Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ የማዕድን ካዳስተር አሠራር ይፋ ተደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፔትሮሊየም መረጃ ቋት ተደራጅቷል

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የማዕድን ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ሥራውን የሚያዘምን፣ ብሔራዊ የማዕድን ካዳስተር አሠራር ይፋ አደረገ፡፡

ትሪምፕል በተባለ ዓለም አቀፍ ሶፍትዌር አበልፃጊ ኩባንያ የተሠራው ‹ላንድፎሊዮ› የተሰኘው የማዕድን ካዳስተር በማዕድን ፍለጋና ልማት መሰማራት የሚፈልጉ ኩባንያዎች፣ ማመልከቻቸውን በአካል ሳይሰጡ በተዘጋጀው ድረ ገጽ አማካይነት በማስገባት ጉዳያቸውን መከታተልና ክፍያ መፈጸም የሚያስችል ነው፡፡

የካዳስተር ሲስተሙ አዲስ ማመልከቻዎችንና ነባር የማዕድን ሥራ ፈቃዶችን በዘመናዊ መንገድ ማስተዳደር እንደሚያስችል፣ የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ የክልል ማዕድን ቢሮዎች ከካዳስተር ሲስተሙ ጋር የተገናኙ ስለሆኑ፣ ከክልሎች ጋር የሚደረገው የሥራ ግንኙነትም በሲስተሙ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የካዳስተር ፕሮጀክት በካናዳ መንግሥት ድጋፍ እየተተገበረ እንደሆነ ታውቋል፡፡

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሐምሌ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. 50 ያህል የማዕድን ኩባንያዎችን በመጋበዝ የካዳስተር ሲስተሙን አስተዋውቋል፡፡ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰፋ ኩምሳ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ሚኒስቴሩ ይከተል የነበረው የማኑዋል ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓት አድካሚ፣ ብዙ ጊዜና ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ በተጠቃሚዎች ቅሬታ ሲፈጥር እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አዲሱ የካዳስተር ሲስተም ኩባንያዎች በአካል ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መምጣት ሳያስፈልጋቸው፣ ለማዕድን ፍለጋ ሥራ የሚፈልጉትን መሬት በመለየት ማመልከቻቸውን በድረ ገጽ በማስገባት አፋጣኝ የሆነ ምላሽ እንደሚያገኙ፣ ክፍያዎችንም መፈጸም እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ የካዳስተር አሠራር ጊዜና ወጪ ከመቆጠቡም በላይ ግልጽነት እንደሚያሰፍን ተናግረዋል፡፡

‹‹የሰጠናቸውን ፈቃዶች በትክክል ማወቅ፣ ማስተዳደርና ያሉትን ችግሮች መለየት እንችላለን፤›› ያሉት አቶ አሰፋ፣ ክልሎች ከሲስተሙ ጋር የተገናኙ በመሆናቸው በክልል ስለሚገኙ የማዕድን ቦታዎች መረጃ ለማግኘት የደብዳቤ ልውውጥ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቱን በገንዘብና ባለሙያ በማቅረብ ለደገፉት የካናዳ ኢንተርናሽናል ሪሶርስስ ዲቨሎፕመንት ኢንስቲትዩትና ሰም ፕሮጀክት ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በ2002 ዓ.ም. በዓለም ባንክ ድጋፍ ፍሌክስ የተባለ የካዳስተር ሲስተም ዘርግቶ የነበረ ቢሆንም፣ ብዙም ሳይጠቀምበት መክኖ መቅረቱ የሚታወስ ነው፡፡

ስለአዲሱ ካዳስተር ሲስተም ማብራሪያ የሰጡት የትሪምፕል ኩባንያ ኃላፊ ሚስተር ቲም ዋሊስ መሠረተ ልማቱ አዲስ ማመልከቻዎችን ለማስተናገድ፣ ነባር የማዕድን ፈቃዶችን ለማስተዳደርና ክፍያዎችን ለመፈጸም እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡ የካዳስተር ሲስተሙ ገቢ እንደሚጨምር፣ የባለሀብቶች እምነት እንደሚገነባና ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር እንደሚያሰፍን ዋሊስ አስረድተዋል፡፡

የማዕድን ፈቃድ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አያሌው፣ አዲሱ የካዳስተር አሠራር የሥራ ሸክም እያቃለለ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በስብሰባው ላይ የተካፈሉ የኩባንያዎች ተወካዮች የካዳስተር አሠራር በመጀመሩ እንደተደሰቱ ተናግረዋል፡፡ የክልሎች በካዳስተር ሲስተም የመጠቀም ብቃት ላይ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ የመረጃ ደኅንነት ጥበቃው ምን ያህል ነው? የማለፊያ ቁልፍ ቢሰረቅ መጠባበቂያ አለ ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡ ቀደም ሲል የማዕድን ሚኒስቴር የዘረጋውን የካዳስተር ሲስተም ሳይጠቀምበት መቅረቱን አስታውሰው፣ አዲሱን አሠራር ሙሉ በሙሉ እንደሚተገብረው ማረጋገጥ ይቻላል? የሚል ጥያቄም አቅርበዋል፡፡

ከኩባንያዎች ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አቶ ሲሳይ ከክልል ለተውጣጡ ባለሙያዎች በደቡብ አፍሪካ ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸው፣ ክልሎች በካዳስተር ሲስተሙ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር የተሳሰሩ ስለሆኑ ኩባንያዎቹ ሥጋት ሊገባቸው እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡ ቀደም ሲል የነበረውን ካዳስተር ሲስተም ሚኒስቴሩ ሳይጠቀምበት የቀረው በባለሙያና በመሠረተ ልማት ችግር እንደሆነ ጠቁመው፣ አሁን ግን በቂ ባለሙያ እንዲሠለጥን መደረጉን፣ የኮምፒዩተር፣ የኔትወርክና አማራጭ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዳታ ክላውድ የሚጠቀም በመሆኑ፣ አስተማማኝ መጠባበቂያ መረጃ እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡

ሚስተር ዋሊስ በበኩላቸው የካዳስተር ሲስተሙ አስተማማኝ የደኅንነት መቆጣጠሪያ መሠረተ ልማት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ እያንዳንዱ ኩባንያ የራሱ መለያና የይለፍ ቃል እንደሚኖረው ገልጸው፣ በካዳስተር ሲስተሙ ላይ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ቅኝት እንደሚደረግና መረጃዎችን መለወጥ እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

የካናዳ ኢንተርናሽናል ሪሶርስስ ዴቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት ፕሮግራም ኦፊሰር አቶ ፍፁም አሰፋ፣ የካዳስተር ሲስተም ዝግጅቱ በታኅሳስ 2011 ዓ.ም. መጀመሩን ገልጸው ከሚኒስቴሩና ከክልሎች ለተውጣጡ 12 ባለሙያዎች በኬፕታውን ደቡብ አፍሪካ ሥልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ሶፍትዌሩን ያዘጋጀው ትሪምፕል ኩባንያ በቀጣይ ለአንድ ዓመት የአቅም ግንባታ ዕገዛ የሚያደርግ በመሆኑ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ሆነ የክልል ማዕድን ቢሮዎች በአጠቃቀም ዙሪያ ችግር እንደማይገጥማቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አዲስና ዘመናዊ የሆነ የፔትሮሊየም መረጃ ቋት አዘጋጀ፡፡ ሚኒስቴሩ የአገሪቱን የፔትሮሊየም መረጃዎች የሚቀመጥበት ሕንፃና የአይቲ መሠረተ ልማት መገንባቱ ታውቋል፡፡

ከአገሪቱ ከተለያዩ ሴዲመንታሪ ቤዚኖች የተሰበሰቡ የሴይስሚክ መረጃዎች  በሂውስተን ቴክሳስ በሚገኝ የጂኦሎጂ ቤተ መዛግብት በክፍያ ለረዥም ዓመታት ይቀመጥ እንደነበር የገለጹት ምንጮች፣ መረጃዎቹ ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲቆዩ በዓመት እስከ 8,000 ዶላር ድረስ ይከፈል እንደነበር ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የፔትሮሊየም ሥራዎች ዳይሬክቶሬት ከአማካሪ ድርጅት ጋር በመተባበር አዲሱን  የፔትሮሊየም መረጃ ቋት ማደራጀቱን የገለጹት ምንጮች፣ በቅርቡ ይፋ አንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ በውጭ አገር ይቀመጡ የነበሩት የፔትሮሊየም መረጃዎች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ መደረጉ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች