የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በዚህ ክረምት ከ600 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች 7.2 ሚሊዮን ደብተር ለመሰብሰብ ባቀረቡት ጥሪ መሠረት የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች የደብተር ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የደብተር ድጋፉ ካደረጉ ድርጅቶች መካከል የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሁለት ሚሊዮን ደብተር፣ የጤና ሚኒስቴር አንድ ሚሊዮን ደብተር፣ የዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትሱ ‹‹ኤግል ሂልስ›› በለገሃር ፕሮጀክት ስም 1.5 ሚሊዮን ደብተር፣ የሥልጤ ልማት ማኅበር 500 ሺሕ ደብተር፣ አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖሩ የሐረሪ ማኅበር አባላት 200 ሺሕ ደብተር፣ የኢቢኤስ ቴሌቪዥን 50 ሺሕ ደብተር፣ በላይ አብ ሞተርስ 100 ሺሕ ደብተር፣ እንዲሁም ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማኅበር 350 ሺሕ ደብተርና 150 ሺ እስክሪፕቶ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሐሙስ ሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ከንቲባው ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የ2011 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ላይም ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን 7.2 ሚሊዮን ደብተር በነፃ የማቅረብ ዕቅድ በተሳካ ሁኔታ እንደተከናወነ ገልጸዋል፡፡ ፎቶዎቹ የልግስናውን ከፊል ገጽታ ያሳያሉ፡፡