266 ቡና ላኪዎች ከዋጋ በታች በመሸጣቸው በብሔራዊ ባንክ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከዋጋ በታች በመሸጥና የሽያጭ ስምምነት ሲጥሱ በተደጋጋሚ የተገኙ ባላቸው ቡና ላኪዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥሪም ማስጠንቀቂያም ቢሰጥም ሊቀርቡ አልቻሉም ያላቸውን 81 ነጋዴዎች ላልተወሰነ ጊዜ ግብይት እንዳይፈጽሙ ከማገዱም ባሻገር፣ ከእነዚህ ውስጥ 26 ቡና ላኪዎች የንግድ ፈቃዳቸው እንዲታገድ መወሰኑን አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ ከኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ጋር በመሆን ለሁለት ቀናት በቢሾፍቱ ባካሄደው ውይይት ወቅት፣ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር ይፋ እንዳደረጉት እስካሁን ከ266 ያላነሱ ቡና ላኪዎች ለመሸጥ የገቡትን ኮንትራት ሲጥሱና ከዋጋ በታች ሲሸጡ በመገኘታቸው፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ባለሥልጣኑ በማስታወቂያ ጥሪ አቅርቦላቸዋል፡፡
በዚህ ጥሪ መሠረት ቀርበው ችግሮቻቸውን ላስረዱ በማስጠንቀቂያና በምክር፣ እንዲሁም የገጠማቸውን ችግር ለመፍታት ባለሥልጣኑ እንዳገዛቸው ተገልጿል፡፡ ይህም ሆኖ እስካሁን ጥሪ ቢደረግላቸው ሊቀርቡ ያልቻሉ 81 ላኪዎች የግብይት ዕገዳ እንደወጣቸው ሲገለጽ፣ ከእነዚህ ውስጥ 26ቱ በቡና ንግድ ዘርፍ እንዳይንቀሳቀሱ የንግድ ፈቃዳቸው ይታገዳል ተብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአገር ውስጥ በኮንቴይነር አሽገው ወደ ውጭ የላኩት ቡና በሥውር እየተከፈተ እንደተሰረቀባቸው ያስታወቁ ላኪዎች ያቀረቡትን አቤቱታ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይህንን ዝርፊያ የፈጸሙ ወንጀለኞችን ለመከታተልና ድርጊቱን ለማስቆም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፡፡
የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሑሴን ስለጉዳዩ ሲያብራሩ መንግሥት ባቋቋመው ግብር ኃይል በኩል ክትትል እያደረገ ቢሆንም፣ ላኪዎችም በውስጣቸው በዚህ ስርቆት ተባባሪ የሆኑትን እንዲያጋልጡ ጠይቀዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲህ ባለው ድርጊት ተባባሪ የሆኑ አካላት ‹‹የተሰረቀውን ቡና አብሮ የሚያፋልጉ ከሆነ መቼም ማግኘት አይቻልም›› በማለት ቡና ነጋዴዎችን አሳስበዋል፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ይህንኑ በማስመልከት ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር)፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር ለሚመራው የወጪ ንግድ ማስተባበሪያ ኮሚቴ መቅረቡን መግላጻቸው ይታወሳል፡፡
ስለዝርፊያው ሲገልጹም፣ ‹‹ረቀቅ ባለ መንገድ እየመጣ ያለ የቡና ቅበሻ ተግባር ነው፡፡ በሞጆና በጂቡቲ መካከል ባለው የጉዞ መስመር እየተከሰተ ነው፡፡ ላኪዎቹ አምነው ነው ቡናቸውን የሚያጓጉዙት፡፡ ከዚህ በፊትም ይህ ዓይነቱ ዝርፊያ የተፈጸመባቸው ኩባንያዎች አሉ፡፡ ለፖሊስም ለሚመለከተው አካልም ጉዳዩን አቅርበናል፡፡ እኛም እየተከታተልነው ነው፤›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ እስካሁን ከ500 ኩንታል በላይ ወደ ውጭ የተላከ ቡና ከኮንቴይነር መቀሸቡን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡