Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዙረት አይታክተን እስኪ እንወዝወዘው!

እነሆ መንገድ። ከስታዲየም ወደ ቃሊቲ ልንጓዝ ነው። ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?›› ይላል ጋቢና የተሰየመ ባለባርኔጣ። ‹‹ቀን ምን አለበት ቤንዚን አይፈልግ ናፍጣ አይፈልግ። እኛ ነን እንጂ ሄድ ቆም እያልን የተቸገርነው፤›› አለ ሾፌራችን መጠጥ ያለ ጉንጩን እየፈተገ። ‹‹ቆይ ምንድነው ችግሩ?›› ጠየቀች ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ወይዘሮ። ‹‹ዝናብ!›› አለ ወያላው ነገር ባዘለ ድምፀት። “ኤታኖል አልበቃን ብሎ ደግሞ ብለን ብለን ነዳጅ በዝናብ ውኃ ማቅጠን ጀመርን እንዴ?›› ትላለች ልጅ በመታቀፊያ ዕድሜያዋ ጣሊያን የሠራው አንዳች የሚያህል ቦርሳ ታቅፋ። ‹‹ምናችን ይገባና ልጄ? እጥረት የሚተካው በሌላ እጥረት ነው። ዝናብ ሲያጥረን ነዳጅ ይሞላል። ዝናብ ስንጠግብ ነዳጅ ይጠፋል. . .›› ብለው መሀል መቀመጫ የተሳፈሩ አዛውንት አጉተመተሙ፡፡ ‹‹ዓለም ዘጠኝ ነው አይሉም በአጭሩ. . .›› ብሎ ከሦስተኛው ረድፍ ከጦር የሚረዝም መፋቂያ አፉ ውስጥ የሸጎረ ወጣት ተናገረ፡፡ ‹‹የለም እኛስ ላይ ስድስትም ሰባትም አትደርስ፤›› ብለው ዞረው አጠኑት።

ይኼኔ ደግሞ መጨረሻ ወንበር የተሰየመች የቀይ ብስል፣ ‹‹ዝናብ ብላችሁ በደንብ ሳታስረዱን ስለዓለም ጎዶሎነት የምታወሩት ነዳጅ ከየት ቀድታችሁ ነው?›› ብላ ጨዋታውን መለሰችው፡፡ ‹‹ጂቡቲ ወደብ የጣለ ኃይለኛ ዝናብ ነው ይላሉ የአቅርቦት እጥረቱን የፈጠረው፤›› ብሎ ወያላው አንጠልጥሎ የተወውን መረጃ ደመደመው። ‹‹አሁን አንሄድም እንሄዳለን? ወሬ ነው ነዳጅ ነው ያጠረህ ሾፌር? ለምን አንቀሳቀስም?›› ባዩ ቶሎ ተቆጪ ደግሞ ከመጨረሻ ወንበር አንባረቀ። ‹‹ቆይ ትንሽ ይሙላ፤›› አለው ወያላው። ‹‹አሥራ ሁለት ሰዎች ጭነሃል። በቃ ግባና ዝጋው፤›› ቁጣው ጨመረ። ‹‹ምን አዳረቀህ ልጄ? በቃ እኮ ነገረህ። ጎድለናል ተብለናል ጎድለናል ነው። እሱ ሞልታችኋል እስኪለን ዝም አትልም? በገዛ እጃችን ያለ አቅም ግንባታ ተዋልደን ተዋልደን በዝተን የጎደልን እኛ። ተወው እስኪ. . .›› ብለው አዛውንቱ በምፀት ተናገሩ። በክረምት ምድር ውኃ ሞልቶ ስለነዳጅ እጥረት ሲወራ ምን ይባል ታዲያ?

ጉዟችን ተጀምሯል። ሾፌሩ ቀልቡን ሰብስቦ ያዳምጥ ይመስል ሬዲዮኑን ከጣቢያ ጣቢያ ይፈትሻል። ጣቢያው ሁሉ በአሸሼ ገዳሜ መንፈስ የታጠነ ነው። ይኼኔ ወይዘሮዋ “ይገርማል እኮ!” ትላለች። “ምኑ?” ትላታለች ከጎኗ። “እንዲያው የእኛ ነገር። መንግሥትና ታጣቂ ሲባል እየፈራን አድገን ልማትና ራዕይ አንጋራም እየተባለ፣ አሁን ማን እንደሚያዛልቅና እንደማያዛልቅ አየን፤” አለቻት በደፈናው። “አልገባኝም?” ስትላት፣ “ይኼው እኔ ኮንዶሚኒየም ተመዝገቢ ስባል እንቢ ብዬ ሪልስቴት የሚባል ነገር አምኜ ከገንዘቤም ከቤቴም ሳልሆን አሥራ አንድ ዓመት አለፈኝ። ሌላው ቢቀር ዝም ብዬ ያን ያህል ዓመት የከሰከስኩትን ገንዘብ ይዤ ዛሬ ካርድ እየሞላሁ ብጨርስው ኖሮ፣ ወይ ከግድቡ ወይ ከቤት ተሸላሚዎቹ ስም ዝርዝር ስሜ አይጠፋም ነበር፤” አለቻት። “አሁንም አረፈደም!” ብሎ ባለመፋቂያው ሊያጽናና ፈለገ።

“ልክ ነው ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው፤” ወይዘሮዋ ድጋፉን አጣጣለችበት። “እሱ እንደ አቀማመጡ ይወሰናል፤” ባዩ መጨረሻ ወንበር ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ተሳፋሪ ነው። “ምን ማለት ነው?” አዛውንቱ ጠየቁት። በየሜዳው የዘራና ቦንድ የገዛ አንድ ነው እንዴ አባታችን?” ሲላቸው፣ “ወደን መሰለህ በየሜዳው የምንዘራው? አምነን እንጂ፤” አሉት አቀርቅረው። “እሱ ነዋ ችግሩ። ዕድገታችን በትጋትና  በሥራ ነዋ ዕውን መሆን ያለበት፤” ብሎ ቀጠለ። “ተወኝ እስኪ ልጄ። ምጥ ለእናቷ አታድርገውማ። ወደን አይደለም አልኩህ የተቀጠፍነው፡፡ ወደን አይደለም ዘር ሁሉ በወደቀበት መሬት እንደማያፈራ ቀድሞም ልቦናችን ያውቀው ነበር፤” ከማለታቸው ከአፋቸው ነጥቆ፣ “ዕድሜ ለለውጥ ዘመናችን ያለውን የማይሰጥ መሬት የለንም፤” ቢላቸው፣ “ማዳበሪያው ከእኛ ነው ከመንግሥት?” ብለው አዩት። “እሱ እንደ አደረጃጀታችን ይወሰናል፤” ብሎ አረፈው። ወይ ሰውና ነገሩ! 

ወያላው ገንዘቡን በንቃት ይሰበስባል። መጨረሻ ወንበር ያለው ተሳፋሪ ሦስተኛ አጠገቡ የተሰየመችውን እንስት በፌስታል የተቋጠረ አረንጓዴ ቅጠል አውጥቶ እያሳያት ዝገኝ ይላታል። “ኧረ በስመአብ በል። ደግሞ ብዬ ብዬ ጫት ልቃም?” አለችው ድፍረቱ ገርሟት። “ታዲያ ምን ልጋብዝሽ የእኔ ቆንጆ? ሰው ባለው ነው፤” ማባበል ያዘ። “ባይሆን ፆም እስኪያልፍ ምናለበት ብትተወው?” አለችው በቀናነት ከሥጋው አልፋ ለነፍሱ ተጨንቃ። “እንዴ ይኼም እኮ ጎመን በይው አልተቀቀለም እንጂ፤” ይላታል። “ኧረ ይቅር ይበልህ፤” ብላ ልትዘጋው ስትል፣ “ጎመንም ጫትም፣ አበባም ሱፍም ይብቀሉ ያለው አምላክ ነው። ቆይ ሰው ምንድነው ችግሩ? ያለ መፈራረጅ መኖር አንችልም በቃ? ሰው ላይ ለመፍረድ አንደኞች ነን። በፍትሕ ዕጦት ተሰቃይቶ ሰው በቁሙ ማቆ ሲሞት ያላየን ያልሰማን መሆን የተካንበት ነው። ምንድነን ግን እኛ?” እያለ ተፈላሰፈ፡፡ ጎልማሳው ዘወር ብሎ፣ “ገባልህ መሰለኝ፤” አለው እየሳቀ። “እንደ ነገሩ ባይሆንም እየገባልኝ ነው። ግን በፈጠረህ ልጠይቅህ እስኪ እኛን ለሥራ፣ ለልማት፣ ለትምህርትና ለፈጠራ እንዳንነሳሳ የሚያዳክመን እውነት ቀጭ ቀጭ ነው? ቢሮክራሲው ነው?” አለው። ጎልማሳው ብዙ ሳያስብ፣ “ሁለቱም!” አለው። “የቱ ይብሳል እሺ?” በአግቦ፣ በሽሙጥና በተቃውሞ የተሞላው ቃሚ ተብሰልስሎ ጠየቀ። “ከዋለ ካደረ እንኳን ይኼ ውኃም ደስ አይልም። እንኳን ይኼ ያመኑት ፈረስም በደንደስ መጣሉ አይቀሬ ነው። አንተስ ብትሆን ይኼን ያህል ተቀባይነት ለማግኘት ለምን ተጭነህ ያዝከን? ክፉና ደጉን ልቦናህ እየነገረህ ከራስህ ስለምትጣላ አይደለም?” ብሎ ዝም አስባለልን። ፀባችንና ምላሳችን የራሳቸው ካምፕ አላቸው ማለት ነው?

ጉዟችን ቀጥሏል። መጨረሻ ወንበር ላይ ከተቀመጡት ወጣቶች በወዲያ በኩል በሾፌሩ ትይዩ ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ተሳፋሪ ደግሞ በስልክ ይነጋገራል። “እንዴት ነሽ? ደህና ነሽልኝ? ወይ አትጋበዢ ወይ አትጋብዢ? ቆይ ግን አንቺ ምን ይሻልሻል?” ይላል። ሌላ ነገር ያወራል ስንለው አሁንም፣ “ወይ አትጋበዢ? ወይ አትጋብዢ” ይላታል። ይህቺኑ ሦስት አራት ጊዜ ደጋገማት። “ለካ ለአንዳንዱ ስልክ የሚሠራው በውኃ ሆኗል፤” ብሎ አንዱ አሽሟጠጠ። “ሥራ የፈታ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል ሲባል አልሰማህም፤” ትላለች ሌላዋ። “እኔ ምለው ጎበዝ በረባ ባረባው ቴሌ የሚያንጋጋብንን ቴክስት ማስቆም የሚቻለው እንዴት ነው?” ጎልማሳው ይጠይቃል። “ቆይ እስኪ ተረጋጉ። አንድን ነገር አንድ ጊዜ ነው መከወን የሚቻለው። መጀመርያ ምድረ አገር አፍራሽ አደብ ይግዛ። ከዚያ ስለ ቴሌ እንነጋገራለን፤” ብለው አዛውንቱ ጨዋታው ላይ ተሳታፊ መሆን ጀመሩ።

“ቆይ ግን አንቺ አትጋብዢ ወይ አትጋበዢ?” ባለ ስልኩ ሞዛዛ ወቀሳውን ደገመው። “ኤጭ! ምንድነው ይኼ ሰውዬ ወይ አይጋብዘን ወይ አያስጋብዘን አደረቀን እኮ ባዶ ሆዳችንን፤” ብላ ያቺ የቀይ ዳማ ስትናገር ጋባዥና ተጋባዥ፣ ጉዳይና ባለጉዳይ፣ ሸማችና ኑሮ ያልተገናኙበት ዘመን፤” ብሎ ጎልማሳው ጠቀሳት። ያ ቅጠል ቀንጣሹ ተሳፋሪ በበኩሉ፣ “አልሰማችሁም እንዴ?” ብሎ ጣልቃ የገባው ይኼኔ ነው። “ምኑን?” አልነው አንድ ላይ። “ባለቀ ሰዓት የአሸናፊነትና የአቻነት ጎል እየተቆጠረ መሆኑን?” አፈጠጠብን። “ምንድነው የሚያወራው?” ተባብለን ሳንጨርስ፣ “ተስፋ አለመቁረጥ ነው። ልክ እንደ ጎበዝ ቡድን በባከነ ሰዓት ጭምር ከታገልን ከመመራት ወደ መምራት የምንሸጋገርባቸው ጊዜያት ይመጣሉ። ጋባዥና ተጋባዥ፣ ጉዳይና ባለጉዳይ የሚገናኝበት ዘመን ቅርብ ነው፤” ብሎ አብራራው። በባከነ ሰዓት ባክኖ የማይቀር ምንኛ ዕድለኛ ነው!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ረዥሙ ጉዟችን ሊገባደድ ጥቂት ቀርቶታል። “የሲዳማው ጭፍጨፋ ልቤን እንዴት እንደሰበረው ብታይ?” ትላለች ወጣቷ የወይዘሮዋን ዓይን ዓይን እያየች። “መቼስ ምን ይደረጋል? አንዳንዱ የሰው ልጅ ገና ብዙ የሚቀረው መሆኑን ታያለሽ። አንዳንዱ ደግሞ ከራሱ፣ ከዘመዱና ከአገሩ አልፎ ለከዋክብቱና ለጨረቃ ሲተርፍ ትታዘቢያለሽ። አስቸጋሪ እኮ ነው፤” ብላ ወይዘሮዋ እንደተናገረች፣ “እንዲያው ሌላው ቢቀር የመንግሥት ባለሥልጣናት ንፁኃንን የሚጨፈጭፉና የሚያፈናቅሉ ሕግ ፊት በፍጥነት መቅረባቸውን ቢነግሩን? የኑሮ ውድነቱ እንዴት ሊረግብ እንደሚችል የፖሊሲ መፍትሔዎችን ቢነግሩን? አገራችን በየትኛው የተሻለ አማራጭ ብትመራ ነው የምታድገው? ሌሎችንም ጥያቄዎች እያነሳን መነጋገር ሲገባን፣ ነጋ ጠባ እንደ ሌሊት ወፍ ካገኘነው ነገር ጋር እየተላተምን እርስ በርስ ጣት እንቀሳሰራለን. . .” ሲሉ አዛውንቱ ፈገግ አልን።

“እውነት ነው። በብዙ ሥፍራዎች አስተዋይነት፣ ንቃትና ብስለት ገና ብዙ ስለሚቀሩ ግጭቶች ቢከሰቱ አይገርምም። ግን እኔን የገረመኝ በስመ አክቲቪስትነት ተምረናል የሚሉ መሃይሞች በማኅበራዊ ትስስሮች አገር ለማጥፋት ታጥቀው መነሳታቸው ነው፤” አለ ጎልማሳው። “ምን የማይሉት አለ እነሱማ። በሰው ደም እየነገዱ አጉል ተቆርቋሪ ሆነው ሲቀርቡና ሲያታልሉ ዝም መባላቸው ያበግናል፤” የሚለው አንድ ታዳጊ ነው፡፡ አዛውንቱ፣ “የእነሱ ጉዳይ ተከድኖ ይብሰል፡፡ እስኪ መጀመርያ ችግኞቻችንን እናፅድቅና ወደ እነሱ እንመለሳለን፡፡ የእጃቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ ደግሞ እያንዳንዱን ድርጊታቸውን መመዝገብ አለብን፡፡ ይህ ሪከርድ ፍርድ ቤት ለማቅረብ ያገለግለናል. . .” ሲሉን ወያላው “መጨረሻ!” ብሎ በሩን ከፈተው። ቃሊቲ ደርሰናል። አዛውንቱ ቀድመውን እየወረዱ፣ ‹‹እንግዲህ ነገራችንን እዚህ ላይ ስናጠናቅቅ አንድ ነገር መርሳት የለብንም፡፡ ‹ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት› እንዲሉ እስከዚያው ድረስ ዙረቱም አይቀርም፣ እኛም መወዝወዛችን ይቀጥላል. . .›› ብለውን ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት