Tuesday, July 23, 2024

አጉል ፉክክር ኢትዮጵያን ከመንገድ ያስቀራታል!

ከዛሬ አንድ ዓመት ከአራት ወራት በፊት ኢትዮጵያ የለውጡን ጉዞ ስትጀምር፣ የነበረው ስሜትና አሁን የሚታየው ከፍተኛ ልዩነት አለው፡፡ ይህ ልዩነት መፈጠሩ ሊገርም አይገባም፡፡ ለውጡን ማስቀጠልና አቅጣጫ ማስያዝ ላይ ልዩነቶች መኖራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን በጋራ የተጀመረውን ለውጥ አደጋ ውስጥ መክተት መዘዝ አለው፡፡ ለውጡ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን እያሳተፈና አስተዋጽኦዋቸውን እያጠናከረ መጓዝ ሲገባው፣ በረባ ባልረባው በየፌርማታው ላይ መንጠባጠብ የማይወጡት ቀውስ ውስጥ ይከታል፡፡ አንዱን የለውጡ ባለቤት ሌላውን ደግሞ ከዳር ታዛቢ እንዲሆን የሚያደርግ አሠራርን ማስወገድ የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በተለያዩ የታሪክ ምዕራፎች ውስጥ የገጠሟት ፈተናዎች፣ ከእልህና ከአጉል ፉክክር የመነጩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ አሁንም እነዚያው ችግሮች በአራቱም ማዕዘናት ይስተዋላሉ፡፡ የመነጋገርና የመደማመጥ ባህል ባለመለመዱ፣ በወዳጅነት ተቀራርቦ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ባላንጣነት ይበረታል፡፡ ውድድሩም ሆነ ፉክክሩ በገንቢ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን፣ በመጠፋፋት ላይ ስለሚያተኩር ለአገር ጠቃሚ ይሆኑ የነበሩ በርካታ ወገኖች ተቀጥፈዋል፣ ተሰደዋል፣ በዝምታ ተሸብበው ዕውቀታቸው ባክኗል፡፡ አሁንም አጉል ፉክክር ውስጥ መዘፈቅ የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ ከስሜት ይልቅ በምክንያታዊነት የሚመራ አዲስ ትውልድ ያስፈልጋታል፡፡ ይህንን ትውልድ መቅረፅ ያለባቸው ምሁራንና ልሂቃን ግን የአጉል ፉክክር ተዋናይ ስለሆኑ፣ ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ የቆመች ትመስላለች፡፡ አሁን ቆም ብሎ በስክነት መነጋገር የሚያስፈልገው፣ ኢትዮጵያውያን የመሰላቸውን ሐሳብ በነፃነት የሚያራምዱላቸው በርካታ መድረኮች እንዲፈጠሩ ለማድረግ ነው፡፡ ዜጎች በነፃነት መነጋገር ሲጀምሩ መደማመጥ ከባድ አይሆንም፡፡ ይልቁንም የትውልዱ ንቃተ ህሊና ይዳብራል፡፡ ንቃተ ህሊና ሲዳብር መነጋገርም ሆነ መደማመጥ ይለመዳል፡፡ ጥራት ያላቸው ሐሳቦች የበለጠ ተቀባይነት ያገኛሉ፡፡ ተቃዋሚን በሐሳብ የበላይነት መብለጥ ዋጋ እንዳለው ስለሚታወቅ፣ ጉልበተኞች ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ ሐሜት፣ አሉባልታና ጭፍን ጥላቻ ይናቃሉ፡፡ ሰብዓዊነት ከምንም ነገር በላይ ክብር ያገኛል፡፡ ፉክክሩ ጤናማና ሥልጡን እየሆነ ሲሄድ መግደል፣ ማፈናቀል፣ መዝረፍና ማውደም የኋላቀሮች መገለጫ ይሆናሉ፡፡ ኢትዮጵያ በፍጥነት አሁን ካለችበት አሳዛኝና አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ መውጣት ይኖርባታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በበርካታ አካባቢዎች ከምክንያታዊነት ጋር የተጣሉ ድጋፎችና ተቃውሞዎች ይሰማሉ፡፡ ባህር ማዶ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም አሉበት፡፡ ድጋፍና ተቃውሞ የሰው ልጅ ባህሪያት ቢሆኑም በአሁኑ ጊዜ ግን ዘር፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ የፖለቲካ አቋምና የመሳሰሉት ላይ ብቻ በመንጠላጠል በስሜት መነዳት በስፋት ይስተዋላል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከናወን እያንዳንዱ ጉዳይ የሚበየነው ከመርህ አንፃር ሳይሆን፣ ይወክለኛል ተብሎ ከሚታሰበው የጎራ አሠላለፍ አኳያ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ውሉ የጠፋበት አሠላለፍ በተለይ ተምረናል በሚሉት ላይ ብሶ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ምክንያት የረባ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጉዳይ አጀንዳ የሌላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ግጭት ይቀሰቅሳሉ፡፡ የሕግ የበላይነት ይከበር ሲባል በምክንያታዊነት ሳይሆን ከጎራቸው ጥቅም አንፃር ሥሌት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የምታስተናግድ አገር ለማደራጀት እንቅስቃሴ እንጀምር ሲባል፣ እንወክለዋለን የሚሉትን ጎራ ቀዳሚ ተጠቃሚነት ያራግባሉ፡፡ ለብሔር ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ጭምር የሚጠቅም ሥራ ያስፈልጋል ሲባሉ፣ ሰብዓዊነትን በማንኳሰስ የአውሬ ተግባር ይፈጽማሉ፡፡ አገሪቱን የገጠማት ፈተና እንዲህ የተወላገደ ነው፡፡

ሌላው ችግር ፖለቲከኛ ተብዬዎችም ሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት ሰሌዳ የለጠፉ አስመሳዮች፣ ኢትዮጵያ ሰላማዊ ሽግግር አድርጋ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዳትዘጋጅ መሰናክል ይፈጥራሉ፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በነፃ፣ ፍትሐዊና አሳማኝ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተይዞ ኢትዮጵያ ከድህነት ውስጥ መውጣት ይገባታል፡፡ በሕግ የበላይነት የሚመራ፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለበት፣ አሠራሩ ግልጽ የሆነ፣ የኢትዮጵያውያንን መብት የሚያስከብር፣ ኢትዮጵያንም ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበቃና የዜጎችን ሁለንተናዊ ችግሮች የሚፈታ መንግሥት በሕዝብ ድምፅ መመሥረት አለበት፡፡ ይህንን ዕውን ለማድረግ ግን አሁን ከተያዘው አላስፈላጊ ፉክክር ውስጥ መውጣት ይገባል፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንዳችም ፋይዳ የሌላቸው ጉዳዮች ላይ ውሎ ማደር ተገቢ አይደለም፡፡ በመብት ጥየቃ ስም የአገሪቱን ሰላም ማደፍረስና ቀውስ መፍጠር፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መደረግ ያለበትን ጥረት ያመክናል፡፡ ከአገር በላይ ግላዊና ቡድናዊ ጉዳዮች ላይ መሽጎ በሴረኝነት መጠላለፍ መጨረሻው ተያይዞ መውደቅ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተደጋጋሚ ተሞክሮ ያልተሳካ ከመሆኑም በላይ፣ የብዙዎችን ሕይወት በከንቱ አስገብሯል፡፡

ካለፉት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ስመ ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋች ነን ባዮች፣ አሁንም በዚያ የጥፋት መንገድ ላይ እየነጎዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዘመናት ችግሮቿ ጋር ተፋጣ ሌሎች ችግሮችን በየቀኑ ይጭኑባታል፡፡ ትናንት ሥልጣን ላይ ሆነው በሕዝብ ላይ ይቀልዱ የነበሩ እንዴት እንደወደቁ መማር የሚገባቸው፣ ዛሬ ያንኑ ተመሳሳይ ስህተት ሲፈጽሙ ያስገርማል፡፡ ትናንት በደልና ግፍ ደርሶብናል እያሉ ይጮኹ የነበሩ፣ በእስር የተንገላቱ፣ በስደት መከራቸውን ያዩና የቅርብ ሰዎቻቸውን የተነጠቁ ጭምር መርህ አልባ ሆነው ሲገኙ ያሳዝናልም፣ ያሳፍራልም፡፡ ለሐሳብ ነፃነት ስንጮህ ነበር ብለው በየገመገሙ ሲያስተጋብሩ የነበሩ፣ የሌሎችን የተለየ ሐሳብ አንሰማም ብለው ሲወራጩ አንገት ያስደፋል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እያስተማሩ ያሉና የዕውቀት አባት ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱ፣ ቁልቁል ወርደው የዘረኝነትን መርዝ ሲረጩ ያማል፡፡ በአጠቃላይ የብልሆች መሰባሰቢያ መሆን የሚገባውን ፖለቲካ የመንደር ጨዋታ የሚያደርጉ እየበዙ ናቸው፡፡ በመርህ ሳይሆን በስሜት ነው የሚመሩት፡፡ የእነሱ ሳያንስ የሚያሠልፉት መንጋ ደግሞ ዓይኑን ጨፍኖ ስለሚደግፍና ስለሚቃወም፣ ከሐሳብ ልውውጥ ይልቅ የሚቀናው መግደልና ማውደም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ካሰበችው ሳትደርስ ከመንገድ የምትቀረው በእንዲህ ዓይነቶቹ አጉል ፉክክር ምክንያት ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...