Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየካሳ አዋጁ የነበሩትን ቅሬታዎች እንዲፈታ ሆኖ መሻሻሉ ተነገረ

የካሳ አዋጁ የነበሩትን ቅሬታዎች እንዲፈታ ሆኖ መሻሻሉ ተነገረ

ቀን:

በቅርቡ በፓርላማ ተሻሽሎ የፀደቀው የካሳ አዋጅ፣ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታቸውን ለሚለቁ ዜጎች በልማት እንዲሳተፉ እንደሚረዳቸው ተገለጸ፡፡

አቅሙ ያላቸው በግልም ሆነ በማኅበር ተደራጅተው እንዲያለሙ ቅድሚያ ለባለይዞታዎች መብት የሚሰጥ መሆኑን፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታዜር ገብረ እግዚአብሔር አዋጁን አስመልክቶ ማክሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ አስታውቀዋል፡፡

ሕዝቡ በልማት ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ መሆን የለበትም የሚል መርህ ያነገበው አዋጁ፣ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የሚነሱ ዜጎች ከነበራቸው ኑሮ የተሻለ መኖር የሚችሉባቸው ዕድሎች እንዲመቻቹም ያስገድዳል ተብሏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

 ከዚህ ቀደም የነበረውን የካሳ አከፋፈል ሥርዓት የተነሺዎችን ተጠቃሚነት እንዲያረጋገጥ እንዲከለስ መደረጉንና የጊዜያዊና የቋሚ ተነሺዎችን የካሳ አከፋፈል እንደ ሁኔታው ተለያይተው እንደሚታዩ የገለጹት ሚኒስቴር ዴኤታው፣ ተነሺዎች ከሚታሰብላቸው የንብረት ግምት ባሻገር በመነሳታቸው ለሚያጋጥማቸው የገቢ መቋረጥና የወጪ መጨመርን ታሳቢ የተደረገ ክፍያ ያገኛሉ ብለዋል፡፡

በመነሳታቸው ምክንያት እንደ ዕድር ላሉ የማኅበራዊ ትስስር መቋረጦችና ለሚደርስባቸው የሥነ ልቦና ጫና (በመነሳታቸው የተሻለ ጥቅም ቢያገኙም እንኳ) ካሳ እንዲከፈላቸው አዋጁ እንደሚያስገድድ፣ በሚኒስቴሩ የከተማ ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብዙዓለም አድማሱ ገልጸዋል፡፡

‹‹አንድ በእርሻ የሚተዳደር አርሶ አደር በልማት ተነስቶ ወደ ከተማ ቢካተት የከተማን ኑሮ ለመልመድ ይቸገራል፡፡ ከእርሻ ውጪ የሚያውቀው ሥራ ስለሌለም ሥራ ይፈታል፡፡ ከዚያ ባሻገር ካሳ ተብሎ የሚሰጠውን ገንዘብ እንዴት መጠቀም እንዳለበት ስለማያውቅ ገንዘቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከእጁ ጠፍቶ ለችግር ይዳረጋል፤›› ያሉት አቶ ብዙዓለም፣ አዋጁ ተነሺዎችን መልሶ የማቋቋም ግዴታ እንደሚጥል ገልጸዋል፡፡

ተነሺ ዜጎችን መልሶ ማቋቋሚያ ፈንድ ክልሎች እንዲያቋቁሙ አዋጁ እንደሚጠይቅ፣ በልማት መካተትና የራሳቸውን ድርሻ መግዛት የቻሉ ግን በዘላቂ ማቋቋሚያ ፕሮግራም አይካተቱም ብለዋል፡፡ ዜጎች ሙሉ ካሳ ሳይከፈላቸው በፊት እንዲነሱ እንደማይገደዱ፣ ቦታውን የሚፈልጉ አልሚዎችም በቂ የዝግጅት ጊዜ እንዲኖር ለከተማ ወይም ለወረዳ አስተዳደሩ ከዓመት በፊት ማሳወቅ እንዳለባቸው በተሻሻለው አዋጅ ተደንግጓል፡፡ አልሚው ቦታውን ከማግኘቱ በፊት ለታቀደው ልማት የሚያስፈልገውን ወጪና ለተነሺ ዜጎች የሚያስፈልገውን አጠቃላይ ካሳ መክፈል እንደሚችል መታወቅ እንደሚኖርበት ተደንግጓል፡፡

ተሻሽሎ የፀደቀው የካሳ አዋጅ 455/1997 ከዚህ በፊት ለከተማና ለወረዳ አስተዳደር የሰጠውን ፕላን የማፅደቅ፣ ንብረት የመገመትና የማስነሳት ሥልጣን ለገለልተኛ አካል እንዲሰጥም ያስገድዳል፡፡ ‹‹መንግሥት ራሱ ገማች፣ ራሱ አስነሺ፣ ራሱ ቅሬታ አድማጭ መሆን የለበትም፤›› ያሉት አቶ ብዙዓለም፣ የተነሺዎችን ንብረት የሚገምት ገለልተኛ ተቋም መቋቋም እንደሚኖርበትና ይህ ተቋም እስኪፈጠር ግን ሥራው በኮሚቴ እንደሚተዳደር ገልጸዋል፡፡ ፕላን የሚፀድቀውም እንደ ቀድሞው በወረዳና ከተሞች አስተዳደር ሳይሆን በከተሞች ምክር ቤት እንዲሆን አዋጁ ያዛል፡፡ ገለልተኛ አቤቱታና ይግባኝ ሰሚ አካል እንዲቋቋምና የተነሺዎች አቤቱታም በ30 ቀናት መልስ ማግኘት እንዳለበት አዋጁ ያስገድዳል፡፡

የካሳ አዋጅ 455/1997 ወቅታዊ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ ክለሳ ሳይደረግበት ለ13 ዓመታት በሥራ ላይ ውሏል፡፡ ‹‹ወቅታዊነት የጎደለው›› በተባለው በዚሁ አዋጅ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታቸውን የለቀቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ ያለ በቂ ካሳ ከይዞታቸው እንዲነሱ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ ለተነሱ ግጭቶች በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡

‹‹የተሻሻለው አዋጁ ወደ ኋላ ተመልሶ አይሠራም፡፡ የነበረውን አዋጅ በአግባቡ ከመተግበር አንፃር በነበሩ ክፍተቶች በርካታ አርሶ አደሮች መቸገራቸውን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን እነዚህን አርሶ አደሮች ለማቋቋም ቀደም ሲል የተጀመረ እንቅስቃሴ አለ፤›› ሲሉ አቶ ታዜር አስረድተዋል፡፡

ለ13 ዓመታት ሲሠራበት በቆየው አዋጅ እስካሁን ምን ያህል ዜጎች በልማት እንደተነሱ በግልጽ የሚታወቅ ቁጥር የለም ተብሏል፡፡

በመልሶ ማልማትና ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ረገድ ስድስት ከተሞች ማለትም አዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ፣ ሐዋሳና ደሴ ላይ ተመሥርቶ በተደረገ ጥናት በርካታ ዜጎች መነሳታቸውን ለሪፖርተር የነገሩት የከተማ ልማት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ዘልዑል ናቸው፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ 4,000 ሔክታር መሬት በመልሶ ማልማት ፕሮግራም ለመድረስ በዕቅድ ተይዞ እንደነበር፣ ከዚያ ውስጥ 300 ሔክታር ማልማት እንደተቻለ፣ በእያንዳንዱ ሔክታር በአማካይ 55 ሰዎች ይኖሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በማስፋፊያ ፕሮጀክትም እንዲሁ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች መነሳታቸውን ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ውስጥ 23 ገበሬ ማኅበራት ነበሩ፡፡ በእያንዳንዱ ገበሬ ማኅበርም ከ5,000 ያላነሱ አርሶ አደሮች ይኖሩ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ሁለቱ ብቻ ሲቀሩ ሌሎቹ ወደ ከተማነት ተቀይረዋል፡፡ ‹‹ይህ ቁጥር በአገር አቀፍ ደረጃ ሲሰላ ብዙ ነው፡፡ በአጭሩ ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ የሚነሳው ሕዝብ ነበር፡፡ የተነሺዎች ቁጥር ስለበዛ ብቻ ሳይሆን ትንሽም ቢሆን በልማት መጎዳት የለበትም፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

‹‹በከተማ ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮች ከተሜነት እንደ ሥጋት ሳይሆን እንደ ተስፋ ነው ማየት ያለባቸው፤›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የተሻሻለው አዋጅ ተነሺዎችን እንደሚጠቅም እንጂ እንደማይጎዳ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...

አማርኛ ተናጋሪዋ ሮቦት

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የሳይንስ ሙዚየም፣ ሚያዝያ 2 ቀን...

ወዘተ

ገና! ከእናቴ ሆድ ሳለሁ፤ ጠላት ሲዝትብኝ ሰምቻለሁ። በዳዴ ዘመኔም፣ በ'ወፌ ቆመችም!'፤ አውዴ ክፉ ነበር...

የአስፕሪን ታሪክ

በቤት ውስጥ የሚገኝ የመድኃኒት መደርደሪያ፣ ምንም ቢሆን፣ እስፕሪንን ሳይጨመር...