ክፍል ሁለት
በፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የሊበራል አስተሳሰብ ሲስፋፋ ዋና ዓላማውም ኋላቀር አስተሳሰቦችን በማስወገድና በመደምሰስ የሪፐብሊካንን አስተሳሰብና አገዛዝ በመትከል ነበር፡፡ አንድ ወጥ የሆነውን የፈላጭ ቆራጭ (Despotic) አመለካከት በመጋፈጥ ለሲቪል እንቅስቃሴ በሩን በመክፈት ሳይንስና ጥበብ ዋናው መመርያ ይሆናሉ፡፡ ኢንላይተንሜንት (አብርሆት) እየተባለ የሚታወቀው ምሁራዊ እንቅስቃሴም ዋናው ትርጉሙና ዓላማው በጭንቅላት ውስጥ ብርሃን ተፈናጥቆ የሰው ልጅ ታሪክን እንዲሠራ ማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም ኢንላይተንሜንት የሚባለው እንቅስቃሴ የአሪስቶክራሲውንና የፊውዳሉን አገዛዝና አስተሳሰብ በመደምሰስ የሲቪል ነፃነት ወይም ሊበሪቲን ማወጅ ነበር፡፡ ዋናው ዓላማው ይህ ቢሆንም የሊበራል እንቅስቃሴ መሠረታዊውን የፕላቶንና የሶክራተስን አስተሳሰብ ማለትም ዕውቀት ከጭንቅላት ውስጥ ነው የሚፈልቀው የሚለውን የሚቃወምና ክስተታዊ አመለካከትንና ከዚህም በመነሳት ሁኔታዎችን ማንበብ የዕውቀት መነሻ ዋናው ምክንያት ነው ብሎ የተቀበለና የሚሰብክ ነው፡፡ ይሁንና ከውጭ ወደ ውስጥ የገባው ክስተታዊ አስተሳሰብ በጭንቅላት ውስጥ መብላላትና ወደ ተግባርም መመንዘር እንዳለበት ለኢንላይተንሜንት እንቅስቃሴ ምሁሮች ግልጽ ነበር።
ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠው በታሪክ ውስጥ የጭንቅላት ተሃድሶ ባልተካሄደባቸው አገሮች ውስጥ ታሪክን መሥራትና ከውስጥ ደግሞ የተረጋጋ ኅብረተሰብ መገንባት እንዳማይቻል ነው፡፡ በማንኛውም መልክ የሚገለጽ ጭቆና ዋናው ምክንያትም ጭንቅላት በአዲስ ዕውቀት መታደስ አለመቻሉ ነው፡፡ ከአንድ ኅብረተሰብ ውስጥም ጭቆናን ማስወገድ የሚቻለው አንዱ ኃይል ተወግዶ በሌላ ስለተተካ ሳይሆን ጭንቅላትን የሚያድስ ምሁራዊ እንቅስቃሴና አዲስ ዕውቀት ሲዳብርና ሲስፋፋ ብቻ ነው፡፡ በሌሎች አገሮችም ሆነ በአገራችን እንዳየነውና መገንዘብ እንደቻልነው አንድ ጨቋኝማ ፀረ ዕድገት አገዛዝ ስለተወገደ ብቻ የግዴታ ኅብረተሰብዓዊ ለውጥ ይመጣል፣ የፈጠራ ሥራ ይዳብራል፣ ቴክኖሎጂና ሳይንስ ይስፋፋሉ፣ እንዲያም ሲል ሁለገብ የሆነ ማኅበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይመጣል ማለት አይደለም፡፡ በአጭሩ የድሮ አገዛዝ ከተባረረና አዲስ ኃይል ሥልጣን ከያዘ ጭንቅላትን የሚያድስ ሁለገብ ዕውቀት እስካልተስፋፋ ድረስ አንድ ሕዝብ ነፃነቱን በምንም ዓይነት እንደማይጎናፀፍ የብዙ አገሮችና የአገራችንም ታሪክ ያረጋግጣል፡፡ አንድ አገርም ብሔራዊ ነፃነቷን በማስከበር ሕዝቡ ተዝናንቶና ነፃነቱን ተጎናጽፎ ሊኖርባት የሚችል አገር መመሥረት አይቻልም፡፡ የአንድን ሕዝብ ነፃነት፣ ታሪክን መሥራት መቻልና አለመቻል፣ ከዚህ አጠቃላይና ሁለገብ ሁኔታ ተነስቶ መመርመር የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ በዛሬው ወቅት በአገራችን ምድር የተከሰተውን አስቸጋሪ ሁኔታና የአገዛዙንም መደናበርና ወደ ሌላ የጭቆና አገዛዝ ማምራት ከላይ ከተተነተነው ሁኔታ መመልከቱ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ የአገራችን የተወሳሰበ ሁኔታና የሕዝብ መፈናቀልና የፅንፈኝነት መስፋፋት በመደመርና በፍቅር ያሸንፋል መፈክር ብቻ እንደማይፈታ የአንድ ዓመቱ የአዲሱ አገዛዝ ሁኔታ ያረጋግጣል፡፡ የለውጥ ኃይል እየተባለ የሚወደሰው አገዛዝ በእርግጥም የለውጥ ኃይል እንዳልሆነ እያረጋገጠልን ነው፡፡ ከድሮው የወረሰውን የጭቆና መሣሪያ በማንቀሳቀስ ለማያልቅ ጦርነትና ለሕዝቦች የእርስ በርስ መተላለቅ ሁኔታውን የሚያመቻች ይመስላል፡፡
አስቸጋሪው ጉዳይ የአገራችንን ሁኔታና የአገዛዙን መንፈስና ተልዕኮ መረዳት!
በሁላችንም ዘንድ አንድ የተለመደ አነጋገርና የምንዝናናበት ነገር አለ፡፡ ይኸውም ኢትዮጵያ የጥንት ታሪክ ያላትና የሥልጣኔ አገርም እንደሆነች ነው፡፡ የሰውም ልጅ ዘርም ከዚያ የፈለቀ መሆኑ ሁላችንንም ያኮራናል፡፡ ይህ ትክክል የሆነውን ያህል እስከዚህም ድረስ የሚያዝናናን አይደለም፡፡ የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪና ከኒውተን በተጨማሪ የካልኩለስ አፍላቂ የሆነው ጀርመናዊው ላይብኒዝ እንደሚያስተምረን ማንኛውም አዲስ ትውልድ በድሮ ዝና መደሰትና መዝናናት ያለበት ሳይሆን ዛሬ የሚታየውን ችግር በመረዳት ለመፍታት ታጥቆ መነሳት እንዳለበትና ለሚቀጥለውም ትውልድ የሥልጣኔ መሠረት ጥሎ ማለፍ እንዳለበት ያሳስባል፡፡ ተከታታዩ ትውልድ መነሻ የሚሆነው የሥልጣኔ መሠረት እስከሌለው ድረስ የግዴታ ኅብረተሰብዓዊ ትርምስ መፈጠሩ የማይቀር ግዴታ እንደሆነም ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ስለሆነም እኛም በጥንቱ ታሪካችን ይህንን ያህልም የሚያዝናናን ነገር የለም፡፡ የጥንት አባቶቻችንና እናቶቻችን ብቻ ሳይሆኑ በታሪክ ውስጥ የተለያዩ አገሮች ሥልጣኔን በመሥራት ለምዕራብ አውሮፓ ሥልጣኔና ለካፒታሊዝም ዕድገት መሠረት ጥለው አልፈዋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳም በሥልጣኔያቸው ሊገፉበት አልቻሉም፡፡ የግብፅ ሥልጣኔ፣ የባቢሎን፣ የኢራቅና የሶሪያ ሥልጣኔዎች ከፍተኛ ደረጃ የደረሱበት ሁኔታ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በታሪክም የተረጋገጠ ነው፡፡ ይሁንና ግን ሁኔታው ስላልፈቀደ ወይም የበሰለ ስላልነበረ በነዚህ አገሮች ውስጥ የካፒታሊዝም ሥርዓት ብቅ ሊል አልቻለም፡፡ የነዚህ ሥልጣኔዎች ተጠቃሚ የሆነው ምዕራብ አውሮፓ ነው፡፡ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የተለያዩ አጋጣሚዎች በመገጣጠም በአውሮፓ ምድር ውስጥ በተለያየ ጊዜና ቦታ ካፒታሊዝም ብቅ ሲልና ሲስፋፋ ዛሬ ደግሞ ዓለምን ሊቆጣጠር ችሏል፡፡ እዚህ ላይ ግን መቋጠር ያለበት ነገር ካፒታሊዝም ተፈልጎና ታቅዶ የመጣ ሥርዓት ሳይሆን ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በአሸናፊነት የወጣ ሥርዓት ነው፡፡ ካፒታሊዝም በራሱ ችግር ፈቺ ሥርዓት ሳይሆን በትግል አማካይነት እንደ ሁኔታው የኃይል አሠላለፍ ሲቀየርና የጭንቅላት ብስለት ሲዳብር ለግለሰብዓዊ ድርጊት በሩን የከፈተ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሥርዓቱ በውስጡ ባለው ውስጠ ኃይል የተነሳ ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ያስቻለ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ዕድገትና ለብዙ ችግሮች መሠረታዊ መፍትሔ መሆን ከካፒታሊዝም ውስጠ ኃይል ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ስለዚህም ካፒታሊዝም በአንድ አካባቢ ብቅ ያለ ያደገና የተስፋፋ ሲሆን ሁሉም አገሮች በዚህ ውስጥ ማለፍ አለባቸው ወይም ሥርዓቱን እንዳለ መቅዳት አለባቸው የሚል በተፈጥሮ የተደነገገ ሕግ የለም አይቻልምም፡፡ ይሁንና ግን ለፈጠራና ለዕድገት ያመቻሉ አስፈላጊም ናቸው የምንላቸውን ነገሮች መኮረጅና ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣመር ችግር ፈቺ እንዲሆን ለማድረግ መሞከር የማይታለፍ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ስንነሳና ወደ እኛ አገር ስንመጣ ታሪክን ለመሥራትና አዲስ ኅብረተሰብን ለመገንባት ያልቻልንበትን ምክንያት በመጠኑም ቢሆን ማየት ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ ግን በሰፊው አልሄደበትም፡፡
ለዛሬው አፍጦ አግጦ ለሚታየው የተወሳሰበ ችግራችን ዋናው ምክንያት የሰሜኑ የፊውዳል አገዛዝና ሃይማኖታዊ እምነትን በአዲስና ጭንቅላትን በሚከፍት አዲስ አስተሳሰብ መጋፈጥ ባለመቻላቸው ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ለብዙ መቶ ዓመታት ተንሰራፎት በመቆየቱ ለዕድገትና ለኅብረተሰብዓዊ ለውጥ ማነቆ እንደሆነ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ እንደ አውሮፓው ሁኔታ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ከፍልስፍና ጋር የመጣመርና የመፈተሽ ዕድል ስላላጋጠመው የበላይነትን በመጎናፀፍ አንድ ወጥ አመለካከት በማስፈን ለአዳዲስ አስተሳሰብ መፍለቅ እንቅፋት ሊሆን ችሏል፡፡ በዚህ ላይ የንግድ እንቅስቃሴና የዕደ ጥበብ ሙያ ያልተስፋፋ ስለነበር የሰው የእርስ በርስ ግንኙነት ከክልል አልፎ የሚሄድ አልነበረም፡፡ ይህ ዓይነቱ የተገደበ አኗኗርና የአብዛኛው ሕዝብ ኑሮ ከመሬት ጋር የተያያዘና በእርሻ ላይ የሚመካ ስለነበር አዳዲስ አስተሳሰቦች መፍለቅ አልቻሉም፣ የፈጠራ ሥራም ሊዳብር አልቻለም፡፡ በብዙ ጥናቶች በምርምር እንደተደረሰበት በንግድ ልውውጥ አማካይነትና በዕደ ጥበብ ሙያ መስፋፋት የተነሳ ጭንቅላት ብቻ ሳይሆን ቋንቋ ራሱ ውስጣዊ ኃይል በማግኘት ሥነ ጽሑፍ እንዲዳብር አስተዋጽኦ ሲያደርግ፣ የሰው ልጅ ጭንቅላትም የበለጠ አርቆ አሳቢና ፈጣሪ እንደሚሆን ነው፡፡ ከዚህ ስንነሳ የፊውዳሉ ሥርዓትና ሃይማኖት የሰውን የማሰብ ኃይል በማፈን የመንፈስ ልዩ ልዩ ባህሪዎች እንዳይዳብሩና እውነተኛ ግለሰብዓዊ ነፃነት እንዳይጎለምስና ገበሬውም በራሱ ላይ የሚመካ እንዳይሆንና የምርትን እንቅስቃሴ እንዳያሳድግ አስተሳሰቡን ገድቦበታል ማለት ይቻላል፡፡ የምርት መሣሪያዎችም ውስን ባህሪ ስለነበራቸው የገበሬው የማረስ ኃይል መዳበር አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን፣ ፍራፍሬዎችንና አትክልትን በመትከል የተፈጥሮን ምንነት በመረዳት ኑሮውን ሊያሻሽል በፍፁም አልቻለም፡፡ በዚህ መልክ ከስምንት መቶ ዓመታት በላይ የተንሰራፋው ፊውዳላዊ አገዛዝና እምነት ለፈጠራ ሥራና ኅብረተሰብዓዊ እንቅስቃሴ እንቅፋት በመሆን ኅብረተሰብዓዊ መተሳሰር እንዳይኖር አገደ፡፡ በዚህም ምክንያት በሰሜኑም ሆነ በዛሬው መልክ በተዋቀረችው የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በከተማዎች የሚገለጽ ዕድገትና የከበርቴ መደብና ፈጣሪ የኅብረተሰብ ክፍል ብቅ ሊልና በሌላ ወገን ደግሞ ከሌላ ጋር በንግድ አማካይነት በመገናኘት ኅብረተሰብዓዊ መተሳሰርና በጋብቻ የሚገለጽ ግንኙነት እንዲዳብር ማድረግ አልተቻለም፡፡ ስለሆነም የሕዝቡ አስተሳሰብ ውስን ከመሆኑ የተነሳ ለረሃብ፣ ለድህነትና ለጦርነት እንዲዳረግ ሆነ፡፡ ኅብረተሰብዓዊ ኃይል እንዳይሆንና በአንድነት ተነሳስቶ አገር እንዳይገነባ ታገደ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ለጭቆና መስፋፋትና ለዕድገት ዋናው እንቅፋት የጭንቅላት ተሃድሶ አለመኖርና አዲስ የሪፐብሊካን አስተሳሰብ ያለው ኅብረተሰብዓዊ ኃይል ብቅ ማለት ያለመቻሉ ነው፡፡ ከላይ አንድ ቦታ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ሬናሳንስ፣ ሬፎርሜሽንና ኢንላይተሜንት የቱን ያህል ለአውሮፓው ኅብረተሰብ የአዕምሮና የመንፈስ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ዓይነቱ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ለኅብረተሰብዓዊ ለውጥና ለካፒታሊዝም ዕድገት በሩን መክፍት ችሏል ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም አማካይነት ነው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሊዳብሩና ኅብረተሰቡን ሊያስተሳስሩና የዕድገትም መግለጫ ሊሆኑ የበቁት፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ የኢንላይተንሜንት እንቅስቃሴ ባልተደረገባቸው እንደኛ ባሉ አገሮች መሠረታዊና ሥር ነቀል ኅብረተሰብዓዊ ለውጥ ለማምጣት ያለመቻል ዋናው ምክንያት ይህ ዓይነቱ ጭንቅላትን የሚከፍትና ለሁለገብ ዕድገት፣ እንዲሁም ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ምጥቀት የሚያመች የአዕምሮ ወይም የመንፈስ ተሃድሶ መካሄድ አለመቻል ነው።
በእኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር የኅብረተሰባችንን ውስጣዊ ሕግና የተወሳሰበ ችግር በቅጡ ያለመረዳት ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ አወቃቀር ደረጃ በደረጃ ለማጥናትና ለመተንተን እስከ ዛሬ ድረስ ሙከራ ያደረገ የለም፡፡ ከታሪክ አንፃር የሚጻፉት ሀተታዎች በሙሉ ገለጻዊ (Discriptive) ባህሪ ያላቸው እንጂ በዲያሌክቲክ መነጽር እየታዩ ተተንትነው የቀረቡና የሚቀርቡ ሀተታዎች አይደሉም፡፡ በመሆኑም ተከታታዩ ትውልድ የኅብረተሰብዓችንን አወቃቀርና ታሪክ ትችታዊ በሆነ መልክ እንዳይረዳው ተደርጓል ማለት ይቻላል፡፡ በተማሪው እንቅስቃሴ ጊዜ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ሙከራ ቢደረግም ይህም መሠረት ያደረገው ታሪካዊ ማቴሪያሊዝምን (Historical Materialismm) በተለይም በስታሊን በዶግማ መልክ የቀረበውን የኅብረተሰብ ታሪክ ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ እንዴት እንደሚሸጋገር ያሳየውን፣ ግን ደግሞ እጅግ አሳሳች የሆነውን የትንተና ዘዴ በመውሰድ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አቀራረብ ደግሞ የኅብረተሰብዓችንን አወቃቀርና ለዕድገት ማነቆ የሆኑትን ምክንያቶች በደንብ እንዳናጠና አግዶናል ማለት ይቻላል፡፡ በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ በቀጥታ ያልተካፈለው ምሁር ደግሞ የአገራችንን ችግር ሊረዳ የሚችልበት የትንተና መሣሪያ ሊያዳብር በፍፁም አልቻለም፡፡ ሌላው ከተማሪው እንቅስቃሴ እየተስፈናጠረ የወጣው ደግሞ የአገራችንን ችግር ከብሔረሰብ ችግርና ጭቆና መኖር አንፃር ብቻ በመመልክቱ አቀራረቡ ከስሜታዊነት ያላለፈና ለተከታታይ ጥናትና ትንተና የሚያመች አይደለም፡፡ ያም ሆነ ይህ ፊውዳሊዝምና ሃይማኖት አንድ ላይ በመጣመር ለዕድገት እንቅፋት ለምን እንደሆኑና ለምንስ ለአዲስ ለተገለጸለት የኅብረተሰብ ኃይል መነሳት መፈናፈኛ መስጠት እንዳልቻሉ በሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ ሰፋ ያለ ጥናት ብናካሄድ ኖር ከብዙ ንትርክና ውጣ ውረድ በዳንን ነበር፡፡ ለምንስ አንድ ሥርዓት ለለውጥ የሚያመቹ ሁኔታዎችን ማዘጋጀት እንደተሳነውና ለምንስ የምርት ኃይሎች ማደግ አልቻሉም? በሚለው መሠረታዊ ሐሳብ ላይ ጠለቅ ያለ ጥናት ብናካሂድ ኖሮ ለብሔረሰብ ችግር ሁሉ መልስ መስጠት በተቻለ ነበር፡፡ የአገራችንን ችግር በመደብ ትግልና በብሔረሰብ ጭቆና መኖር ብቻ ባልገደብነው ነበር፡፡ በሳይንስና በአንዳች ሥልት የሚመራም ምሁር ዋና ተግባር በቁንጽል ሐሳብ ላይ በመመርኮዝ እሱን እንደ ቀኖናዊ አስተሳሰብ በመያዝ ለመከራከር መጣር ሳይሆን ከዚያ አልፎ በመሄድ የአንድን ኅብረተሰብ ችግር በዲያሌክቲክ መነጽር መመርመር ነው፡፡ በዚህ መልክና የሐሳብን የበላይነት ስናውቅና በጥሞና ለመወያየትና ለመከራከር ዝግጁ ስንሆን ለአገራችን የተወሳሰበ ችግር ተቀራራቢ መፍትሔ ማግኘት እንችላለን፡፡
ከዚህ ስንነሳ የተማሪውን እንቅስቃሴና ዕድገት ውስን ባህሪና ተልዕኮውን መረዳቱ ከባድ አይሆንም፡፡ የተማሪው እንቅስቃሴ ተራማጅ መፈክር ይዞ ቢነሳም እንደ አውሮፓውያኑ ዓይነት ምሁራዊ እንቅስቃሴ በምሁራዊ ውይይትና ሒደት ውስጥ ያለፈ ስላልነበር ነገሮችን በውስን መልክ ብቻ ነበር ይመለከት የነበረው፡፡ ይህ ዓይነቱ አመለካከት ደግሞ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በ1960ኛው እና በ70ኛው ዓመት የጦር ትግልና ሰላማዊ ሠልፍ እንቅስቃሴ በሚካሄድባቸው የሦስተኛው ዓለም አገሮችና በካፒታሊስት አገሮችም የነበረ ችግር ነው፡፡ ስለዚህም የአገራችንን የተማሪ እንስቃሴ ብቻ መወንጀሉ የችግሩን ምንነት ለመረዳት ብዙም አያግዘንም፡፡ መነሳት ያለበት ጥያቄ የተማሪው እንቅስቃሴ በተለይም ከዚህ የወጡት የማርክሲስት ሌኒንስት ድርጅቶች አብዮቱ ከሸፈ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ምን አዲስ ሐሳብ አፈለቁ? ዛሬስ መመርያቸውና ፍልስፍናቸው ምንድነው? አንዳንዶች እንደሚያደርጉት ስም በመለወጥና፣ የመድበለ ፓርቲና የሕግ የበላይነት መኖር አለበት ስለተባለ ብቻ ውስብስቡና ውጥንቅጡ የወጣው የአገራችን ችግር በዚህ መልክ ሊፈታ ይችላል ወይ? በአንድ ወቅት ሲምሉበትና ሲገዘቱበት፣ እንደ መጽሐፍ ቅዱስም ያነቡ የነበረውን ማርክሲዝምን ለምንስ እርግፍ አድርገው ጣሉት? ብለን እንድንጠይቃቸው እንገደዳለን፡፡
በመሆኑም፣ አንዳንድ የተማሪውን እንቅስቃሴ መጽሔቶች ስናገላብጥ የምንረዳው በተለይም በየዘመኑ የተከሰቱትን የኅብረተሰብዓችንን አወቃቀር፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ኃይሎችን የህሊና አወቃቀርና የመንግሥት መኪናን አገነባብና መንግሥት የሚባለው ፍጡር የምርት ኃይሎችን ዕድገት አጋዥ ከመሆን ይልቅ ለምንስ እንቅፋት ለመሆን በቃ? በሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ በቂ ጥናት እንዳልተካሄደ መገንዘብ እንችላለን፡፡ በእኔ እምነት ይህ ባለመሆኑና በተለይም መንግሥትና የመንግሥት ቢሮክራሲው ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር ያላቸውን ትስስርና መቆላለፍ በሚገባ ካለመገንዘብ የተነሳ አብዮቱ መክሸፉ ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ተተኪ የማይገኝላቸው የአንድ ትውልድ ምሁራንና አገር ወዳዶች ተሟጥጠው እንዲያልቁ ለማድረግ ተበቃ፡፡ በተጨማሪም ይህም የሚያመለክተው የተማሪው እንቅስቃሴ የከበደ አስተሳሰብና ኢትዮጵያን ታላቅ አገር ለማድረግ ያለው ራዕይ እጅግ የጠበበና ትግሉን ከራሱ ባሻገር ለማየት ያልቻለ መሆኑን ነው። ትግሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ መሆኑ መጠን ለመከፋፈል እንዳያመችና ትግልን በማስተባበር ወደፊት በመራመድ አንድ ታላቅ አገር ለመገንባት ስፊ ጥናትን ትዕግሥት እንደሚጠይቅና፣ ኅብረተሰብዓዊና ብሔራዊ ፕሮጀክትን ተግባራዊ ለማድረግ የግዴታ መቻቻልንና አንዳንድ የጎለመሰ አስተሳሰብ ያላቸውን ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶችን ሚና የግዴታ መቀበልና ማክበር እንደሚያስፈልግ የተገነዘበ አልነበረም፡፡ መናናቅና አንዱ በሌላው ላይ ማሾፍ ወይም ስም ማጥፋት አንደኛው የተማሪውም መለዮ እንደነበርና ይህም ለአብዮቱ መክሸፍና ለአንድ ትውልድ መተላለቅ ምክንያት መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ ራሱን ከፊውዳላዊ ግትር አስተሳሰብ ማላቀቅ ያልቻለውና ጭንቅላቱ ያልበሰለና ያልፀዳ የተወሰነው የተማሪው እንቅስቃሴ አመራር ራሱ ባነሳው ጥያቄ ላይ በእልክነት ጦር ሰበቀ፡፡ ከመቻቻልና ከመደማመጥ ይልቅ ‹‹ጩኸቴን ቀሙብኝ›› በማለት አጠቃላይ ጦርነት ከፈተ፡፡ በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ከመጠቀምና የታወጁትን የጥገና ለውጦችን ተግባራዊ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ሁሉም በየፊናው በአገራችን ላይ ጦርነት አወጀ፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ እታገላለሁ ብሎ የተነሳውና ከጭቆናም እላቀቃለሁ ብሎ እዚህና እዚያ ይሯራጥ የነበረው ሁኔታውን በጥሞና ከማንበብና ከመተንተን ይልቅ እልክ ውስጥ በመግባት ችግሩን ውስብስና ድርብርብ በማድረግ ዛሬ የምንገኝበት ደረጃ ላይ እንድንወድቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ አደረገ፡፡ የአብዮቱን የብሔራዊ ባህሪና ለውጥ አምጭነት ያልተረዳው ቢሮክራሲያዊ ኃይል ደግሞ ውስጥ ለውስጥ ተንኮል በመሥራትና ከውጭው ኃይል ጋር በማበር ለወጣቱ ማለቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ አደረገ፡፡ ከዚህ ስንነሳ መገንዘብ የምንችለው ነገር በተለይም ጣሊያን ከአገራችን ከተባረረና ነፃነታችንን ከተቀዳጀን በኋላ የተከሰተው አዲስ ኅብረተሰብዓዊ ኃይል የበሰለ አስተሳሰብ ማዳበር ያልቻለና መንፈሱን ለለውጥ ያላዘጋጀ መሆኑን ነው፡፡ በትንሽ ነገር ተደስቶ እንደሚኖርና ታላቅ አገርና ብሔራዊ ኩራት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ምጥቀትና በከተማዎችና በመንደሮች ዕድገት የሚገለጽና ለዚህም በታታሪነት መሥራት እንደሚያስፈልግ መንፈሱን ያላዘጋጀና የነገሮችንም ሒደት በደንብ የተገነዘበ ኅብረተሰብዓዊ ኃይል እንዳልነበር በሳይኮሎጂና በሶሾሎጂ ዕውቀት ማረጋገጥ ይችላል፡፡ መናናቅና ሌላውን ዝቅ አድርጎ ማየት፣ እንዲያም ሲል ወደ ዘረኝነት ማድላትና ለኢምፔሪያሊዝም ማጎብደድ በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ሰተት ብሎ ከገባው የፍጆታ አጠቃቀም፣ ብዙም ሳይሠሩ ሀብታም ከመሆን ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው።
ነገሩን ለማሳጠር ዛሬም በመካከላችን ያለው ትልቁ ችግር ራሳችንን ማግኘትና ማወቅ አለመቻላችን ነው፡፡ የመንፈስን የበላይነት በመረዳት የመንፈስ ተሃድሶ ለማድረግ ዝግጁ አለመሆናችን ሲያነታርከን ይኖራል፡፡ በመሆኑም ሁሉም በየፊናው ሀቀኛ ታጋይና ለኢትዮጵያ አሳቢ ካለሱ ብቻ ያለ አይመስለውም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ድርጅቶች የሚያስቡት የኢትዮጵያ ጉዳይ የጋራ ጉዳያችንና ሁላችንንም የሚያገባን ሳይሆን ለጥቂቶች ብቻ በሞኖፖሊ የተሰጠ በማስመስል በቁም ነገር ላይ እንዳንወያይና መፍትሔም እንዳንፈልግ በሩን ሁሉ ዘግተዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ጉዳዩን ወደ ተራ ሴሌብሪቲ እየለወጡት ይገኛሉ፡፡ ጠቅላላው ለአገራችን የሚደረገው ትግል በተገለጸለት ምሁራዊ እንቅስቃሴ፣ በሳይንስና በፍልስፍና ላይ ከመመርኮዝ ከመታገል ይልቅ የግለሰቦችን ሚና አጉልቶ በማሳየትና (ፐርሰናሊቲ ስልት) እንዲዳብር በማድረግ ትግሉን ፊውዳላዊ ለማድረግ በቅተዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ትግል ደግሞ ሳንወድ በግድ የዛሬውን ‹‹አዲስ አገዛዝ›› እያጠናከረውና የአገራችንን ችግር እየተወሳሰበ እንዲሄድ መንገዱን ሁሉ ያመቻችለታል፡፡ ከምሁራዊ ውይይትና ክርክር በማምለጥ በሥራችን በመዝናናት በድሮ ዓለም የምንኖር እንዲሁም ደግሞ ሰፋ ያለ ምሁራዊ ውይይትን የምንንቅና ሌላውን የምናጥላላና የምንንቅ ብዙዎች ነን፡፡ ስብሰባ በሚዘጋጅባቸው ቦታዎች ሁሉ የሚደረገውን ሽር ጉድ ስመለከት የቱን ያህል ወደ ኋላ የምንጓዝ መሆናችንን ነው፡፡ ለውጥን መፈልግና የኋሊት ጉዞ አንድ ላይ ሊሄዱ የሚችሉ ነገሮች አይደሉም፡፡
ያም ተባለ ይህ በአገራችን ምድር መሠረታዊና ሁለንታዊ ለውጥ መምጣት አለበት ብለን የምናምን ከሆነ ከመንፈስ ተሃድሶ ውጭ ልናመልጥ አንችልም፡፡ ለመንፈስ ተሃድሶ ደግሞ ራስን መጠየቅ ዋናው መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ያደረግነውን አዎንታዊና አሉታዊ ድርጊቶችን ማውጣትና ማውረድ አለብን፡፡ ስህተት ወይም ደግሞ ኅብረተሰብዓዊ ወንጀል ሠርተን እንደሆን ወደ ውጭ አውጥተን መናገር መቻል አለብን፡፡ ስህተታችንን ስናውቅና ከስህተታችን ለመታረም ስንሞክር ብቻ ነው ለመሠረታዊና ለሁለንታዊ ለውጥ አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው፡፡ ለዚህ ደግሞ የግዴታ የምንመራበት ትክክለኛ ፍልስፍናና ሳይንሳዊ የአሠራር ዘዴ መኖር አለበት፡፡ በአንድ ትክክል ነው ብለን በምናመነው ሳይንስና ፍልስፍና እየተመራን የምንጽፍና የምናስተምር ከሆነ የየበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንችላለን፡፡ በሌላ ወገን ግን ስመለከተውና በጥብቅም ስመረምር አብዛኛዎቻችን ይህንንም ያህል ራሳችንን ለመጠየቅና የመንፈስ ተሃድሶ ለማድረግ ዝግጁ አይደለንም፡፡ ስህተት መሆኑ እየታወቀ ድሮ የሠራነው ሥራ ትክክል ነው ብለን ድርቅ ብለን የምንከራከር አለን። እኛ ሳንሆን ሌላው ነው ጥፋተኛ እያልን አሁንም እንምላለን እንገዘታለን፡፡ አንዳንዶቻችን ደግሞ ከተንኮል ጋር የተወለድን ይመስል ግለሰቦችን እናሳድዳልን፡፡ በዚህም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት የሚደረገውን ትግል እናጨናግፋለን፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ የድርጅትና የግለሰብ ፍቅር እያንገበገበን እውነተኛ ውይይትና ክርክር እንዳይደረግ መንገዱን ሁሉ ለመዝጋት እንሞክራለን፡፡ በዚህም አንዳንድ ድርጅቶችና እንቅስቃሴዎች የሚያካሂዱትን ትግል ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን ሳንመረምርና ሳንጠይቅ ወደ ኩርፊያ እናመራለን፡፡ በእርግጥ ከተንኮል ጋር የተወለደን ማዳን አይቻልም፡፡ በቀና መንፈስ እንታገላለን ብለው እዚህና እዚያ የሚሉትን ግን ወደ አንድ ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ሰፊ ጥናትና ምርምር ማድረግና እንዲሁም በቂ ግንዛቤ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ልናሳስባቸው እንወዳለን፡፡ እንደምናየው የዓለም ሁኔታ እየተወሳሰበና አስቸጋሪ እየሆነ የመጣ ነው፡፡ ስለሆነም ትክክለኛ ወይም ሳይንሳዊ አመለካከትን ለማዳበርና አገራችንን ካለችበት ችግር ለማላቀቅ የምንፈልግ ከሆነ ካለንበት ሁኔታ ባሻገር መመልከት ይኖርብናል፡፡ አስተሳሰባችንን ለመለወጥ ዝግጁ መሆን ይኖርብናል፡፡ አንድን ሐሳብ ከመቀበላችንና እንደ እምነት ከመውሰዳችን በፊት ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን መመርመር መቻል አለብን፡፡ የተለያዩ ሐሳቦችንና ቲዎሪዎችን ማወዳደር አለብን፡፡ ችግር ፈጣሪዎች ሳንሆን ችግርን ፈቺ ለመሆን ከፈለግን የሚያዋጣው መንገድ ሳይንሳዊ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ካልኩኝ በኋላ የወያኔንም ሆነ ዛሬ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራውን አገዛዝ የሐሳብ ችግርና ግትርነትን ምንጭ ወይም ምክንያት መረዳቱ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡
በአገራችን ታሪክ ውስጥ ከየብሔረሰቡ የተውጣጡ ምሁራን ነን ባዮች የየብሔረሰቦቻቸውን የአስተሳሰብ ችግርና የማቴሪያል ዕድገት ኋላ ቀርነት በማንሳት ሰፊ ጥናት ለማድረግ አልሞከሩም፡፡ ሁሉም ነገር ከብሔረሰብ ጭቆና አንፃር በመታየቱ ከኅብረተሰብ የባህል ታሪክ ዕድገትና (Socio Cultural Studies) ከማወዳደር አንፃር (Comparative Studies) ጥናት ስላልተደረገ የበሽታችንን ዋና ምክንያት ወይም መነሾ ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ስለሆነም አንዳንድ ሙከራ በሚደረግበት ጊዜ ፈላስፋ ነኝ፣ ማንም የሚወዳደረኝ የለም የሚለው የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የያዘው ሁሉ መሳደብና መደንፋት ይጀምራል፡፡ የአገዛዙንና የመሪዎችን የአስተሳሰብ ችግር ሲነግሩት ብሔረሰቡን እንዳለ ለመስደብ ወይም ለማንቋሸሽ የሚደረግ አካሄድ ይመስለዋል፡፡ በዚህ መልክ ሳይንሳዊ ጥናትና ውይይት ከማድረግ ይልቅ ችግሩ በይደር እንዲታለፍና በላዩ ላይ ሌላ ችግር እንዲደረብበት ይደረጋል፡፡ ለነፃነት በሚደረገው ትግል ውስጥ ከማንኛውም ወገናዊነት መላቀቅ የመጀመርያው ተግባር መሆኑ ብዙዎቻችን የተረዳን አይመስለኝም፡፡ በተጨማሪም አብዛኛዎቻችን የአንድን ብሔረሰብ ችግርና የህሊና አወቃቀር ለመረዳት የምናደርገው ጥረት ይህንን ያህልም አይደለም፡፡ ለመሠረታዊ ለውጥ እንታገላለን የምንል ከሆነ ካለንበት ሁኔታ ባሻገር ማየት መቻል አለብን፡፡ መለኪያችን የብሔረሰብና የሃይማኖት ጭቆና ሳይሆኑ ሳይንስና ፍልስፍና ብቻ መሆን አለባቸው፡፡ ማንኛውም ኅብረተሰብ ችግሩን የሚፈታውና የሠለጠነ ኅብረተሰብ ለመመሥረት የሚችለው በሳይንስ አማካይነት እንጂ የብሔረሰብና የሃይማኖቶች ጭቆናን አጉልቶ በማሳየቱ አይደለም፡፡ ማንኛውም ብሔረሰብም ሆነ ይኸኛው ወይም ያኛው የሃይማኖት ተከታይ የሆነ በመጀመርያ ደረጃ መሠረታዊ ፍላጎቱ መሟላት አለበት፡፡ መብላትና መጠጣት እንዲሁም ተጠልሎ መኖር አለበት፡፡ ሕክምና እና ትምህርትም ማግኘት መቻል አለበት፡፡ የአንድን ሕዝብ መሠረታዊ ችግርና ጥያቄዎች በብሔረሰብና በሃይማኖት መፍታት አይቻልም፡፡ የብሔረሰብና የሃይማኖት ጥያቄዎችን አጉልቶ ማሳየትና በእነዚህ ዙሪያ አስተሳሰባችን እንዲሽከረከር ማድረግ ያለብንን ኋላ ቀርነት ያጠናክረዋል፡፡ ችግራችንን ያባብሰዋል፡፡ እንደ ማኅበረሰብ እንዳንኖር ያግደናል፡፡ የብሔረሰብ ጥያቄን በሳይንስ አማካይነት ብቻ መፍታት የሚቻል ሲሆን፣ የሃይማኖት ጥያቄ ግን ግላዊ ነው፡፡ ሃይማኖትን የኅብረተሰብ ጥያቄ አድርጎ ማንሳትና የተወሰነው የኅብረተሰብ ክፍልም ጭንቅላቱ በዚህ እንዲጠመድ ማድረግ መሞከር ልንወጣው የማንችለው ችግር ውስጥ ይከተናል፡፡ ሃይማኖት እምነት ነው፡፡ በሳይንስ የሚረጋገጥ አይደለም፡፡ በሌላ ወገን ግን ማንኛውም ሃይማኖት መከበር ያለበት ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ሰው መሆናችንና አንደኛው ከሌላው እንደማይበልጥ የምንረዳው ሳይንስንና ፍልስፍናን እንዲሁም ዲያሌክቲክን መሠረት አድርገን ከታገልን ብቻ ነው፡፡ ይህንን ካልኩኝ በኋላ ወደ ዋናው ፍሬ ነገር ላይ ላምራ፡፡
የቀድሞው የወያኔም ሆነ የዛሬው አገዛዝ የሐሳብ ግትርነት ዋና ምክንያት ምንድነው? ለምንድነው አገዛዞቹ እንደዚህ አምርረው በጥፋታቸው እንዲቀጥሉ የተገደዱት? በአዕምሮ ጉድለትና በሐሳብ አለመዳበር የተነሳ? ወይስ አንዳች ከውጭ ሆኖ የሚቆጣጠራቸውና የሚገፋፋቸው ኃይል ስላለ ነው ወይ እንደዚህ አምረው የሚገፉ? ብለን መጠየቅና ተቀራራቢ መልስ ለመስጠት መሞከር አለብን፡፡ የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ ታሪክ በደንብ ለተከታተለ የፊውዳሊዝም ጥንስስ የተጣለው ትግራይ ውስጥ ወይም አክሱም ግዛት ነው፡፡ ይህ ግዛት በዘመኑ ታላቅ ሥልጣኔዎች ከሚባሉት ውስጥ ቢጠቃለልም ወደ ውስጥ ሲታይ ግን ኅብረተሰቡ በሥራ ክፍፍል የዳበረና ሐሳብ የሚንሸራሸርበት አልነበረም፡፡ የአገዛዙም ገቢ ከውጭ ንግድ በሚገኝ ገቢና በግብር (Tributary) ላይ የተመሠረተ ስለነበር ወደ ውስጥ ቢያንስ እንደ ቻይና ሥልጣኔ የሥራ ክፍፍልን በማዳበርና ቢሮክራሲያዊ አሠራርን በማጎልመስ የሚታማ አልነበረም፡፡ በዚህም የተነሳ የሰው ኑሮና የአሠራር ዘዴ ተደጋጋሚና አሰልቺ ስለነበር ለመንፈስ ተሃድሶው የሚያግዘው አንዳችም ነገር አልነበረም፡፡ የሥራ ክፍፍሉም ውስን ስለነበረና በግብርና ላይም የተመካ ስለነበር በተፈጥሮ ላይ ከፍተኛ ዘመቻ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ትግራይ ውስጥ በተደጋጋሚ ይከሰት ለነበረው ድርቅና ረሃብ ዋናው ምክንያት ከብዙ መቶ ዓመታት ጀምሮ ሲሠራበት የነበረው የአስተራረስ ዘዴ ነው፡፡ ተከታታይነት (Sustainable) ያለውና የተፈጥሮን ምንነት በመረዳት እንክብካቤ የሚደረግለት የአስተራረስ ዘዴና የአኗኗር ሥልት ስላልነበረ ለም የነበረው የትግራይ መሬት ቀስ በቀስ ወደ በረሃነት እንዲለወጥ ተገደደ፡፡ በዚህም ምክንያትና ከሌላው ኅብረተሰብ ጋር በንግድና በሥራ ክፍፍል አማካይነት መገናኘት ያልቻለው ሕዝብ በአስተሳሰሰቡ ውስንና ተጠራጣሪ ሆነ፡፡ በራሱ ብቻ ተገልሎ እንዲኖር የተገደደው ሕዝብ በአጠቃላይ ሲታይ አገሪቱ ካሳየችው በጣም ደካማ ዕድገት ጋር ተያይዞ ወደ ፊት መራመድና የሐሳብ ለውጥ ማድረግ አልቻለም፡፡ ይህ ጉዳይና የሐሳብ ውስንነትና የፈጠራ ችሎታ አለመዳበር በአብዛኛዎቹ የአገራችን የሰሜኑ ክፍልም በጉልህ ይታያል፡፡
ከዚህ ዓይነቱ ኅብረተሰብ የፈለቀውና የፔሪፈሪ ካፒታሊዝም ዕውቀት ጭንቅላቱን የገረፈው የትግራይ ኤሊት የትግራይን ክፍለ አገር ወደ ኋላ መቅረት የተረጎመው ከአጠቃላዩ ከአገሪቱ ሁኔታና ከአገዛዙ ባህሪ ጋር ከማያያዝ ይልቅ፣ የአማራው ኤሊት የትግራይን ዕድገትና የሕዝቡን የኑሮ መሻሻል እንደማይፈልግ አድርጎ ነው፡፡ ይህ አመለካከቱና አተረጓጎሙ ደግሞ በሳይንስ የሚደገፍ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከ1940ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በአገሪቱ ውስጥ በአዲስ አበባና በአካባቢው የተተከሉት ኢንዱስትሪዎች የማደግና የማባዛት እንዲሁም የፈጠራን ችሎታ የማዳበር ባህሪ አልነበራቸውም፡፡ አዲስ አበባ ላይ በአማራ የሚታማ አገዛዝ ስለተቀመጠ የአማራው ክፍለ አገሮች ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡ ከደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍለ ግዛት በስተቀር ጠቅላላው የአማራው ግዛትና ትግራይም ጭምር በአገዛዙ አተኩሮ ያልተሰጣቸውና ዘመናዊ ተቋማት ያልነበራቸው ነበሩ፡፡ ስለሆነም በአዲሱ የኢንዱስትሪ ተከላ ፖሊሲ አማካይነት ጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን ተጠቃሚው አምስት በመቶ የማይበልጥ የኅብረተሰብ ኃይል ብቻ ነበር፡፡ ስለሆነም ሌላው የኢትዮጵያ ግዛት ሲያድግ ትግራይ ብቻ ወደ ኋላ ቀረ የሚለው ኢሳይንሳዊ፣ በኅብረተሰብ ሳይንስና በኢኮኖሚ ቲዎሪ ያልተደገፈ አባባል የትም ሊያደርሰን አይችልም፡፡ ይሁንና ግን ከአማራው ኤሊት ጋር እልክ የተጋባውና የአማራን ኤሊት የበላይነት መስበር አለብኝ ብሎ የተነሳው የተወሰነው የትግራይ ኤሊት በጠባብ አስተሳሰብ በመደገፍ በዚያው በማምራት ጦርነት አወጀ፡፡ ይህንን ህልሙን ተግባራዊ ለማድረግ ሲል ውስጥ ለውስጥ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሥራት ሁኔታዎችን አመቻቸ፡፡ የቀድሞው የወያኔ አገዛዝ በጦርነት ዘመኑ ቀና አመለካከትና ብሔራዊ ባህሪ ያላቸውን እየመነጠረ ለድል የበቃ ኃይል ነበር፡፡ የሚያሳዝነውና የሚያስገርመው ግን ይህ ተገንጣይና ከፋፋይ ኃይል በማርክሲዝም ስም መማሉና ለሶሻሊዝም ራዕይ እታገላለሁ ብሎ መነሳቱና ብዙውን የትግራይ ወጣት ማሳሳቱ ነው፡፡ ለወያኔ ማደግና ወደ ድል ማብቃት ሻዕቢያ የማይናቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ችሏል ማለት ይቻላል፡፡ ሁለቱም ኃይሎች በመተባበር አገራችንን እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከተዋት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሻዕቢያም በበኩሉ ከ400 በላይ የሚበልጡ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑና ተራማጅ አስተሳሰብ የነበራቸውን ኤርትራውያን እንደጨፈጨፈ ይታወቃል፡፡ ይህም ማለት ሁለቱም ኃይሎች በወንድሞቻቸው ደም የታጠቡ ናቸው፡፡ ርህራሄ የሌላቸው፣ የሰው ነፍስ የቅንጣትም ያህል የማያሳሳቸው ፍጡሮች ናቸው፡፡ ስለሆነም ወያኔ በወንድሞቹ ሞት የሚደሰትና ይህንንም እንደ ድል የሚቆጥርና ጭንቅላቱ የደነደነ ነበር፡፡ ጦርነት ማካሄድና ሰውን መግደል እንደ ሙያና ባህል የወሰደና ከደሙ ጋር ያዋሃደ ነበር፡፡ የሌላው ሰው መሞት ምንም ስሜት የማይሰጠው ከአውሬ በታች ያለ ፍጡር ነው ማለት ይቻላል፡፡ አዋቂዎች እንደሚሉት መንፈሱ የተሰለበና ራሱም ሰው መሆኑን የተረዳ አልነበረም፡፡ የሰው ልጅ ባህሪዎችና ስሜቶች ሁሉ ተሟጠው ያለቁበትና ሰውነቱ ብቻ የሚንቀሳቀስ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሰውን ከማሰቃየት በስተቀር ለምን እንደሚኖር የተገነዘበ አይደለም፡፡ ፍቅር፣ ስሜት፣ ፀፀት፣ ርህራሔ፣ መቧቧት፣ ለሕፃናት ማዘንንና እንክብካቤ ማድረግ፣ ሽማግሌዎችን ማክበርና ተፈጥሮን መንከባከብ የሚሉት በሙሉ በጭንቅላቱ ውስጥ የሌሉ ናቸው፡፡ በአፈጣጠሩ የሰው ልጅና የተፈጥሮ ጠላት ይመስል የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ሁሉ የሚያስገርሙም የሚያሳዝኑም ናቸው፡፡ ሎጂስቲክንና የኅብረተሰብን ሕግ ያልተከተሉ፣ አገራችንን ለከፍተኛ አደጋ የጣሉ ድርጊቶች ነበሩ፡፡ ባለፉት 28 ዓመታት ተግባራዊ የሆኑት ፕሮጀክቶች የአገዛዙን የመንፈስ መቀጨጭ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የተከናወኑትንና የሚካሄዱትን ፕሮጀክቶች ስንመለከት የዚህ ዓይነቱ በሥነ ሥርዓት ያልተገራና ጥበብና ሳይንስን ውስጣዊ ኃይሉ ያላደረገ የጭንቅላት ውጤቶች መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡ በእልህና በአወቅኹኝ ባይነት የሚሠሩ ብዙ ሀብትና የሰው ጉልበት የፈሰሰባቸው ናቸው፡፡ ኅብረተሰብዓዊ ሀብትን መፍጠር የማይችሉና ለፈጠራ ሥራ የማያመቹ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ በአጭሩ ቀደም ብሎም ሆነ ዛሬ በአገራችን የሚታየው የተዘበራረቀና ቆሻሻ ሁኔታ የወያኔና ግብረ አበሮቹ ጭንቅላት መበላሸት ውጤቶች ናቸው፡፡ ከላይ በተጠቀሰው ሒደት ውስጥ የመጣ ኃይል ደግሞ ከጥፋት ሌላ ታሪካዊና የተቀደሰ እንዲሁም አንድን ሕዝብ እንደ ኃይል የሚያሰነሳ ፕሮጀክት ከቶም ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለሆነም ይህ ዓይነቱ ኃይል ራሱን ሥልጣን ላይ ለማቆየት ሲል ከውጭ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር በመተባበርና ትዕዛዝ ተቀባይ በመሆን አገራችን በችግር ተጠምዳ ዘለዓለሟን ፍዳዋን እያየች እንድትኖር የማያደርገው ጥረት አልነበረም፡፡ በዶ/ር ዓብይ አህመድ የሚመራው አገዛዝም ከወያኔው የአገዛዝ ሥልት የተላቀቀ የሚመስል አይደለም፡፡ የአገራችን ተጨባጩ ሁኔታ እንደሚያረጋግጠው አገዛዙ አገራችንን ወዴት አቅጣጫ እንደሚወስዳት ግልጽ የሆነለት አይመስልም፡፡ በሌላ አነጋገር ሕዝባችን እየተፈራራ የሚኖርባትና እንዲያም ሲል ወደ መተላለቅ በማምራት የውጭ ኃይሎች አገሪቱን እንዲወሩ ሁኔታውን እያመቻቸ እንደሆነ በፍፁም የተገነዘበ አይደለም፡፡
በአጭሩ ፊውዳላዊ ባህሪ ከውስን ካፒታሊዝም ሒደት ጋር በመዋሃድ የቀድሞውንም ሆነ የዛሬውን አገዛዝ ጭንቅላት ሊያደነድንና ጥያቄ እንዳይጠይቅና ለተለየ ሐሳብ ጭንቅላቱን ክፍት እንዳያደርግ አግዶታል ማለት ይቻላል፡፡ ሥልጣን መያዝና በሀብት መደለብ ደግሞ የወያኔን አገዛዝ የባሰ ሐሳቡን እንዳጨለመበት ግልጽ ነበር፡፡ ሰብዓዊ ባህሪውን እንዳለ ገፎታል፡፡ ሰውን በጅምላ መግደል፣ የሚታየውንና የሚዳሰሰውን ነገር መካድ፣ ዕድገት ሳይኖር ዕድገት አለ ብሎ ድርቅ ማለት፣ ከፋፍሎ መግዛት፣ የሃይማኖት መሪዎችን በጥቅም በመግዛት መከፋፈልና ግጭት እንዲፈጠር ማድረግ፣ አንድን ብሔረሰብ ለሁለትና ለሦስት በመከፋፈል በመካከላቸው ግጭት እንዲፈጠር ማድረግ፣ እኔ ብቻ ነኝ ሁሉንም ነገር መሥራት አለብኝ በማለት ለግል መዋዕለ ንዋይ መንገዱን መዝጋት፣ ማንኛውም ነገር ከሱ ቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ማድረግና በአጠቃላይ ሲታይ አገራችን ዘለዓለሟን በትርምስ ዓለም ውስጥ እንድትኖር የማይሸርበው ተንኮል አልነበረም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ባህሪና የሐሳብ መቀጨጭ በማንኛውም የኅብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ያልታየና ያልተለመደ ነው፡፡ ሒትለርና ተከታዮቹ እንኳ እንደዚህ ዓይነት የሐሳብ መቀጨጭ አልታየባቸውም፡፡ የተከተለው ርዕዮተ ዓለምና በይሁዲዎች ላይ ያደረሰው ድርጊትና ያወጀው ጦርነት የሚኮነን ቢሆንም፣ የሒትለር አገዛዝ ጀርመንን ለማጥፋትና የሕዝቡን ቅስም ለመስበር የተነሳ አልነበረም፡፡ ከዚህ ስንነሳ የአገዛዙን ርዕዮተ ዓለምና የሚመራበትን ፖሊሲ በቀላሉ መተንተንና መረዳት ያስቸግራል፡፡ በአንድ በኩል በዝቅተኛ ስሜት የተወጠረ፣ በሌላ ወገን ደግሞ እኔው ብቻ ነኝ የሠለጠንኩትና የማውቀው ብሎ በመዝናናት የበላይነቱን ለማሳየት የሚጥር አገዛዝ ነበር፡፡ ስለሆነም ለትግል የሚያስቸግር ነው፡፡ በጊዜው በምን ዓይነት የትግል ዘዴ መጣልና ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደሚቻል ግራ ያጋባ አገዛዝ ነበር፡፡ ሌላው አስቸጋሪው ነገር ደግሞ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከውጭ ኃይሎች ጋር የገባውና የተዋዋለው ስምምነት የአገራችንን ሁኔታ ውስብስብ ማድረጉ ነው፡፡
በዶ/ር ዓብይ አህመድ የሚመራው አዲሱ አገዛዝም ወያኔ ይከተል ከነበረው ኢሳይንሳዊና ኢኅብረተሰብዓዊ ፖለቲካ ትምህርት የቀሰመ አይመስልም፡፡ ወያኔ 28 ዓመት ኢትዮጵያን ረግጦ ሲገዛ ያደረሰውን ባህላዊና ማኅበራዊ ውድቀት፣ እንዲሁም ብሔራዊ ውርደት የተገነዘበ አይመስልም፡፡ በተለይም ጊዜው የኛ ነው፤ ይህንን ዕድል ካልተጠቀምንበት መቼ ነው የምንጠቀመው እያሉ የሚያወሩ አንዳንድ የኦሮሞ ኢሊቶችና መሪዎች ከፍተኛ የታሪክ ወንጀል እየሠሩ ለመሆናቸው የተገለጸላቸው አይመስልም፡፡ ዝም ብለው በስሜት እየተገፉ የሚወስዷቸው ፖሊሲዎችና ሕዝብን ‹‹መጤ›› እያሉ ማፈናቀል የተቀረውን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን እንወክለዋለን የሚሉትን ብሔረሰባቸውንም ወደ ኋላ እንዲጓዝ እያደረጉት ለመሆናቸው በፍፁም የተገነዘቡ አይመስልም፡፡ ካላቸው አስተሳሰብና ከሚያካሄዱትም ፖለቲካ የምንረዳው ነገር አዲሶቹ መሪዎች ስለኢኮኖሚና ስለኅብረተሰብ ዕድገት ይህን ያህልም ግንዛቤ ያላቸው አይመስልም፡፡ የፖለቲካ ሥልታቸው በሙሉ የፈጠራ ሥራንና አጠቃላይ የሆነን የሥራ ክፍፍልን የሚፃረር ነው፡፡ ሕዝባችን ለዝንተ ዓለሙ በድህነት ዓለም ውስጥ እየማቀቀ እንዲኖር የሚያደርግ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የፍልስፍናን፣ የሳይንስን፣ የባህልን፣ አርክቴክቸርንና ለአንድ ማኅበረሰብ ዕድገት የሚያስፈልጉ ዕውቀቶችን በሙሉ የሚቀናቀን ነው፡፡ ተግባራቸው በሙሉ ለውጭ ኃይሎች የሚሠሩ ነው የሚያስመስላቸው፡፡ ስለሆነም ከዚህ ዓይነቱ እጅግ አደገኛ ከሆነ አመለካከትና አገርን በታኝ ፖለቲካ መላቀቅ አለባቸው፡፡ ዛሬ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከሚገኙት እነ ኢራቅ፣ ሶሪያና ሊቢያ ከመሳሰሉት አገሮች ውድቀት ትምህርት መቅሰም አለባቸው፡፡ ሌሎችም እንደ ክልል መታወቅ አለብን የሚሉ አንዳንድ ብሔረሰቦች የዩጎዝላቪያን ዕጣ ማየትና ከዚያ ትምህርት መቅሰም አለባቸው፡፡ በመበታተንና አትድረሱብኝ በማለት ሳይሆን አንድ ክልልም ሆነ አገር ሁለገብ በሆነ መልክ ሊገነቡ የሚችሉት በመተባበርና ሐሳብ ለሐሳብ በመለዋወጥና በመመካከር ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ለመጪው ትውልድ ጥሩና ቋሚ ነገር ጥለንለት ለማለፍ የምንፈልግ ከሆነ የሐሳብ ተሃድሶ ማድረግ አለብን፡፡ ከግትርነት፣ ከእልከኝነት፣ ከአወቅኹኝ ባይነትና ከጠባብ አስተሳሰብ መላቀቅ አለብን፡፡ መልካም ንባብ!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡