Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ከዕቅዱ በላይ 850 ሚሊዮን ብር ገቢ ማስገኘቱ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከወጪ ንግድ 200 ሺ ዶላር ለማስገኘት አቅዶ 465 ዶላር ማግኘቱ ተመልክቷል

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ በሥሩ የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶችን የ2011 ዓ.ም. አፈጻጸም መገምገም መጀመሩን አስመልክቶ ሰሞኑን ከተመለከታቸው መካከል፣ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በሽያጭም በገቢም ከዕቅዱ በላይ በማስመዝገብ ከ850 ሚሊዮን ብር በላይ ማስገኘቱን አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ የፋብሪካው አፈጻጸም ሐምሌ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በተገመገመበት ወቅት እንደተጠቀሰው፣ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በበጀት ዓመቱ 13.5 ሚሊዮን ሊትር አልኮል መጠኑና ስድስት ሚሊዮን ሊትር ንፁህ አልኮል አምርቷል፡፡

የሁለቱም ምርቶች አፈጻጸም በተናጠል የ111 በመቶ ውጤት እንደተመዘገበበት ተጠቁሟል፡፡ በመሆኑም ከአልኮል መጠጥ፣ ከንፁህ አልኮልና ከእሳት አልኮል ምርቶች 750 ሚሊዮን ብር የሽያጭ ገቢ ለማግኘት አቅዶ፣ በውጤቱ 850 ሚሊዮን ብር ማግኘቱን የኤንሲው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በትርፍ ረገድም 200.6 ሚሊዮን ብር ገደማ ለማግኘት አስቦ ከ233.5 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉ ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወደ ውጭ ከሚልካቸው ምርቶች 202 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ቢያቅድም፣ በአፈጻጸሙ 465 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገባቱን ኤጀንሲው አመልክቷል፡፡ ውጤቱም ከዕቅዱ በላይ ከ230 በመቶ በላይ ጭማሪ የታየበት ሆኗል፡፡

ከብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በተጨማሪ በዕለቱ የተገመገመው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ሲሆን፣ ከኅትመት ውጤቶች ሽያጭ 538 ሚሊዮን ብር ገቢ አስመዝግቧል፡፡ ዕቅዱ ከ639 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገባት ነበር፡፡ በትርፍ ረገድም ከ198.5 ሚሊዮን ብር በላይ በማስገባት የዕቅዱን 95 በመቶ አሳክቷል ተብሏል፡፡ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ የሚያወጡ የኅትመት ውጤቶችንም ማምረቱ ተጠቁሟል፡፡

እንዲህ ያሉት የዓመቱ የግምገማ ሒደቶች በተቀሩት የልማት ድርጅቶች ላይ እንደሚከናወን ለሪፖርተር የገለጹት የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ፣ አጠቃላይ የልማት ድርጅቶቹ አፈጻጸም የግምገማ ውጤት ተጠቃሎ ሰሞኑን ይፋ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

በኤጀንሲው ሥር 22 የልማት ድርጅቶች አሉ፡፡ 2011 ዓ.ም. ዘጠኝ ወራት ከታክስ በፊት 37.5 ቢሊዮን ብር ለማትረፍ አቅደው 29.6 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡ የልማት ድርጅቶቹ በባለፉት ዘጠኝ ወራት 122 ቢሊዮን ብር የሚገመት የምርትና አገልግሎት ሽያጭ አቅደው፣ 100 ቢሊዮን ብር በላይ አከናውነዋል፡፡ በወቅቱ የልማት ድርጅቶቹ ካገኙት አጠቃላይ የምርትና አገልግሎት ሽያጭ ገቢ 100.8 ቢሊዮን ብር ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 37.7 በመቶ፣ ኢትዮ ቴሌኮም 28.9 በመቶና የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት 13.9 በመቶ ድርሻ በመያዝ ከፍተኛ አፈጻጸም አስመዝግበዋል፡፡

በአጠቃላይ ከታክስ በፊት ከተገኘው 29.6 ቢሊዮን ብር ትርፍ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት ኢትዮ ቴሌኮም 62.07 በመቶ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 43.98 በመቶ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት 3.75 በመቶ ድርሻ እንደነበራቸው ይታወሳል፡፡ በአንፃሩ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት አክሲዮን ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)፣ የኢትዮጵያ ንግድራዎች ኮርፖሬሽንና ሸበሌ ትራንስፖርት ክሲዮን ማኅበር በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ኪሳራ ማስመዝገባቸው በኤጀንሲው ሪፖርት ቀርቦ ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች