Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ደስ የሚያሰኝ ቀን ያለውን ያህል አንዳንዱ ቀን ሲፈጥረው ነጃሳ ነው፡፡ የእኔ ቀን የተነጀሰው ደግሞ በራሴ ጥፋት ሳይሆን በሌሎች ሰዎች ምክንያት ነው፡፡ እንደተለመደው በማለዳ ተነስቼ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እያደረግኩ ነው፡፡ በመጀመርያ ሰውነቴን ካሟሟቅኩ በኋላ ሩጫዬን ጀምሬያለሁ፡፡ ሾላ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቴ ወጥቼ በተመጠነ ፍጥነት እየሮጥኩ እንግሊዝ ኤምባሲ አጠገብ ስደርስ፣ አንድ አዛውንትና ሁለት ጎረምሶች እየተጨቃጨቁ ነበር፡፡ የጭቅጭቁ መነሻ ደግሞ መሬት ላይ ወድቆ የተገኘ የኪስ ቦርሳ ነው፡፡ አዛውንቱ ዕርዳታ እንደሚፈልግ ሆነው እየጮሁ ቦርሳውን በሁለት እጆቻቸው ይዘው አለቅም ብለዋል፡፡

ሁለቱ ጎረምሶች ደግሞ አዛውንቱን አንቀው ይዘው ቦርሳውን ስጡን ይላሉ፡፡ አዛውንቱ ደግሞ በጭራሽ ብለዋል፡፡ በዕድሜ የገፉ አዛውንት መሬት ላይ ወድቆ በተገኘ ቦርሳ ምክንያት አደጋ እንዳይደርስባቸው በማሰብ ለማገላገል እቆማለሁ፡፡ አዛውንቱ እኔን ሲያዩ፣ ‹‹በሕግ አምላክ!›› ማለት ይጀምራሉ፡፡ እኔም ጠጋ ብዬ፣ ‹‹ወድቆ የተገኘው ቦርሳ ለሁላችሁም ስለማይገባ ለፖሊስ መሰጠት አለበት፤›› እላለሁ፡፡ በቅርበት የሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ የካ ሚካኤል አጠገብ ስለሆነ ወደዚያ እንድንሄድ ማሳሰቢያ ሳቀርብ አዛውንቱ ‹‹አይደረግም!›› አሉ፡፡ ጎረምሶቹም ‹‹በጭራሽ!›› ማለት ያዙ፡፡

‹‹በሉ እናንተ ታገሉ እኔ ግን ፖሊስ እጠራለሁ፤›› ብዬ ሩጫዬን ስጀምር አዛውንቱ ሳላስበው በያዙት ዱላ ከኋላ ጀርባዬን ብለው ጣሉኝ፡፡ ከወደቅኩበት ልነሳ ስል ጎረምሶቹ ተረባረቡብኝ፡፡ ራሴን ስቼ ስወድቅ በአሥር ሺሕ ብር የገዛሁትን ሞባይል ስልኬንና ከአንድ ሺሕ ብር በላይ የያዘውን የኪሴን ቦርሳ ዘርፈውኝ ሁሉም ተሰወሩ፡፡ ከአፍታ በኋላ ሰዎች ደጋግፈው ሲያነሱኝ ጀርባዬ ላይና ጎኔ ላይ ከፍተኛ ሕመም ይሰማኝ ነበር፡፡ እንደ ምንም ብዬ ላዳ ታክሲ ይዤ ወደ ቤቴ ተመልሼ፣ ከዚያም ሕክምና አግኝቼ ካገገምኩ በኋላ የሆነውን ሳስብ በጣም አዘንኩ፡፡ ዕድሜ የጠገቡት አዛውንት ከጎረምሶች ጋር ተባብረው ዘረፋ ላይ መሰማራታቸው አሳዘነኝ፡፡ ለማይረባ ዝርፊያ ሕይወቴን አጥፍተውት ቢሆን ኖሮስ ብዬ ተበሳጨሁ፡፡ በእንዲህ ዓይነት ወረበሎች የስንቱ ሕይወት ጠፍቶ ይሆን? የስንቱስ ቤት ተዘግቶ ይሆን?

ከሕመሜና ከብስጭቴ አገግሜ ከሰነበትኩ በኋላ በግሌ እነዚህን ሰዎች ለመከታተል ጥረት ጀመርኩ፡፡ ይህንን ያደረግኩት ፖሊስ ዘንድ ብሄድ ትኩረት ተሰጥቶት ክትትል ይደርጋል የሚል እምነት ስላልነበረኝ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ጎረቤቴ አንድ ሰው ሕይወታቸውን ለማጥፋት ስለሚፈልግ፣ እጀ ጥብቅ ዋስ እንዲጠራላቸው ፖሊስን ቢጠይቁ መልስ አጥተው በዚያ ሰው እጅ ሕይወታቸው ማለፉን ስለማውቅ ነው ፖሊስን ያልፈለግኩት፡፡ ስለዚህ በጠዋት እየተነሳሁ በከፍተኛ ጥንቃቄ ከሾላ እስከ መገናኛ ያለውን መንገድ ግራና ቀኝ ሳስስ ሰነበትኩ፡፡ ሰዎቹ ግን የውኃ ሽታ ሆነዋል፡፡ ብወጣ ብወርድ ለአንድ ወር ያህል ያደረግኩት ፍለጋ ከንቱ ሆነብኝ፡፡

በቅርቡ ከሳሪስ አቦ ወደ መገናኛ የሚወስደው የቀለበት መንገድ ላይ አንድ አይሱዙ የጭነት መኪና ከጎኔ ይሄዳል፡፡ ድንገት ቀና ብዬ ሳይ ሾፌሩን የማውቀው መሰለኝ፡፡ የመኪናዬን የቀኝ መስታዎት ዝቅ አድርጌ ስመለከት ሾፌሩና አጠገቡ ያለውን ጎረምሳ አስታወስኳቸው፡፡ ከአዛውንቱ ጋር የነበሩት ጎረምሶች ናቸው፡፡ ጥቁር መነጽሬን ዓይኔ ላይ ሰክቼ ከጎኔ ካለው አይሱዙ ጋር በእኩል ፍጥነት መጓዝ ስጀምር፣ ከፊቴ ያለው መኪና ድንገት በመቆሙ አይሱዙው በፍጥነት አመለጠኝ፡፡ የሰሌዳ ቁጥሩን እንኳ ለመያዝ አልቻልኩም፡፡ በጣም ተናደድኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ለተወሰኑ ቀናት ከመገናኛ እስከ ቃሊቲ ድረስ አሰሳዬን ብቀጥል አልተሳካልኝም፡፡

ይሁንና ሰሞኑን ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ መኪናዬን እያሽከረከርኩ ጉርድ ሾላ ሳህሊተ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አጠገብ አደባባዩን ስዞር፣ እኚያን ጉደኛ አዛውንት አለባበሳቸው ሳይቀየር አየኋቸው፡፡ አደባባዩን ዞሬ ወደ ወሰን ግሮሰሪ የሚወስደውን መንገድ ከያዝኩ በኋላ አልፌያቸው አቆምኩና ወረድኩ፡፡ ‹‹አባት እርስዎንና ጎረምሶቹን እየተከታተልኩ ነበር፡፡ ይኼው አሁን ተገናኘን. . .›› እያልኩ ስጠጋቸው፣ ‹‹በሕግ አምላክ! በመንግሥት ይዤሃለሁ. . .›› እያሉ በጩኸት አካባቢውን አደበላለቁት፡፡ ይኼኔ የደንብ ልብስ የለበሱ ሁለት የጥበቃ ሠራተኞች አጠገባችን ደረሱ፡፡

ለጥበቃ ሠራተኞቹ ካሁን ቀደም እሳቸውና ጎረምሶቹ ያደረሱብኝን ድብደባና ዝርፊያ አስረድቼ ወደ ሕግ እንዲወስዱን ስነግራቸው፣ ሰውየው ከነጠላ ጋቢያቸው ሥር ያንጠለጠሉትን ከቆዳ ከተሠራ ቦርሳ የፀሎት መጽሐፋቸውን በማውጣት፣ ‹‹እኔ ካህን ነኝ፡፡ የፍልሰታ ፆም ከመግባቱ በፊት ከአምላኬ ጋር በምነጋገርበት ጊዜ፣ ሰይጣን ሊያጠፋኝ ሲመጣ ዝም ትላላችሁ እንዴ?›› ብለው የጥበቃ ሠራተኞቹ ላይ ሲያፈጡ ገረመኝ፡፡ ‹‹እንዲህ ብሎ ቀልድ የለም፡፡ ወደ ሕግ እንሂድ. . .›› ስል ሰውየው መቼ ሊበገሩ? ‹‹እሱ የሰይጣን መልዕክተኛ ነው፡፡ ከእሱ ጋር ብትተባበሩ ትቀሰፋላችሁ. . .›› እያሉ ሲንጨረጨሩ ጥበቃዎቹ ጭራሽ እኔን መታወቂያ አምጣ አሉኝ፡፡ በዚህ መሀል ሚኒባስ መጥቶ ሲቆም ዘራፊው አዛውንት ዘለው ገቡ፡፡ ለጥበቃዎቹ የዘራፊውን አዛውንት ታክሲ ውስጥ መግባት ስነግራቸው ከቁም ነገር አልቆጠሩኝም፡፡ ይልቁንም በመጣሁበት ሁኔታ በሰላም ካልሄድኩ አካባቢውን በመረበሽ እንደሚከሱኝ ሲነግሩኝ እያበድኩ ተለየኋቸው፡፡ ይኼው አንጀቴ እንደተቃጠለ አለሁ፡፡

(ብዙነህ አሥራት፣ ከሾላ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...