ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር የሆኑት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በበዓለ ሲመታቸው ወቅት፣ በአገሪቱ ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን በአገር ውስጥ ማድረግ የሚችሉ መሆኑን በመግለጽ፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ የሚከተሉትን የትግል ሥልትም ሰላማዊ በማድረግ ለአገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትና ዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ የበኩላቸውን ለመወጣት ቃል ገብተው፣ በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች ደጋፊዎቻቸውን ሲያገኙ፣ አባላት ሲመለምሉ፣ እንዲሁም የተወሰኑት ደግሞ የውህደት፣ የጥምረት፣ አብሮ የመሥራትና አዲስ ፓርቲ የመመሥረት ዘመቻ ውስጥ መሰንበታቸው የሚታወቅ ነው፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ አመራሮች ዘለግ ላሉ ጊዜያት ከመንግሥትና ከገዥው ፓርቲ ጋር ስለአጠቃላይ የአገሪቱ ሁኔታና በየሥፍራው ስለሚቀሰቀሱ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች፣ እንዲሁም የመጪውን ዓመት አጠቃላይ ምርጫን ዕጣ ፈንታ የተመለከቱ ውይይቶች ሲያከናውኑም ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲዎቹ ከዚህ ቀደም አፋኝ ናቸው ብለው በሚገልጿቸው ምርጫና ተያያዥ ሕጎች ላይ ውይይት በማድረግ፣ አዋጆቹን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ በመግለጽ አዲስ የሚረቀቁ አዋጆች ምን ዓይነት ቅርፅና ይዘት ሊኖራቸው እንደሚገባ ሐሳባቸውን ሲሰነዝሩ ነበር፡፡
ከሁሉም በላይ ግን በአብዛኛው ኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ጉዞ በሚከታተሉ ዘንድ ባለፈው አንድ ዓመት ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እንደ ስኬት ሊነሳ የሚችለው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት በፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት ለማረቅ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል የተባለለትን የቃል ኪዳን ሰነድ መፈረሙ ነበር፡፡
በቃል ኪዳን ሰነዱ መሠረት ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን ለማሻሻልና ለመመካከር የሚያስችል የጋራ ምክር ቤት እንደሚቋቋም የተገለጸ ሲሆን፣ የሚቋቋመው ምክር ቤትም በፓርቲዎች መካከል የሚፈጠር አለመግባባትንና ማንኛውንም ልዩነት ለመፍታት ዒላማው ማድረጉ ከቃል ኪዳን ሰነዱ መረዳት ይቻላል፡፡
የቃል ኪዳን ሰነዱን መፈረም ተከትሎ ፓርቲዎች ከምርጫ ቦርድ፣ ከምርጫ ሕጎችና ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ያላቸውን ጥያቄችና አስተያየቶች ለቦርዱ በማቅረብ ውይይት እያካሄዱም ነበር፡፡ በውይይታቸው መሠረትም ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የተመለከተ አዲስ ረቂቅ አዋጅ እንዲዘጋጅ ማስቻል ነበር፡፡
የፓርቲዎቹን ጥያቄዎች፣ አስተያየቶችና ሐሳቦችን በቃልና በጽሑፍ የተቀበለው በወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ አዲስ ረቂቅ አዋጅ በማዘጋጀት ለሕዝብ አስተያየት አቅርቧል፡፡
ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ የሲቪል ማኅበረሰቡ አባላት፣ እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ለውይይት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ግን በቀላሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ይሁንታ ማግኘት አልቻለም፡፡
በመጀመርያ ቀን ውሎው ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የረቂቅ አዋጁን ይዘት በመቃወም በርካታ አንቀጾች እንዲሻሻሉና እንዲሰረዙ እየጠየቁ የነበረ ሲሆን፣ በሁለተኛው ቀን ደግሞ በፓርቲዎቹ ተወካዮች ጥያቄዎችና በቦርዱ የሥራ ኃላፊዎች ከአዋጁ ይዘት ጋር በተያያዘ የነበረው ልዩነት በመስፋቱ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ውይይቱን ረግጠው ወጥተዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውይይቱን ረግጥው መውጣታቸው በቀጣይ ለሚደረጉ ውይይቶች እንቅፋት እንዳይሆን የሠጉ በርካቶች ናቸው፡፡ ስብሰባውን ረግጠው የወጡት የ33 ፓርቲ አመራሮች ግን ሐሙስ ሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ጽሕፈት ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ‹‹ስብሰባውን ረግጠን የወጣነው ለስብሰባው፣ ለስብሰባው አዘጋጆች፣ ወይም ለምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች ክብር ስለሌለን ሳይሆን፣ ተቃውሞአችንን ለመግለጽ በማሰብ ነው፡፡ በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶች ይህ ክስተት የሚያጠላው ጥላ አይኖርም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሆኖም ባለፈው ሐሙስ መግለጫ የሰጡት የ33 የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አፅንኦት ሰጥተው የገለጹት ነገር ቢኖር፣ ያለ ቀጣይ ውይይትና ድርድር አሁን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ መፅደቅ እንደሌለበት ነው፡፡
‹‹በአፋኝና አፍራሽ አንቀጾች የተሞላው ረቂቅ አዋጅ ሳይሻሻል እንዳይፀድቅ አጥብቀን እንጠይቃለን፤› በሚል ርዕስ ባወጡት መግለጫ 33ቱ ፓርቲዎች፣ ‹‹ላለፉት 27 ዓመታት ያሳለፍናቸው መራራ የትግል ወቅቶች አሁንም ከዓመት ዕረፍት በኋላ ወደ ቦታቸው ሊመለሱ እንደሆነ የሚያሳዩ ብዙ ምልቶች እያየን ነው፤›› ሲሉ፣ ከዓመት በፊት ወደነበረው የፖለቲካ ምስቅልቅል እየተመለሱ እንደሆነ በመግለጫቸው አውስተዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ‹‹ወደ ነበርንበት የፖለቲካ ባህል እየተመለስን ነው፤›› ያስባለቸውን ዋነኛ ምክንያት ሲገልጹ ደግሞ፣ ‹‹በመንግሥት የተቋቋመው የሕግ ማሻሻያ ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሻሻልኩ ያለው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲ ረቂቅ አዋጅ ምስክር ነው፤›› በማለት ክስተቱን እንደ አስረጂነት ይጠቅሳሉ፡፡
እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዋነኛነት ተቃውሞአቸውን የሚያሰሙት ደግሞ፣ ‹‹ቀደም ባሉት ጊዜያት በድርድርም ሆነ በውይይት ወቅት ስንሰነዝራቸው የነበሩ አስተያየቶች ሙሉ በሙሉ በረቂቅ አዋጁ አልተካተቱም፤›› በማለት ነው፡፡
‹‹በዚህ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅ ላይ በስፋት ተመካክረን የተስማማንበት ሲሆን፣ በቀሩት ጉዳዮችም ላይ በቡድንና በተናጠል ያልተካተቱ ሐሳቦች በጽሑፍ ያስገባን መሆኑ እየታወቀ፣ በረቂቅ አዋጁ ስምምነቶችንና ማሻሻያዎችን ወደ ጎን በመተው ለጥቂቶች ብቻ የታሰበ በሚመስል ሁኔታ አሻሽያለሁ ብሎ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ፣ የሕግ ማሻሻያ ምክር ቤቱንም ሆነ የምርጫ ቦርድን ገለልተኛነት ከወዲሁ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆኖ አግኝተነዋል፤›› ሲሉም፣ ከዚህ ቀደም ወደ ምርጫ ቦርድ ይሰነዘሩ የነበሩ የገለልተኝነት ጥያቄዎች ከዓመት ያህል ቆይታ በኋላ መመለሳቸውን ጠቁመዋል፡፡
ሰላሳ ሦስቱ ፓርቲዎች በዋነኛነት አንኳርና ወሳኝ የሆነው የምርጫ ሥርዓት ላይ ረቂቅ አዋጁ ምንም አለማለቱ፣ የረቂቅ ሕጉ ‹አፋኝነት› ማሳያ ነው በማለት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡
የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓት በተመለከተ ረቂቅ አዋጁ፣ ‹‹በፌዴራል ሕገ መንግሥት መሠረት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚደረግ ምርጫ፣ በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከሚወዳደሩት ዕጩዎች መካከል አብላጫ ድምፅ ያገኘው አሸናፊ ይሆናል፤›› በማለት፣ የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት እንደሆነ ተደንግጓል፡፡
ይህ የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ተቃውሞ ይቀርብበት የነበረ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) እና የጋራ ምክር ቤት አባል በነበሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ሲደረግ በነበረው ድርድር፣ ወደ ቅይጥ የምርጫ ሥርዓት እንዲቀየር መስማማታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ከዚህ አንፃር 33ቱ ፓርቲዎች፣ ‹‹መንግሥት ለኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ለፓርቲዎች በተደጋጋሚ ቃል ሲገባ ከነበረባቸው ጉዳዮች አንዱ የምርጫ ሕጉን ማሻሻል ነው፡፡ የምርጫ ሕጉን ማሻሻል ካስፈለገበት ጉዳይ አንዱ የምርጫ ሥርዓቱን ማሻሻል ነው፡፡ ስለዚህ የምርጫ ሥርዓቱ ተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት ሆኖ እንዲቀየር በሕግ መደንገግ አለበት፤›› በማለት፣ የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓት መቀየር ዋነኛ ጉዳይ በመሆኑ፣ በዚህ አዋጁ አለመካተቱ ተገቢ እንዳልሆነ በመጥቀስ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡
ሌላው 33ቱ ፓርቲዎች በፅኑ የተቃወሙት የረቂቅ አዋጁ ይዘት ደግሞ ለፓርቲዎች ምዝገባ መመዘኛነትና ለዕጩ ተወዳዳሪዎች የቀረበውን መሥፈርት ሲሆን፣ ‹‹ይህ የረቂቅ አዋጁ መሥፈርት በፍፁም ተቀባይነት የሌለውና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን የሚጨፈልቅ ነው፡፡ የምርጫውን አሸናፊ ቀድሞ የሚበይን የፀረ ዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ የያዘ በመሆኑ፣ አገሪቱን ወዳልተፈለገ የፖለቲካ ውዝግብ የሚወስድ ሕግ ሆኖ አግኝተነዋል፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡
ከዚህ መሥፈርት ጋር በተያያዘ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲነት የሚመሠረተው አሥር ሺሕ አባላት ሲኖሩት ነው የሚለው አሁን በአገሪቱ ባለው የፀጥታ ችግር ይህንን ማድረግ ስለማይቻል፣ እንዲሁም ምኅዳሩን ስለሚያጠብና አሳታፊ ሆኖ ስላላገኙት ለአገር አቀፍ ፓርቲ 3,000፣ እንዲሁም ለክልል 1,500 ሆኖ ይሻሻል የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በዚህ የመሥፈርት ጉዳይ ላይ የተለያዩ አካላት አስተያታቸውን እየሰጡ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ አንድ ፓርቲ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚኖርበት አገር ውስጥ 10,000 ሺሕ ፊርማ ማሰባሰብ ካልቻለ፣ መጀመርያ ራሱን እንዴት እንደ አገር አቀፍ ፓርቲ ይቆጥራል በማለት የተቀመጠው መሥፈርት የተጋነነ አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም ፓርቲዎች በራሳቸውም ምክንያት ሆነ ከመንግሥት ይደርስባቸው በነበረ ጫና መሠረታዊ የሚባሉ ፓርቲ ለመመሠረት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያሟሉ፣ ለይስሙላ ምርጫ በደረሰ ቁጥር ብቅ በማለት ከሚያካሄዱት የምረጡኝ ቅስቀሳና ዘመቻ ባለፈ ወጥ የሆነ የአባል አመላመል መሥፈርት፣ የውስጠ ዴሞክራሲን ማጠናከር፣ የርዕዮተ ዓለም ግልጽነትና ከአገሪቱ ነባራዊ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ጋር ማስተሳሰርና መተንተን አለመቻላቸውን እንደ ድክመት በመቁጠር፣ አሁንም በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠው መሥፈርት ካሉበት ሁኔታ እንጂ ያን ያህል የሚከብድ እንዳልሆነ በመግለጽ የፓርቲዎችን ጥያቄ ይሞግታሉ፡፡
ምንም እንኳን እነዚህን የመሳሰሉ ትችቶች ወደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢሰነዘርም፣ 33ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን ከረቂቅ አዋጁ ውስጥ 20 አንቀጾች እንዲሰረዙና 13 አንቀጾች ደግሞ እንዲሻሻሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፓርቲዎቹ እንዲሻሻሉ የጠየቋቸው 13 አንቀጾች ደግሞ አንቀጽ 4፣ 13፣ 17፣ 18(ሐ)፣ 25፣ (3)፣ 31፣ 33 (ሐ)፣ 34፣ 44፣ 46፣ 64 (ሀ)፣ 80 (2) እና 160 (2) ሲሆኑ፣ እንዲሰረዙ የጠየቋቸው 20 አንቀጾች ደግሞ አንቀጽ 32፣ 64፣ 65፣ 66፣ 71፣ 74(1)፣ 74(3)፣ 75፣ 78 (1)፣ 82 (3 እና 4)፣ 91(3)፣ 93፣ 96 (2)፣ 98 (1 እና 2)፣ 100 (1)፣ 100 (3)፣ 102፣ 111(1)፣ 160(2) እና 160 (3) ናቸው፡፡
እነዚህ አንቀጾች ሳይሻሻሉና ሳይሰረዙ ረቂቅ አዋጁ እንዳይፀድቅ ፓርቲዎቹ በአጽንኦት ከመጠየቅ ባለፈ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ በተገኙበት በረቂቅ አዋጁ ላይ እንደገና ለመወያየት በቂ ጊዜና ሰፊ መድረክ እንዲዘጋጅላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በረቂቅ አዋጁ ላይ በግልጽ የሚታዩ የሕግ ክፍተቶችና ‹አፋኝ› አንቀጾች ተለይተው ሳይስተካከሉና ሳይሰረዙ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ረቂቁን ወደ ውሳኔ እንዳያቀርበው ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
ይህን ጥያቄ ካቀረቡ ፓርቲዎች መካከል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት (ኢዴኀ)፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የመጪው አጠቃላይ ምርጫ መከናወን አለመከናወን ባልተወሰነበት ሁኔታ፣ ፓርቲዎች በረቂቅ አዋጁ ላይ የያዙት አቋም በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ቀጣዩን አጠቃላይ ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ለማከናወን ሌላ ፈተና ሊሆን እንደሚችል የሚጠቅሱ ወገኖች ሲኖሩ፣ ምርጫ ቦርድም የተነሱትን የልዩነት ነጥቦች በመወያየትና በመግባባት በመፍታት በመጠኑም ቢሆን ያገኘውን ቅቡልነት አስጠብቆ ለመጓዝ ጥያቄዎቹን በጊዜ እንዲመልስ የሚያሳስቡም አሉ፡፡
በ33ቱ ፓርቲዎች አማካይነት የቀረበው ጥያቄ ቀጣዩን ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ከማከናወን አንፃር አዲስ ፈተና ነው የሚሉ ወገኖች በመኖራቸው፣ የመጪውን አጠቃላይ ምርጫን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም ካሉ ክስተቶች በተጨማሪ ሌላ ሥራ ተፈጥሮበታል፡፡ የፓርቲዎቹን ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ በመመለስ፣ የቀጣዩ ዓመት ምርጫ መከናወንና አለመከናወን በሒደት የሚታይና የሚጠበቅ ጉዳይ ሆኗል፡፡