የሞተር ብስክሌት አገልግሎት በአዲስ አበባ ለሚገኙ በርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረና ለተጠቃሚውም ሥራን ያቀለለ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሞተር ብስክሌት ላይ ተፈናጠው ዝርፊያ የሚፈጽሙ በመበራከታቸውና በየመንገዱም አስከፊ የትራፊክ አደጋዎች በመብዛታቸው የከተማዋ አስተዳደር ፈቃድ ያልተሰጣቸው የግል ሞተር ብስክሌቶች እንዳይንቀሳቀሱ ማገዱ ይታወቃል፡፡
በየጎዳናው መንቀሳቀስ የሚችሉት በድርጅት ሥር ሆነው ሰሌዳ ቁጥራቸው ኮድ ሦስት ባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪዎች ብቻ ሲሆኑ፣ ሞተረኛው የሚሠራበትን ድርጅት ዓርማና ስልክ ቁጥር የተለጠፈበትን ሞተር ብስክሌት እንዲያንቀሳቅስ ብሎም የደንብ ልብስ እንዲለብስ አዲሱ አሠራር ያስገድደዋል፡፡ በዚህ መመርያ ምክንያትም በርካታ ሞተረኞች ሥራ ለማቆም በመገደዳቸው ቅሬታና ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ሰንብተዋል፡፡
ሆኖም ‹‹ተላላኪ ኤክስፕረስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› የተባለው ድርጅትና የከተማውን አስተዳደርና ባለሞተር ብስክሌቶቹን ሊያስታርቅ የሚችል ሐሳብ ይዞ እንደመጣ በማስታወቅ ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
አቶ ናትናኤል ኤቲቻ የተላላኪ ኤክስፕረስ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ‹‹የተፈጠሩትን ችግሮች ግራና ቀኝ በመመልከት ወጣቶቹ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ መንግሥትም ለቁጥጥር በሚያመቸው መልኩ እንዲንቀሳቀስ ድርጅታችን በጂፒኤስና በፊሊት ማኔጅመንት ተደራጅቶ ሞተረኞች አስፈላጊውን መሥፍርቶች አሟልተው በዘመናዊ መልኩ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ድርጅታችን ዝግጅቱን ጨርሷል፤›› ብለዋል፡፡ ሞተረኞቹን መመዝገብ እንደተጀመረም አስታውቀዋል፡፡
በመሆኑም አቅጣጫ አመላካች ወይም ጂፒኤስን ጨምሮ ሌሎችም አገልግሎቶችን አካቶ በመጣው ሥርዓት ለመሳታፍ ምዝገባ ተጀምሯል ያሉት የድርጅቱ ኃላፊዎች፣ ስለምዝገባ ሒደቱ ሲናገሩ ሞተረኞቹ ወደ ድርጅቱ ሲሄዱ ስለራሳቸውና ስለንብረታቸው የሚገልጹ መረጃዎችን ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ኩባንያውም የቀረቡለት መረጃዎች ትክክለኛነታቸውን በአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በኩል አጣርቶ ሕጋዊነታቸውን ሲረጋገጥ እንደሚመዘግባቸው አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ኮድ ሁለት ለሆኑና የክልል ታርጋ ላላቸው ሞተረኞች ኩባንያው ሒደቱን በራሱ እንደሚያስጨርስ ገልጸው፣ ባለንብረቶቹ ወይም ሞተረኞቹ መረጃዎቻቸውን አደራጅተው መቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አክለዋል፡፡ ሥራውን ከብርሃን ባንክና ከብርሃን ኢንሹራንስ ጋር በመተባበር የተደራጀ የሞተረኛ አገልግሎት ለመስጠት ኩባንያው መነሳቱን የጠቀሱት፣ የተላላኪ ኤክስፕረስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ዮሐንስ ናቸው፡፡ ‹‹ሞተር ኢንሹራንስ ኖሮት አያውቅም፡፡ እኛ በምንሰጠው አገልግሎት ግን ከሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ በተጨማሪ ዋስትና ይኖራቸዋል፤›› በማለት ይህን ሥራ ዓይተው ፍላጎቱ ለሚኖራቸው ሌሎች አገልግሎት አቅራቢዎችም ብድር ማግኘት የሚችሉበት መንገድ መመቻቸቱን ጠቅሰዋል፡፡
ተላላኪ ኤክስፕረስ ለሞተረኞቹ ስለሚሰጣቸው አገልግሎት ሲያብራሩም፣ ባለንብረቶቹ በራሳቸው ሞተር ብስክሌቶች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ያግዛቸዋል ብለዋል፡፡ ለወጣት ሞተረኞች የሥራ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ ለብዙዎች የገቢ ምንጭ እንደሚሆን አክለዋል፡፡
ተላላኪ ኤክስፕረስን የሚቀላቀሉ ሞተረኞች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል ተብለው ከተቀመጡ መሥፈርቶች መካከል ኮድ ሦስት ታርጋ ያለው ሞተር ብስክሌት ማስመዝገብ፣ ሙሉ የመድን ዋስትና መግባት፣ ሞተር ብስከሌት ለማሽከርከር የሚያበቃ መንጃ ፈቃድ ማቅረብ፣ ጂፒኤስ ማስገጠም፣ የዕቃ ማስቀመጫ ሳጥን መግጠም፣ ሥልጠና መውሰድና ሙሉ የሞተር ብስክሌት ደንብ ልብስ ማሟላትን ያካትታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሞተር ብስክሌቶቹ የጎን ቁጥር ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
በደኅንነት ዙሪያ ኩባንያው ጥብቅ የአሠራር ሥርዓት እንደሚከተል አቶ ዳንኤል ገልጸው፣ ሞተረኞቹ ውድ ንብረቶችን ወይም ሰነዶችን ከቦታ ቦታ በሚያጓጉዙበት ወቅት፣ ለሚጓጓዘው ዕቃ የመድን ዋስትና እንደሚሰጥ ይፋ አድርገዋል፡፡ በቴክኖሎጂ የታገዘ የ24 ሰዓት ጥበቃ በየፈረቃው እንደሚኖርም ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ማንኛውንም ዕቃ ሲያደርሱና ሲረከቡ ዕቃውን እንዲረከብ ለተመዘገበው ሰው ብቻ እንደሚያስረክቡም ተብራርቷል፡፡ ከዕቃ በስተቀር ተሳፋሪ ማጓጓዝ እንደማይችሉ የገለጹት አቶ ዳንኤል፣ ዕቃ የማድረስና የመላላክ አገልግሎት ብቻ እንደሚሰጡ አስምረውበታል፡፡ የሥራ ሰዓታቸውም ከጠዋቱ 12፡00 እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ የአገልግሎት ታሪፋቸው ምን ያህል እንደሚሆን ወደፊት ይገለጻል ብለዋል፡፡
ስለጂፒኤስ ሥርዓቱ ሲገልጹም፣ ቴክኖሎጂዎቹ በቀላሉ የማይበላሹና በእርጥበትና በመሳሰሉት ችግሮች ሥራ የማያቆሙ ‹‹ልክ እንደ ብላክ ቦክስ›› በማንኛውም የአየር ፀባይ ውስጥ መረጃ የሚልኩና የሚያሳዩ ለክትትል የሚያመቹ ስለመሆናቸው አስረድተዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉትን ሞተር ብስክሌቶች በጠቅላላ ማሠራት የሚችል አቅም እንዳላቸውም ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡
ይሁንና ድርጅቱ ለዚህ ሥራ ከመንግሥት ፈቃድ ማግኘቱን በተመለከተ ለማጣራት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) ከሪፖርተር ተጠይቀው እንደገለጹት፣ ‹‹ድርጅቱን አናውቀውም፡፡ ከየትኛው ክፍለ ከተማ ፈቃድ እንዳገኘ እያጣራን ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ዳንኤል በበኩላቸው፣ ‹‹ይኼ የትራንስፖርት አገልግሎት አይደለም፡፡ ይኼ የፈጣን አገልግሎት መልዕክት ስለሆነ ፈቃዱን ያገኘነው ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ነው፤›› ብለዋል፡፡ ወደ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪው አካል የሚያስኬዳቸውም ኮድ ሁለት የሆኑትን ሞተር ብስክሌቶች ወደ ኮድ ሦስት ለመቀየር ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሕጉ የሚጠይቀውን እስካሟላን ድረስ ፈቃድ ሊሰጠን ግድ ይላል፤›› ብለዋል፡፡
ተላላኪ ኤክስፕረስ 100 ሞተር ብስክሌቶች እንዳሉት የገለጹት አቶ ዳንኤል፣ ሰኞ ከሰዓት ጀምሮ ወደ ሥራ እንደገቡም ይፋ አድርገዋል፡፡ ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን ለማግኘት የማስተግበሪያና አጭር የስልክ መልዕክትና ጽሑፍ መላኪያ ቁጥር እንደተዘጋጀ ገልጸው፣ ይህም በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ከተላላኪ ኤክስፕረስ በተጨማሪም ሌሎች በተደራጀ መንገድ የሞተር ብስክሌት አገልግሎት ለመስጠት እንቅስቃሴ የጀመሩ ግለሰቦችና ድርጅቶችም ሥራ ለመጀመር ዳር ዳር እያሉ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡