Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጡት ማጥባት ለምን?

ጡት ማጥባት ለምን?

ቀን:

በየአብያተ እምነቱ በገበያ ቦታ፣ በዘመድ አዝማድ ቤትም ሆነ በትራንስፖርት ውስጥ ኢትዮጵያውያን እናቶች ልጆቻቸውን ለማጥባት ሲያንገራግሩም ሆነ ሲሰስቱ ማየቱ አልተለመደም፡፡ በርካታ በጉሊት ንግድ ሥራ አሊያም በሌሎች ሥራዎች የተሰማሩ እናቶችም ቢሆኑ ሲያሻቸው ነጠላ ወይ ሻሽ ቢጤ ጣል አድርገው አሊያም እንደተገላለጡ ልጆቻቸውን ሲያጠቡም ይስተዋላሉ፡፡

ይህ በገጠርም ሆነ በከተማ የተለመደው እናትን ከልጇ በእጅጉ የሚያስተሳስራት ጡት ማጥባት፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ደግሞ ሲተጓጎል ይታያል፡፡ ይህ እንዳይሆን ጤና ሚኒስቴርም ሆነ የተለያዩ አካላት እናቶች ጡት እንዲያጠቡ፣ የሥራው ፀባይ ልጆቻቸውን ለማጥባት ለማይፈቅድላቸው እናቶች የፖሊሲ ማሻሻያ እየተደረገ ችግሮች እንዲቀረፉ መሥራት ከተጀመረም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሆኖም የሚያጠቡ እናቶች ቁጥር በመቶኛ ሲሰላ ከ60 እንኳን የሚዘል አይደለም፡፡

የእናት ጡት ከዱቄት (ፎርሙላም) ሆነ ከከብት ሲነፃፀር፣ በሌሎቹ የማይገኝ ጠቃሚ ንጥረ ነገር የያዘ መሆኑ፣ ይህም ለሕፃናት አዕምሮአዊ፣ አካላዊና ማኅበራዊ ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ በተለያዩ ጥናቶች ቢረጋገጥም፣ ጡት ለማጥባት እንቅፋት የሆኑ ምክንያቶች አሉ፡፡

በኢትዮጵያ እናቶች ጡት የማጠባት ባህላቸው የዳበረ ቢሆንም፣ መንግሥት ከሦስት እስከ ስድስት ወራት የወሊድ ፈቃድ እንዲሰጥ መወሰኑ፣ በሁሉም ባይባልም በየመሥሪያ ቤቱ የሕፃናት ማቆያ መኖሩ ትልቅ አስተዋጽኦ ቢያበረክትም በርካቶች ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ጡት አያጠቡም፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የሕፃናትና የጨቅላ ሕፃን ስፔሻሊስት  ገስጥ መታፈሪያ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ 59 በመቶ የሚሆኑት እናቶች ብቻ ጡት ያጠባሉ፣ በመሆኑም ይህን ቁጥር ለማሳደግ ከእርግዝናቸው ጀምሮ የጡት ማጥባት ጠቀሜታን ለእናቶች ማስገንዘብ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

እናት በበቂ ሁኔታ ጡት ማጥባት እንድትችል የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ በቀን ሦስት ጊዜ ከምትመገበው በተጨማሪ ሁለት ጊዜ ተጨማሪ ምግብ ማግኘት  አለባት የሚሉት ዶ/ር ገስጥ፣ ይህም ለልጁ ማግኝት ያለበትን ያህል የእናት ጡት ወተት በበቂ ሁኔታ ለማግኘት ያስችለዋል፣ ከተለያዩ በሽታዎችም ይከላከላታል ብለዋል፡፡

የመጀመርያ የእናት ጡት (እንገር) በተለይ ከተወለደ በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠብቶ ያላደገ ሕፃን ከመጠን በላይ የሰውነት ውፍረት፣ እያደገ ሲመጣ የልብና የስኳር ሕመም ሊያጋጥመው እንደሚል ዶ/ር ገስጥ አክለዋል፡፡

ለእናትየውም ከወሊድ በኋላ የሚያጋጥምን ደም መፍሰስ  በከፍተኛ መጠን ሊቀንስ፣ የእናት ማህፀን ቶሎ ወደ ቦታው እንዲመለስም ያደርጋል፡፡  ከልብና ከደም ግፊት ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎችንና የጡት ካንሰርን የመከላከል ዕድልንም ይጨምራል፡፡

በጣም የተሳካ የጡት ማጥባት ሒደት ለማድረግ እንደ አገር ፖሊሲ ያስፈልጋል ያሉት ስፔሻሊስቱ፣  እናትና ልጆችን ይበልጥ ለማቀራረብ ምቹ አካባቢ መፍጠር እንደሚገባ፣ መንግሥት ለዚህ ጉዳይ የራሱን በጀት መያዝ እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ አብዛኛውን ጊዜ ስለ ጡት ማጥባት ጠቀሜታ እናቶች የሚገነዘቡት ከወለዱ በኋላ ወይም ሁለተኛ ልጃቸውን ወልደው ነው የሚሉት ዶ/ር ገስጥ፣ ግንዛቤ ማስጨበጡ በእርግዝና ወቅት መሠራት የነበረበት እንደሆነ አክለዋል፡፡

ከወሊድ በኋላ የእናትና ልጅ ንክኪ የራሱ የሆነ ጥቅም ያለው ሲሆን፣ የእናት ጡት ወተት የያዘው ረቂቅ፣ ድንቅ የተፈጥሮ ምግብና መድኃኒት ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለእናት የሚደረግ የምክር አገልግሎት ያልተለመደ ቢሆንም ተግባራዊ ማድረግ ግን ተገቢ መሆኑን፣ ባደጉ አገሮች ስለ ጡት ማጥባት ምክር የሚሰጡ የራሱ የሆኑ ባለሙያዎች እንዳሉና በኢትዮጵያም ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ አክለዋል፡፡

ለኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ የሆነው የምግብ ሳይንስና ሥነ ምግባር መርሆችን መከተልም እናቶች በበቂና በተገቢው ምግብ እንዲመገቡ ሕፃናትም ማግኘት ያለባቸውን ተፈጥሮአዊ የእናት ጡት እንዲያገኙ እንደሚያደርግ የሥነ ምግብ ባለሙያዋ ወ/ሮ ስንቴ መንገሻ ተናግረዋል፡፡

የምግብ ሳይንስና ሥነ ምግብ ባለሙያዋ ወ/ሮ ስንቴ፣ ሕፃናት ስድስት ወር እስኪሞላቸው ሁሉም ቫይታሚኖች ያሉትን የእናት ጡት ወተት ብቻ ቢመገቡ ከበሽታ መከላከል ያስችላል ብለዋል፡፡

በአዳማ ሪፍት ቫሊ ሆስፒታል የሕጻናት ስፔሻሊስት መልኩ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ በተለያዩ የሕመም ምክንያት ጡት ማጥባት የማይችሉ እናቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ሕፃኑ ጋላክቶሴሚያ ካለበት፣ እናት ኬሞቴራፒ ወይም የካንሰር መድኃኒት የምትወስድ ከሆነ ጡት መጥባትም ሆነ ማጥባት አይፈቀድም፡፡

የእናት ጡት ማጥባት ከሚከለከልባቸው ሁኔታዎች፤ ሕፃኑ በተፈጥሮ የጤና እክል ሲኖረው ለምሳሌ ጋላክቶሴሚያ (Galactosmia) የመሳሰሉት ችግሮች ሲኖርባቸው፣ ጨቅላ ሕፃናቱ ጡት በሚጠቡበት ወቅት ለከፍተኛ የጤና መታወክ ይዳረጋሉ፡፡

ይኼም የሚሆነው ጋላክቶሴሚያ ጨቅላ ሕፃናት ጋላክቶስዋን ፎስፌት ዩሪዲልትራንስፍሬዝ (Galactose -1- Phosphate Uridyitransferase) የተባለ ኢንዛይም ስለሌላቸው ወይም ስለማይሠራ ከወተት የሚገኘውን ጋላክቶስ ማብላላት (መሰባበር) ይሳነዋል፡፡ ፊና ይልኬቶኑሪያ  (Phenylketonurie) የሚኖርባቸው ጨቅላዎች ደግሞ (Phenylanine Lanie Hydoxylase) የሚባል ኢንዛይም ስለማይኖራቸው ፌናይል አለጊን ሐይምዝሌስ የተሰኘው ከወተት ተዋጽኦ የሚገኘውን ‹‹Amino Acid›› ማብላላት ይሳናቸዋል፡፡ እነዚህም መብላላት የሚገባቸው ንጥረ ነገሮች በደም ውስጥ ሲከማቹ፣ ጨቅላ ሕፃናቱ ለከፍተኛ ሕመምና ሞት ይዳረጋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ከተወት ተዋጽኦ እስከ መጨረሻው ይከለከላሉ፡፡

በሌላ በኩል የተወሰኑ የሕመም መድኃኒቶች የሚወስዱ በተለይ ለእነዚህ እናቶች መድኃኒቱን መውሰድ ግድ ከሆነ ጡት እንዳያጠቡ ይደረጋሉ፡፡

በአብዛኛው ጊዜ ባደጉ አገሮች በዚህ በሽታ ለተጠቁ ሕፃናት ከሌሎች ንጥረ ነገሮች የተሠራ ወተት በመመገብ ሕፃናት እንዲያድጉ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ በዚህ የተጠቁ ቢኖሩም እንኳን ለማወቅ በቂ የመመርመርያ መሣሪያና ከሌሎች ንጥረ ነገሮች የተዘጋጁ የወተት ዓይነቶች አለመኖራቸው ሕፃናት በሽታቸው ሳይታወቅ ሊሞቱ እንደሚችሉ ዶ/ር መላኩ ተናግረዋል፡፡

ኤችአይቪ ያለባት እናት ከእርግዝናዋ ጀምሮና ከወሊድ በኋላ ለልጇና ለእሷ በምትወስደው መድኃኒት ሙሉ ለሙሉ ከኤችአይቪ ነፃ የሆነ ልጅ ማሳደግ ትችላለች ያሉት ዶክተሩ፣ ይህ ግን ጡት በማጥባት ሒደት ውስጥ ሌሎች ምግብም ሆነ ውኃ፣ ፈሳሽ ነገሮች ሳይካተቱ መሆን እንዳለበት አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል ቲቢ ያለባት እናት በጡት ወደ ልጇ የሚተላለፍበት መንገድ ባይኖርም ባላቸው የእናትና የልጅ ቅርበት ሳቢያ ልታስተላልፍ ትችላለች፡፡ ነገር ግን እናት የቲቢ መድኃኒት ከወሰደችና ልጇም ፀረ ቲቢ መድኃኒት የሚወስድ ከሆነ የመተላለፍ መንገዱን መግታት ያስችላል፡፡

ቢሆንም ግን በኤችአይቪና በቲቢ ለተያዙ እናቶች ጡት ማጥባት በአንፃራዊ የተከለከለ ሲሆን፣ አቅም ባላቸው ወይም ባደጉ አገሮች ውስጥ በእነዚህ ሕመሞች የተያዙ እናቶች እንደሚከለከሉም ገልጸዋል፡፡

በዓለም የጡት ማጥባት ሳምንት ከኦገስት 1 እስከ 7 ቀን ‹‹Empower Parents Enable Breast Feeding›› በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡

ጡት ማጥባትን ይበልጥ ለማበረታታት ኢትዮጵያም ለ11ኛ ጊዜ ከሐምሌ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ማክበር ጀምራለች፡፡

በሔለን ተስፋዬ

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...