Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊትራንስፎርመርም ከምሰሶው ሲዘረፍ

ትራንስፎርመርም ከምሰሶው ሲዘረፍ

ቀን:

ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ማነቆ ከሆኑት ምክንያቶች መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት በቂ አለመሆን ይጠቀሳል፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም መንግሥት መብራትን በፈረቃ የመስጠቱ አሠራር ለብዙ ድርጅቶችንና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ትልቅ ፈተና እየፈጠረ ማለፉ የተለመደ ነው፡፡ ማኅበረሰቡም ሥራዎችን በአግባቡ ለመሥራት እንቅፋት ሲሆን ማየቱ፣ ላልተፈለገ ወጪና እንግልት መዳረጋግም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይባስ ብሎም የራስ ጥቅምን በማስቀደም የሕዝብ የጋራ መገልገያ የሆኑ ትራንስፎርመሮችን በመዝረፍ ለራሳቸው የግል ጥቅም የሚያውሉ ግለሰቦች መብዛታቸው ሌላ ችግር ሆኗል፡፡

በአዲስ አበባ የትራንስፎርመሮች ዝርፊያ ከተካሄደባቸው ሠፈሮች መካከል አንዱ ገርጂ አካባቢ የሚገኘው 18 ሠፈር ወረዳ 11 ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ አበበ ከበደ ከወንድማቸው ጋር በትንሽ ግሮሰሪያቸው ውስጥ የራሳቸውን ሥራ በመሥራት ይተዳደራሉ፡፡ በአሁን ሰዓትም መብራት ከጠፋ አንድ ወር ያህል እንደሆናቸውና ይህ ችግርም በኑሮ ውድነት ላይ ተደምሮ ላልተፈለገ ወጭ እንደዳረጋቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ጄኔሬተር ተከራይቶ ሥራቸውን ለመሥራትም አቅማቸው እንደማይፈቅድና ትልቅ ኪሳራም እንደደረሰባቸው ነው የተናገሩት፡፡

በአካባቢው ላይ የሚገኙ የወንድና የሴት ፀጉር ቤቶች ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ በሆነበት ጊዜ መብራት ባለመኖሩ ምንም ዓይነት ሥራ እየሠሩ እንዳልሆኑና ሌላ የገቢ ምንጭ ማስገኛ መንገድ እስከሚያገኙ የቤት ኪራይ በሚደርስ ጊዜም በመሳቀቅ እንደሚያሳልፉ አቶ አበበ አስረድተዋል፡፡

አቶ አበበ እንዳሉት፣ ትራንስፎርመሩ በሚዘረፍበት ወቅት የአካባቢ ነዋሪዎች በመድረሳቸው ትራንስፎርመሩን ለመታደግ ቢችሉም ትራንስፎርመሩ ተፈታቶ በመውረዱና የሚመለከተው አካልም ስላልሠራላቸው መብራት ማጣታቸውን አክለዋል፡፡ መንግሥትም ይህን ችግር በመመልከት ዕልባት መስጠት እንደሚገባው ጠይቀዋል፡፡

ሌላኛዋ ነዋሪ ወ/ሮ ፀጋ ማሞ መብራት በመጥፋቱ ምክንያት አንዳንድ ጊዜም በቤት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ እንደሚታጣ አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም ምግብ ለማብሰል፣ እንጀራ ለመጋገር በእንጨት እንደሚጠቀሙና ይህም ላልተፈለገ ወጭ እንደዳረጋቸው አስታውሰዋል፡፡ ‹‹የሚመለከተው አካል ጋር ብንሄድም ምንም ዓይነት መፍትሔ ልናገኝ አልቻልንም›› ብለዋል፡፡

አካባቢውም ለሌብነት አመቺ በመሆኑ ጨለማን ተገን በማድረግ የተለያዩ ዝርፊያዎች እንደሚካሄዱ አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ክፍሌ እንደሚሉት፣ በገርጂና በለገጣፎ አያት ኮንዶሚኒየም አካባቢ ባለፉት ወራት አመሻሽ ላይ ሰባት ትራንስፎርመሮች መሰረቃቸውን ተናግረዋል፡፡ ሁለቱ ትራንስፎርመሮች በኅብረተሰቡ ኃይልና በፖሊስ እገዛ መገኘታቸውን፣ አብዛኞቹ ትራንስፎርመሮች በገርጂ የተለያዩ ቦታዎች ሊሰረቁ እንደቻሉም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከተሰረቁት ትራንስፎርመሮች መካከል በቦሌ ክፍለ ከተማ ገርጂ ማርያም ሠፈር፣ ወረገኑ፣ ጎሮ ሚካኤል፣ 18 ሠፈር፣ ለገጣፎ አያት ኮንዶሚኒየም አካባቢ ሲሆኑ፣ ትራንስፎርመሮቹ እንደ ኪሎዋታቸው ይለያያሉ፣ ትንሹ ትራንስፎርመር 100 ለሚሆኑ ደንበኞች አገልግሎት የሚሰጥ እንደነበረ አቶ በቀለ አስረድተዋል፡፡

የአንድ ትራንስፎርመር ዋጋ እንደ ኪሎዋታቸው የሚለያይ ሲሆን፣ ትንሹ ትራንስፎርመርም 300,000 ብር እንደሚሸጥ ሥራ አስኪያጅ ገልጸዋል፡፡ አምስቱ ትራንስፎርመሮች የት እንደገቡ ባይታወቅም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ጉዳዩን በመያዝ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ የትራንስፎርመር እጥረት እያለበት እንደዚህ ዓይነት ነገር መከሰቱ ከኢኮኖሚ አንፃር ኪሳራ ውስጥ እንደገባ፣ አገሪቷ ላይ የመብራት ችግር እያለ እንደዚህ ዓይነት አሳፋሪ ድርጊት መፈጸሙ ችግር እንደሆነና መፍትሔ ሊገኝለት ይገባል ብለዋል፡፡ መንግሥትም ለእንደዚህ ዓይነት ችግሮች ትኩረት እንዲሰጥ ከችግሩ አንፃር ማኅበረሰቡም አንድ ላይ በመሆን ዝርፊያ እንዳይፈጸም በመጠበቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጠይቀዋል፡፡

በተመስገን ተጋፋው

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...