Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ላኪዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል አዲስ አሠራር ተግባራዊ ሊደረግ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከዓመት ወደ ዓመት እየቀነሰ ለመምጣቱ አንዱ ምክንያት ላኪዎች ከመሸጫ ዋጋ በታች (አንደር ኢንቮይስ) የሚፈጽሙት ያልተገባ ድርጊት በመሆኑ፣ ላኪዎችን መቆጣጠር የሚያስችል አዲስ አሠራር ተግባራዊ እንደሚደረግ ተመለከተ፡፡ የ2011 ዓ.ም. የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከአምናው በ170 ሚሊዮን ዶላር በመቀነስ፣ 2.67 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ተገኝቷል፡፡

የ2011 ዓ.ም. የወጪ ንግድ አፈጻጸም አስመልክቶ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዓርብ ሐምሌ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ በበጀት ዓመቱ ከውጭ ምንዛሪ ይገኛል ተብሎ ከታቀደው ማሳካት የተቻለው 61 በመቶ ነው፡፡

የሚኒስቴሩ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንዳሉት፣ በበጀት ዓመቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም የቀነሰው በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ በአገሪቱ የተፈጠረው አለመረጋጋትና የዓለም ገበያ ዋጋ መቀነስ የመሳሰሉትን ጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ ግን ላኪዎች በአንደር ኢንቮይስ የሚፈጽሙት ድርጊት በዋናነት ተጠቅሷል፡፡    

እንዲህ ያሉ ችግሮች የሚያጋጥሙት በላኪዎች አሠራር ምክንያት በመሆኑ፣ ችግሮቹን ለመቅረፍ እንደ መፍትሔ ከቀረበው በርካታ ድርጊቶች መካከል ከመሸጫ ዋጋ በታች ስለሆነ፣ ሚኒስቴሩ አዳዲስ የመቆጣጠሪያ ሥልቶችን ተግባራዊ ያደርጋል ብለዋል፡፡

እስካሁን የተፈጠሩ ችግሮችን ለማስተካከልና በ2012 በጀት ዓመት የታቀደውን ገቢ ለማሳካት፣ የንግዱን ዘርፍ በአገር ደረጃ ሪፎርም የማድረግ ሥራ እንደሚከናወን የጠቆሙት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ፣ ችግሮችን ለማቃለል በመፍትሔ ደረጃ ከተቀመጡት ውስጥ የመጀመርያው የወጪ ንግድን በኮንትራት አድሚኒስትሬሽን በአግባቡ እንዲተገበር ማድረግ ነው፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ እያንዳንዱ ላኪ የሚልከውን የምርት በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማስመዝገብ ይኖርበታል፡፡ የገባውንም ከዓመታዊ ኮንትራት በየጊዜው ማሳወቅ አለበት፡፡ በኮንትራቱ ውስጥ የምርት ጥራት፣ ዋጋና ምርቱ የሚወጣበት ጊዜ አለ፡፡ እንዲህ ያሉ መረጃዎችን የያዘውን የኮንትራት ስምምነት በየጊዜው ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስቴሩ ይህንን መረጃ በየጊዜው ኦዲት ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም ለወጪ ንግድ እንደሚሰጠው ድጋፍ ሁሉ ቁጥጥርም ማድረግ ያለበት በመሆኑ ይህ ይተበገራል፤›› ሲሉ አቶ ወንድሙ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት እንዲህ ያለው ድምዳሜ ላይ የደረሰው የወጪ ንግድ አፈጻጸም ሲገመገም በአብዛኛው የውጭ ምንዛሪ ግኝት መዳከምና ማነስ፣ የመንግሥት ገቢ መቀነስና ባንኮች ያበደሩትን ገንዘብ በጊዜው ማግኘት ያልቻሉበት ምክንያት በአንደር ኢንቮይስ ምክንያት መሆኑ በመረጋገጡ ነው ብለዋል፡፡ ይህም በመሆኑ አብዛኛው ገንዘብ ባለሀብቱ እጅና በውጭ አገር እንዲሆን እንዳደረገው፣ ከዚህ በኋላ እያንዳንዱ ላኪ የኮንትራት ስምምነቱን ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መቅረብ አለበት ሲሉም አክለዋል፡፡

እንዲህ ካሉ ውሳኔዎች ሌላ ተጨማሪ አዳዲስ አሠራሮችን የሚከተል መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ላኪዎች አስመጪዎች ጭምር ሆነው የሚሠሩ ስለሆነ፣ እዚህ አካባቢም ችግር በመታየቱ ቁጥጥሩን ማድረጉ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ንግድ ሚኒስቴር መረጃ የ2011 የበጀት ዓመት ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ 4.32 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፣ በአፈጻጸም የተመዘገበው 2.67 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ አፈጻጸም ከአምናው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ከተገኘው 2.84 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ170 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል፡፡

ታንታለም፣ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ የቅባት እህሎችና አበባ ከዕቅዳቸው ከ75 በመቶ በላይ ክንውን ሲያስመዘግቡ ቡና፣ ዓሳ፣ ኤሌክትሪክ፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ሻይ ቅጠልና ሰም ከተያዘላቸው ዕቅድ ከ50 በመቶ እስከ 74 በመቶ ክንውን ያስመዘገቡ ምርቶች መሆናቸውንም መረጃው ያመለክታል፡፡

በሌላ በኩል ሥጋ፣ ወተትና የወተት ተዋጽኦ፣ የተፈጥሮ ሙጫና ዕጣን፣ ቅማማ ቅመም፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ምግብ፣ መጠጥና ፋርማቲዩቲካልስ፣ ማር፣ የሥጋ ተረፈ ምርት፣ ሌሎች ማዕድናት፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓት፣ ወርቅ፣ የብዕርና የአገዳ እህሎችና ብረታ ብረት ከተያዘው ዕቅድ አንፃር በውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ50 በመቶ በታች ዝቅተኛ ገቢ ያስመዘገቡ የወጪ ንግድ ምርቶች ሆነዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ አፈጻጸም መቀነስ እንደ ምክንያት ከተጠቀሱት ውስጥ የምርት አቅርቦትና የጥራት ችግሮች፣ የኮንትሮባንድ ንግድ መበራከት፣ የዓለም ገበያ ዋጋ መዋዠቅ፣ የኃይል አቅርቦት እጥረትና በአንዳንድ አካባቢዎች ከፀጥታ ጋር በተያያዘ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች በተግዳሮትነት ተጠቅሰዋል፡፡ በተለይ እንደ ወርቅ ያሉ ምርቶች ገቢ ማሽቆልቆል በዋናነት የኮንትሮባንድ ንግድ ተጠቅሷል፡፡ አገራዊ አለመረጋጋትና የጥቁር ገበያው መስፋፋት ለችግሩ ምንጭ ሆኗል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በአገር ደረጃ በትብብር የሚፈጸሙ የተለያዩ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱና ለወጪ ንግዱ ተግዳሮት ናቸው የተባሉ ጉዳዮችን ለመቅረፍ፣ ሚኒስቴሩ ስለመዘጋጀቱ ከተደረገው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በየዓመቱ እያሽቆለቆለ ያለው የወጪ ንግድ ለመታደግ መንግሥት በተለያዩ ሪፎርሞች ማስተካያዎችን በማድረግ በ2012 በጀት ዓመት ከተለያዩ የወጪ ንግድ ምርቶች 4.69 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ማቀዱን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ ግብርና ዘርፍ 3.32  ቢሊዮን ዶላር፣ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ 1.02 ቢሊዮን  ዶላር፣ የማዕድን ምርቶች 265.82 ሚሊዮን ዶላርና ከኤሌክትሪክ አገልግሎትና ከሌሎች ወጪ ንግድ ምርቶች 83.66 ሚሊዮን ዶላር ድርሻ የያዘ ገቢ ይገኛል ተብሎ ታቅዷል፡፡

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይህንን ዕቅድ የያዘው ለ2012 በጀት ዓመት መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻዎች የወጪ ንግዱን የሚያበረታቱ ስለሆኑ፣ የታቀደውን ለማሳካት ይቻላል የሚል እምነት አለው፡፡ የፖለቲካ ውሳኔ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ መንግሥትና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ድጋፍ እንደሚጠናከርና በ2012 በጀት ዓመት፣ ከዘንድሮ በአንዳንድ የወጪ ንግድ ምርቶች የተሻለ ምርት የሚጠበቅ ይሆናል ተብሏል፡፡        

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች