Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኢድ አል አድሃ - አረፋ

ኢድ አል አድሃ – አረፋ

ቀን:

እስላማዊው ቅዱስ ቀን አረፋ ዘንድሮ በዓመተ ሒጅራ መሠረት በሐሳበ ጨረቃ 12ኛው ወር ዙልሂጃ 10 ቀን (በፀሐይ ነሐሴ 6 ማለት ነው) ላይ ይውላል፡፡ ኢድ አል አድሃ የመስዋዕት በዓል ተብሎ ይከበራል፡፡ ይሄም ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ዒስማኤል ለመስዋዕት ሲያዘጋጁ በምትኩ በግ ለመስዋዕትነት የቀረበበት መሆኑ የሚያመላክት መሆኑን ድርሳናት ያመላክታሉ፡፡

ዐረፋእናዒድ አልአድሐ” በሚል ርዕስ  አፈንዲ ሙተቂ እንደጻፉት፣ የዒድ አል-አድሓ ታሪካዊ ዳራ ደግሞ ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ለአላህ ለመሰዋት ያደረጉት ቁርጠኝነት የተመላበት ውሳኔ እና ለመስዋዕትነት የቀረበው ልጅ ያሳየው የተለየ ጽናት ነው፡፡ ነቢዩ ኢብራሂም የበኩር ልጃቸው የሆነውን ዒስማኢልን ያገኙት በእርጅና ዘመናቸው ነው፡፡ ታላቅ ሚስታቸው ሳራ ለፍሬ ባለመብቃቷ “ያ አላህ ያለ ዘር አታስቀረኝ፤ እኔን የሚተካ ሷሊህ የሆነ ልጅ ስጠኝ” በማለት ዱዓ አደረጉ፡፡

በዚሁ መሰረት በሳራ ፈቃደኝነት ሐጀራ የምትባለውን የቤት ሰራተኛቸውን አገቡ፡፡ ሐጀራም ዒስማኢል የተባለ ልጃቸውን ወለደችላቸው፡፡ ይህ ልጅ በአላህ ፈቃድ በመካ ከተማ እንዲያድግ የተወሰነ ስለነበረ ኢብራሂም ሐጀራን እና ዒስማኢልን ወደ ዐረቢያ ከተማ ወሰዷቸው፡፡  

ዒስማኢል ካደገ በኋላ ደግሞ አላህ “ልጅህን እንድትሰዋ ታዘሃል” የሚል ትዕይንት በህልማቸው አሳያቸው፡፡ የነቢያት ህልም ደግሞ ከራዕይ የሚቆጠር ነው፡፡ ስለዚህ ኢብራሂም በህልማቸው ያዩትን በዝምታ አላለፉትም፡፡ በወቅቱ የሆነውን ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይተርካል፡፡ “ከርሱ ጋር ለስራ በደረሰ ጊዜም “ልጄ ሆይ! እኔ በህልሜ የማርድህ ሆኜ አይቻለሁ፤ (እስቲ አንተም ነገሩን) ተመልከት፡፡ “ምን ይታይሃል” አለው፡፡ (ልጁም) አባቴ ሆይ! የታዘዝከውን ፈጽም፤ አላህ ቢሻ ከታጋሾቹ ሆኜ ታገኘኛለህ አለ” (ሱረቱ -ሷፍፋት፤ 102)

የዙልሂጃ ወር በገባ የሚኖሩት የመጀመርያዎቹ አሥር ቀናት በፆም በፀሎት ያልፋሉ፡፡ ይህ ፆም ግን እንደ ረመዳን ፆም ግዴታ አይደለም፡፡ ነገር ግን በፈጣሪ ዘንድ ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል፡፡ ፆሙ ሲገባደድ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች ይደምቃል፡፡ የዕርድ በዓል በመባል ለሚታወቀው የአረፋ በዓል ከተገኘ በግ፣ ፍየል፣ በሬ የመሳሰሉትን ማረድ ግድ ይላል፡፡ አቅሙ ለሌላቸው ደግሞ ሰደቃ መስጠት ኢስላማዊ ግዴታ ነው፡፡

የአረፋ አከባበር በየቦታው

ኢትዮጵያ ውስጥ በዓሉ ከሚከበርባቸው አካባቢዎች አንዱ ስልጤ ዞን ነው፡፡ ስለ ስልጤ ብሔረሰብ የአረፋ በዓል አከባበር የመስክ ጥናት ያደረገው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ነው፡፡ የኢንታንጀብል (የማይዳሰሱ) ባህላዊ ቅርሶች ምዝገባ (ኢንቬንተሪ) ብሎ ባሳተመው ድርሳን የሚከተለውን አስፍሯል፡፡ በከተማ የሚኖረው ሕዝብም ለበዓሉ ወደ ሀገሩ የሚተምበት የናፈቁትን ወላጅ ዘመዶቹን የሚጠይቅበት ትልቅ በዓላቸው ነው።

በስልጤ ብሔረሰብ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበረው ትልቅ በዓል አረፋ ነው፡፡
አረፋ ገና ከመድረሱ ቀደም ብሎ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ከፍተኛ ዝግጅት ይጀመራል፡፡ ሴቶች ቅቤ፣ ቅመማ ቅመምና ቆጮ ያዘጋጃሉ፣ አባወራዎች ለእርድ የሚሆን ሠንጋና የማገዶ እንጨት ያቀርባሉ፡፡ ልጃገረዶች ቤቶቹን በተለያዩ የማስዋቢያ ቀለማት በመጠቀም ይቀባሉ፣ ግቢን ያፀዳሉ፡፡በበዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ለወላጆቻቸው ስጦታ በመያዝ ወደየአካባቢያቸው ይገባሉ፡፡ በአረፋ ወደ ቤተሰቡ ያልመጣ በሕይወት እንደሌለ ይቆጠራል፡፡ቤተሰብንም ሥጋት ላይ ይጥላል፡፡ የአረፋ በዓልን በስልጤ ልዩ ድምቀት የሚሰጠው በበዓሉ ሰሞን የሚጀመረው የልጃገረዶች ጭፈራ ነው፡፡ በየመንገዱ ያሉ ልጃገረዶች ከአካባቢያቸው ራቅ ብለው በመሄድ በነፃነት የሚጫወቱበትና የሚጨፍሩበት ወንዶች ወጣቶችም በመሄድ አብረው ሲጫወቱ ለወደፊት የምትሆን የትዳር አጋራቸውን የሚያጩበት ወቅት ነው፡፡ በዚህም የአረፋ በዓል በአብዛኛው የመተጫጫ የጋብቻ ወቅት ነው፡፡በበዓሉ ዋዜማ የሚከበረው የሴቶች አረፋ ሲሆን የወንዶች ደግሞ የበዓሉ ስግደት በሚከናወንበት ዕለት ነው፡፡ በሴቶች አረፋ ክልፋን (የተከተፈ ጐመን) አተካና (ቡላ፣ አይብና ቅቤ) የተለመዱ ባህላዊ ምግቦች ናቸው፡፡ እርዱ የሚከናወነው በበዓሉ ዕለት በሽማግሌ ከተመረቀ በኋላ ነው፡፡የአረፋ በዓል ብሔረሰቡ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠውና ዝግጅት የሚያደርግበት የተለያዩ የቤተሰብ አባላት የሚገናኙበት ስጦታ የሚለዋወጡበት ትዳር ያልያዘ የሚተጫጭበት ትዳር የሚመሠርቱበት በዓል በመሆኑ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፡፡

በዓሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች መካከል ደቡብ ወሎ ይገኝበታል፡፡ የደቡብ ወሎ ነዋሪዎች የበዓሉ ዕለት ማልደው በመነሳት ገላቸውን ታጥበው ለበዓሉ የገዙትን አዲስ ወይም የታጠበ ልብስ ለብሰው የሚሰግዱበትን አነስተኛ ምንጣፍ መስገጃ አንጠልጥለው በጀመዓ (በኅብረት) ወደ ሚሰግዱበት ስታዲየም ያመራሉ፡፡ ከመስገጃው ቦታ እስኪደርሱ  ተክቢራ  (ፈጣሪን ማወደስ) ይላሉ፡፡ ከቦታው ወንዶች ለብቻ ሴቶች ለብቻ ሆነው በጀመአ ይሰግዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...