ሆነ ያለማሰብ፣ ቁጠኛ መሆንም ሆነ አለመሆን፣ አመፀኛ መሆንም ሆነ፣ አንድን ነገር በሰላምና በውይይትም ሆነ በክርክር መፍታት መቻል ወይም ያለመቻል፣ ስለሰው ልጅ የሚኖረን ግንዛቤም ሆነ ግንዛቤ ያለመኖር፣ ስለ ነፃነትም ሆነ ስለ ዕድገት የሚኖረን ግምትና ግምት ያለመኖር፣ በጠቅላላው ከየት እንደመጣን፣ በዚህች ዓለም ላይ ለምን እንደምንኖርና ምን መሥራት እንዳለብንና ወዴት እንደምንጓዝ ማወቅና መረዳት የምንችለው በመንፈስና በአዕምሮ ኃይላችን አማካይነት ብቻ ነው። በአጭሩ፣ መጥፎ ነገርም ሆነ ጥሩ ነገርን ማድረግ የምንችለው በአዕምሮአችንና በመንፈሳችን እየተመራን ነው፡፡ ለማንኛውም ዓይነት ድርጊታችን፣ በተለይም ለኅብረተሰብ ዕድገት በሚደረገው ትግል የመንፈስ አወቃቀራችና የንቃተ ህሊናችን ሁኔታ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛሉ ማለት ነው፡፡ ከመንፈስና ከአዕምሮ እንዲሁም ከንቃተ ህሊና ውጭ የምናደርገው ምንም ነገር የለም፡፡ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚዳሰሰውና በግልጽ የሚታየው አካላችን የመንፈሳችን ተገዥ ወይም በመንፈሳችን የሚመራ ነው፡፡ በሌላ ወገን ግን መንፈሳችን የአካላችን ተገዥ በመሆን ድርጊታችንን ወደ ማይሆን አቅጣጫ በመመራት ችግር ፈጣሪዎች እንድንሆንና ኅብረተሰብንም እንድናመሰቃቅል ያደርገናል፡፡ ይሁንና ግን የማሰብ ኃይላችን የዳበረ፣ የተወሳሰቡ ነገሮችን መረዳት የሚችልና የመተንተንም ኃይል ካለው የምናደርገውን እናውቃለን ማለት ነው፡፡ መንፈሳችን የሰውነታችን ወይም የአካላችን ተገዥ መሆኑ ቀርቶ መንፈሳችን የበላይነትን በመቀዳጀት ታሪካዊ ነገሮችን መሥራት እንችላለን፡፡
በብዙ ምርምሮችና ጥናቶች እንደተደረሰበት ለአንድ ሰው የማሰብ ኃይልና ማመዛዘን እንዲሁም በረቀቀ መልክ ማሰብ መቻልና ያለመቻል የተወለደበትና ያደገበት ኅብረተሰብ ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የምርት ኃይሎች ማደግ ወይም አለማደግ፣ የባህል ዕድገት መኖር ወይም አለመኖር፣ የከተማዎች በቆንጆ መልክ መሠራትና ያለመሠራት፣ በገጠር ውስጥ ማደግና ያለማደግ፣ ወዘተ. በአሰተሳሰባችን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል። የቤተሰብ ሁኔታ፣ የማኅበረሰብ የአኗኗር ሥልትና እንዲሁም አጠቃላዩ የኅብረተሰብ አወቃቀር የአንድን ሰው አስተሳሰብ ይቀርፁታል ድርጊቱንም ይወስናሉ፡፡ ለዚህ ነው መጀመርያ የግሪክ ፈላሳፎች ምርምር ሲጀምሩ ለአዕምሮ ከፍተኛ ቦታ የሰጡት፡፡ በእነሱ እምነትም የማንኛውም የሰው ልጅ ድርጊት በአርቆ የማሰብና ያለማሰብ ኃይሉ የሚወሰን ሲሆን፣ ይህ በአንፃሩ ደግሞ ሊወሰን የሚችለው በቀሰመው ዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው፡፡ በተለይም ሶፊስቶችን አጥብቀው ይዋጉ የነበሩት ሶክራተስና ፕላቶ አርቆ የማሰብ ኃይልን ሚና ሲያነሱ ትክክለኛ ዕውቀት ለማሰብ ኃይላችንና ለፈጠራ ሥራችን የቱን ያህል ወሳኝ ሚና እንዳለው በማስመር ነው፡፡ ለዚህም ነው በሚታዩ ነገሮች ላይ ብቻ ያተኮረውንና በጥቂት ሰዎች ተደንግጎ የሚቀርበውን ሕግም ሆነ ዕውቀት እንደ መመርያ አድርገው ማስተማርና መስበክ የጀመሩት፣ ሶፊስቶችን ወይም የተሙለጨለጨ አስተሳሰብ ያላቸውን ምሁሮች አጥብቀው መዋጋት የጀመሩት፡፡ በሶክራተስና በፕላቶም እምነት ግሪክ በጊዜው የነበራትን የበላይነትና ኃያልነት ልትነጠቅና የመጨረሻ መጨረሻም ሥልጣኔዋ ሊዳከም የቻለው በጊዜው የነበሩት አገዛዞች በሶፍስቲያዊ ዕውቀት በመሠልጠናቸውና ከዚህም በመነሳት በሥልጣንና በሀብት በመመካታቸውና በመባለጋቸው ነበር፡፡ ሌሎች ሥልጣኔዎችና ኃያላን መንግሥታትም ሊፈራርሱና ሊወድሙ የቻሉት በጉልበትና በሀብት በመመካት ብቻ በመስፋፋታቸውና የመጨረሻ መጨረሻ ኃይላቸው በመዳከሙ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የአዕምሮና የመንፈስ አለመዳበር፣ አርቆ አለማሰብና ባሉት ነገሮች ብቻ ጠግቦ ወይም ተደስቶ መኖርና፣ ይህንን እንደ ባህል አድርጎ ማስፋፋትና ማስተማር ለዕድገት ከፍተኛ እንቅፋት እንደሚሆን የታወቀ ጉዳይ ነው። ፈላስፋዎች ትችታዊ አመለካከት ወይም እየመላለሱ መጠየቅ የሚሉት ቁም ነገር አለ። ይህም ማለት አንድ የሚነገርን ነገር ዝም ብሎ መቀበል ሳይሆን መመርመርና ትክክል መሆኑና አለመሆኑን በጥያቄ ውስጥ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ አጥብቀው ያስተምራሉ፡፡ ስለሆነም በፕላቶ እምነትና መመርያ አንድን ነገር ዝም ብሎ ከመቀበል በፊት የግዴታ እየመላለሱ መመርመርና ማገናዘብ እንደሚያስፈልግ ያስተምራል፡፡ አንድ ነገር ተቀባይነትን ከማግኘቱ በፊት በዲያሊክቲክና በፍልስፍና መነጽር መመርመርና መታሸት አለበት፡፡ በዚህ አማካይነት ብቻ ሀቀኛውን ከአሳሳቹ፣ ለዕውቀትና ለሥልጣኔ የሚታገለውን ለሥልጣንና ለራሱ ዝና ብቻ ከሚታገለው ነጥሎ ማወቅ ይቻላል፡፡ ይህንን ሳያደርግ ዝም ብሎ በጭፍን በትግል ዓለም ውስጥ የገባ የአንድ ሰው ወይም የአንድ ድርጅት ጭራ በመሆን የራሱን ነፃነት ማጣቱ ብቻ ሳይሆን ለእውነተኛ ሕዝባዊ ነፃነት የሚደረገውን ትግል ያደናቅፋል፡፡ በየጊዜው ጠብ ጫሪ በመሆን ኅብረተሰብዓዊ ስምምነት እንዳይኖር በማድረግ የአንድ ሕዝብ ዕድል በውጭ ኃይሎች እንዲወሰን ያደርጋል፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ መንፈስ ወይም አዕምሮ በመሠረቱ የቆንጆ ነገሮች ማፍለቂያ ነው፡፡ አንድን ነገር በሥነ ሥርዓት እንድንሠራ ወይም እንድናደራጅ፣ እንድናቅድ፣ እንድናቀናጅና መልክ እንድንሰጠው የሚመራን ነው። መንፈስ ወይም አዕምሮ የሙዚቃ፣ የሥዕል በአጠቃላይ ሲታይ ደግሞ የዕውቀት ምንጭ ሲሆን፣ በዚህ እየተመራን ቆንጆ ቆንጆ ነገሮችን እንድናስብና ተግባራዊ እንድናደርግ መመርያ የሚሰጠን ነው፡፡ ለሕይወታችን ትርጉም እንድንሰጠው ሰው መሆናችንን የሚያረጋግጥልን ልዩ ነገር ነው፡፡ እንደሚባለው መንፈሱ ቆንጆ የሆነና የማሰብ ኃይሉ የዳበረ ሰው ተዓምር ይሠራል፡፡ በረሃውን ወደ ገነት መለወጥ ይችላል፡፡ ልዩ ዓይነት ቅርፅና ውበት በመስጠት የሰው ልጅ ኑሮ ዝርክርክ እንዳይሆን ያደርጋል። ስለሆነም ቆንጆ መንፈስ የፍቅር፣ የሰላም፣ የሥርዓት፣ የጥበብና የፈጠራ ምንጭ ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ መንፈሱ የተረበሸ ወይም በልጅነቱ በደንብ ያልተኮተኮተ የተቃራኒውን የሚያደርግ ነው፡፡ ከበጎ ነገር ይልቅ ክፉ ነገርን የሚሻ መንፈሱ ለተንኮል ብቻ የተፈጠረ ይመስል ተንኮልን የሚያውጠነጥን፣ ከፍቅር ይልቅ ጦርነትን የሚናፍቅ፣ የሌላውን ሰው ደስታ የማይሻ፣ በሰው ስቃይ የሚደሰት፣ ስለሆነም ሰውን በመጉዳት ወይም ተንኮል በመሥራት የተሻለ ነገር የሚያገኝ የሚመስለው፣ በአጠቃላይ ሲታይ የአንድ አካባቢ ሕዝብ በሰላምና በደስታ ቢኖር ደስ የማይለው ነው፡፡ ከመሰሉ ጋርም በማበር ዘለዓለማዊ ጦርነት እንዲሰፍን የሚያደርግና የአንድ አገር ሀብትና የታሪክ ቅርስ እንዲወድም የሚያደርግ ነው። በመሆኑም በራሱ ስግብግብ ፍላጎት በመመራትና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር አንድ ሕዝብ ታሪክ እንዳይሠራ እንቅፋት የሚሆን ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ሰው የማሰብ ኃይሉን በሚገባ የማይጠቀም ሰው መሆኑን የዘነጋና ታሪካዊ ኃላፊነትም እንዳለበት የሚገነዘብ አይደለም፡፡ አንድ ቦታ ላይ ቆሞ ድርጊቱን የሚያወጣና የሚያወርድ፣ እንዲሁም የሚያመዛዝን አይደለም። በአጭሩ መንፈሱ የተሰለበና የሚሠራውን የማያውቅ፣ እንዲሁም ለመኖር ብቻ የሚኖር የሚመስለው ነው።
ጭንቅላታችን አርቆ የማሰብ ኃይል ያለውን ያህል ሌሎች የሰው ልጅ ባህርያት ሊገለጹና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉት በማሰብ ኃይላችንና በቀሰምነው ዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው፡፡ የመንፈስ ጥንካሬና በመርህ (ፕሪንሲፕል) መመራት፣ በቀላሉ ያለመታለልና ያለመደለል፣ ለምናምነው ዓላማ መቆምና እሱን በጥሞናና በውይይት ለማሳመን መሞክር፣ ለነፃነት መቆምና ለሌላው ላልተማረው ጠበቃ መሆንና እውነተኛውን የነፃነት ፈለግ እንዲከተል መንገዱን ማሳየት፣ የአንድን ኅብረተሰብ ሁኔታና ችግር ከብዙ አኳያ ማየትና መገምገም፣ ከዚህም በመነሳት ለሥልጣኔ መቆምና እስከ መጨረሻው መታገል፣ እነዚህና ሌሎች ነገሮች ሁሉ በጭንቅላታችን ውስጥ የሚውጠነጠኑና የሚገነቡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ለምን በተለያዩ ሰዎች ዘንድ የተለያየ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ከላይ የዘረዝርኳቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ ብለን? ጥያቄ በምናስቀምጥበት ጊዜ የምናገኘው መልስ በአጭሩ አስተዳደጋችንና የገበየነው ዕውቀት ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወቱ እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን። በተለይም የአንድ ኅብረተሰብ አወቃቀርና የታሪክ ሒደት እንዲሁም የባህል ሁኔታ ባህሪያችንን ይወስኑታል፡፡ ስለዚህም ነው ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት ከሞላ ጎደል የኅብረተሰቡ ግልባጭ ወይም ኮፒ ነው የሚባለው፡፡ ከዚህ ስንነሳ አንደኛው ቀጣፊና ውሸታም፣ አድሀሪና ወላዋይ፣ አጎብዳጅና ነገር አቀባይ፣ ራሱን ለሌላው ለመሸጥ የሚዘጋጅ፣ ሰላይና በራሱ ላይ እምነት የሌለው፣ እንደየሁኔታው ሐሳቡን የሚቀያየር፣ አለሁ አለሁ ባይነት የሚያጠቃው፣ ስግብግብነትና አገር ለመሸጥ መዘጋጀት፣ ለአገር ነፃነት ጥብቅና ከመቆም ይልቅ የሌላውን አገር ጥቅም በማስቀደም አገር ማፈራረስ፣ ታሪክን በተጣመመ ሁኔታ ማቅረብና ሌላውን አሳስቶ አንድ ሕዝብ ተስማምቶ እንዳይኖር ማድረግ፣ ጠባብ አስተሳሰብ እንዲስፋፋ በማድረግ ግለሰቦችም ሆነ የተለያዩ እምነት ተከታዮችም ሆነ ከዚህም ሆነ ከዚያ ብሔረሰብ የተወለዱ በጥላቻ መንፈስ በመጠመድ በመፈራራትና የጎሪጥ እየተያዩ እንዲኖሩ ማድረግ፣ ቀጥሎም ወደ ጦርነት እንዲያመሩ ማድረግ፣ ለውንብድና በመዘጋጀት አንድን አገር የጦር አውድማ በማድረግ ታሪክ እንዳይሠራ ማድረግ፣ እነዚህ ሁሉ በማሰብ ኃይል ድክመትና በተሳሳተ ዕውቀት ምክንያት የሚፈጠሩ ድርጊቶች ናቸው፡፡ በተጨማሪም በተንኮል ተጠምዶ ሌላውን ከሱ የላቀን ሰው ለማጥፋት የሆነ ያልሆነ ምክንያት መፈለግና ስም ማጥፋት፣ የጭንቅላት አርቆ ያለማሰብ ችግር ነው፡፡ በተሳሳተ ዕውቀት በመመራትና በዚህም ምክንያት ጭንቅላት በትክክል ለመገራት ያለመቻሉ የሚገለጽ ችግር ነው፡፡ በተጨማሪም ሌላው ደግሞ የአንድን ተንኮለኛ አነጋገር ሰምቶና አምኖ የሚያስተጋባና ለትግል እንቅፋት የሚሆን እንደዚሁ ጭንቅላቱ በደንብ ያልተገራ ወይም ደግሞ የቀጨጨ አስተሳሰብ ስላለው ነው።
ይህም ማለት ምን ማለት ነው? ለአንድ ሕዝብ በሰላም መኖር፣ ራሱን መለወጥና ማደግ እንዲሁም ታሪክ መሥራት መንፈስ፣ ጭንቅላትና አዕምሮ ከፍተኛ ሚናን የሚጫወቱ ብቻ ሳይሆኑ ወሳኞችም ናቸው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ አንድ ሰው የፈለገውን ያህል የተማርኩ ነኝ ቢልም እና አሥር ጊዜ ካለ እኔ በስተቀር ታጋይ የለም እያለ ቢምልና ቢገዘትም ጭንቅላቱ ውስጥ የተቀበረውን ወደ መጥፎ ነገርና ተንኮል እንዲያመራ የሚያደርገውን የተወላገደ ባህሪ ማስወገድ እስካልቻለ ድረስ በምንም ዓይነት ለኅብረተሰብ ዕድገትና ለነፃነት አስተዋጽኦ ሊያበረክት አይችልም፡፡ በአገራችንም ሆነ በልዩ ልዩ አገሮች የደረሱትን ዕልቂቶች፣ የታሪክና የሀብት ውድመቶች፣ የሕዝብ መበታተንና በሌላ አገር ባክኖ እንዲኖር ማድረግ፣ በአጠቃላይ ሲታይ ለዕድገት እንቅፋት መሆን ዋናው ምክንያት በትንሽ ዕውቀት እየታገዘ ሥልጣን ለመውጣት እታገላለሁ በሚል አጉል ግብዘኛ ምክንያት የተነሳ ነው፡፡ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ባልተማሩ ስዎች ወይም በደሃ ገበሬና ወዝ አደር ጦርነት የተቀሰቀሰበትና አገር የወደመበት ሁኔታ በፍፁም አልታየም አልተመዘገበምም። እስከ ዛሬ ድረስ ብዙ አገሮች የወደሙትና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ እንዲያልቅ የተገደደው ተማርኩ ባሉ ጥቂት ኤሊቶች አማካይነት ነው፡፡ የሰውን ልጅ ለመግደልና ለማሰቃየት ተብለው የሚሠሩት የተወሳሰቡ መሣሪያዎች በተማሩ ሰዎች አማካይነት ነው፡፡ ትዕዛዝ የሚሰጡትም እንዲሁ በሕዝብ ተመርጠናልና ውክልናን አግኝተናል ብለው በሚዘባነኑ ፖለቲከኞች አማካይነት ነው፡፡ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ውዝግብ፣ በሃይማኖት አሳቦ ዕልቂት ማስከተል፣ የብዙ ሺሕ ዓመታትን ታሪክና ባህል ማውደምና የብዙ ሺሕ ሰዎችን ሕይወት መቅሰፍ ስንመለከት የምንደርስበት መደምደሚያ ይህ ሁሉ አሰቃቂ ግፍ የሚፈጸመው በሀብት በናጠጡና በሥልጣን ጥም በሰከሩ ኤሊት ነን በሚሉት አማካይነት ነው፡፡ ወይም ደግሞ አንድን መመርያና ዕውቀት የሚሉትን ራሳቸው በፈለጉት መልክ ስለሚተረጉሙት ብቻ ነው፡፡ የዩሁዲው ማርክሲስትና ምሁር አዶርኖ እንደሚለው ለዚህ ዋናው ምክንያት ገለብ ገለብ ያለ ዕውቀት ነው፡፡ በእሱ እምነት የታሪክን ሒደትና አመጣጥ የአንድን ኅብረተሰብ አወቃቀር ውጣ ውረድነት ያለው መሆኑን ያልተገነዘበ ኤሊት በስሜት ብቻ እየተነዳ የሚያካሂደው ፖለቲካ የሚሉት ፈሊጥ የግዴታ ለታሪክ መበላሸት፣ ለሕዝቦች ዕልቂትና ለአገር መፈራረስ ዋናው ምክንያት ይሆናል፡፡ ሒትለር በስድስት ሚሊዮን ሕዝቦች ላይ ያደረገው ዕልቂትና የሌሎችንም አገሮች በመውረር ወደ ሃምሳ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ እንዲሞትና አገሮችም እንዲፈራርሱ የተደረገው ይሁዲዎች ለጀርመን ሥልጣኔ ያደረጉትን አስተዋጽኦ ለመገንዘብ ባለመቻሉና ወደ ኋላ መለስ ብሎ የታሪክን ሒደት ለማጥናት ባለመቻሉ ብቻ ነው፡፡ በዘረኝነት ቲዎሪ በመመራቱና የጀርመንም ሕዝብ ከሁሉም ዘር በላይ ይበልጣል ብሎ በማመኑ ነው፡፡ ይህም የሚያረጋግጠው የተቆራረሰ ዕውቀት ጭንቅላትን እንደሚጋርድና ሌላውን በመናቅና በማንቋሸሽ ለብዙ ሚሊዮን ሕዝቦች መሞትና ለባህልና ለታሪክ መፈራረስ ምክንያት እንደሚሆን ነው፡፡ የአገራችንንም የአብዮት ታሪክና የደረሰውን ዕልቂት ስንመረምር ለችግሩ መንስዔ የሆኑ ሰዎች ተማርን የሚሉ ሲሆኑ የታሪክን ውጣ ውረድነት ያልተገነዘቡ፣ በየታሪክ ደረጃዎች ላይ የነበረውን ንቃተ ህሊና ያላገናዘቡ፣ አንድ ኅብረተሰብም ሆነ አገር ለመረጋጋትና ታሪክን ለመሥራትና እንዲሠራበትም ለማድረግ አንድ ሕዝብና አገዛዝ ኅብረተሰብዓዊ መመሰቃቀሎችንና ውህደቶችን ማለፍና ራሳቸውን ለመገንዘብ በብዙ መቶ ዓመታት የሚቆጠር ዕድሜ እንደሚያስፈልግ ባለመረዳታቸው ነው፡፡ ፍሪድሪሽ ሽለር የተባለው ታላቅ የድራማ፣ የፍልስፍናና የሳይንስ ምሁር እንደሚያስተምረን የሰው ልጅ ራሱን በራሱ እስኪያገኝ ድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፍ እንዳለበት ነው፡፡ በእሱ እምነት የሰው ልጅ አርቆ የማሰብ ኃይሉን ማዳበር ከፈለገ የግዴታ መንፈሱ ከልጅነቱ ጀምሮ በጥሩ ዕውቀትና ጥበብ መኮትኮት አለበት፡፡ ጥበባዊ ጭንቅላትን የመኮትኮቻ ትምህርት (The Aesthetic Education of the Human Mind) በሚለው መጽሐፉ ውስጥ የሚያመለክተውና የሚያረጋግጠው ይህንን ነው፡፡ የሰው ልጅ ጭንቅላት ከልጅነቱ ጀምሮ በጥሩ ዕውቀት እስካልተኮተኮተ ድረስ ሰብዓዊ ባህሪ ሊኖረው አይችልም፡፡ ቆንጆና የተረጋጋ ማኅበረሰብም ሊገነባ አይችልም፡፡ ሜንደልሰን የሚባለውና የጀርመኑ ሶክራተስ እየተባለ የሚጠራው ይሁዳዊው ምሁርም የሚያረጋግጠውም ይህንን ነው፡፡ ጭንቅላቱ በሚገባ ያልተኮተኮተና ያልዳበረ እንደ አውሬ እንደሚሆንና ለሌላው እሱን ለሚመስለው ሰው ምንም ዓይነት ርህራሔ እንደማይኖረው ነው፡፡ ኢማኑኤል ካንትም በተለይም በሰው አዕምሮ ላይ ከፍተኛ አትኩሮ በመስጠት የሰው ልጅ በአጠቃላይ ሲታይ ወደ ውስጥ ራሱን መመልከት እንዳለበትና ድርጊቱን ሁሉ መቆጣጠር እንዳለበት ያስተምራል። አዌርነስ (Awarness) በሚለው ሀተታው የሰው ልጅ የግዴታ ለድርጊቱ ሁሉ ተገቢውን ግንዛቤ ማድረግ እንዳለበት ያስተምራል፡፡ በመሆኑም የሰውን ልጅ የጭካኔ ባህሪ የተረዱት የ18ኛው እና የ19ኛው ክፍለ ዘመን የጀርመን ምሁራን ምርምር ያደርጉ የነበረውና አጥብቀውም ያነሱ የነበረው የሰውን ባህሪ በመኮትኮት ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖረው ማድረግ ነበር፡፡ ጠቅላላው የጀርመን ፈላስፋዎች ምርምርም በዚህ ዙሪያ ያተኮረ ሲሆን፣ አንድ ሕዝብ ታሪክን ሊሠራ የሚችለው በየጊዜው ራሱን መጠየቅና ጭንቅላቱን መኮትኮት የቻለ እንደሆን ብቻ ነው፡፡ የሚያስገርመውና የሚያሳዝነውም በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ፈላሳፋዎችና ምሁራን ብቅ ባሉበትና ሳይታክቱ ባስተማሩበት፣ እንዲሁም ትምህርታቸውን ተግባራዊ ባደረጉበት አገር ሒትለርና ፋሺዝም መነሳታቸውና ለብዙ ሚሊዮን ሕዝብ መሞት ምክንያት መሆናቸው ነው፡፡
ወደ አገራችን ስንመጣም ያለው ችግር ለመንፈስና ለአዕምሮ መዳበር አትኩሮ ያለመስጠትና የመንፈስ መበላሸትም ሆነ በጥሩ ዕውቀት መኮትኮት ያለውን አሉታዊና አዎንታዊ ሚና ያለመገንዘቡ ነው፡፡ ለአንድ አገር ዕድገት፣ አንድ ሕዝብ ኋላ ቀር ከሆኑ አመለካከቶች ተላቆ በመተባበር አገር እንዲገነባ ከተፈለገ ትክክለኛ ዕውቀት አስፈላጊና በዚህ ላይ መረባረቡ የሁሉም ነገር ቁልፍ መሆኑን ግንዛቤ ያለመደረጉ ነው፡፡ በመሆኑም በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የገባው ይህንንም ያህል ለጭንቅላት መዳበር፣ ለአርቆ አሳቢነትና ለፈጠራ ሥራ የማያመቸው ትምህርት ኅብረተሰብዓዊ መዘበራረቅን እንዳስከተለና አቅጣጫ እንዳሳጣን ምርምር ያለመደረጉ በጣም የሚያሳዝንም የሚያስገርምም ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ቸልተኝነትና ንቀት ደግሞ የግዴታ በየኤፖኩ (በየዐረፍተ ዘመኑ) የተነሱትን ሁኔታዎች እንደፈለግን ልንተረጉማቸው ተገደናል፡፡ ለምሳሌ አብዛኛው ተንታኝ በአብዮቱ ወቅት የተፈጠረውን ትርምስና እጅግ ለጭንቅላት የሚዘገንን ድርጊት ለማያያዝ የሞከረው ዝም ብሎ በደፈናው ከማርክሲዝም ጋር ነው፡፡ ፊውዳሊዝምና እጅግ ተበጣጥሶ የገባው የካፒታሊዝም የፍጆታ አጠቃቀምና አመራረት በህሊና አወቃቀራችንና በመንፈሳችን መበላሸት ላይ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ የተገነዘበ ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህም አብዛኛው ሰው ወይም ምሁር ነኝ ባይ በአብዮቱ ጊዜ የደረሰውን ዕልቂትና መተራረድ የተገነዘበው ከውጭ ከመጣው የማርክሲስት ሌኒንስት ርዕዮተ ዓለም ጋር በማያያዝ ነው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ የጦር ኃይል እንዳለ የሠለጠነው በአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም የጦር ሳይንስ በሚሉት ነው፡፡ መሣሪያዎቹም የመጡት ከዚያ ነው፡፡ ፖሊሱ ደግሞ በጀርመን ፖሊሶች የሠለጠነ ሲሆን፣ የማሰቃያ መሣሪያዎችም በሙሉ ከዚያ የመጡ ነበሩ፡፡ በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ የጦር ኃይልና ፖሊስ በኢምፔሪያሊዝም የጭቆናና የማሰቃያ እንዲሁም ሰውን የመግደያ ሥልት ነው የሠለጠነው፡፡ ስለሆነም በአብዮት ጊዜ የተካሄደው መተላለቅ ከማርክሲዝምና ከሶሻሊዝም ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ማርክሲዝምና ሶሻሊዝም የብዙ መቶ ዓመታትን የደነደነ አስተሳሰብና መንፈስ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የመቀየር ኃይል የላቸውም፡፡ የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል በክንውንና በሒደት ውስጥ የሚቀረፅ ነው፡፡ በተለይም ፍሪድሪሽ ሄግል ይህንን ነው የሚያስተምረን፡፡
ከዚህ ስንነሳ በአጠቃላይ ሲታይ የብዙ የሦስተኛውን ዓለም አገሮች የተዘበራረቀ ሁኔታና የየመንግሥታቱን የመጨቆኛ መሣሪያና አለመደላደልን ስንመለክት ከአገራችን ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ የሚለዩት ግን አብዛኛዎቹ አገሮች እንደኛው በፊውዳል ሥርዓት ውስጥ አለማለፋቸው ብቻ ነው። ያም ሆነ ይህ የአንድን ኅብረተሰብ ዕድገት ሁለንተናዊ ከሆነ ሁኔታ ያላጤኑ መንግሥታትና ሁለገብ ዕርምጃ ለመውሰድ ያልሞከሩ አገሮች አንዳች ነገር በሚፈጠርበት ጊዜ ወደ መረጋጋት ከመምጣት ይልቅ ወደ ውዝግብና መተረማመስ ያመራሉ፡፡ በአገራችን በአብዮቱ ዘመን የታየው የመንፈስ መረበሽና ለጭንቅላት የዘገነነ ድርጊት ዋናው መነሾው ጭንቅላትን ለማደስና መንፈስን ለማረጋጋት የሚያስችል ዕውቀት ባለመስፋፋቱ ብቻ ነው፡፡ ዛሬም ያለው ችግርና የሕዝብ መፈናቀልና የመንግሥትም ቸልተኝነት ዋናው ምክንያት ሰው መሆናችንን የሚያረጋግጥልንና ታሪክ ሠሪ መሆናችንን የሚያስጨብጠን ዕውቀት ከጭንቅላታችን ጋር እንዲዋሃድ ባለመደረጉ ነው፡፡ ስለሆነም አብዮቱ ከመተባበር ይልቅ ቡድናዊ ስሜትን አጠናከረ፡፡ ወደ ጤናማ ፉክክር ሳይሆን ወደ ጦርነት የሚያመራና ደም መፋሰስን ወደ ሚያስከትል አጉል እልከኝነት ውስጥ ከተተን፡፡ ሁሉም በየፊናው በመራወጥ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ዝግጅት ማድረግ ጀመረ፡፡ ሁሉም በየፊናው በቀላሉ ድልን የሚቀዳጅና ሥልጣን የሚጨብጥ መስሎ ታየው፡፡ ብሔረሰቤን ነፃ አውጣለሁ ብሎ የሚታገለው ደግሞ አገሪቱን ወደ ጦር አውድማነት ለወጣት፡፡ አብዛኛው ታጋይ ነኝ ባይና ቢሮክራሲው ሁሉ ሳይቀሩ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሆኑ፡፡ የሥልጣኔና የዕድገት ጠንቅ በመሆን ውስብስብ ሁኔታዎችን ፈጠሩ፡፡ በመሠረቱ እነዚህ ሁሉ ኃይሎች ትንሽም ቢሆን ፊደል የቆጠሩና የተማሩም ነበሩ፡፡ የተማሩት ትምህርት ግን የማሰብ ኃይላቸውን እንዲጠቀሙ አላገዛቸውም፡፡ የመንፈስን የበላይነት በማስቀደም የወንድማማች ደም እንዳይፈስ ጥረት እንዲያደርጉ አላስቻላቸውም፡፡ በተንኮልና አገርን በማፈራረስ፣ እንዲሁም ሳይቀድመኝ ልቅደመው በሚል ፈሊጥ በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ለጋ ወጣቶች ሕይወታቸውን እንዲያጡ ሁኔታውን አመቻቹ፡፡
ያም ሆነ ይህ በአጠቃላይ ሲታይ የሰው ልጅ ጭንቅላትም ሆነ መንፈስ አንድ ዓይነት ቅርፅ ነው ያላቸው፡፡ ይህም ማለት በየትኛውም አገር የተወለደና ያደገ ሰው ሁሉ የሁሉም የሰው ልጅ ባህሪዎች ይኖሩታል፡፡ ከላይ እንዳልኩት የየግለሰቡ ባህሪና ድርጊት ሊቀረፅና ሊወሰን የሚችለው በአስተዳደጉ፣ በአካባቢው ሁኔታና በአጠቃላይ ሲታይ ደግሞ በጠቅላላው የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህል ዕድገት ሁኔታ ነው፡፡ ይሁንና ግን አንዳንድ ሰው ሲወለድ ከመጀመርያውኑ ተቀድሶ የሚወለድና ጭንቅላቱ ወደ ተንኮልና ወደ መጥፎ ነገር የማያመራ አለ፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ እንደ ሶክራተስና ፕላቶንን፣ እንዲሁም ታላላቅ የሳይንስና የፍልስፍና ሰዎች የመሳሰሉት ብቅ ባላሉ ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ደግሞ ወደ እግዚአብሔርም የሚጠጉ ናቸው፡፡ ለጥሩ ነገር እንጂ ለመጥፎ ነገር ያልተፈጠሩ ጠቅላላው አስተሳሰባቸው የሰውን ልጅ ታሪክ ሠሪነት ማስታወስና ማስተማር ተልዕኳቸው የሆነ ልዩ ዓይነት ፍጡሮች ናቸው። በመሆኑም እንደነዚህ ዓይነት ስዎች ባይፈጠሩ ኖር የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን ባልቻልን ነበር፡፡ ኑሮአችን ሁሉ የጨለመና እየተንከራተትን እንደ እንስሳ የምንኖር ነበርን፡፡ ተግባራችን ሁሉ ጦርነትና መተላለቅ ብቻ በሆነ ነበር፡፡ የዓለምና የሰው ልጅ አስደናቂውና በቅራኔዎች መወጠር የሚያስገርመው ነገር እዚህ ላይ ነው፡፡ በአንድ በኩል ለቅዱስ ሥራ የተፈጠሩና የተካኑ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ለተንኮልና ለጥፋት እዚያው በዚያው መኖራቸው የሰው ልጅና የተፈጥሮ ግዴታ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ጨለማና ብርሃን፣ የሚያቃጥልና ቀዝቃዛ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ የሰው ልጅ ባህሪም በአጥፊዎችና በተንኮለኞች በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በፈጣሪዎችና ለተቀደሰ ዓላማ በቆሙ ሰዎች የሚገለጽ ነው፡፡
ከዚህ ስንነሳ የጭንቅላትን ሚና ታሪክ ሠሪነትና አጥፊነትን መረዳቱ የሚታለፍ ነገር አይደለም፡፡ እንደገና የፕላቶንን ቁም አባባል ለማስታወስ፣ የሰው ልጅ ችግር አርቆ አለማሰብና በትክክለኛ ዕውቀት አለመኮትኮት ነው፡፡ ለመጥፎ ድርጊትና ለችግር መፈጠር እንዲሁም ለጥሩ ሥራ ዋናው ተጠያቂው የሰው ልጅ ራሱ እንጂ ከላይ ሆኖ የሚቆጣጠር ኃይል ወይም ደግሞ አንዳች ዓይነት ርዕዮተ ዓለም በመከተሉ አይደለም፡፡ እንደየአስተዳደጋችን እኛው ራሳችን የአስተሳሰባችንና የድርጊታችን ተጠያቂዎች ነን፡፡ ሌላ ሰው የሚያሳስተን ከሆንና የእሱን አስተሳሰብ ተከትለን ወደ መጥፎ ነገር የምናመራ ከሆነ ጭንቅላታችን በጥሩ ዕውቀት አልተኮተኮተም ማለት ነው፡፡ የማመዛዘንና ጥያቄን የመጠየቅ ልምድ አላካበትንም፣ ከጭንቅላታችንም ጋር አልተዋሃደም ማለት ነው፡፡ ዝም ብለን የምንመራ፣ ሌላው ሲጮህ የእሱን የምናስተጋባ ከሆነ ጭንቅላታችን እውነተኛ ነፃነትን አልትጎናፀፈም ማለት ነው፡፡ እውነተኛ ግለሰባዊነትና በራስ ላይ መተማመንን አላዳበርንም ማለት ነው፡፡ በጭፍን የምንመራ እንጂ በራሳቸን የማሰብ ኃይል የምንመራ አይደለንም ማለት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ደግሞ ማንኛውንም መጥፎ ነገር ከመሥራት አይቆጠቡም፡፡
ሁለገብ የመንፈስ ተሃድሶ ዘዴ የሰላምና የዕድገት ዋናው ቁልፍ ነው!
በታሪክ ውስጥ ሥልጣኔና ዕድገት የተካሄደባቸውንና የሰውም ልጅም እውነተኛ ግለሰባዊ ነፃነትን የተቀዳጀበትን ሁኔታና ታሪክን ስንመለከት የመንፈስ ተሃድሶ መሠረታዊ የሆነና ከፍተኛውን ሚናም እንደሚጫወት እንገነዘባለን፡፡ በታሪክ ውስጥ የመጀመርያው ሁለገብ የመንፈስ ተሃድሶ ተግባራዊ የሆነው ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን፣ ይህንንም ተግባራዊ ያደረገው ሶሎን የሚባለው ታላቅ ፈላስፋና የአገር መሪ ነበር፡፡ ለሶሎን መነሳትና የተቀደሰ ድርጊት ደግሞ ቀደም ብለው የተካሄዱት በተፈጥሮ ፈላስፋዎች የተደረጉት ምርምሮችና የሆሜር ድርሰት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ማለት ይቻላል፡፡ በጊዜው የነበረውን የእርስ በርስ ጦርነትና የገዥ መደቦችን ቅጥ ያጣ ብዝበዛና ግፍ የተመለከተው ከመሳፍንት ዘር የተወለደው ሶሎን በጊዜው የነበረውን አስቀያሚ ሁኔታ ያያዘው ከመንፈስ ወይም ከአዕምሮ መበላሸት ወይም በጥሩ ዕውቀት ካለመታነጽ ጋር ነው፡፡ ስለሆነም ሥልጣን ሲጨብጥ በአካባቢው ያሉትን በማሳመን ሁለገብ ጥገናዊ ለውጥ በማካሄድ በታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ልዩ ዓይነት በሳይንስ፣ በሒሳብ፣ በፍልስፍና፣ በድራማና በአርክቴክቸር የሚገለጽ የዕውቀት መሠረት ይጥላል፡፡ ለሶክራተስ፣ ለፕላቶን፣ ለአርቺሜዲስና ለአርስቲቶለስና እንዲሁም መጠናቸው ለማይታውቅ ፈላስፋዎችና የሳይንስ ሰዎች መነሳት ዋናው ምክንያት ይሆናል፡፡ ታላቁ አሌክሳንደር ሲነሳ ይህንን መሠረት በማድረግ ሥልጣኔውን ማስፋፋት ይጀምራል፡፡ በእሱ ስም በሚጠራውም የግብፅ ከተማ የመጀመርያውን መጽሐፍ ቤት ይከፍታል፡፡ አስተሳሰቡ ከዚያ በመነሳት በአካባቢውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይንስና ጥበብን ማስፋፋት ነበር፡፡ ይህ ህልሙ ግን በሮማውያን ወራሪዎች ድምጥማጡ ይጠፋል፡፡ ከሰባት መቶ ሺሕ በላይ የሚጠጉ መጻሕፍትም ይቃጠላሉ፡፡ የግሪክና የግብፅ ሥልጣኔ መውደም፣ በአውሮፓ ውስጥ የጨለማው ዘመን እየተባለ ለሚጠራው መነሻ ሲሆን፣ ይህ በራሱ በምዕራብ አውሮፓ ምድር ከሃይማኖት ጋር የተጣመረ ፊውዳላዊ የጨለማ አገዛዝ እንዲስፋፋ ያደርጋል፡፡ የአውሮፓ ሕዝብ ዕጣ በሽታ፣ ረሃብና ጦርነት ይሆናል፡፡ የሰፊውን ሕዝብ አስተሳሰብ በጭፍን እምነት እንዲጋረድ ያደረጉት የካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎች የአውሮፓ ሕዝብ ታሪክ እንዳይሠራና እውነተኛ ነፃነቱን እንዳይቀዳጅ ያደርጉታል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ቀስ በቀስ የሚለወጥበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ዳንቴ የደረሰው የአምላኮች ኮሜዲ ለጭንቅላት ተሃድሶ በሩን ይከፍታል፡፡ የሰው ልጅ ከጨለማው ዓለም በመላቀቅ እንዴት አድርጎ ብርሃንን እንደሚጎናፀፍ ዳንቴ በግሩም ድርስቱ ውስጥ ያመለክታል፡፡ የዳንቴ ድርሰት ለሬናሳንስ መነሳት መሠረቱን ይጥላል፡፡ የእሱን ድርሰት ያነበቡት መልዕክቱን በመረዳት ለአዲስና ለታሪካዊ ሥራ ይነሳሳሉ።
በዓረቦችና በይሁዲዎች አማካይነት ወደ ምዕራብ አውሮፓ የገባው የግሪኩ ዕውቀት ወደ ላቲን በመተርጎምና የነበረውን ጨለማዊ አገዛዝ በመጋፈጥ በአውሮፓ ምድር ውስጥ በተለይም በጣሊያን ሬናሳንስ የሚባለው ዕውቀትን መልሶ የማግኘት ዘዴ ይስፋፋል፡፡ ዛሬ ኢስታንቡል ተብላ ከምትታወቀው በድሮ ስሟ ኮኒስታንቲኖፕል ተብላ ከምትጠራው ከተማ ፈልሰው የመጡ ቀሳውስት የፕላቶንን ሐሳብ በማስፋፋት አዲስ የሥልጣኔ ፈለግ ይቀዳሉ፡፡ የንግድና የዕደ ጥበብ መስፋፋት አዳዲስ ኃይሎችን ሲያፈልቅ፣ የድሮው ጨለማዊ አገዛዝ በድሮ መልኩ የማይቀጥልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ እነ ኬፕለርና ጋሊሊዮ እንዲሁም ብሩኖ ጋርዲያኖ የመሳሰሉት ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያላቸው ምሁራን ያፈለቁትና ያዳበሩት አዲስ ዕውቀት የካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎችን ጭፍን ትምህርት በመቀናቀን መፈናፈኛ ያሳጣዋል፡፡ የእነ ዳቪንቺና ሚካኤል አንጀሎ ልዩ ሥዕላዊና የአርክቴክቸር ሥራዎች ለአውሮፓው ሥልጣኔ መነሻ ይሆናሉ፡፡ ይሁንና ግን ፊውዳላዊው ሥርዓትና የሃይማኖት እምነት ሙሉ በሙሉ ተዳክሞ ሕዝቡ ግለሰባዊ ነፃነት እስኪቀዳጅ ድረስ ረዥም መንገድ መጓዝ ነበረበት፡፡ ለብዙ መቶ ዓመታት የተንሰራፋውን አስተሳሰብና የኃይል አሠላለፍ ለማሸነፍ ቀላል አልነበረም፡፡ ስለሆነም ሪፎርሜሽን ተብሎ የሚጠራው የካቶሊክን ሃይማኖት የሚቀናቀን ሃይማኖት በማርቲን ሉተርና በተከታዮቹ አማካይነት በመዳበርና በመስፋፋት የካቶሊክን ጭፍን አመለካከት ይጋፈጣል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ግለሰብዓዊ ሥነ ምግባርን በማዳበር ለካፒታሊዝም ዕድገት ልዩ እምርታን ይሰጣል፡፡ ይህ አዲሱ ሃይማኖት በተስፋፋባቸው ቦታዎች ሳይንስ፣ ጥበብና ንግድ በመዳበር ለከበርቴው መደብ መነሳት ምክንያት ይሆናል።
ይቀጥላል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡