ፀደቀ አባተ (ዶ/ር) የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማትን በመምራት ረገድ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ የግብርና ባለሙያ ናቸው፡፡ በውጭ ከ20 ባላነሱ አገሮች የግብርና ዘርፍ የሚከታተል ዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን በመምራት ለረዥም ጊዜ አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያም ለበርካታ ዓመታት በከፍተኛ የምርምር ሳይንቲስትና ኃላፊ በመሆን በመስኩ የካበተ የአመራር ልምድ ነበራቸው፡፡ በግብርናው መስክ እስከ ላይኛው የትምህርት ዕርከን በመማር በካናዳ ቫንኩቨር ሳይመን ፍሬዠር ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ ወይም የፒኤችዲ ዲግሪያቸው ያገኙት ፀደቀ (ዶ/ር)፣ የመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአሜሪካው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፍሎሪዳ፣ ጌይንስቪይል አግኝተዋል፡፡ ለዓመታት የካበተው የግብርና ዕውቀታቸውና የአመራር ክህሎታቸው ብቻም ሳይሆን፣ በተመራማሪነትም በአገር ውስጥና በውጭ ብዙ ልምድ አካብተዋል፡፡ በአፍሪካ፣ በእስያና በመካከለኛው ምሥራቅ ከረዥም ጊዜ የተመራማሪነትና የአመራርነት ሚናቸው በተጓዳኝ፣ በበርካታ ዓለም አቀፍ የሳይንስ ጆርናሎችም በርካታ ጽሑፎችን አሳትመዋል፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህም ሙሉ ጊዜያቸውን በኢትዮጵያ ግብርና ላይ በማዋል ጥናትና ምርምር እያካሔዱ ሲሆን፣ በዘርፉ መሻሻል ስለሚገባቸውና ቢወሰዱ ለውጥ ሊያስገኙ የሚችሉ የመፍትሄ ዕርምጃዎችን የሚያመላክት መጽሐፍ እያዘጋጁ ነው፡፡ በግብርናው መስክ የቀደመውንና የአሁኑን፣ እንዲሁም የወደፊቱን አቅጣጫ በማስመልከት ከሪፖርተር ጋር ያደረጉትን ቆይታ ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ግብርና በአሁኑ ወቅት ስለሚገኝበት ሁኔታ ቢያብራሩልን?
ፀደቀ (ዶ/ር)፡–የኢትዮጵያን ግብርና በሶሺዮ ኢኮኖሚያዊ ይዘቱ ካየነው፣ ለአገሪቱ ሁለመናዋ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ለምግብ ዋስትናችን፣ ለወጪ ንግድ ገቢ ምንጭነት፣ ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ አቅርቦትና ገቢ ንግድን ለመተካት ስናስብ ዋነኛው መንጠላጠያችን ግብርና ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሁለት ሚሊኒየም በላይ ለሚሆን ጊዜ በእርሻ ሥራ ስትተዳደር የቆየችበት የረዥም ጊዜ ታሪክ አላት፡፡ ይሁንና እስካሁን ድረስ ግብርናው በአብዛኛው በባህላዊነቱ የቆየ፣ አሁንም ድረስ የእጅ ማረሻ ዋናው የእርሻ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ የግብርና ሥነ ምኅዳር ዞኖች ያሏት እንደ መሆኗ በርካታ የዝርያ ዓይነት ያላቸውን ሰብሎች ማብቀል የምትችል፣ ሰፊ የእንስሳት ሀብት ያላት፣ ሰፊ የግብርና መሬት ያላት፣ ሰፊ የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር ውኃ ያላት፣ በሚገባ የተደራጀ የግብርና ምርምር ሥርዓት ያላትና በተለይ በርካታ የወጣት ኃይል ስብስብ ያለበት የሕዝብ ብዛት ያፈራች፣ በውጭና በአገር ውስጥ ያሉ ዕውቀቱና ክህሎቱ ያላቸው ባለሙያዎችንም ያፈራች አገር ስለሆነች፣ እነዚህ ሀብቶቿ በሚገባ ቢቀናጁ ለአገር ልማትና ለውጥ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ይህ ሁሉ ባለበት አገር ውስጥ ግን የምግብ ዘይት፣ ስንዴ፣ ስኳር፣ የምግብ ማብሰያ ምርቶች፣ ሩዝና ሌሎች ሰብሎች ታክለውበት የሁለት ቢሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው የግብርና ምርቶች በየዓመቱ ከውጭ ይገባሉ፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ በመላክ ከግብርና ውጤቶች የምታገኘው ገቢም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 3.6 ቢሊዮን ዶላር ይገኝ የነበረው በ2016 ወደ 2.2 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ በማለቱ፣ ወደ 40 በመቶ በሚጠጋ መጠን ቀንሷል፡፡ የግብርናው ዘርፍ የወጪ ንግድ አፈጻጸም መቀነስ ከምርትና ምርታማነት መቀነስ ብሎም በዓለም ገበያ ከሚታያው የግብርና ሸቀጦች ዋጋ ተለዋዋጭነት ጋር ይያያዛል፡፡
ሪፖርተር፡– በኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ከምግብ ምርት መጠን በላይ እያደገ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ይህም ከፍተኛ አለመጣጣም በማስከተል የምግብ አቅርቦቱ ዕድገት ከፍላጎቱ አኳያ ሊመመጣጠን እንዳልቻለ ያሳያል፡፡ ኢኮኖሚው ላይ ጫናውን እያበረታ በመጣው የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው? ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ፀደቀ (ዶ/ር)፡- በጣም ትክክል ነው፡፡ ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ የሚገኝ የሕዝብ ቁጥር አላት፡፡ በከተሞች አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ ቁጥርም በገጠር አካባቢ ከሚኖረው የበለጠ በፍጥነት እያደገ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1950ዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 19 ሚሊዮን ገደማ እንደነበር ይገመታል፡፡ በወቅቱም የከተማ ነዋሪው ሕዝብ ብዛት አምስት በመቶ ብቻ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለይ በዚህ ዓመት የሕዝቡ ብዛት 110 ሚሊዮን እንደደረሰና 21 በመቶው ሕዝብም በከተሞች አካባቢ እንደሚኖር ይታመናል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2050 ሕዝባችን ወደ 191 ሚሊዮን ገደማ እንደሚደርስ፣ ይህም የሰሜኑን የአፍሪካ ክፍል ሳይጨምር ከናይጄሪያና ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመከተል ሦስተኛው ሰፊ የሕዝብ ብዛት የሚኖርባት አገር ኢትዮጵያ እንደምትሆን ያመላክታል፡፡ በዚህን ጊዜ ውስጥ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥርም ወደ 38 በመቶ እንደሚያሻቅብ ይጠበቃል፡፡ የሥነ ሕዝብ ባለሙያ ባልሆንም ይህ በፍጠነት እየጨመረ የመጣው የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ግን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫና እንደሚያሳድር ይሰማኛል፡፡ እዚህ ላይ ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ተገቢውን የምግብ፣ የመጠለያ፣ እንዲሁም እንደ አልባሳት ያሉትን አስፈላጊ አቅርቦቶች ብሎም የትምህርት፣ የጤናና የሥራ ዕድል አሟልተህ የተፈጥሮ ሀብትህን ችግር ውስጥ ሳትከት እንዴት ነው ይህን ሁሉ ማቅረብ የሚቻለው የሚለው ነው፡፡ በፍጥነት እያደገ የመጣው የሕዝብ ቁጥር የገጠር የግብርና መሬት ይዞታዎችን በየጊዜው እያጠበበ በመምጣት ጫናውን ማሳየት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ትልልቆችም ሆኑ አነስተኛ ከተሞች በሕዝብ ብዛት ተጨናንቀዋል፡፡ እያደገ የመጣው የምግብ ዋጋና የኑሮ ውድነትም እየተወነጨፈ የመጣው የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ያስከተላቸው ጫናዎች ናቸው፡፡ ምንም እንኳ እንዲህ በፍጥነት እያደገ ለሚገኘው የሕዝብ ቁጥር ተገቢውን የምግብ፣ የመጠለያና የሌሎችም መሠረታዊ ፍላጎቹን ማሟላቱ ከፍተኛ ጫና ቢኖረውም፣ ፖሊሲ አውጪዎች ግን የሕዝቡን ብዛት ወደ ሠለጠነ የሥራ ኃይል ምንጭነት በመቀየር ለዘመናዊ ግብርና መስፋፋት፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ብልፅግና ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ብርቱ ሕዝብ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡
ሪፖርተር፡– በሌላው ዓለም እጅግ የተራቀቁ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ሥራ ላይ ቢውሉም፣ ኢትዮጵያ ግን አሁንም ጥንታዊ የእርሻ መሣሪያዎችን እየተጠቀመች ነው፡፡ ይህንን እውነታ እንዴት ነው ወደ ዘመናዊ ግብርና ኢኮኖሚ መቀየር የሚቻለው?
ፀደቀ (ዶ/ር)፡– የኢትዮጵያን ግብርና ዘርፍ ለመቀየር የመገልገያ መሣሪዎቹን ከመቀየር በላይ ትልቅ ሥራ የሚጠይቅ ነው፡፡ የአገሪቱ የግብርና ሥርዓት ፈርጀ ብዙና ውስብስብ በመሆኑ ፖሊሲ አውጪዎቹ የሚገጥማቸውን ፈተና ለመወጣትና ውስብስቡን ችግር ለማስተካከል፣ በቅድሚያ የግብርናውን ዘርፍ በጥልቀት ሊያውቁትና ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ምን ማድረግ እንደምንፈልግ የጠራና ግልጽ ግንዛቤ ሊኖረንና ትርጉም ያለውን ትራንስፎርሜሽን እንዴት እንደምናመጣ በሚገባ ማወቅ አለብን፡፡ ከመነሻው የጠራ፣ ግልጽ ዓላማ ሊኖረን ይገባል፡፡ ካለፉት አሠርት ዓመታት ወዲህ ወይም ከዚያም በላይ በዚህ አገር ውስጥ ስለትራንስፎርሜሽን ብዙ ሲወራ ቆይቷል፡፡ ብዙ ይባላል፡፡ አንዳንዴ ትራንስፎርሜሽን ማለት ለአንዳንዶች የተለየ ነገር ማለት ይሆን እንዴ እያልኩ እገረማለሁ፡፡ ተቋማትን በማደራጀትና መልሶ በመገንባት ላይ ብዙ ጥረትና ጉልበት አፍስሰናል፡፡ ችግሬ ተቋማቱ መልሰው መላልሰው በመዋቀራቸው ላይ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ይህንን የምናደርገበት በቂ ምክንያትና ማረጋገጫ ያስፈልገናል፡፡ ይልቁንም የችግሩን ሥረ መሠረት መለየትና ማስተካከሉ ተቋማትን ለማሸጋሸግና ዳግም ለመፐወዝ፣ አንዱን ተቋም ወደ ሌላ ድርጅትነት ለመቀየር የምንዋከብበትን ሩጫ ይቀንስልናል፡፡ ‹‹ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥ›› ነው ከእነ አባባሉ፡፡ መንግሥት የኢትዮጵያን ግብርና ለመለወጥ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አማካይነት ብዙ ሞክሯል፡፡ ያሰበውን ያህል ግን ግቡን አልመታለትም፡፡ ምናልባትም ሁሉን አቀፍና ተመጋጋቢ የአካዴሚ ጥናቶች አግዘውት ቢሆን ኖሮ፣ የዕቅዱን ዓላማ ይበልጥ ግልጽ በማድረግና በማጥራት ስኬታማነቱን ማረጋገጥ ይቻል ነበር፡፡ ይልቁንም በአብዛኛው ከላይ ወደታች የወረደና በተለይም የአገር ውስጥ ባለሙያዎችና ምሁራንን ያላሳተፈ ዕቅድ ነበር፡፡ ይህ ባለመደረጉም ዕቅዱን ለማሳካት የሚችልበት አመቺ ዕድል እንዲታጣ ከማድረጉም በላይ፣ በሚገባ ጥቅም ላይ ውሎ ተገቢውን ውጤት ማስገኘት የሚችል ሀብት እንዲባክን ምክንያት ሆኗል፡፡ ወደፊትም በግብርናው ዘርፍ ለሚደረጉ የለውጥ ጥረቶች ፖሊሲ አውጪዎቹ ከእስካሁኑ አካሄድ ጥሩ ትምህርት መቅሰም ይኖርባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደሚታየው የፖለቲካ ሥርዓቱ በፖሊሲ አውጪዎች፣ በግብርና ምሁራንና በሌሎችም ባለድርሻዎች መካከል ምክክር ማድረግ የሚቻልበት በር እየተከፈተ መምጣቱን የሚጠቁሙ ጠንካራ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ ሁሉም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በመቀራረብና ጠንክሮ በመሥራት ሌላ ዕድል እንዲያመጣልን ማድረግ አለባቸው፡፡
ሪፖርተር፡– የሜካናይዜሽን እርሻን ወደ ታችኛው ገበሬ በማውረድ በአነስተኛ ማሳ ይዞታ ደረጃ መተግበር የሚቻልበት መንገድ እስከምን ድረስ አዋጭና የሚያስኬድ አሠራር ነው?
ፀደቀ (ዶ/ር)፡- ሜካናይዜሽን ለግብርና ለውጥ በጣም ጠቃሚ ከሚባሉ ክፍሎች አንዱ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ግን ለውጥ በአንድ ጀንበር እንደማይመጣ ነው፡፡ ይህም ማለት አነስተኛ ግብርና ወደፊትም ለተወሰነ ጊዜ አብሮን እንደሚቆይ በሚገባ መገንዘብ ነው፡፡ እዚህ ላይ ሜካናይዜሽን ስንል ለአነስተኛ ግብርና ተስማሚ የሆኑ እንደ ተሻሻሉ ማረሻዎች፣ አነስተኛ ጉልበት ያላቸው ትራክተሮች፣ የሰብል መዝሪያዎች፣ የምርት መሰብሰቢያ ማሽኖች፣ መውቂያዎችና ማበጠሪያ ማሽኖችን የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎችን ማለታችን ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ኢትዮጵያ እስከ መቼ ነው በአነስተኛ ገበሬ ጉልበት ላይ ብቻ ጥገኛ የምትሆነው? ገበሬው ለዘመናት በሚችለው አቅሙ ጥሯል፡፡ ምናልባትም እስካሁን ማምረትና መስጠት ከቻለው በላይ ማምረት የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ይሆናል፡፡ በእዚህ ላይ ያለዎት ሐሳብ ምንድነው?
ፀደቀ (ዶ/ር)፡- ይህም ቅድም ባነሳኸው ጥያቄ ላይ ስለትራንስፎርሜሽን ከገለጽኩት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች ሙሉ በሙሉ ጠቀሜታ የሚያስገኙት ተመጣጣኝ ግብዓት በተለይም ማዳበሪያ ሲያገኙ ነው፡፡ እስካሁን በኢትዮጵያ ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ አነስተኛ አርሶ አደሮች የሚቀርብላቸውን ምክረ ሐሳብ ተቀብለው ሙሉ በሙሉ ለመተግበራቸውና ለመጠቀማቸው ማረጋገጫ እንደሌለ ነው፡፡ ይህ በተለይ አነስተኛ የእርሻ ማሳ ያላቸውን ገበሬዎች ያየን እንደሆነ ነው፡፡ ከ50 ዓመታት በላይ ከዘለቀ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ጥረት በኋላም፣ የኢትዮጵያ አነስተኛ ገበሬ አሁንም የሚጠቀመው የማዳበሪያ ብዛት በሳይንሱ ከሚመከረው ከግማሽ በታች ነው፡፡ 42 በመቶ የታረሰ መሬት ብቻ ነው በዘመናዊ ማዳበሪያዎች የሚጠቀመው፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያ የሚጠቀመው ገበሬ 11 በመቶ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ይህም ቢሆን ቁጥሩ በፍጥነት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ምርጥ ዘር፣ ፀረ ተባይና መስኖ የመጠቀም ልምዱ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ፣ አሁን ባለው ሁኔታ አነስተኛ ገበሬውን ብቻ ተጠቅሞ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል ሰብሮ መውጣት የሚቻልበት ዕድል አለ ወይ? የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ይጋብዛል፡፡ በመሆኑም የግብርና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳው ሀቀኛና እውነተኛ የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ ሰፋፊና ለንግድ የሚያመርት ግብርናን ማካተት ወሳኝ ሥራው ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ግን በአንድ ጊዜ አነስተኛ ይዞታ ያለውን ገበሬና ግብርናን እናስቀር ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ለተፋጠነ የግብርና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ብቁ የሆነ ዕቅድ ከወዲሁ ማዘጋጀት እንድንጀምር የሚጠይቅ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ከዚህ ቀደም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ሲተዳደሩ ከነበሩና ፍፃሜያቸው ውድቀት ከሆኑ ሰፋፊ እርሻዎች ተሞክሮ በመነሳት፣ ኢትዮጵያ ምን ማድረግ ይጠበቅባታል?
ፀደቀ (ዶ/ር)፡- ቀደም ብዬ የሰጠሁት ምላሽ ይኼንን ጥያቄ የሚመልስ ይመስለኛል፡፡ ልጨምር የምችለው ነገር ቢኖር፣ አነስተኛ ይዞታ ያለው ግብርና የ21ኛውን ክፍለ ዘመን ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚችልበት አቅሙ እጅግ ደካማና ብቃት እንደሚያጥረው ነው፡፡ በተጨማሪም በዚያን ጊዜ ማለትም እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ መጨረሻና በ1970ዎቹ መጀመርያ ላይ የመጡትን የግል ሰፋፊ እርሻዎች፣ እንዳልተሳኩ ወይም እንደከሸፉ ጅምሮች አልመለከታቸውም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው በወቅቱ የነበሩትን የኮሌጅ ተማሪዎችና ለወደፊቱ ሥራ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎችን ቀልብ መሳብ የቻሉ ነበሩ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቻችን ከነበሩንና ማግኘት ከምንችላቸው ሌሎች ሰፋፊ የትምህርት ዕድሎች ይልቅ ግብርናን የመረጥነው፣ እርሻዎቹን ባስተዋወቁት ስኬታማ የንግድ ሰዎች ውጤት ተነሳስተንና እነሱንም ለመተካት በማሰብ ጭምር ነው፡፡ የሰፋፊ እርሻ ግብርናን ከእንቡጡ ነቅሎ የጣለው፣ በተሳሳተ መንገድ ሶሻሊስታዊ ዕርዮተ ዓለምን መከተል የጀመረው ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ነው፡፡ የመንግሥት እርሻዎችም ለውድቀት የበቁት ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣው ድክመታቸው ይልቅ በአብዛኛው የተጠያቂነት ችግር ስለነበረባቸው ነው፡፡
ሪፖርተር፡– የግብርናው ዘርፍ አሁን ባለው አካሄድ ይቀጥላል ብለን ብናስብ፣ በመጪዎቹ አምስትና አሥር ዓመታት ውስጥ ምን ሊከሰት ይችላል?
ፀደቀ (ዶ/ር)፡- ምን ሊከሰት እንደሚችል ማሰብ ይከብደኛል፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና አሁን ባለው ሁኔታ የሚቀጥልበት ምንም ምክንያት የለውም፡፡ ሳይለወጥ ከቀጠለ ግን አጠቃላይ የሶሺዮ-ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያስከትል አደጋ ይደቅናል ማለት ነው፡፡ ከመነሻው እንዳልኩት ግብርና ለኢትዮጵያ ሁለመናዋ ነው፡፡ የግብርናው ቀውስም የቀውሶች ሁሉ እናት ነው የሚሆነው፡፡ አሁን ያለው የመንግሥት ፖለሲ ለግብርናው ትልቁን ቦታና ቅድሚያ የሚሰጥ በመሆኑ፣ ወደ ትራንስፎርሜሽን የሚወስደንን መንገድ ሳይረፍድብን ከወዲሁ እንድንጀምር ተስፋ ይደረጋል፡፡
ሪፖርተር፡– ግብርናው የአገሪቱ ሕዝብ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደኅንነቱ ምንጭ መሆኑ እየታወቀ፣ በየጊዜው ሥልጣን የጨበጡ መንግሥታት ግን ስኬታማ የግብርና ምርምርም ሆነ የኤክስቴንሽን ሥርዓት በመዘርጋት ለሕዝቡ በቂና ተመጣጣኝ ምግብ እንዲመረት ማድረግ ያልቻሉት በምን ምክንያት ነው? ይህን ማድረግ ለመንግሥታቱ በሥልጣን መቆየት ወሳኝ ከመሆኑም ባሻገር፣ ሕዝቡን መመገብ ያልቻለ መንግሥትም ህልውናው እንደማይቆይ የታወቀ ነው፡፡
ፀደቀ (ዶ/ር)፡- በየጊዜው ወደ ሥልጣን የወጡ የኢትዮጵያ መንግሥታት ግብርናውን የማሻሻል ተነሳሽነት አጥሯቸው እንደማያውቅ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ያለፉት ሦስት የፖለቲካ ሥርዓቶች ማለትም የንጉሠ ነገሥቱ፣ የደርግና የኢሕአዴግ ሥርዓት ሁሉም በተለያየ የስኬት ደረጃና በራሳቸው አካሄድ ግብርናውን ለማሻሻል ሞክረዋል፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ግብርናን በማስተዋወቅ ቀዳሚው ሲሆን፣ በአምቦና በጅማ የግብርና ቴክኒክ ትምህርት ቤቶችን በመመሥረት፣ በማስከተልም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የግብርናና የሜካኒካል ጥበብ ኮሌጅን በአለማያ (የአሁኑ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ) ያቋቋሙት ከ60 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ በማስከተል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ወይም የአሁኑ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እ.ኤ.አ. በ1966 የተመሠረተው በከፊል ከመንግሥት ቁጥጥር ነፃ ሆኖ፣ በአማካሪ ቦርድ የሚመራ ተቋም ሆኖ ነበር፡፡ ወታደራዊው መንግሥትም የጥናትና የልማት ሥራዎችን በማጠናከር፣ ብሎም የግብርና ምርምር ማዕከላትን በማበራከትና በማጠናከር፣ እንዲሁም ንዑስ ማዕከላትን በማስፋፋት በርካታ የግብርና ሥነ ምኅዳሮችን ለመሸፈን ይፈልግ ነበር፡፡ አዴት፣ ፓዌና ሲናና የተሰኙት የግብርና ማዕከላት ለአብነት ከምጠቅሳቸውና ከማስታውሳቸው መካከል የሚመጡልኝ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም በዚህ ወቅት ነበር በግብርናው ምርምር መስክ በሰው ኃይል ራሷን ወደ መቻሉ ደረጃ የደረሰችው፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥትም በነበሩ ዕውቀቶች ላይ በመመርኮዝ ለተጠቃሚው ማለትም ለአነስተኛ ገበሬው የዕውቀቶቹን ውጤቶች ማዳረሱ ላይ መሥራት ጀመረ፡፡ የምርምር ሥርዓቱንም ዳግም በማዋቀር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሥር የነበሩ በርካታ ነባር ማዕከላትንም አዲስ ወደ ተፈጠሩት ወደ ክልሎች ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቶች ማስረከብን ያስከተለ ለውጥ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት 90 ያህል የምርምር ማዕከላትና ንዑስ ማዕከላት በፌደራሉና በክልል ምርምር ኢንስቲትዩቶች፣ በግብርና ኮሌጆችና በዩኒቨርሲቲዮች በኩል እየተመሩ ይተዳደራሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1963 የግብርና ኤክስቴንሽን ኃላፊነት የተሰጠው ለግብርና ሚኒስቴር ነበር፡፡ አካሄዱ ግን በየጊዜው በርካታ ለውጦች ተደርገውበታል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ማዕከላትም በአጋርፋና በአርዳኢታ የተቋቋሙት በደርግ መንግሥት ነበር፡፡ የኤክስቴንሽን ሠራተኞች ቁጥር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት የግብርና ሚኒስቴር ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ ከ67 ሺሕ በላይ የልማት ወኪሎችና በዘርፉ የሠለጠኑ ባለሙያዎች ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ከቀደምት ታሪኮች ጀምሮ እንደሚታየው በየጊዜው የመጡት መንግሥታት የሚችሉትን ያህል ግብርናውን ለማሻሻል ሞክረዋል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ከዚህ ሁሉ ጥረት በኋላ ዘላቂ ስኬት ማግኘት ያልቻለችባቸውን በርካታ ችግሮች ነቅሶ ማውጣት ይቻላል፡፡
በእኔ የግል አስተያየት ግን የፖሊሲ አውጪዎች የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን ምክር ለመስማትም ሆነ የጋራ መግባባትን ለማስፈን ያሳዩ የነበረው ግትርነት ነጥሮ የሚነቀስ ይመስለኛል፡፡ መልካም የሥራ አፈጻጸም ታሪካቸውን፣ ራዕያቸውንና ለሙያ ሥነ ምግባር ተገዥነታቸው በመመልከት እንኳ የራሳቸውን ሰዎች ማመንና መቀበል አልቻሉም፡፡ ምክክርና ተነሳሽነትን በመዝጋት ከላይ ወደታች የሚወርድ አካሄድን መረጡ፡፡ ለአመራርነት የሚሾሙት ኃላፊዎችም በሥራቸው ብቃት፣ ባሳዩት ውጤታነትና በሙያ ሰብዕናቸው መሆኑ እየቀረ መጣ፡፡ የመጨረሻ ውጤቱም የግብርናው መዳከም ብቻ አልነበረም፡፡ አንዱ ማሳያ እ.ኤ.አ. በ2000ዎች መጨረሻ የዘር ብዜት ላይ የተሻሻለ የበቆሎ ዘር በበርካታ ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ለማልማት በታችኛው አዋሽ በአንድ የምርት ዘመን ብቻ ለማምረት የተሞከረበት አካሄድ፣ እንዲሁም ሳይሳካ የቀረው ቅይጥ ማዳበሪያ የማምረት ጅምር በአገሪቱ ላይ በአሥር ቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ኪሳራ ማስከተሉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ውድቀታችን በኋላ በቂ ትምህርት እንዳገኘን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሪፖርተር፡– እርስዎ የአገሪቱ ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪ ቢሆኑ፣ ግብርናውን ለመለወጥ ተቀዳሚ ዒላማዎ የሚያደርጉት ጉዳይ ምንድነው?
ፀደቀ (ዶ/ር)፡- ለውጡን ለማምጣት በርካታ መንገዶች ይኖራሉ፡፡ አንዱን መንገድ ልንገርህ፡፡ በመጀመርያ ዕውቀቱ፣ በሙያ የተፈተነ ልምድ ያላቸውንና በስኬታቸው የተከበሩ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶችን የያዘ ግብረ ኃይል አቋቁማለሁ፡፡ ሐሳቤ ምን እንደሆነ ለማስረዳት ስብሰባ ጠርቼ ለኢትዮጵያ ግብርና የማስፈጸሚያውን ጨምሮ ወሳኝ ዕቅድ እንዲያወጡ አደርጋለሁ፡፡ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወራት የሙሉ ጊዜ ሥራቸው ይኸው እንዲሆን በማድረግ እከታተላለሁ፡፡ ግብረ ኃይሉ እንደ ቢሮ፣ አጋዥ ኃይልና በአገሪቱ መንቀሳቀስ ወደሚፈልጉባቸው አካባቢዎች እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችሉና ሌሎችም አቅርቦቶች በሙሉ እንዲሟሉላቸው አደርጋለሁ፡፡ ግብረ ኃይሉ ወርኃዊ የድርጊት ሪፖርቱን በቀጥታ ለእኔ እንዲያቀርብ አልያም በእኔ ጽሕፈት ቤት ሥር ለተመደበ አካል ሪፖርት እንዲያቀርብ አደርጋለሁ፡፡ ሪፖርቱ እንደተጠናቀቀም፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የግምገማ ዓውደ ጥናት አዘጋጃለሁ፡፡ ይህ ከተከናወነ በኋላ ለጋሾችን በማሰባሰብ ለዕቅዱ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ ኢትዮጵያ ክፍተት ባሉባት መስኮች ዕውቀታቸውን እንዲያጋሩንና ወደፊት ለመራመድ የሚያግዙ የሐሳብ ልውውጦች እንዲፈጠሩ አደርጋለሁ፡፡
ሪፖርተር፡– በግብርናው መስክ በርካታ ተቋማት ተፈጥረዋል፡፡ አብዛኞቹ ግን ረሃብንም ሆነ ድህነትን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት አላስቻሉም፡፡ እዚህ ላይ የፖሊሲ ችግር ያለ ይመስልዎታል?
ፀደቀ (ዶ/ር)፡- እንደማስበው ይኼንንም ጥያቄ ቅድም የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ስኬታማነት ዘላቂ ማድረግ ስላልተቻለበት ጉዳይ ሳብራራ አንስቼዋለሁ፡፡ ተገቢነት ያለውን በሳል አመራር በማትሰጥበት፣ ዕውቀቱና ልምዱ ከተልዕኮው ጋር ባልተገናኘበት ቦታ ላይ ስኬታማነትን መጠበቅ ከባድ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ልምዱና ዕውቀቱ ሳይኖር የሚከናወን ሥራ ራሱኑ ሲደጋግሙ የመኖር፣ ከችግሩ ሥረ መሠረት ይልቅ ምልክቶቹን በማከም ላይ ያነጣጥራል፡፡ የትኛውን መሥሪያ ቤት እያሰብክ እንደሆነ ባላውቅም፣ ለእኔ ግን የግብርና ለውጥን ለማምጣት ኃላፊነቱ ያለበት የትኛውም ተቋም መመዘን ያለበት ምን ያህል ሰዎችንና ተቋማትን ማብቃት እንደቻለና እንዳፈራ፣ በምን አግባብ የአመራርነት ሚናውን እንደተወጣ እንጂ ምን ያህል የምርምር ሙከራ እንዳካሄደና ግኝቶችን እንዳሳተመ በማሳየት መሆን የለበትም፡፡ እንዲያውም ስለስኬታማ ሥራዎች ቢናገሩ የሚያምርባቸው ያበቋቸው ተቋማትና ሰዎች ናቸው፡፡ እርግጥ ስህተት ከሠሩም ይህ ተፈጥሯዊ ስለሆነ ሊፈቀድላቸውና ከስህተታቸው እንዲማሩ ዕድሉ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን በሚሠሩት ሥራ ላይ በራስ መተማመን እንዲያዳብሩና በተጎናፀፉት መልካም ውጤትም ጥሩ ስሜት እንዲያድርባቸው ያስችላቸዋል፡፡ በአጭሩ የለውጥ ወይም የትራንስፎርሜሽን ተቋማት የራሳቸውን አቅም ከመገንባት በላይ፣ የሌሎች ችሎታና አቅም እንዲገነባ የአስቻይነትና የደጋፊነት ሚና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ይህ ሊሆን አልቻለም፡፡
ሪፖርተር፡– አሁን ያለው መንግሥት ግብርናን በማሻሻል ረገድ ተገቢነት ያለው የሙያ ድጋፍና ምክር እያገኘ ነው ይላሉ?
ፀደቀ (ዶ/ር)፡- አሁን ያለውን የመንግሥት አስተዳደር ማን እንደሚያማክረው መረጃው የለኝም፡፡ መረጃው በሌለኝ ጉዳይ ላይ ማውራቱም መልካም አይሆንም፡፡
ሪፖርተር፡– የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ሒደት ውስጥ ሚናው እንዴት ይታያል?
ፀደቀ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ጥሩ ግንኙነት አላት፡፡ በተለይም ከዓለም አቀፉ የግብርና ምርምር የምክክር ቡድን ጋር ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ግንኙነት መሥርታለች፡፡ ዋናው ስኬታቸውም በብርዕ ሰብሎች የዝርያ ማሻሸያ ሥራዎች ላይ የሚሰጡት ድጋፍ ነው፡፡ ተነፃፃሪና ተመጋጋቢ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መንገድ ብሔራዊ ፕሮግራምን ለማሳካት፣ የበለጠ አጋዥ የሚሆን ግንኙነት እንደ አዲስ ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከአገር አቀፍ ተቋማት ጋር የሀብት ሽሚያ ውስጥ በመግባት ለምርምር ውጤቶች ከውጭ የገባውን ዕርዳታ ለማዋል የጠየቁበት ወቅትም ነበር፡፡ አንዱ ተቋም ለሌላው ፍፁም ተመጋጋቢ መሆን እንጂ ተወዳዳሪው መሆን አይበጀውም፡፡ እንዲህ ካሉት ተሞክሮዎቻችንም ትምህርት እንደቀሰምን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ነባሩ አካሄድ በነበረበት መንገድ ሊቀጥል እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተሞክሯቸውን ሊያካፍሉን ይችላሉ፡፡ ሆኖም ዋናው የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ግን መመራት ያለበት በአገራችን ብሔራዊ ፕሮግራም ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገር በቀል መፍትሔዎችን በመጠቀም ዘላቂ ልማቷን ማረጋገጥ እንደሚገባት ማስረገጥ እፈልጋለሁ፡፡
ሪፖርተር፡– ከምታመርተው ይልቅ ጥራጥሬውን፣ የምግብ ዘይቱንና ሌላውንም ዓይነት በርካታ የምግብ ሸቀጥ በገፍ በማስገባት ኢትዮጵያ በተጣራ የገቢ ንግድ ላይ ጥገኛ ሆና ትገኛለች፡፡ ይሁንና መንግሥት ከመጪው ዓመት ጀምሮ ይህንን አካሄድ እንደሚቀይረው አስታውቋል፡፡ ይህ አቋሙ ምን ያህል የሚያስኬድ ነው?
ፀደቀ (ዶ/ር)፡- መንግሥት በምግብ ራስን መቻል ብቻም ሳይሆን ከጊዜ በኋላም ለኢትዮጵያ የ‹‹ምግብ ሉዓላዊነት››ን ማረጋገጥ በሚችልበት መንገድ ላይ ጠንክሮ መሥራቱ የሚበረታታ ነው፡፡ እኔ እንደገባኝ እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት ከመጪው ዓመት ጀምሮ እንደሚንቀሳቀስ እንጂ፣ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ችግሩን እንደሚያስቆመው አይደለም፡፡ በግልጽ እንደሚታወቀው ችግሩን በአንድ ዓመት መቅረፍ አይቻልም፡፡ ሁሉም ችግር በአንድ ጊዜ እንደማይፈታ በማስገንዘብ ሕዝቡ በትዕግሥት እንዲጠባበቅ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ መንግሥትን ምን ይመክራሉ?
ፀደቀ (ዶ/ር)፡- እንደማምነው ይህ ጉዳይ ቅድም ስንነጋገር ቢቋቋም ይበጃል ያልኩት ልዩ ግብረ ኃይል ዋናው ትኩረት ቢሆንም፣ አንዳንድ ጠቋሚ ነጥቦችንም ጨምሬ ማጋራት እፈልጋለሁ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡት በቶሎ ውጤት የሚያስገኙ፣ ያለ ብዙ ዝርዝር ጥናትና ትንተና አፋጣኝ ውጤት ላይ የሚያደርሱት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ አንድ ምሳሌ መጥቀስ ቢያስፈልግ፣ አሁን ያሉትና ተስፋ የሚሰጡ ቴክኖሎጂዎችን በሚገባ መጠቀሙ አማራጭ ነው፡፡ ምርምር ለበርካታ ዓመታት በርካታ ቴክኖሎጂዎችን አውጥቷል፡፡ አንዳንዶቹ በተወሰነ ደረጃ ተግባር ላይ ውለዋል፡፡ ይህንን ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ተስፋ ሰጪ የሆኑትን ቴክኖሎጂዎች በሠርቶ ማሳያና በሌሎችም መንገዶች ዕውቅናና ተቀባይነት እንዲያገኙ በሰፊው መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ይሁንና የምርምር ሥርዓቱ በአሁኑ ወቅት የሚገኝበት ደረጃ የማያስደስት በመሆኑ፣ ይህንንም ማየት ይገባል፡፡ የምርምር ሥርዓቱ እንዲለወጥ ቅንጅትን የማስተባበር ሥራ መነሻ ሊሆን ይገባል፡፡ የምርምር ዘርፉን የሚመራውን አካል በአጣዳፊ ሁኔታ ማጠናከርና ማብቃት ያስፈልጋል፡፡ ሌላው በአሁኑ ወቅት ሰፊው የኢትዮጵያ የግብርና ወጪ ምርት በጥሬው እየተሸጠ በመሆኑ፣ ይኼንን በመቀየር አገሪቱ እሴት በመጨመር ተጠቃሚ የምትሆንበት መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ጥሬ ምርቶችን ከመላክ ይልቅ፣ የተቀነባበሩ ወይም በከፊል የዘተጋጁ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ እንዲልኩ የሚያነሳሱ መመርያዎችና አሠራሮች መዘርጋት አለባቸው፡፡ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ እዚሁ ተዘጋጅተው ሙሉ በሙሉና በከፊል ያለቀላቸው የቆዳ ውጤቶችንና የፍየል ሥጋ ወደ ውጭ መላክ የተቻለባቸው መልካም ተሞክሮች ስላሉ ከእነሱ መማር ይቻላል፡፡
በመካከለኛ ጊዜ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ጉዳይ አገር በቀል ሰብሎችን ያላቸውን ያልተነካ አቅም በሚገባ መጠቀም መቻል ላይ ነው፡፡ ለዓመታት የምግብ ዋስትናችንን በብርዕና በአገዳ ምርቶች ላይ ጥገኛ በማድረጋችን፣ ሌሎች ምርቶችን ማስፋፋቱ ብዙም ግድ አልሰጠንም ነበር፡፡ ሌሎች አገሮች ግን ለኢኮኖሚም ሆነ ለአካባቢ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ አማራጭ የሰብል ምርቶችን አበራክተዋል፡፡ በሰፊው ጥቅም ላይ ያልዋሉ አገር በቀል ሰብሎችን ከመጠቀም አኳያ፣ ለአብነት እንሰት እስካሁን ተስፋፍቶ ከሚገኝበት ከደቡብና ከመካከለኛው ኢትዮጵያ ባሻገር ወደ ሌሎች ተመሳሳይ የግብርና ሥነ ምኅዳር ወዳላቸው አካባቢዎች ማስፋፋት ለምግብ ዋስትና ብቻም ሳይሆን ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለቡና ምርታማነት መሻሻል፣ በተለይም በተፈጥሮው የካፌን ይዘቱ የቀነሰ (ዲካፊኔትድ ኮፊ) ቡና ለማምረትና ለገበያ ለማቅረብ፣ ብሎም የወጪ ንግድ ገቢያችንን ለማሻሻል፣ የተለምዶውን የቅባት እህሎች ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል ለምሳሌ እንደ ጎመን ዘርና እንደ ሱፍ ያሉት ተሻሽለው ቢመረቱ ከውጭ የሚገባውን ምርት በመተካትና ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችም የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ምንጭ በመሆን ትልቅ ድርሻ ያበረክታሉ፡፡ እዚህ ላይ ማከል የምፈልገው ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለአገር በቀል ሰብሎች ትኩረት ይሰጥ ሲባል፣ እንደ አኩሪ አተር ያሉትንና ያልተለመዱ የቅባት እህል ሰብሎችን ለማጣጣል ወይም ገሸሽ ለማድረግ ግን አይደለም፡፡
በረዥም ጊዜ በምንሠራቸው ሥራዎች ላይ አዳዲስ አቅጣጫዎችን ለመፍጠር ማሰብ መጀመር ይጠበቅብናል፡፡ አነስተኛ ገበሬዎች በመካከለኛና በከፍታማ አካባቢዎች የቻሉትን በማምረት አሁን ደርሰዋል፡፡ አሁን ላይ ባላቸው አቅምና ዕውቀት የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፣ ሠርተዋል፡፡ ያልታረሱ አዳዲስ መሬቶች ማስፋፋትም ለእነዚህ ገበሬዎች ከዚህ ቀደም እንደነበረው አማራጭ መንገድ መሆኑ አብቅቷል፡፡ የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር ውኃን በመጠቀም ሰፈፊ የመስኖ እርሻ ሥርዓትን በመዘርጋት፣ ትርፍ ምርት ብሎም በአንድ ምርት ዘመን የምናገኘውን ውጤት በብዙ መጠን ለመጨመር የሚያስችለን በመሆኑ ይህንን ዘርፍ ማጎልበት አለብን፡፡ የግብርና ልማት ፖሊሲያችንን መለስ ብለን ማየት ይጠበቅብናል፡፡ አሁንም በአነስተኛ ግብርና ላይ ትኩረታችንን በማድረግ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ችግሮች እንቀርፋለን ወይ? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ በዚያው ልክ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እንዴት እንጠቀማለን? የአካባቢ ጉዳትን እንዴት እንከላከላለን? እየቀነሰ የመጣውን የአፈር ለምነት እንዴት እናሻሽላለን? እንዲሁም የነባርና የመጤ ነፍሳትን ወረርሽኝ እንዴት እንቋቋማለን? የሚሉት ጉዳዮች ላይ ማሰብና መሥራት ይጠበቅብናል፡፡