Monday, December 4, 2023

አማራጭ ሐሳብ ባለማቅረብ የሚተቹት ተቃዋሚ ፓርቲዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በአሜሪካ የበላይነት መጠናቀቅን ተከትሎ ለታዳጊ አገሮች ያበረከተው አስተዋጽኦ በውክልና ሲደረጉ የነበሩ ጦርነቶች መጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን፣ የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ሥርዓት ግንባታ መጀመርም እንዲሁ ተጠቃሽና ዋነኛው ትሩፋት ነው፡፡

በታዋቂው የፖለቲካ ሳይንስ ሊቅ ሳሙኤል ሐንቲንግተን ዴሞክራሲ ወደ ታዳጊ አገሮች በዋነኛነትም ወደ አፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካና የእስያ አገሮች ያደረገውን መስፋፋት ሦስተኛው ማዕበል (The Third Wave) በማለት የሚገልጸው ሲሆን፣ በዚህ የምዕራባውያን የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳቦችና እሴቶች ወደ ከተጠቀሱት ክፍለ አኅጉራት ለመዛመትና የፖለቲካ ሥርዓቱ መገለጫ ለመሆን ተሸጋግረው ነበር፡፡

በ1983 ዓ.ም. የሥርዓት ለውጥ ያደረገችው ኢትዮጵያም የዚህ የሦስተኛ ማዕበል አካል የነበረች በመሆኗ፣ ለ17 ዓመታት ያህል ሲካሄድ የነበረውን የትጥቅ ትግል በአሸናፊነት ያጠናቀቀውና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመመሥረት የቻለው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)፣ በአገሪቱ ውስጥ የመደራጀትንና  የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋምንና መታገልን ሕጋዊ ዕውቅና ሰጥቶት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመመሥረት በቅተዋል፡፡

ምንም እንኳን ቅድመ 1983 ዓ.ም. የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴና ተሳትፎ ሕጋዊ ዕውቅና ባይቸረውና የተከለከለ ቢሆንም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጅማሮ ግን ወደ 1960ዎቹ ዘመን የሚያመራ ነው፡፡ እርግጥ ነው በወቅቱ የነበሩ ፓርቲዎች ሕጋዊ ዕውቅና ባለማግኘታቸውና በወቅቱ በነበረው ወታደራዊ ሥርዓት እንደ ጠላት በመቆጠራቸው ምክንያት፣ አብዛኛው የከተማ እንቅስቃሴያቸው በህቡዕ የነበረ ከመሆኑም በላይ የትጥቅ ትግል ማካሄድና ሥርዓቱን መለወጥ ዋነኛ የፖለቲካ መንገዳቸው ነበር፡፡ ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰባቸውም በወቅቱ ፋሽን በነበረው በሶሻሊዝም የተቃኘ ነበር፡፡

በ1983 ዓ.ም. የተከሰተውን የሥርዓት ለውጥ ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲ መመሥረት በሕግ መደንገጉን፣ እንዲሁም የሽግግር ጊዜ ቻርተሩ ከተጠናቀቀ በኋላ በፀደቀው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ሕጋዊ ዕውቅና ማግኘት ተከትሎ፣ በአገሪቱ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሥርተው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

ምንም እንኳን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በርካታ ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሆነ በመጥቀስ መኖራቸው አስፈላጊና ጠቃሚ እንደሆነ በመግለጽ ቢያትቱም፣ በበርካታ የዘርፉ ምሁራንና አስተያየት ሰጪዎች ዘንድ ግን በተቃራኒው በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የተቃውሞ ጎራው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ያህል አስተዋጽኦ አላበረከቱም በሚል ተቃውሞ ይሰነዘርባቸዋል፡፡

በዋነኛነት ይህን አስተያየት የሚሰነዝሩ የዘርፉ ምሁራንና ባለሙያዎች ፓርቲዎቹ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ያዳገታቸው የሚመሠረቱበትና የሚደራጁበት ምክንያት ብሶትን ለማርገብ፣ በብሔር ዙሪያ ተደራጅተው አገራዊ ከሆኑ የጋራ አጀንዳዎች ይልቅ ክልላዊ አስተሳሰቦች ላይ ማተኮራቸው እንደሆነ በመግለጽ፣ የጠራ የርዕዮተ ዓለም በመሰነቅ በአገሪቱ ለሚስተዋሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችና ፈተናዎች አማራጭ የሆኑ ሐሳቦችን በማመንጨት ለሕዝቡም አማራጭ መሆን፣ መንግሥትንም በቅጡ የሚሞግትና የሚፈትን ሐሳብ ማመንጨትና መወዳደር ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

ይህን ሐሳብ የሚሰነዝሩት ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ሁኔታ መንግሥት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማዳከም የሚያወጣቸው ሕጎችና አሠራሮች አስቸጋሪ መሆናቸውን እንደሚገነዘቡ በመግለጽ፣ ይህም ቢሆን ግን ፓርቲዎች የተጠናከረ አደረጃጀትና በተለይም የጠራ የርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ አቋም በመያዝ ሊቋቋሙት እንደሚችሉ ይሞግታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድክመትን በተመለከተ ሁለት ዓበይት ምክንያቶች በዋነኛነት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ እነሱንም ውስጣዊና ውጫዊ በማለት ይገልጹዋቸዋል፡፡ ውጫዊው በዋነኛነት ከመንግሥት በሚደርስ ጫና እንደሚገለጽ ውስጣዊው ደግሞ የተጠናከረና ሁሉን አቀፍ አደረጃጀት መፍጠር አለመቻልና የርዕዮተ ዓለም ግልጽ አለመሆን ማለትም የውስጥ ዴሞክራሲ፣ የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎ ውስን መሆን፣ የገንዘብ ችግር፣ እንዲሁም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የዓላማ አንድነት በመሰነቅ መንግሥትን መፎካከር አለመቻል መገለጫዎቹ እንደሆነ ያብራሩታል፡፡

‹‹Political Parties Party Program Matocity and Party System in Post 1991 Ethiopia›› በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የፕሮግራም አዘገጃጀትና ጥንካሬን በተመለከተ ጥናት ያደረጉት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ሰለሞን ገብረ ዮሐንስ፣ በተፈጠሩበት የብሔር ሥርዓት ወይም ደግሞ በሌሎች ምክንያቶች የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሻለና አስተማማኝ አማራጭ ሐሳቦችን አለማመንጨትና ግልጽ የሆነ የርዕዮተ ዓለም መስመር አለመያዛቸው ለትችት እንደሚዳርጋቸው ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአብዛኞቹ የተቃውሞ ጎራው ፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔር በመደራጀታቸው ከጠንካራ የሲቪል ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ መሆናቸው ወጥና ጠንካራ ፕሮግራም እንዳይኖራቸው እንቅፋት እነደሆነ በመግለጽ፣ ዓይነተኛ ሚናቸውን ይጫወቱ ዘንድ ፕሮግራማቸውና ግባቸው ምን እንደሆነ በማስታወቅና በመተንተን ሕዝቡን ከጎን በማሠለፍ ሚናቸውን መወጣት የሚያስችል መደላድል መፍጠር እንደሚገባቸው ያሳስባሉ፡፡

በዚህ አጠቃላይ ብያኔ የሚስማሙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ባልደረባ አቶ አዳነ አለማየሁ በበኩላቸው፣ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ከታች ጀምረው ሐሳባቸውን በመቀመር ሕዝቡን ለማንቃትና ለማታገል ያላቸው ሚና አነስተኛ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ድርጅት ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲ አለ ወይ የሚለው መታየት አለበት፤›› በማለት፣ በአገሪቱ ውስጥ ፖለቲካን እንደሚሠሩ የሚገልጹ የፖለቲካ ድርጅቶች እንጂ፣ በመሠረታዊ የፖለቲካ ፓርቲ ባህሪያት ዙሪያ  የተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለመኖራቸው ይጠይቃሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምሥረታ ከ1960ዎቹ ህቡዕ እንቅስቃሴ የተቀዳ መሆኑን በመጥቀስ፣ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ‹‹በተደራጀ መልኩ አቋም ይዘውና ለማሳካት የምንፈልገውና የምንመኘው ይህን ነው በማለት የጠራ አቋምም ሆነ ርዕዮተ ዓለም ይዘው ዓይቼ አላውቅም፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በእርግጥ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር በአጠቃይ አሳታፊ በሆነ መንገድ መታከም እንዳለበት ቢገልጹም፣ ከዚህ እኩል ግን ግለሰባዊ ምኞቶችና ህልሞች ላይ የተንጠለጠሉት የአገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ራሳቸውን መመልከትና ማከም አለባቸው ብለዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ አማራጭ ለማቅረብ ውስጣቸውን መፈተሽ እንደሚኖርባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ለውይይት የቀረበው ረቂቅ የፖለቲካና የምርጫ አዋጅ ላይ ተቃዋሚዎች ለምሥረታ ለአገር አቀፍ ፓርቲ 10,000፣ እንዲሁም ለክልል ፓርቲዎች ደግሞ 4,000 ፊርማዎች ያስፈልጋሉ የሚለውን መሥፈርት መቃወማቸው፣ ምን ያህል ከሕዝብ እንደተነጠሉና የ10,000 ሕዝብ ፊርማ እንኳን ማሰባሰብ እንደሚከብዳቸው መጥቀሳቸው የድክመታቸው ማሳያ እንጂ ሌላ ሊሆን እንደማይችል በመግለጽ አሠራራቸውንና ውስጣቸውን መፈተሽ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

በዋነኛነት ግን ፓርቲዎች ሲመሠረቱ ለምን ዓላማ ነው የሚቋቋሙት የሚለውን ሊመልሱልን ይገባል በማለት ከፕሮግራም፣ ከርዕዮተ ዓለም ግልጽነት፣ እንዲሁም ውስጣዊ ዴሞክራሲ ጋር ተያይዞ የሚሰነዘረውን ትችትና አስተያየት አስመልክቶ ያለውን ሁኔታ ለማቅረብ ስለሚያግዝ፣ የሚቋቋሙበትን ዓላማ ለማሳካት የሚፈልጉትን በግልጽ፣ ይናገሩ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የብሶት ፖለቲካ

ምንም እንኳ አንደኛው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና የመንግሥትን ስህተት እግር በእግር እየተከተሉ በመንቀስ ለሕዝብ ማሳወቅና እነሱም ቢመረጡ ያንን ስህተት እንዴት ሊያስተካክሉት እንደሚችሉ አማራጭ ሐሳቦችን መግለጽ ላይ የሚያተኩር ቢሆንም፣ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ግን እንዲህ ያለ ትንተና ከማቅረብ ይልቅ ማማረርና ብሶትን ዋነኛ መተዳደሪያቸው እንዳደረጉ የሚገልጹ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡

ከዚህ አንፃር አቶ አዳነ፣ ‹‹ፓርቲዎቻችን የለመዱት ነገር በዋነኛነት ስሞታ ማቅረብን ነው፡፡ በሚያወጡት ተደጋጋሚ መግለጫም ይሁን በሌሎች በሚያገኙዋቸው ዕድሎች ብሶትን ከመደርደርና ስሞታን ከማስተጋባት ባለፈ ያላቸውን አማራጭ ቢያቀርቡ፣ በተለይ በዚህ የሽግግር ወቅት ከፍተኛ ሚና መጫወት ይችሉ ነበር፤›› በማለት፣ የብሶት ፖለቲካ ገዥ በመሆኑ ሕዝቡ ለአማራጭ ሐሳቦችና አቅጣጫዎች አለመታደሉን ይገልጻሉ፡፡

በዚህም ምክንያት ወትዋቾች (አክቲቪስቶች) ያሻቸውን ለማድረግ ሕዝቡን ውዥንብር ውስጥ እንዲከቱት መንገድ ከፍቶላቸዋል ሲሉም ይተቻሉ፡፡ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች የጠራ አቋማቸውን ሕዝቡ ውስጥ ማስረፅና ከብሶት ይልቅ አማራጭ ሐሳቦችን ማቅረብ ቢችሉ፣ የሕዝቡን የፖለቲካ ንቃተ ህሊና በማዳበር ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ከመበተን ይታደጉት ነበር፤›› ያሉት አቶ አዳነ፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ የሚታየው የወትዋቾች መፈንጨት የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅጡ ካለመደራጀታቸው የሚመዘዝ እንደሆነ ይሞግታሉ፡፡

ሌላኛው የብሶት ፖለቲካ ተንሰራፍቶ ፓርቲዎች ዓይነተኛ ሚናቸውን እንዳይወጡ ያደረጋቸው ደግሞ፣ ግለሰቦች በፓርቲዎች ስም የሚያገኙትን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከግምት በማስገባት የሚመሠረቱ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት የፓርቲ ኢኮኖሚ ተፈጥሯል፡፡ ፓርቲ መመሥረት ለተወሰኑ ግለሰቦች መተዳደሪያ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ በግለሰቡ መረዳትና አተያይ ልክ ብሶቶችን በማጉላት ተዋናይ ሆኖ ለመቀጠል ጥረት ይደረጋል፤›› ሲሉ እንደ አሸን በፈሉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ለገቢ ማስገኛነት እንደሚጠቀሙባቸው በመግለጽ፣ ይህ ደግሞ በመሠረታዊነት ፓርቲዎች ሊጫወቱት የሚገባውን ሚና እንዳንሸዋረረው አምርረው ይተቻሉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ፓርቲዎች ወጥ የሆነ ጠቅላላ ጉባዔ አለማከናወን፣ የውስጥ ዴሞክራሲ አለመዳበርና አለመጎልበት፣ ግልጽ የሆነና ከአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና  ማኅበራዊ ችግሮች ጋር የተሰናሰለ ርዕዮተ ዓለም አለማዳበርና አለመከተል፣ ከሌሎች ኃይሎች ጋር በጋራ በሚያሠሩ አጀንዳዎች ላይ አለመተባበር፣ ከመንግሥት ጫና ጋር ተዳምሮ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን ያህል ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓተ ግንባታ ሚና እንዳይጫወቱ አድርጓቸዋል የሚለው አስተያየት ላለፉት በርካታ ዓመታት የሚሰማ ቢሆንም፣ ይህንን ትችትና አስተያየት ለማረም በፓርቲዎቹ የተከናወኑ ሥራዎች መኖራቸውን መናገር አስቸጋሪ ነው የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡

የአገሪቱ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚሰነዘርባቸው ትችትም ሆነ አስተያየት ራሳቸውን በማጥራትና ወደ ውስጥ በመመልከት አለን የሚሉትን አማራጭ ሐሳብ በሕዝቡ ዘንድ ለማስረፅ ተፎካካሪነታቸውን እንዲያስመሰክሩና አማራጭ እንዲሆኑ የሚቀርበው ጥሪ አስቸኳይ ምላሽና መፍትሔ እንደሚሻ በርካቶች ይገልጻሉ፡፡ ይህንንም መመልከት የብዙዎች ጥበቃ ነውና ፓርቲዎቹም ይህን ቢፈጽሙ መልካም ነው በማለት ምክር የሚለግሱ በርካቶች ናቸው፡፡ ፓርቲዎቹ እንዲህ ላሉ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ጆሮ ሰጥተው ምላሽ የሚሰጡት መቼ ይሆን በማለትም ይጠይቃሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -