Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄዎች ጥናት ላይ ሕዝብ ለማወያየት ዕቅድ ወጣ

  በደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄዎች ጥናት ላይ ሕዝብ ለማወያየት ዕቅድ ወጣ

  ቀን:

  የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ከፍተኛ አመራሮች ማዕከላዊ ኮሚቴው ባቀረበው ክልሉን ‹55 ለአንድ› በማደራጀት ሐሳብ ላይ ሙሉ በሙሉ ሳይስማማ ስብሰባውን ቢያጠናቅቅም፣ በቀጣይ አሥር ቀናት ውስጥ የክልሉን አደረጃጀት በተመለከተ የተደረገው ጥናት ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች ላይ በየአካባቢው ውይይቶችን ለማድረግ ዕቅድ ወጣ፡፡

  ክልሉን 55 ለአንድ ማደራጀት ማለት ሲዳማን ክልል አድርጎ፣ ሌሎቹን 55 ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ ላይ ክልል ሆነው እንዲቀጥሉ ማድረግ እንደሆነ ታውቋል፡፡

  በደቡብ ክልል በተለይ ከአንድ ዓመት ወዲህ በስፋት እየተነሱ ያሉት የራስን ክልል የመመሥረት ጥያቄዎችን ‹ሳይንሳዊ› በሆነ መንገድ ለመመለስ ያስችለኛል በማለት፣ የክልሉ መንግሥትና ደኢሕዴን ያስጠኑት ጥናት፣ ግኝትና ምክረ ሐሳቦች ይፋ ከተደረጉና ማዕከላዊ ኮሚቴው ከተወያየበት በኋላ በሐዋሳ የደኢሕዴን ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ አድርገው ነበር፡፡ ሆኖም የወላይታና የካፋ ዞን አመራሮች የማዕከላዊ ኮሚቴውን የአደረጃጀት አማራጭ አንቀበልም በማለታቸው በልዩነት ስብሰባውን አጠናቀዋል፡፡

  የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴው ክልሉን ባለበት ማስቀጠል፣ ካልሆነም የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ የክልሉን ምክር ቤት የተሻገረና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ለምርጫ ቦርድ የሕዝበ ውሳኔ ጥያቄ የቀረበበት በመሆኑ፣ ሲዳማን እንደ ክልል በማደራጀት ሌሎቹን እንዳሉ ማስቀጠል የሚል ምርጫ አስቀምጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ አዳዲስ ማዕከላትን (ከተሞችን) በማደራጀትም ቀድሞ ከነበረው በአንድ ማዕከል የታጠረ አደረጃጀት የተለየና በየአካባቢው አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ የሚሉ አማራጮችን ይዟል፡፡

  ሆኖም ሁለቱ ዞኖች (ወላይታና ካፋ) ሕዝቡ ካቀረበው ጥያቄና ለክልል ማዕከል ካላቸው ርቀትና ከፍትሕዊ ተጠቃሚነት አኳያ ሲታይ፣ በማዕከላዊ ኮሚቴው የተቀመጠው አቅጣጫ ተቀባይነት እንደማይኖረው በመከራከር በልዩነት ወጥተዋል፡፡ በተጨማሪም የተከናወነው ጥናት አደረጃጀትን እንደ አንድ ችግር አለማንሳቱ ጥያቄ የቀረበበት ሲሆን፣ ‹‹ሕዝቡ መቼስ እነዚህን ችግሮች ቢፈቱልህ ባለህበት መቆየት ይሻልሃል?›› ተብሎ ቢጠየቅ መሪ ጥያቄ በመሆኑ ‹‹አዎ›› ማለቱ ስለማይቀር፣ የጥናቱ መነሻ የተዛባ ነው የሚሉ ክርክሮችም በስብሰባው ተደምጠዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ አደረጃጀቱ ያመጣቸው ችግሮች የጥናቱ አካል ሆነው መጠናት ነበረባቸው በሚሉ መከራከሪያዎች፣ መደምደሚያ ላይ የደረሰ ጥናት ነው በሚል ትችት ቀርቦበታል፡፡

  ልዩነቱን ይዞና በማጠቃለያ ሪፖርቱ አካትቶ ከሐምሌ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለሰባት ቀናት የተካሄደውን ስብሰባ ያጠናቀቀው የደኢሕዴን ከፍተኛ አመራሮች መድረክ በየደረጃው ሕዝቡ እንዲወያይ የሚል አቅጣጫ ማስቀመጡን፣ በዚህም መሠረት ሕዝቡ የሚወያይበት መርሐ ግብርና ዕቅድ ወጥቶ እየተሠራ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

  የክልሉን የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ለማጥናት የተቋቋመው 20 አባላት ያሉት ቡድን ለሰባት ወራት ጥናቱን ማካሄዱን ሐምሌ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል በሰጠው መግለጫ ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን፣ ጥናቱ ሦስት ምክረ ሐሳቦችን አቅርቧል፡፡ የመጀመርያው ምክረ ሐሳብ ክልሉን አሁን ባለበት ቅርፅ ማስቀጠል፣ ሁለተኛው ክልሉን በሁለት ወይም ከአምስት ባልበለጡ የተለያዩ ክልሎች ማዋቀር፣ ሦስተኛው ደግሞ አሁን እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ለአገራዊ ደኅንነት ሥጋት የሚሆኑ ከሆነ ጥያቄዎችን ለጊዜው ማቆየት ተገቢ ነው የሚሉ ናቸው፡፡

  ጥናቱ ‹ሳይንሳዊ› መንገድን ተከትሎ እንደተካሄደ ባለሙያዎቹ የገለጹ ቢሆንም፣ የተለያዩ አካላት ጥናቱን ሲያጣጥሉና ሲተቹ ተደምጠዋል፡፡ ሆኖም የጥናቱ ቡድን አባላት ጥናቱ ያስቀመጣቸው ሦስት ምክረ ሐሳቦች ለሁሉም የፍላጎት ቡድኖች የሚሆኑ ናቸው በማለት ይከራከራሉ፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...