ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማና ሌሎች ከተሞች ላይ በተፈጸመ ግድያ፣ አካል ማጉደል፣ ማፈናቀል፣ አብያተ ክርስቲያናትና የንግድ ተቋማትን በማቃጠል ምክንያት ክስ የተመሠረተባቸውን የሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዚዳንትን ለማስለቀቅ ሴራ አቀነባብረው የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡
ድርጊቱ ሊፈጸም የነበረው ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲሆን፣ ተከሳሹ የቀድሞ ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት የነበራቸውን ቀጠሮ ጨርሰው ወደ ማረሚያ ቤት ሲሄዱ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ቃሊቲ ማረሚያ ቤት መግቢያ አካባቢ መኪና አዘጋጅተው ነበር የተባሉት ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች የተከሳሹን መምጣት በመጠባበቅ ላይ እያሉ፣ ያቆሙትን መኪና ከማረሚያ ቤቱ አካባቢ እንዲያነሱ በትራፊክ ፖሊስ ሲጠየቁ ‹‹አናነሳም›› የሚል ምላሽ መስጠታቸውንም ምንጮች አስረድተዋል፡፡
በዚህ ጊዜ የቆመው መኪና እንዲፈተሽ ሲጠየቁ በፈጠሩት አታካራ ሳቢያ ተኩስ መለዋወጣቸውንና ከየትኛው ወገን እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም፣ አንድ ሰው መመታቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ከግለሰቦቹ መካከል የተወሰኑት ሲያመልጡ አንዲት ሴትን ጨምሮ አብዛኞቹ በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ መሆናቸውንም ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡
ግለሰቦቹ በማረሚያ ቤቱ አቅራቢያ ቤት ተከራይተው እንደነበርና በርካታ የጦር መሣሪያዎችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡
ድርጊቱ በተፈጸመበት ጊዜ ተከሳሹ አቶ አብዲ ከፍርድ ቤት ወደ ማረሚያ ቤት አለመመለሳቸውን ከምንጮች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ተፈጽሟል የተባለውን ሙከራ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተርን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ለማግኘት ቢቻልም፣ በኔትወርክ ችግር ምክንያት መነጋገር ባለመቻሉ ሙሉ መረጃውን ማካተት አልተቻለም፡፡