Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚፈቅደው አዋጅ ፀደቀ

የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚፈቅደው አዋጅ ፀደቀ

ቀን:

የጉምሩክና ለሕዝብ ጥቅም የሚለቀቅ መሬትን በተመለከተ አዋጆች ፀድቀዋል

ለበርካታ ዓመታት ለውጭ አገር ዜጎች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ እንዳይሰማሩ በሚከለክለው የባንክ ሥራ አዋጅ ተሻሽሎ፣ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በባንክ ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ የሚያስችለው ረቂቅ አዋጅ በምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ ፀደቀ፡፡

ተሻሽሎ የፀደቀው ይኸው አዋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወለድ ነፃ ባንክን ለማቋቋም የሚያስችል ፈቃድ እንዲሰጥ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቡዕ ሐምሌ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው  ሁለተ አስቸኳይ ስብሰባ የባንክ ኢንዱስትሪውን ለማዘመን፣ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትና ቅልጥፍናን ለማጎልበት፣ እንዲሁም ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ አስቸጋሪ ሆነው የተገኙትን የአዋጁን አንቀጾችና ንዑስ አንቀጾች በማሻሻል በአሠራር ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን መፍታት እንዲቻል ተደርጎ መቅረቡ ተነግሯል፡፡

የባንክ ማሻሻያ አዋጁ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በባንክ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዳይሳተፉ ተጥሎ የነበረውን የሕግ ክልከላ ሙሉ በሙሉ አንስቷል።

ማሻሻያው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የውጭ አገር ዜጎች በባንክ ዘርፍ በመሳተፍ፣ ለአገሪቱ ግንባታና ለውጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችል ነውም ተብሏል።

አዋጁ በተጨማሪም ከወለድ ነፃ የባንክራን ማከናወን እንዲቻል እንደሚያግዝም ተጠቅሷል። ይህ የተሻሻለው የባንክ አዋጅ ከወለድ ነፃ ባንክ ለማቋቋም የባንክ ለማከናወን የሚያስፈልጉ ቅደመ ሁኔታዎችን በሙሉ እንዲሟሉ ያስገድዳል፡፡

በተጨማሪም ከወለድ ነፃ ባንክ ፈቃድ ለመስጠትና ለመቆጣጠር የሚያስችለውን አስገዳጅ መመርያ ብሔራዊ ባንክ ሊያወጣ እንደሚችል በሕጉ ሠፍሯል፡፡

ምክር ቤቱም በሪፖርቱና ውሳኔ ሐሳቡ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ አዋጁ አዋጅ ቁጥር 1159/2011 ሆኖ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ በዚሁ አስቸኳይ ስብሰባው የጉምሩክ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ፣ እንዲሁም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ የቀረቡ ሪፖርቶችንና የውሳኔ ሐሳቦችን መርምሮ አፅድቋል፡፡

የጉምሩክ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ለአሠራር እንቅፋት ሆነው የቆዩ ችግሮችን በማስወገድ አዲሱን የጉምሩክ አስተዳደር ሥርዓትን ቀላል፣ ቀልጣፋ፣ የተገልጋዮችን ጊዜ የሚቆጥብና በቀረጥ ነፃ መብት ስም የሚፈጸሙ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በር ለመዝጋት የሚያግዝ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

በገቢና በወጪ ዕቃዎች ላይም በመጓጓዣ ሒደት ሲደርስ የነበረውን ቅሸባና መሰል ተግዳሮቶችን ለመቀነስ ሲባል፣ የጭነት ተሽከርካሪዎች የጭነት መቆጣጠሪያ (ካርጎ ትራኪንግ) እንዲገጥሙ ለማድረግና ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አሠራሮች በማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ መካተታቸው ተብራርቷል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ላይ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት የተፈጸመበት ዕቃ በሁለት የሥራ ቀናት ውስጥ ከመጋዘን ያልወጣ እንደሆነ፣ አስመጪው ሦስት ሺሕ ብር መቀጫ ከፍሎ ዕቃውን ከመጋዘን ይወስዳል የሚለው ቀኑ አንሷል ሲሉ የምክር ቤት አባላት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የጉምሩክ አዋጅን ለማሻሻል በቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ላይ ምክር ቤቱ በዝርዝር ከተወያየበት በኋላ አዋጅ ቁጥር 1160/2011 አድርጎ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

በተመሳሳይም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን የቀረበውን የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በሚመለከት፣ በከተማም ሆነ በገጠር ባለይዞታዎች ለሕዝብ ጥቅም መሬት እንዲለቁ ሲደረግ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ የመብት ድንጋጌዎችን ያከበረና በዘርፉም የመልካም አስተዳደር ሥርዓትን በዘላቂነት ለማስፈን የሚደረገውን ርብርብ የሚደግፍ፣ እንዲሁም የመንግሥትን ልማታዊነት ለማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡

የልማት ተነሺዎችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልገውን በጀት፣ እንዲሁም በጀቱ በማን እንደሚሸፈን የሚወስነውን አካል ረቂቅ አዋጁ በግልጽ ያመላከተ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ለልማት ተነሺዎች ፈንድ መቋቋም እንዳለበት አስገዳጅ ድንጋጌዎችን ያካተተ እንደሆነም ተብራርቷል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው የልማት ተነሺዎች ካሳና ተያያዥ ቅሬታቸውን ማቅረብ ሲፈልጉ ቅድሚያ መሬት አስረክበው በፍርድ ቤት እንዲከራከሩ መደረጉ፣ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን የጣሰና የነፈገ መሆኑን ገልጸው፣ ካሁን በፊት የተከሰቱ ችግሮች እንዳይደገሙ በትኩረት መታየት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ በቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ላይ በስፋት ተወያይቶ፣ አዋጅ ቁጥር 1161/2011 ሆኖ በአምስት ተቃውሞና በአምስት ድምፅ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...