Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአቶ ጌታቸው አሰፋና አቶ ያሬድ ዘሪሁንን ጨምሮ በሰባት ተከሳሾች ላይ ዓቃቤ ሕግ...

አቶ ጌታቸው አሰፋና አቶ ያሬድ ዘሪሁንን ጨምሮ በሰባት ተከሳሾች ላይ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን አሰማ

ቀን:

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀሎች ክስ ተመሥርቶባቸው በሌሉበትና በማረሚያ ቤት ባሉ ተከሳሾች ላይ፣ ማለትም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋናና ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋና አቶ ያሬድ ዘሪሁንን ጨምሮ በሰባት ተከሳሾች ላይ ምስክሮቹን አሰማ፡፡

ዓቃቤ ሕግ ማክሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ሦስት ምስክሮችን ማቅረቡን አሳውቆ፣ ሁለት ምስክሮች በአንድ ተከሳሽ ላይ፣ እንዲሁም አንድ ምስክር በአምስት ተከሳሾች ላይ እንደሚያሰማ ጭብጥ በማስያዝ አስመስክሯል፡፡ በአንድ ተከሳሽ ላይ የቆጠራቸውን የስሚ ስሚ ምስክሮች እንደሚያሰማ ጭብጥ ያስያዘ ቢሆንም፣ ትንሽ ቆይቶ ሐሳቡን በመቀየር ‹‹አልፈልጋቸውም›› በማለት ያስመዘገበውን ጭብጥ ውድቅ ማድረጉን በማስታወቅ ቀሪዎቹን ምስክሮች አሰምቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ 20ኛ ተከሳሽ ያደረጋቸው አቶ እዮብ ተወልደ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም እነ አቶ ጌታቸው አሰፋ ሕገወጥ ተግባር ለመፈጸም በሚያስችል ሁኔታ ባዘጋጁት አደረጃጀት ውስጥ ተሳታፊ በመሆን፣ በራሳቸውና በክትትል ሠራተኞች በምስክርነት የቆጠራቸውን ሁለት ተበዳዮች ከሕግ ውጪ በኃይል አስገድደው በመያዝ በደል እንደፈጸሙባቸው ምስክሮቹ እንደሚያስረዱለት ጭብጥ አስይዞ ምስክርነቱ ተጀምሯል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የመጀመርያው ምስክር ቀርበው እንዳስረዱት፣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበሩበት ሚያዝያ 2 ቀን 2003 ዓ.ም. ከጓደኛቸው ጋር ተከራይተው በሚኖሩበት ቤት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ወደ መፀዳጃ ቤት እየሄዱ እንዳሉ ተከሳሹ አቶ እዮብና ሌሎች ሰዎች በድንገት ሽጉጥ ደቅነው ይዘዋቸዋል፡፡ ቤታቸውን ፈትሸው እንደጨረሱ እሳቸውን፣ ጓደኛቸውንና ዕቃዎቻቸውን በመኪና ጭነው በቅርብ የሚገኝ ቢሮ ውስጥ እንደወሰዷቸውም አክለዋል፡፡

አቶ እዮብ በዩኒቨርሲቲው አካባቢ ይመላለሱ ስለነበር እንደሚተዋወቁ የገለጹት ምስክሩ፣ ‹‹ምን አጥፍተን ነው?›› ሲሏቸው፣ ‹‹በሽብርተኝነት ተጠርጥራችኋል›› በማለት በወሰዷቸው ቢሮ ውስጥ ለሦስት ሰዓታት ያህል እንዲቆዩ ካደረጉ በኋላ፣ በፀጥታ ሰዎች ታጅበው ወደ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) እንዳመጧቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የተከሳሹ የአቶ እዮብ ጠበቃ ለምስክሩ ያቀረቡላቸው የመጀመርያ ጥያቄ፣ ‹‹ከአቶ እዮብ ጋር ከመቼ ጀምሮ ነው የምትተዋወቁት?›› የሚል ነበር፡፡ ምስክሩ በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ይተዋወቃሉ፡፡ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ አቶ እዮብ በተደጋጋሚ ይኼዱ ነበር፡፡ በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ችግሮች ሲኖሩ ይደውሉላቸው እንደነበርም አክለዋል፡፡ አቶ እዮብ ሽጉጥ ደቅነው ቢይዟቸውም፣ ወደ አዲስ አበባ እንዲወሰዱ ትዕዛዝ ከመስጠት ባለፈ ምንም እንዳላደረጓቸውም ምስክሩ አስረድተዋል፡፡ ምስክሩ ተከሰው እንደነበር ጠበቃው ጠይቀዋቸው ‹‹አዎ ተከሳሽ ነበርኩ›› ብለዋል፡፡ ሁለት ዓመታት ከስድስት ወራት ፍርድ ቤት መመላለሳቸውንም ተናግረዋል፡፡ የተከሰሱት ‹‹የኦነግ አባል ነህ›› ተብለው ስለመሆኑ ተጠይቀው፣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለብጥብጥና ረብሻ አነሳስችኋል በማለት መሆኑን ጠቁመው ሠልፍ ሊደረግ አንድ ቀን ሲቀረው መያዛቸውንም አስታውሰዋል፡፡

አቶ እዮብን ከአንድ ቀን ሌላ አይተዋቸው ወይም ሌላ ጉዳት አድርሰውባቸው ከሆነ ተጠይቀው፣ ከያዟቸው ቀን ውጪ አይተዋቸው እንደማያውቁና ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳላደረሱባቸው አስረድተዋል፡፡

ሁለተኛው ምስክርም በአቶ እዮብ ተወልደ ላይ ሊመሰክሩ ፍርድ ቤት መቅረባቸውንና የሚመስክሩት በእውነት ስለመሆኑ መሀላ ፈጽመው በሰጡት ምስክርነት፣ አቶ እዮብን ከጓደኛቸው ጋር ሲይዟቸው አንድ ቀን ብቻ እንዳዩዋቸው ቢናገሩም፣ ከስድስት ዓመት ቆይታ በኋላ በመልክ ለይተው ማሳየት ችለዋል፡፡ አንደኛው ምስክር በተያዙበት ዕለት እሳቸውም አብረው ይኖሩ ስለነበር መያዛቸውንና የተያዙትም ምሽት አራት ሰዓት እራት እየበሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመጀመርያው ምስክር ሲመሰክሩ ከቤታቸው ተይዘው የተወሰዱት የሆነ ቢሮ የሚመስል ቤት መሆኑን እንደገለጹት፣ ሁለተኛውም ምስክር ‹‹የሆነ ቢሮ ውስጥ ወሰዱን›› ብለዋል፡፡ ቢሮ መሆኑን እንዴት እንዳወቁት ተጠይቀው፣ ‹‹ገምቼ ነው፣ ፎቅ ስለሆነ ነው›› ብለዋል፡፡ እሳቸው በጊዜ ቀጠሮ የተወሰነ ጊዜ ከታሰሩ በኋላ በነፃ መለቀቃቸውንም አስረድተዋል፡፡ አቶ እዮብ ላይ እንደሚመሰክሩ እንዴት እንዳወቁ ተጠይቀው፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ቃላቸውን ሰጥተው ስለነበር ምስክር ሆነው ሊቀርቡ እንደሚችሉ ማወቃቸውን አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የማጣሪያ ጥያቄ አቅርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የስሚ ስሚ ምስክሮች እንዳሉትና በ21ኛ ተከሳሽ አቶ ሰይፈ በላይ ላይ እንደሚያስመሰክር ዓቃቤ ሕግ ከገለጸ በኋላ ራሱ ምስክርነቱን ውድቅ አድርጎታል፡፡ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰዱት የዓቃቤ ሕግ ምስክር ደግሞ በ16ኛ ተከሳሽ አቶ ተመስገን በርሄ ላይ የመሰከሩ ምስክር ናቸው፡፡

ዓቃቤ ሕግ ከላይ በተከሳሽ አቶ ተወልደ ላይ ያስያዘው ጭብጥም ለሦስተኛውም ምስክር የሚሆን እንደሆነ በመግለጹ ምስክሩ በአቶ ጌታቸው አሰፋ (በሌሉበት)፣ በአቶ ያሬድ ዘሪሁን፣ በአቶ መአሾ ኪዳኔ፣ በአቶ አማኑኤል ኪሮስና በዋናነት በአቶ ተመስገን በርሄ ላይ ምስክርነታቸውን አሰምተዋል፡፡

የደረሰባቸውን ድብደባና እሳቸው ታስረው በነበረበት እጅግ ጠባብ ማሰሪያ ቤት ውስጥ ለሰባት ቀናት በቆዩበት ጊዜ፣ ሌሎች እየተገረፉ የሚያሰሙትን የጩኸትና የልመና ድምፅና ሌሎች ደረሱብኝ ያሏቸውን በደሎች ከአያያዛቸው ጀምሮ መስክረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሰበታ ከተማ በኃላፊነት ደረጃ እንደሚሠሩና የሚመሰክሩትም በእውነት ለመሆኑ ቃለ መሀላ በመፈጸም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሰበታ ከተማ በሕገወጥ መንገድ ታጥሮ የነበረ 3,000 ካሬ ሜትር ቦታ ሰነድ እንዲሠራለትና ለእሳቸውም በወቅቱ ከነበሩበት ኃላፊነት በላይ ዕድገት እንደሚሰጣቸው በመግለጽ ተከሳሹ አቶ ተመስገን ሲጠይቋቸው፣ ትክክለኛ ሰነድ ይዘው የሚቀርቡ ከሆነ እንደሚያስተካክሉ ነግረው እንደመለሷቸው አስረድተዋል፡፡ በተደጋጋሚ ተመላልሰው ሲጠይቋቸውም ምላሻቸው ተመሳሳይ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በሕገወጥ መንገድ የታጠረውን ቦታ አጥሩን ማፍረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ እንዴት አጥሩን ሊያፈርሱ እንደቻሉና ለምን እንዳፈረሱ በዓቃቤ ሕግ ተጠይቀው፣ ከሌሎች ኃላፊዎች ጋር በመሆን ሕገወጥ ግንባታን የመከላከል ሥራ ያከናውኑ እንደነበርና መሬቱም የአርሶ አደሮች መሆኑን ስለሚያውቁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቦታውን ለማን እንደሚስተካከልና የይዞታ ሰነድ እንዲሠራለት እንደተጠየቁ ሲጠየቁ፣ ተከሳሹ ‹‹ለባለሥልጣን ነው›› ከማለት ባለፈ ስማቸውን እንዳልነገሯቸው አስረድተዋል፡፡ ተከሳሹ አቶ ተመስገን እንዳሰቡትና እንደፈለጉት ሊታዘዙላቸው ስላልቻሉ፣ እሳቸውን መከታተል እንደጀመሩና ቤታቸው ሲወጡና ሲገቡ ለሦስት ቀናት እንዳጠኗቸው ተናግረዋል፡፡

ግንቦት 13 ቀን 2005 ዓ.ም. ለዘመድ ሠርግ ወደ ወሊሶ ሄደው እያለ፣ አቶ ተመስገን በካኪ ወረቀት የታሸገ ነገር አምጥተው ለእሳቸው እንድትሰጥ ለእህታቸው ሰጥተዋት እንደሄዱ የገለጹት ምስክሩ፣ እሳቸው አምሽተው በመምጣታቸው የተላከላቸውን እሽግ ደብዳቤ ሳያዩት ማደራቸውን ገልጸዋል፡፡ በማግሥቱ ግንቦት 14 ቀን 2005 ዓ.ም. ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ላይ ቤታቸው ሲንኳኳ በበር ቀዳዳ ሲመለከቱ፣ ፖሊሶች ማየታቸውንና በራቸውን መክፈታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የሰበታ ከተማ ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስና አቶ ተመስገንን ጨምሮ ሲቪል የለበሱ የፀጥታ ሰዎች ዙሪያውን ከበዋቸው እንዳገኙ የገለጹት ምስክሩ፣ መጀመሪያ እሳቸውን ፈትሸው በቀጥታ ወደ ቤታቸው ውስጥ ገብተው ሲፈትሹ፣ ተከሳሹ አቶ ተመስገን እንደታሸገ የተቀመጠውን ፖስታ በቀጥታ ሄደው በማንሳት እንደከፈቱት ተናግረዋል፡፡ በታሸገው ፖስታ ውስጥ በርካታ በእጅ የሚያዙ የኦነግ ባንዲራዎችና ዓርማዎች ባሉበት ደስታ ወረቀት የተጻፈ ጽሑፍ በማውጣት ‹‹አሸባሪ ኦነግ›› ብለው አቶ ተመስገን በጥፊ እንደመቷቸው ተናግረዋል፡፡ እህታቸው እየጮኸች ‹‹የሰጠኝ እሱ ነው›› በማለት አቶ ተመስገንን እንዳሳየች ወደ ሰበታ ፖሊስ ጣቢያ ይዘዋቸው እንደሄዱ ገልጸዋል፡፡ የሰበታ ፖሊሶች ‹‹አንቀበልም›› ሲሉ ‹‹ሽብርተኛ ነው፣ እምቢ ካላችሁ እናንተም ትታሰራላችሁ›› ሲሏቸው ፈርተው እንዳሰሯቸው፣ ‹‹እናንተን ከዚህ ምድር ላይ እንጨርሳችኋለን፣ አትኖሩም›› እያሉ አቶ ተመስገን ሲደበድቧቸው ሌሎች ፖሊሶች እንዳዳኗቸውም ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ ሲፈተሹ የከተማ አስተዳደሩ የሰጣቸው ሕጋዊ ሽጉጥ የነበራቸው መሆኑን፣ አቶ ተመስገንና አብሯቸው የነበረ ሰው እንደወሰዱትም አክለዋል፡፡ ከሰበታ ፖሊስ ጣቢያ ዓይናቸውን በፎጣ ሸፍነው ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዷቸውና ከሁለት ቀናት በኋላ ፍርድ ቤት እንዳቀረቧቸውም ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በዋስ እንዲለቀቁ ሲፈቅድላቸው፣ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ በመተላለፍና ዋስ ሊሆኑ የቀረቡ አጎታቸውን በማስፈራራት ወደማያውቁበት ቦታ በመውሰድ ለሰባት ቀናት በጨለማ ቦታ እንዳቆዩአቸው ተናግረዋል፡፡ በሰባት ቀናት ቆይታቸው ሦስት ቀን እጅግ ጠባብ በሆነና በማያስቆምና በማያስተኛ ቦታ ላይ አድርገው በኤሌክትሪክ ገመድ ሲገርፏቸው እንደቆዩ ለፍርድ ቤቱ አስረድተው፣ ኮታቸውን አውልቀው የለበሱትን ነጭ ሸሚዝ ወደ ላይ በማድረግ እምብርታቸው አካባቢ፣ ቀኝ እጃቸው፣ እግራቸው አካባቢ በደረሰባቸው ድብደባ አማካይነት በልዞ የሚታይ አካላቸውን አሳይተዋል፡፡ በርካታ ቦታ ላይም ጠባሳ እንዳላቸውና የእጃቸው የተወሰኑ ጣቶች እንደማይሠሩም ተናግረዋል፡፡ ልብሳቸውን ለብሰው ሳግ እየተናነቃቸው ምስክርነታቸውን ቀጥለው እንዳስረዱት፣ ‹‹ከዚህ በኋላ ሬሳህ ነው የሚወጣው›› እያሉ ይደበድቧቸውና ሲሚንቶ ወለል ላይ ያሳድሯቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከሰባት ቀናት ውስጥ አራቱን ቀናት ወደማያውቁት ቦታ ወስደዋቸው በበረዶ የቀዘቀዘ ውኃ በባልዲ እየደፉባቸው  ይደበድቧቸው እንደበርና ተከሳሹ አቶ ተመስገንም ተባባሪ ደብዳቢ እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡

በቅዝቃዜውና በደረሰባቸው ድብደባ ምክንያት የሳንባ ሕመምተኛ ሆነው ለአንድ ዓመት በሕክምና ላይ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ድብደባ በኋላ መልሰው ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሲወስዷቸው ፍርድ ቤት የለቀቀውን እስረኛ እንደማይቀበል ሲነግራቸው፣ አቶ ተመስገን ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ወስደው እቴነሽና ተኽላይ ለሚባሉ መርማሪዎች እንዳስረከቧቸው ተናግረዋል፡፡ ሲያስረክቧቸው ቃላቸውን እንዲሰጡ አድርገው በግዳጅ እንዳስፈረሟቸውም አክለዋል፡፡ የማዕከላዊ ምርመራ ፖሊስ ፍርድ ቤት አቅርቦ 28 የምርመራ ቀናት በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ እንደጠየቀባቸውና በእስር ላይ እያሉ በጠና በመታመማቸው፣ ተኽላይ የሚባለው የማዕከላዊ መርማሪ ‹‹በአስቸኳይ ልቀቁት›› በማለቱ እንደተፈቱ አስረድተዋል፡፡

የዓቃቤ ሕግ ምስክርነታቸውን እንደጨረሱ የአቶ ያሬድ ዘሪሁን ጠበቃና የአቶ ተመስገን ጠበቃ መስቀለኛ ጥያቄዎች አቅርበውላቸዋል፡፡ ሰባት ቀናት በጨለማ ቤት ሲታሰሩ ምግብ ማን ያቀርብላቸው እንደበር ተጠይቀው፣ የሆኑ ሴቶች ዳቦና ሻይ ያቀርቡላቸው እንደነበር፣ ነገር ግን ስለሚፈሩ (በመርዝ ያጠፉኛል በሚል) ከዳቦው ውጪ ሌላ ነገር እንደማይመገቡ አስረድተዋል፡፡ ለብቻቸው ታስረው በነበረ ጊዜ አጠገባቸው ባለ ክፍል ውስጥ ያሉ ሰዎች በምን ምክንያት እንደጮኹ እንዳወቁ ተጠይቀው፣ ዱላው ሲያርፍባቸው ይሰማ እንደበርና ‹‹አትግደሉኝ›› የሚል ድምፅ ይሰሙ ስለነበር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ መቼ እንደታሰሩና እነ ማን እንደያዟቸው ተጠይቀው፣ የተያዙት ግንቦት 14 ቀን 2005 ዓ.ም. መሆኑንና የያዟቸው ተከሳሽ ተመስገን ታዬ፣ ኮማንደር አበበ፣ አንድ ጥርሰ ፍንጭት፣ ራሰ በረሃና ሌሎችም ሰዎች መሆናቸውን ዘርዝረዋል፡፡ በታሸገው ካኪ ወረቀት ውስጥ ስንት የኦነግ ባንዲራ እንደተገኘ፣ ስንት ወረቀት እንደተገኘ፣ ለእህታቸው የተሰጠው ካኪ ወረቀት መጠን ምን ዓይነት እንደሆነ፣ ለእህታቸው የታሸገውን ወረቀት ተመስገን መስጠቱን እንዴት እንዳወቁ፣ ቃላቸውን ስለመስጠታቸውና በግዳጅ ስለመፈረማቸው፣ የሳንባ ሕክምና ሲታከሙ ለፍርድ ቤቱ ያሳዩትን የሰውነት ጉዳት ለምን እንዳልታከሙ ጠበቆች ጠይቀዋቸው፣ ሁሉንም ከላይ ለዓቃቤ ሕግ እንዳስረዱት ምላሽ ሰጥተው ሌላውን የሰውነታቸውን ጉዳት ያልታከሙት ከፍለው ለመታከም አቅም ስለሌላቸው በመሆኑ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ባቀረበላቸው የማጣሪያ ጥያቄ፣ የሰበታ ከተማ የፀጥታ ሠራተኛ ሆነው ሲሠሩ ከማን ጋር ይሠሩ እንደነበር ጠይቋቸው፣ ከከተማው ፖሊስ ጋር ይሠሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከአቶ ተመስገን ጋር እንዴት እንደተዋወቁ፣ አጥሩን ስላፈረሱ በዚያ ቂም ይዞና የኦነግ አባል እንደሆኑ በማስመሰል ወረቀት በማስቀመጥ እንዳሰሯቸው ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከተፈቱ በኋላ ያላግባብ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደደረሰባቸው ስለማመልከታቸው ተጠይቀው፣ ‹‹እንዴ! ለማነው የማመለክተው? ለመታሰር?›› በማለት ጥያቄውን በመገረምና በጥያቄ መልሰው የምስክርነት ቃላቸውን አጠቃለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...