Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበእነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ ምስክር የነበሩ ግለሰብ በእነ ጌታቸው አሰፋ...

በእነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ ምስክር የነበሩ ግለሰብ በእነ ጌታቸው አሰፋ መዝገብም ምስክር ሆነው ቀረቡ

ቀን:

ከ10 ዓመታት በፊት ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለማፍረስና በመፈንቅለ መንግሥት ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው በነበሩት በእነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ ውስጥ ተካተው በነበሩ ተከሳሾች ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩ ግለሰብ፣ በእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ በተካተቱ ተከሳሽ ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው ቀረቡ፡፡

በሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀል ክስ በተመሠረተባቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ፣ ሰባተኛ ተከሳሽና የደኅንነት ሠራተኛ በነበሩት አቶ ተስፋዬ ገብረ ፃዲቅ ላይ ዓቃቤ ሕግ የቆጠራቸው ምስክር፣ ሐሙስ ሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በጭብጡ ምስክሩ በ2001 ዓ.ም. በመኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ፣ የማያውቁት ድብቅ እስር ቤት ተወስደው በማስገደድ መረጃ እንዲያወጡ ሲደበደቡ እንደ ነበርና በተከሻሱ የደረሰባቸውን አጠቃላይ ሁኔታ እንደሚያስረዱ ገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ምስክሩም ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ በጥር ወር 2001 ዓ.ም. ሁለት ሰዎች ሌሊት ላይ ቤታቸው በመምጣት ሽጉጥ ደግነው ይዘዋቸው ይሄዳሉ፡፡ በካቴና እጅና እግራቸውን አስረው እንዳሳደሯቸውና በጥፊና በእርግጫ እንደመቷቸው ገልጸዋል፡፡  በሚስጥር ስማቸው ‹‹አጎቴ›› ከሚሏቸው ተከሳሽ አቶ ተስፋዬ ጋር እንዳገናኟቸውና ተከሳሹም ‹‹ሁሉንም ነገር አውቀነዋል፣ ደርሰንበታል፣ የምታውቀውን ሁሉ ንገራቸው፤›› እንዳሏቸውም መስክረዋል፡፡ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ሲነግሯቸው ወስደው እንዳሰሯቸውም ገልጸዋል፡፡ ‹‹የምታውቀውን ነገር ተናገር›› እያሉ እንደ ደበደቧቸው፣ ቆይተው ቄራ መሆኑን ወዳወቁት ቦታ እንደወሰዷቸውና እዚያ እንዳቆዩዋቸው መስክረዋል፡፡ የሆነ ቀን ማዕከላዊ እንደወሰዷቸውና የምስክርነት ቃላቸውን እንደሰጡም ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ፍርድ ቤት ቀርበው ለዓቃቤ ሕግ ከመሰከሩ በኋላ፣ ወደ ቤተል አካባቢ ወስደው ቤት በመከራየት እንዳስቀመጧቸውም ገልጸዋል፡፡ ለስድስት ወራት የቤት ኪራይ እንደከፈሉላቸውና ‹‹አጎቴ›› በማለት በሚስጥር ስም የሚጠሯቸው ተከሳሹ አቶ ተስፋዬ በየወሩ 500 ብር ሲሰጧቸው ቆይተው፣ በኋላ የራሳቸውን ሱቅ በመክፈት ሥራ መጀመራቸውን በመግለጽ መስክረዋል፡፡

መስቀለኛ ጥያቄ በጠበቃቸው አማካይነት ያቀረቡት ተከሳሽ አቶ ተስፋዬ ፍርድ ቤት ቀርበው የመሰከሩት በማን ላይ እንደሆነ ጠይቀዋቸው፣ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወንጀል ተከሰው በነበሩት የግንቦት ሰባት አመራሮች በእነ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ላይ መሆኑን ገልጸዋል (የነብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) እና የብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ በአንድ ላይ ሲታይ እንደነበረ ይታወሳል)፡፡

የመፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ በተዘጋጀው የአገር ውስጥ ሴል አካል ስለመሆናቸው ሲጠየቁ፣ ‹‹አዎ ነበርኩ››  ብለዋል፡፡ ተከሳሹ አቶ ተስፋዬ መረጃ ከመጠየቅ ውጪ ያደረጓቸው ነገር ስለመኖሩ ተጠይቀው፣ ‹‹ምንም የለም፤›› ብለው፣  መረጃ ብቻ እንደተቀበሏቸው አክለዋል፡፡ በማዕከላዊ ስለሰጡት መረጃ ሊጠይቋቸው፣ የሚውቁትን ሁሉ እንደተናገሩ ገልጸዋል፡፡ ስለምን ሲባሉ፣ ስለ እነ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) የሚያውቁን ሁሉ መናገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤት ቀርበው ስለምን እንደመሰከሩ ተጠይቀው፣ ማዕከላዊ የተናገሩትን ሁሉ ለፍርድ ቤቱም ማስረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

ተከሳሹን አቶ ተስፋዬን ‹‹አጎቴ›› እንደሚሏቸው፣ ምስክሩም የሚስጥር ስም እንደነበራቸው ሲጠየቁ፣ ‹‹አዎ ነበረኝ›› በማለት ‹ግዛው› የሚባል ሚስጥር ስም እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡ ከትራፊክ ፖሊስ የተነጠቀ የሬዲዮ መገናኛ ስለመኖሩ ተጠይቀው፣ ‹‹አዎ ነበር፣ እሱን አስረክቤያለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ማን እንደሰጣቸውና ሌላም ተጨማሪ ነገር ስለመቀበላቸው ተጠይቀው፣ የሰጣቸው ከእነ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ጋር አብሮ ተከሶ የነበረ ዘለዓለም የሚባል ሰው እንደ ሰጣቸውና ተጨማሪም መጽሐፍ (የሥልጠና ማኑዋል) እንደተቀበሉ መስክረዋል፡፡

ለአገርና ለወገን የሠራኸው በሚል ሱቅ እንደተከፈተላቸው ተጠይቀው ‹‹ተከፍቶልኛል›› ብለዋል፡፡ በየወሩም ‹‹አጎቴ› ተከሳሽ አቶ ተስፋዬ 500 ብር ይሰጧቸውና የቤት ኪራይ ይከፈልላቸው እንደነበር አስረድተዋል፡፡ በወቅቱ በእነ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ላይ ለፍርድ ቤቱ የሰጡት ምስክርነት እውነት እንደነበርና በተያዙበት ወቅት መረጃ አልሰጥም ያሉት፣ እንደ ድርጅት አባልነታቸው ሚስጥር መደበቅ ያለባቸው በመሆኑ ቢሆንም ቆይተው መናገራቸውን መስክረዋል፡፡ ለተከሳሹ ቃል ስለመስጠታቸው ተጠይቀው፣ ‹‹አልሰጠሁም፤›› ብለዋል፡፡ ምስክሩ ከእነ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ጋር ይሠሩ እንደነበርና ለመንግሥት መረጃ መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የማጣሪያ ጥያቄዎች አቅርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...