Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የፍርድ ቤት ትዕዛዞችና ውሳኔዎች መተግበር ካልቻሉ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ሕዝቡ የሚያደርገው ጥሪ...

‹‹የፍርድ ቤት ትዕዛዞችና ውሳኔዎች መተግበር ካልቻሉ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ሕዝቡ የሚያደርገው ጥሪ ባዶ መፈክር ነው›› ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት

ቀን:

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ለ50 ቀናት በከፊል ዝግ ሆነው በውዝፍ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ይሰጣሉ

ዓርብ ሐምሌ 26 ቀን 2011 ዓ.ም.  በፍትሕ አካላት ሪፎርምና ችግሮች ላይ በተደረገ ውይይት ላይ የፍርድ ቤት ትዕዛዞችና ውሳኔዎችን ለማስከበር ችግር እየገጠመ መሆኑን በማስመልከት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ምክንያት፣ በማኅበራዊ ትስስሮች ጥያቄ የተነሳባቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ ‹‹የፍርድ ቤቶች ትዕዛዞችና ውሳኔዎች መተግበር ካልቻሉ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ሕዝቡ የሚያደርገው ጥሪ ባዶ መፈክር ነው፤›› አሉ፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጠው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት፣ ‹‹የሕግ ተገዥ ነኝ›› በሚል ርዕስ በተካሄደው ውይይት ላይ ለፕሬዚዳንቷ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው እንደነበር አስታውሷል፡፡ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኩል ዳኞች የፌዴራል ሕግ ጉዳዮች ላይ ዳኝነት ለመስጠት በአንዳንድ ክልሎች ሲንቀሳቀሱ ያጋጠማቸውን ዕክል፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝና ውሳኔ የማስከበር ችግር፣ በአጠቃላይ በፌዴራልና በክልል መንግሥት በሕግ ማስከበር ዙሪያ ስለሚታዩ ችግሮች አስተያየቶች መቅረባቸውንና ፌዴራል ፍርድ ቤቱ በዚህ ረገድ ምን ዓይነት መፍትሔ መስጠት እንደሚችል ጥያቄዎች ተነስተው እንደነበር ዳይሬክቶሬቱ ጠቁሟል፡፡

ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ወ/ሮ መዓዛ፣ ‹‹በዴሞክራሲ፣ በልማትም ሆነ በሰላም ጉዳዮች እንደ ምሳሌ የምንወስዳቸው የምዕራብ አገሮች እንደኛው በርካታ ውስብስብ ሒደትን አልፈው አገር ግንባታ የፈጸሙ ናቸው፤›› ብለው፣ ብዙ ጊዜም የእነዚህ አገሮች ልምድ የሚጠቀስ ቢሆንም ልምዶቹ በቀጥታ እዚህ ተፈጻሚ ላይሆኑ እንደሚችሉ በማስረዳት፣ እ.ኤ.አ. በ1957 በአሜሪካ ከተሰጠ የፍርድ ቤት ውሳኔ አፈጻጸም ጋር በተገናኘ አንድ ታሪክ ለተወያዮች ማካፈላቸውን ዳይሬክቶሬቱ ገልዷል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1954 በአሜሪካ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነጮችና ጥቁሮች በተለያዩ የትምህርት ተቋማት መማራቸው ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ብሎ መወሰኑን፣ ይህንን ውሳኔ አርካንሰስ የተባለው ግዛት ለመፈጸም ባለመቻሉ በጊዜው ፕሬዚዳንት የነበሩት ድዋይት አይዘናወር ኃይል በመላክ የማስፈጸማቸውን ታሪክ መናገራቸውን ዳይሬክቶሬቱ አስረድቷል፡፡

እንደ ዳይሬክቶሬቱ ገለጻ ወ/ሮ መዓዛ ይህንን ምሳሌ ያቀረቡት፣ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ለማስከበር አገሮች እስከ ምን ድረስ እንደሚሄዱ ታሪክን ማወቅ ግንዛቤን ስለሚያሰፋ ነው፡፡ ‹‹በአገራችን ዳኞቻችን በየክልሉ በመዘዋወር የፌደራል ጉዳዮችን ለማየትና ለመወሰን የፍርድ ቤት ትዕዛዞችና ውሳኔዎች መተግበር ካልቻሉ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ሕዝቡ የሚያደርገው ጥሪ ባዶ መፈክር ነው፡፡ ይህንንም ሕዝቡ በሚገባ ይነገዘበዋል፤›› ማለታቸውን ዳይሬክቶሬቱ አውስቷል፡፡

‹‹ፍርድ ቤታችን ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለሕዝቡ ለማረጋገጥ ይወዳል፤›› እንዳሉም ዳይሬክቶሬቱ በላከው መግለጫ አስረድቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከረቡዕ ነሐሴ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. እስከ መስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በከፊል ዝግ ሆነው በውዝፍ መዝገቦች ላይ ውሳኔ እንደሚሰጡ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ዳኞች የዕረፍት ጊዜያቸውን ተጠቅመው ፍርድ ቤቶች ያሉባቸውን ውዝፍ መዝገቦች መርምረው ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ ፍርድ ቤቶች የዜጎች መብቶችን የሚያስከብሩ ተቋማት ስለሆኑ በከፊል ዝግ ሆነው በሚቆዩባቸው 50 ቀናት አስቸኳይና ጊዜ የማይሰጡ፣ ከዜጎች መሠረታዊ መብቶችና ከአገር ሰላምና ፀጥታ ጋር ግንኙት ያላቸው እንደ የጊዜ ቀጠሮ፣ የዋስትናና የዕግድ ጥያቄዎች፣ የመያዣና የብርበራ ትዕዛዞች፣ በተፋጠነ ሥነ ሥርዓት የሚታዩ የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች፣ እንዲሁም ከቤተሰብና ከሕፃናት ቀለብና አስተዳደግ ጋር የተያያዙ አጣዳፊ መሠረታዊ ጉዳዮች በተረኛ ችሎቶች እንደሚስተናገዱ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ በሚሆኑበት ጊዜ በዳኞች መልካም ፈቃድ የዕረፍት ጊዜያቸውን ተጠቅመው ወደ ቀጣዩ ዓመት የተሻገሩ መዛግብትን የማጥራት ሥራ እንደሚያከናውኑ ተገልጾ፣ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በ2011 ዓ.ም. እና ከዚያም በፊት የተከፈቱ ነገር ግን ለምርመራ፣ ለብይንና ለውሳኔ ለ2012 ዓ.ም. የተሻገሩ 4,702 መዛግብትን ለማጥራት ዕቅድ መያዙን ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ችሎቶች በከፊል ዝግ ሆነው በሚቆዩባቸው ቀናት፣ ከጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በፊት የተከፈቱና ወደ ቀጣዩ በጀት ለምርመራና ለውሳኔ ለተቀጠሩ 2,033 መዛግብት ዕልባት ለመስጠት ዕቅድ እንደተያዘም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን በተመለከተ መደበኛ ችሎት እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሚቀጥል፣ ከዚያ በኋላ ግን እስከ መስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም. በከፊል ዝግ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ ከአሥር በላይ የፍርድ ቤቱ ዳኞች ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሹመት የተዛወሩ በመሆናቸው፣ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት በከፊል ዝግ የሚሆኑባቸው ቀናት በ15 ቀናት መራዘሙን ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቶችን በከፊል ዝግ ሆነው እንዲቆዩ ማድረግ አሁንም ድረስ እንደ አንድ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አሠራር ሆኖ እንዲቀጥል ያደረገው ዋና ምክንያት፣ የዳኞች ዓመታዊ የዕረፍት ጊዜን እንደ ማንኛውም የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኛ በመደበኛ ወቅት ማካሄድ አሁን ካለው የዳኝነት አሠራር ጋር የሚጣጣም ሆኖ ባለመገኘቱ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ዳኝነት እንደ ሌላ ሥራ በውክልና የሚሠራ ሙያ ባለመሆኑ፣ አንድ ዳኛ በማንኛውም የሥራ ቀናት ዕረፍት ይውጣ ቢባል የችሎት ሒደቱን ሳይቋረጥ ማስቀጠል የሚቻለው በሌላ ዳኛ መተካት ሲቻል እንደሆነ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በእያንዳንዱ ችሎት ምርመራና ውሳኔ የሚጠብቁ በርካታ መዝገቦች ስላሉ ነው ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...