Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትዴሞክራሲን ራሱን የሚጠይቁ ጉዳዮች የአገር አጣዳፊ ጉዳዮች አይደሉም

ዴሞክራሲን ራሱን የሚጠይቁ ጉዳዮች የአገር አጣዳፊ ጉዳዮች አይደሉም

ቀን:

በገነት ዓለሙ

አገራችን ውስጥ የተጀመረው ለውጥ ያጋጠመው ዋነኛው ችግር የለውጡን ዋነኛና ተቀዳሚ ጉዳይ ለመለየት አለመቻሉና ይህንንም የጋራ መግባቢያና መገናኛ ለማድረግ አለመታደሉ ነው፡፡ የለውጡ ኃይሎች እንደ ፍጥርጥራቸውና እንደ ፍላጎታቸው መጀመርያ ይኼ ነገር ይፈጽልን ከማለታቸው በፊት፣ ይፈጸሙ የሚባሉት ጥያቄዎችም ጉዳዮችም ራሳቸው በቅድሚያ የሚፈልጉዋቸውን መደላድሎችን የጋራ ሥራቸውና አደራቸው ማድረግ አለባቸው፡፡ ሕግና ሰላምን በማስከበርና ዴሞክራሲን በመገንባት የጋራ ግቢ ውስጥ ሳይገናኙ፣ እዚህ ግቢ ውስጥ ሠፍረው ሳይመክሩና ሳይዘክሩ፣ የድምፅ ብልጫ አግኝቶ ፍላጎትን ውሳኔ ማድረግ የሚያስችል የጨዋታ ሕግና ሥርዓት ሊኖራቸው አይችልም፡፡

በዚህም ምክንያት ዛሬ የኢትዮጵያ አጣዳፊ ጉዳይ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል፣ የክልል አቋምና መብት የሚጠይቁትን ማኅበረሰቦች ጥያቄ መመለስ፣ ወዘተ አይደለም፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ይቆያሉ፣ በቀጠሮ ያድራሉ የሚባልበት ምክንያት ጥያቄዎቹ ራሳቸው ዴሞክራሲን የሚጠይቁ በመሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ አጣዳፊ ጥሪ ጨዋታዎችን የማወዳደር ዓይነት ዝግጅት ይጠይቃል፡፡ የተስተካከለ የሜዳ ዝግጅትን፣ በብቃትና በሥነ ምግባር በታነፁ ሰዎች የተሞላ ተቋማዊ አቅምን፣ ፍትሐዊ የጨዋታ መርሐ ግብርን፣ ነፃና ገለልተኛ ዳኝነትን፣ ለጨዋታው ጀርባ ሰጥተው በሥራ ላይ የማተኮር ንቁነትና ዝግጅት ያላቸው የፀጥታ አስከባሪዎችን፣ አቤቱታዎችን ያለ አድልኦ መርምሮ ትክክለኛ ውሳኔ የሚሰጥ አካልን ይፈልጋል፡፡ የዴሞክራሲ ግንባታም፣ ማለትም ዴሞክራሲን የማደላደል ሥራም ከዚህ ጋር በጣም የሚመሳሰል ሳይንስና ጥበብ አለው፡፡ በዚህ ረገድ መሟላት የሚገባቸውና ዴሞክራሲው ራሱም ብዙዎቹ የሚሻቸው ነገሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገና ከመነሻው ሥራ እንደጀመሩ የገለጿቸው ናቸው፡፡ ከቡድን ቁጥጥር የተላቀቁ ኢወገናዊ ተቋማት ባለቤት መሆን ዋነኛው ነው፡፡

መንግሥታዊ ሥልጣንን ከሕዝብ ሿሚነትና ጠያቂነት ጋር ባዳና እንግዳ ያደረገው፣ መንግሥታዊ አውታራት ከቡድን ታማኝነትና ወገንተኝነት ያልተለቀቁ፣ ይልቁንም በቡድኑ አምሳል ተቀርፀው የተሠሩ በመሆናቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው ገዥ ፓርቲ በሕዝብ ድምፅ የሚወርድበትና የሚወጣበት ሥርዓት ለማቋቋም፣ ብሎም የሕዝብና የመንግሥት መተማመንና ፍቅር እንዲኖር፣ የአገርና የሕዝብ ሰላምና ልማትም ከአደጋ እንዲወጣ ለማድረግ፣ የመንግሥት አውታራት ወገንተኛ ፖለቲከኝነት፣ የፖለቲካ ቡድን ታማኝነትና ተቀፅላነት መቋረጥ አለበት፡፡ አነሰም በዛም እንዲሁ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ኃይሎች በፈቀዱለት መጠን ይህ ተግባር እየተንገራገጨም እየተደናገጠም ቢሆን የማይናቅ ዕርምጃ አድርጓል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱን ሪፎርም የሰኔ 15ቱ የአዲስ አበባ ግድያ ያስደነገጠው ወይም ያስደነገጠን ቢሆንም፣ የምርጫ ቦርድን ሻል ያለ አንፃራዊ የለውጥ ግስጋሴ፣ አጠቃላዩ የምርጫ 2012 መርሐ ግብር፣ ኃላም የሲዳማ ሪፈረንደም ‹‹አዋርድሃለሁ›› እያለ ቢያስፈራራውም፣ መንግሥታዊ አውታራትን ከቡድን ታማኝነት የማፅዳት ሥራ የመንግሥት አጀንዳ ከሆኑ የለውጡን ያህል ቆይቷል፡፡ የሁሉም የለውጥ ኃይሎች የጋራ አደራና ግንዛቤ አልሆነም እንጂ፡፡

አምባገነንነትንና የፓርቲ ወገናዊነትን እንዲያገለግሉ የተቀነባበሩ አውታራት ለሕዝብና ለሕግ ብቻ ታምነው እንዲሠሩ ከማድረጋችን፣ ወይም ይህን ከማረጋገጣችን በፊት ስለምርጫ፣ ስለሪፈረንደም፣ ስለሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ፣ ስለክልላዊ መንግሥታትና አዳዲስ አባላት ልናወራ አንችልም፡፡

በዚህ ምክንያት የለውጥ ኃይሎች የመጀመርያ አብሮ የመሥራት ተልዕኮ ሕግና ሰላምን የማስከበር ዴሞክራሲ የሚፈልጋቸውን የታወቁ አስፈላጊ ሁኔታዎች ማመቻቸት ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ሲሆንና በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ኢሕአዴጎች እርስ በርሳቸውም፣ ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎችም በጠላትነት የመወጋገዝ ፖለቲካን አቋርጠው አብሮ ወደ መሥራት ሲያመሩ፣ የሁሉም ወገኖች ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰላምና ግስጋሴ አስፈላጊነታቸው በግልጽ ይወጣል፡፡ በኅብተሰቡም ውስጥ ተሸጋግሮ የነበረውና የኖረው የጠላትና የወዳጅ ፍረጃ መበተን ጀምራል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተደረደሩት የዴሞክራሲ መብቶች ይበልጥ ተግባራዊ ተጨባጭነት ያገኛሉ፡፡ የብዙኃን ማኅበራት ነፃና ንቁ ሕይወት ያገኛሉ፡፡ የፍትሕ አካላት ያለ አድልኦ ለመሥራት የሚመች ነፃ ደመና ውስጥ መኖር ይጀምራሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች እየፈኩ ሲመጡ ከፖለቲካ ወገናዊነት ነፃ/ገለልተኛ መሆን በሚገባቸው የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የነበረና አሁንም ያለ ወገንተኝነትን ትዝብት ውስጥ ይከታል፡፡ እያጋለጠም ለማረም ያበረታታል፡፡ በፖለቲካ ታማኝነት የመንግሥት ሠራተኛን የማንሳትና የመጣል ዘልማድ ይጋለጣል፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ሊይዙት የሚገባቸውን ባህርይና በሚዲያም ሆነ በሌላ መድረክ ሊያራምዱ የሚችሉትን አቋም፣ ልክና ለከት አንድ ሁለት ብሎ ማስቀመጥ፣ ኧረ በሕግ ማለት ይቻላል፡፡ ይህንን በመሰሉ አደፋፋሪ ሁኔታዎች በመታገዝ ባለው የሕግ አውጪ አካል በኩል የማያፈናፍኑ ሕጎች እንዲቃኑና እንዲታረሙ፣ አዳዲሶችም እንዲወጡ ማድረግ ይመጣል፡፡ ለተከታዩ ምርጫም ሆነ አስፈላጊ ሆኖ ለሚመጣ ውሳኔ ሕዝብ በኢወገንተኝነት ከእስካሁኑ በእጅጉ በጣም የተሻለ ምርጫ አስፈጻሚ ማደራጀት ይቻላል፡፡

የዴሞክራሲ መደላድል ሥራ ገና እንደ መጀመሩ፣ ይልቁንም ገና እንዳለመነካቱ ቢሳካልን ተከታዩ የ2012 የምርጫ ወቅት የፖለቲካ ኃይሎች አብሮ መሥራት ማቋረጫ ሊሆን አይችልም፡፡ የመደላድልና ዴሞክራሲን የማፅናት ሥራው ከዚያም በኋላ የአንድ (ቢያንስ የሁለት) ምርጫ ዘመን ትግግዝን ጠይቃል፡፡ የሚደራጀው ምርጫና ዴሞክራሲያዊ መደላድል ያበጀው የምርጫ ውጤት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ተጨባጭ ገጽታ ምክንያት አንዱ ወገን ሙልጭ የሚቀርበት፣ ሌላው ወገን ሁሉንም አግብስብሶ የሚይዝበት ባለመሆኑ ለዴሞክራሲው መደላድል መዝለቅና መጥለቅ ይረዳል፡፡ ይመቻል፡፡ ከዚህም የተነሳ ምርጫን ተከትሎ የሚመጣው የሁለተኛው ዘመን አብሮ የመሥራት መርሐ ግብር ከላይ እስከ ታች ምክር ቤቶች ድረስ የጠለቀ የሁለት በኩል ተሳትፎ ይኖረዋል፡፡ ገለልተኛ አውታራትን የማደራጀቱና ዴሞክራሲን የማጥለቁ ተግባርም ይበልጥ እየሰፋና እየጠለቀ ከሕዝብ ንቁ ተሳትፎ ጋር ይዘልቃል፡፡ እዚህ ሒደት ውስጥ መግባት የምንችለው የዴሞክራሲ ጅምራችንን በጥያቄና በጫጫታ ጋጋታ እንዲቀጭ ዕድል የማንሰጥ፣ የራስን ፖለቲካ ቅዱስ፣ የሌላውን ሰይጣን፣ የራስን ለውዳሴና ለፅድቅ፣ የሌላውን ለኩነኔ ከሚል ፖለቲካችን ከተቆራረጥንና የጋራ የጨዋታ መድረካችንን/ሕጋችንን ለማቋቋም ቅድሚያ ከሰጠን ብቻ ነው፡፡

ቅድሚያ እንስጠው የምንለው የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራ ጥቅም ቀደም ሲል የጠቀስነው፣ ‹‹የድምፅ ብልጫ አግኝቶ ፍላጎትን ውሳኔ ማድረግ የሚያስችል የጨዋታ ሕግ›› ማደላደሉ ብቻ አይደለም፡፡ አዲስ ባህልንም ያነቃንቃል፡፡

አፋኝ ሕጎች ተቃልለው የብዙኃን ማኅበራት ነፃ እንቅስቃሴ ማግኘታቸው፣ ሕዝብና የፖለቲካ ፓርቲዎች አመኔታ የጣሉባቸው የዴሞክራሲ ተቋማት መጎልመስ፣ ከፓርቲዎች አሽቅድምድምና ከወንበር ትርፍ በበለጠ በሸፍጥና በፍርክስ ያልተጨማለቀ ምርጫ መካሄድ ለዴሞክራሲ ሥር መያዝ ያለው ጠቀሜታ ሰፊ ግንዛቤ ማግኘቱ፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ይልቅ ለእውነት፣ ለሚዛናዊነትና ለነባራዊነት ታማኝ የሆኑና በዚህ ምግባር አማካይነት ብልሽቶችንና ጉድለቶችን ከመንግሥት ቤት እስከ ግል ተቋማትና ፓርቲዎች ድረስ እየገላለጡ ለሕዝብ የሚያቀርቡ ሚዲያዎች መፍካታቸው፣ ለአካባቢ ሥልጣንም ሆነ ለፌዴራል ሥልጣን የሚያልሙ ፓርቲዎች በዴሞክራሲው ሜዳ ውስጥ የመግባታቸውም ሆነ በሜዳው ውስጥ ሕጋዊ ሆነው የመቆየታቸው፣ አንጓላይ ባለመሆናቸውና በድርጅታዊ አኗኗራቸው ዴሞክራሲያዊነት መሥፈኑ፣ ፓርቲዎች ብጤ ለብጤ እየተሳሳቡ ማን ምን እንደሆነ ሕዝብ ሊያውቅ በሚችልበት ደረጃ ቁጥራቸው መቃለሉ፣ ፓርቲዎች ምን እየሠሩ እንደሆነ በየጊዜው ማወቅ የሕዝብ መብት መሆኑ አለመዘንጋቱና ከአሁን ጀምሮ አጫፋሪም አዋዳቂም ባልሆነ ጋዜጠኝነት መበራየታቸው፣ እነዚህ ሁሉ የሕዝብ ጥቅምን ያስተዋሉ ሥራዎች የሕዝብን ስሜት እያሞቁ ቅንነትና ትጋቱን እያፋፉ አዲስ የሥራ ባህልን ይጠቅማሉ፡፡

ሕግንና ሰላምን የማስበርና ዴሞክራሲን የመገንባት አጣዳፊና ተቀዳሚ ሥራችንን የሚያደናቅፉት ሰላምና ዴሞክራሲን ራሱን የሚጠይቁ ጥያቆዎችና ተግባራት አጨናጋፊ እየሆኑ ማስቸገራቸው ብቻ አይደለም፡፡ ለዴሞክራሲ ድል ግድና ተቀዳሚ ከሆኑ ማሻሻያዎች በስተቀር ብዙ የሚያወዛግበውን አጠቃላይ የሕገ መንግሥት፣ የፌዴራል አካባቢዎች አወቃቀር ክለሳ ጉዳዮች ሌሎች አዘላለቃችንን የሚወስኑ አደጋዎች እስኪመክኑ ድረስ በቀጠሮ መቆየት አለባቸው ማለትን አልሰማም፣ አላሰማምም ማለትን ያመጣም ችግር አለብን፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ሌላው የህልውና ጥያቄ ሆኖ ቀርቧል፡፡  

የኢትዮጵያ የዛሬው ሌላው ትልቁ የህልውና ጥያቄ፣  አስፈላጊ ግን አወዛጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ወጣቶች በትዕግሥትና ባለመማረር የመከራከር፣ የመወያየትና የመቀራረብ ልምምድ አለማድረጋቸው እንዲያውም የሌላቸው መሆኑ፣ የአገራቸውን ጣጣዎችና ፈተናዎች ለመወጣት አለመሰናዳት (ሲከፋም የጥፋት ማገዶ ለመሆን ተመቻችቶ መጠበቅ) ነው፡፡ ይህ ትልቅ የአገር ክስረት ነው፡፡

ወጣቶች ልዩ ልዩ ተግባራት የያዙ ታላቅ ግዳጅ አለባቸው፡፡ የመጀመርያው ተግባር በኩርፊያ፣ በመራራ ስሜትና በጥላቻ መሞላት ለፀብ ደጋሾች መጫወቻነትና ለእርስ በርስ መተላለቅ የሚዳርገን መሆኑን ከልብ መቀበል ነው፡፡ ሁለተኛው ተግባር አጎብሮ፣ ደርቆ፣ ድርቅ ብሎ ከመተያየት እየወጣን አንድ ዓይነት ሐሳብ ላይ ስለመድረስ ሳንጨነቅ ተከባብሮ የተለያየ ሐሳብ መለዋወጥን በመለማመድ፣ የገረሩ ስሜቶችን መበተንና እንዳይጠራቀሙ መከላከል ነው፡፡ ሦስተኛው ለየትኛውም ጥቃትና በደል አጫፋሪና መሣሪያ አለመሆን ነው፡፡

እነዚህ ሁሉ የሚፈልጉት ራስን ማሳመንና ትንሽ ወኔ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የገረሩ ስሜቶችን የሚፈጥሩና የሚቀሰቅሱ ንግግሮችና ድርጊቶችን  ባጋጠሙን ቦታና ጊዜ ሁሉ ያለ ወገናዊነት መቃወም፣ በተለይ በውይይትና በስብሰባዎች ጊዜ በሕጋዊ ፓርቲዎች ላይ ‹‹የአገር ጠላት››፣ ‹‹ከሃዲዎች››፣ ‹‹ኢትዮጵያዊነታቸው የሚያጠራጥር››፣ ‹‹ፀረ ሕዝብ››፣ ‹‹የዜሮ ድምር ፖለቲከኞች››፣ ‹‹አዲስ  ተረኞች››፣ ‹‹ባለ ጊዜዎች›› የሚሉ ብከላዎችና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ ቅስቀሳዎች ከየትም አቅጣጫ ሲወረወሩ በቅዋሜ ማሳፈር፣ የትኛውንም ፓርቲ ሕዝቦችን ሳያላትም መብቶችን ወደ ማሟላት በመውሰድ ዕርባናውን መመዘን፣ ኢሕአዴጎችም ሆኑ ተቃዋሚዎች (ሚድያዎቻቸውንም ጭምር) ሰብስቤ ልስበክ ሲሉ በሕዝቦች ውስጥ የተፈጠሩ መሸካከሮችንና ጥላቻዎችን የሚያሟሽሹ ምን የተግባር መርሐ ግብር አላችሁ ብሎ መጠየቅ፣ የፀረ ፍጅት መልዕክት መጀመርያ ነው፡፡ ልፋቱ ትንሽ ውጤቱ ግን በጣም ከፍተኛ!!

መጨራረስን የሚደግሱት የዚህ ዓይነቶቹ የአመለካከትና የስሜት ለውጦች (ጉዳቶች) ናቸው፡፡ እናም አደገኛነታቸውን ላለመዘንጋት በህሊና ውስጥ የ‹‹ተጠንቀቅ!›› ምልክት መትከልና ዕውናዊና ህሊናዊ ብልሽቶችን ለመቀየር መጣጣር፣ የገዛ ህሊናን ከመሞገት አንስቶ በባልንጀራነትና በሌሎች ማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ ለስብጥር፣ ለዥጉርጉርነት ቦታ መስጠት፣ በአጠቃላይ ተከፋፍሎ ለመጠቃቃትና ለመባላት የሚያመቹ ጎዳናዎችን እየሸሹ የሚያስተጋግዙ ጎዳናዎችን መጥረግ፣ የመባላት አደጋን ለማራቅ እጅግ የሚበጁ የኑሮ ዘይቤዎች ናቸው፡፡

ያለኔ ሐሳብ፣ ያለኔ መሪነት፣ ያለኔ ሥልጣን ባይነት በኃይለ ሥላሴ፣ በደርግና በኢሕአዴግ ዘመን በሌሎች አገሮችም እንደታየው የአምባገነንነት መሰንቆ ነው፡፡ ለዚህ መሰንቆ መማረክ ማለት ዕጣን ከብቸኛ ሐሳብና ገዥነት ጋር አጣብቆ ማየትና ለፈላጭ ቆራጭነት እጅ መስጠት ነው፡፡ በአማራጭ የለሽ ሐሳብ ውስጥ መኖር ራሱ ባርነት ነው፣ እስረኝነት ነው፡፡ ሐሳቦችን ብቻ ሳይሆን የሐሳብ ነፃነትን ይነጥቃል፡፡ የአዕምሮ ጠያቂነትን ይሰልባል፡፡ በዝምታና በአጨብጫቢነት ሰብዕናን ያስጨርሳል፡፡

በሐሳብ ብዙነት ውስጥ መኖር ግን ወዲህና ወዲያ ያፈናፍናል፣ ነፃነት ነው፡፡ የማንኛችንም ሐሳብ እንዲወጣና ከሌሎች ጋር እየተመዛዘነ እንዲኖር ይፈቅዳል፡፡ የሐሳቦች መመዛዘን አዕምሮን ያሠራል፣ ያበለፅጋል፡፡ ለሐሳብ ብዙነት ደጋፊ ማብዛት፣ በአጠባ የታሰሩ አዕምሮዎችን ብዛት መቀነስ፣ ነፃነትን ማቅረብ የአምባገነንነትን ቅጠል መመልመል ነው፡፡

ይህንን ማካሄድ ማለት ብዙ ሐሳብ በሚንሸራሸርበት ሁኔታ ውስጥ መኖር ያዋጣናል እያሉ መስበክ ሳይሆን፣ ፈላጭ ቆራጮች ከሚወዱት ፀበኝነት፣ ኩርፊያና መፈራራት ወጥተን መነጋገር እንጀምር፣ አንዳችን ሌላችንን ለማጥመቅ ሳንከጅል ከአቋማችን ውስጥ የሚያስማማንን እንፈልግ፣ የሚያስማማንን በማጥበቅና ልዩነታችንን በማክበር መቀራረብን እናበራክት ማለት ነው፡፡

ወጣቱ በግልፍታ ብሔረሰብ ነክ አምባጓሮ እያስነሳ ከመከታከትና ማዶ ለማዶ ከመተያየት እየወጣ ወደ ሥልጡን ውይይት መጣ ማለት፣ ቀስት በጭፍን እያስወነጨፉ ራስን ከመጉዳት፣ ታፍኖ መገዛትን ከማጠንከር እየወጣ ዒላማ ላይ አነጣጥሮ ቀስት ማስፈንጠር ጀመረ ማለት ነው፡፡ የወንዜ ልጅ፣ የብሔር/የፓርቲ ወገኔ ሳይሉ ማንኛውንም በደልና አድልኦ መቃወም ሥር የያዘ መተሳሰብንና መተማመንን ይገነባል፡፡ የብሔር መብትን የመፍራትና ከግል መብት ጋር የማቃረን አስተሳሰብ ውኃ ውስጥ የገባ ጨው የሚሆነውም፣ የዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲገጥመው ነው፡፡ የጥላቻና የጥርጣሬ ወጥመዶች ተሰብረው የዚህ ዓይነት መቀራረብ ተፈጠረ ማለት፣ የዴሞክራሲ ጀንበር ጮራዋ በኢትዮጵያ ምድር ላይ መፈንጠቅ ጀመረ፣ የዴሞክራሲ ትግል ትልቅ ጉልበት አገኘ፣ በቅጥፈትና በአብሽቅ ፕሮፓጋንዳ ሕዝብን መዳፈር ውድቀትን ማነፍነፍ ሆነ፣ አንዱን ከአንዱ አጋጭቶ አምባገነንነትን የማጠናከር ቀዳዳ ተዘጋ ማለት ነው፡፡

እየተቀባበልን ደጋግመን ብለነዋል፣ ዛሬም አስፈላጊ ነውና እንደግመዋለን፡፡ በዕድሜ ሸምግሎ በህሊና ወጣት መሆን እንደሚቻል ሁሉ፣ በዕድሜ ወጣት ሆኖም በእርጅና መያዝና መጃጀት ይኖራል፡፡ የህሊናን እርጅናና ወጣትነት የሚወስነው ከእውነታ ጋር ያለው መቀረረብና መራራቅ ነው፡፡ ህሊና ከተጨባጭ ኑሮ ጋር የሚገናኝበት ገመድ ሲበጠስ ወይም ሲስተጓጎል ሐሳቦች ይሸብታሉ፡፡ ልቅምቃሚ ወሬ በማባዘት ኑሮ ውስጥ መዋጥና የተወራውን ሁሉ ሳይመርጡ/ሳይፈለፍሉ እያስገቡ ራስን መጎሰር ማርጀት ነው፡፡ እንዲህ ያለ እርጅና ውስጥ የገቡ ወጣቶች እንዳሉ ሁሉ፣ የጋራ መግባቢያ የቸገረው የኢትዮጵያ ታሪክ ጉዳይ አሳስቧቸው መጻሕፍት እየተዋዋሱና ተጋግዘው እየገዙ በማንበብና በመወያየት ታሪክን የሚያጠኑ አንዳንድ የባልንጀራ ቡድኖች ብቅ ብቅ ማለታቸው ይሰማል፡፡ ይህ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ጅምር ነው፡፡ የተስፋው አስኳል ያለው ግን ተመሳሳይ ሐሳብና አመለካከትን ማውራት ላይ ሳይሆን፣ የተለያዩ እንዲያውም የተቃራኑ ግንዛቤዎችንና ትርጓሜዎችን እየተደማመጡ ለመለዋወጥ መቻል ላይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ዱሮም ለነበሩም አዲስ ለሚጀመሩም የጥናት ስብስቦች፣ የባልንጀራ ቡደኖች የሚጠቅሙ ጥቂት ነጥቦችን እናካፍል፡፡

ነትበው የሚንቀዋለሉ ሐሳቦችን፣ የየትኛውንም ፓርቲ ቲፎዞነት፣ የፍጥጫ አቋሞችን፣ የሾኬ ውይይት ሥልቶችን ሁሉ ወደ ጎን ብሎ በክፍት አዕምሮና በአዲስ ሙሽት ነገሮችን በማስረጃ እየመዘኑ ለመቀበል መዘጋጀት፡፡

ውይይቶች ያለቀለት ነገርና ሙሉ መግባባት ላይ የመድረስ የቅርብ ውጤት እንደማይኖራቸው አስቀድሞ መግባባት፡፡

በጥናትም ሆነ በውይይት ጊዜ በብዙ መጽሐፍት ላይ ሠፍሮ መገኘትን፣ ተደጋግሞ በመገናኛ ዘዴዎች መነገርን፣ ብዙ መወደስን የእውነተኛነት ማረጋገጫ አድርጎ በመውሰድ ላለመታለል መጠንቀቅ፡፡

የታሪክ ሰውን፣ የታሪክ ሐተታንም ሆነ ትርጓሜን ስለወደድነው ብቻ የሌለ ማስረጃ ሁሉ እየደረደሩ ሽንጥ ገትሮ ጥብቅና በመቆም ድክመት ላለመጠመድ ዘወትር መጣጣር፡፡

የተረዱትንና ያስተዋሉትን ሳይሰስቱ ቅድሚያ የማጋራትና ለውይይት መነሻ የመሆን ቅንነትን መልመድ፡፡ ራስን ደብቆ አንተ ምን ትላለህ በማለት ሌላውን ካናዘዙ በኋላ፣ ሐሳብ ዘርፎ እኔም የምለው ይህንን ነው ከሚል አጭበርባሪነት መራቅ፡፡ የተናጋሪው ሐሳብ አሳምኖን ፊት የነበረንን ሐሳብ ካስለወጠን ስለትዝብት ሳይጨነቁ እውነቱን መግለጽ፡፡

ውይይትንና ክርክርን አስፋፍቶ ለማስኬድ የመረጃ እጥረት ሲያጋጥም በመላ ከመናወዝ ይልቅ፣ የተሻለ የመረጃ ዝግጀት አድርጎ በሌላ ጊዜ ወደ ርዕሰ ጉዳዩ መመለስ፡፡

በውይይት ጊዜ አዋቂነትን ለማሳየት የመሞከር ግብዝነትን፣ እኔ ብቻ ላውራ የማለትን፣ ጋል ጋል የማለትን፣ ባልንጀራን አጣድፎ መሳቂያ የማድረግን ትርፍ የለሽ ፍላጎቶችን መንገድ አለመስጠት፡፡

‹‹ይህማ አለማወቅ ነው፣ ታሪክን/አገርን መካድ ነው፣ ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው›› የሚሉ ችኩልና መግባባትን የሚያደናቅፉ ድምዳሜዎችን መራቅ፣ ሲከሰቱም መገሰጽ፡፡

ከውይይት በኋላ ምን ያህል ለራሴ ሀቀኛና ሚዛናዊ ነበርኩ? ስህተትንና መረታትን መቀበል ምን ያህል ቀሎኝ ነበር? ወዘተ እያሉ ራስን መገምገምና ማረም፡፡

በጥናትና በውይይት ውስጥ አስተማማኝ መረጃዎችና ማስረጃዎች ሊያጥሩ፣ የማውጠንጠን አቅም ሊያንስና የተደራጀና የነጠረ ግንዛቤ መፍጠር ሊያቅት ይችላል፡፡ ሁሉም ግን በሒደት ከልምምድና ከመጎልበት ጋር መሟላታችው አይቀርም፡፡ ትልቁ ነገር፣ ዓብይ ውዝግቦችን ለመፍታት የሚያስፈልገው ተደማምጦ የመነጋገር ልምምድ መቀራረብን፣ መተማመንን፣ መግባባትን በሚያሳድግ አቅጣጫ መጀመሩ ነው፡፡

ዴሞክራሲና ሥነ ምግባር በክፍል ትምህርት ከመጽሐፍና ከአስተማሪ አፍ እየተሰማና በደብተር እየተጻፈ በማጥናትና ለፈተና ተቀምጦ ጥያቄ በመመለስ አይማሩትም፡፡ ዴሞክራሲና ሥነ ምግባርን መማር የሚዋጣልን ስንኖረው ነው፡፡ ተደማምጦ መነጋገርን ሐሳብ መለዋወጥን፣ የተለያዩ ሐሳቦችን አፈላልጎና አሰባስቦ ማገናዘብን፣ ከተቃራኒዎች ውስጥ ዝምድናን ማንጠርን፣ ልዩነት ማክበርን፣ በአቋም ከሚለየን ሰው መጎዳኘትን ስንኖር ዴሞክራሲን መኖራችን ነው፡፡ በይስሙላ ክዋኔ ምላስ ማሥላት ዴሞክራሲን እየኖርን መሆናችንን አያሳይም፡፡ የዘፈን አዝማችን በጭብጨባ እየተቀበሉ እሽክም ከማለት የማይለየው ፕሮፓጋንዳዊ የውይይት ተውኔት አብነቱ ለዴሞክራሲ ሳይሆን ለአድርባይነት ነው፡፡ ዴሞክራሲን በመኖር ውስጥ ስሜትም፣ ርዕሰ ጉዳዮችም የአንጀት የመሆናቸው ነገር ትልቅ ትርጉም አለው፡፡

በመጨረሻም በፈለገው ፌዴራላዊ አወቃቀር ኢትዮጵያ ትደራጅ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ምድር ሁሉ የመላ ሕዝቦች ነው፡፡ የየትኛውም ማኅበረሰብ አባላት ከተከማቹበት ሥፍራ ውጪ ባለ ሥፍራ በእኩል የአገር ልጅነት የመታየት (ያለ ባይተዋርነት የመኖር፣ የመሥራት፣ ንብረት የማፍራት፣ የመምረጥና የመመረጥ) መብት አላቸው፡፡ የትኛውም ማኅበረሰብ ከተከማቸበት ሥፍራ ውጪ ባሉ የኢትዮጵያ ሥፍራዎችና የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ጥቅል የባለቤትነት መብት አለው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ ኢትዮጵያዊን ያለ ቦታህ መጣህ፣ ውጣ ማለት በዋዛ የማይታለፍ/ የሚያስደነግጥ ቅሌት ሊሆን ይገባል፡፡ ለኢትዮጵያ እውነታ የሚስማማው አመለካከት ይህንን መሳይ ነው፡፡ ይህ አመለካከት በሰላም ያኗኑራል፡፡ ከዚህ ያነሰ አመለካከት ያናጫል፡፡ ከዚህ የተጣላ አቋም ሕግና ሰላም የማስከበር፣ ዴሞክራሲ የመገንባት ዋና የመሸጋገሪያ ግዳጃችንን ያጨናግፍብናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...