ሰላም! ሰላም! ዘንድሮ ለተወለደም ለወለደም ክፉኛ እያዘንኩ ነው። ያሳዘነኝ ምኑ መሰላችሁ? ‹‹ክፋት በሰው ልጅ ታሪክ የአንበሳውን ድርሻ እንዳልተጫወተ፣ ጥንትም የሰው ልጅ አገሩን ርስቱን ከማልማት በደም ሲታጠብ ኖሮ ኖሮ ዛሬ ምንድነው እንደ አዲስ የደም ሥር ሕመም የሆነብን?›› ብዬ የባሻዬን ልጅ ስጠይቀው፣ ‹‹ድሮ ‘ፖስት’፣ ‘ሼር’፣ ‘ላይክ’፣ ‘ታግ’ የለ። ዛሬ ድርጊቱ ከተፈጸመ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ጀንበር እዚያ ያየችውን ዓይታ እዚህ ወደ አንተ ሳትዞር ዜናው ኪስህ ውስጥ ይንጣጣል። በዚህ አያያዛችን እኮ ወደፊት ‘የታሪክ ትምህርት’ የሚባል ሳይታጠፍ ይቀራል?›› ሲለኝ ብዙ ነገር አሰብኩ። የተበላሸው የመርዶ ወግ ትዝ አለኝ። ‘እንዴት አድርገን ነው አሁን ቤተሰብ የምናረዳው?’ እያላችሁ ተጨንቃችሁ ተጠባችሁ ሰብሰብ ብላችሁ ስትሄዱ፣ ድንኳን ተተክሎ ‘አይ የዘንድሮ ልጅ! ካስማ አብሮ የማይተክል’ ስትባሉ ትደርሳላችሁ።
ወላጅ እንዲህ እንደ ቀልድ የልጁን አስከሬን፣ እንደ ዋዛ የዕለት ጉርሱን ሲፈልግ ያም ያም ቀዶ ሲለጥፈው ዓይቶ ባለመደንገጡ ብቻ ሲደነግጥ አውጠነጠንኩ። ከሁሉ በላይ ገና አፍ ሳይፈቱ ከእናት አባት ጠረን ይልቅ የቴክኖሎጂ ቱርፋቶችን አንስተው በመጣል ጡንቻቸውን የሚያፈረጥሙ ሕፃናት ትዝ አሉኝ። ከፍ ሲሉ ባላ ከማስፈንጠር ጀምሮ ‘ኤኬ-47’ እያንጣጡ የአሻንጉሊት ሰው አንገት የሚበጥሱበት ‘ጌሞች’ ታወሱኝ። ነፍስ ቀላባቸው ነፍስ የሚያውቁ የዘመኑ ታዳጊዎች ክፉኛ አሳሰቡኝ። ዓይቼም ባሰብኝ። ያየሁትን እስክነግራችሁ ከፈለጋችሁ እናንተ እየዞራችሁ የማጣራት ሕገ መንግሥታዊ መብታችሁ የተከበረ ነው። መቼስ በትንሽ ትልቁ አትተማመኑ ተብለን ተፈጥረን የለ!
እንግዲህ የልጅነት ነገር ትረካው ብዙ ነው። ድሮ ድሮ ‘ልጅነቴ ልጅነቴ ማርና ወተቴ’ን ስንዘምር ብዙዎቻችንን በማርና ወተት ፈንታ ሽሮና ቂጣ ያሰለቸን ነበርን። የምንዘምረውም የመዝሙር አስተማሪያችን ማርክ እንዳይቀንሱብን በመፍራት ነው። ምን ዋጋ አለው? ለካ እውነትም ልጅነት ማርና ወተት ኖሯል ያልነው ዛሬ በጉልምስና የኑሮን ንረት፣ የክፋትን ረቂቅ ሬት ስናይና ስናጣጥም ሆነ። መቼስ ሰው ዕድሜ ካላስተማረው የዚህ ዓለም ፀጋና መርገም አይገባውም አይደል? ‹‹ደግሞ እኮ ክፋቱ ምንም ላንፈይድ ውለን አድረን ነገር የሚገባን መሆናችን ነው፤›› አለኝ የባሻዬ ልጅ። ይኼን የማርና የወተት ‘ቲዮሪ’ ሳጫውተው ‘ነገር’ ያላት ነገር የቀናነት ቀኖናዬ ውስጥ በመሰንቀሯ ደስ አላለኝም።
ስለዚህ፣ ‹‹የምን ነገር ነው የምታወራው?›› ብዬ ዓይን ዓይኑን ሳየው፣ ‹‹በፖለቲከኞች ሴራና ተንኮል ስለሚባክነው የትውልዶች ዕድሜ፣ ከሰፊው ሕዝብ ጥቅም በፊት ስለራሳቸው ስምና ታሪክ በሚባዝኑ ጥቂት ጀብደኞች ምክንያት እያደር ስለከረሩ የኑሮ አጀንዳዎች ነው የማወራው። በቀላሉ የሚስተካከሉ የኑሮ ስንክሳሮች ጠብቀው ጠብቀው እንኳን ማርና ወተት ውኃና እንጀራም ትግል ሆነ አይደል እንዴ?›› አለኝ። ወዴት ወዴት እንደ ተንሸራተተ ገብቶኛል። ጥቂት ሳዳምጠው መጠለያ፣ ኔትወርክና መብራት የሚል ጨመረበት። ‹‹ይኼን ግለትህንና ቁጭትህን እኔ ላይ ብቻ ከምታባክነው ወይ ምርጫ መወዳደር ነው፣ ወይ ጋዜጣ ላይ መጻፍ ነው፣ አልያም ደግሞ ፌስቡክ ላይ መለጠፍ ነው. . .›› ብለው ትኩር ብሎ ዓይቶኝ ሲያበቃ፣ ‹‹ለማን ብዬ?›› ብሎ ጥሎኝ ሄደ። እኔም ጠቀም ያለ ኮሚሽን የማገኝበት ሥራ ስለነበር ወደ እዚያው ከነፍኩ። ይኼ በሰው እጅ ሲያዩት የሚያስቀና ሲይዙት የሚያደናግር ከበሮ እኮ እንዴት እንደሚያስተዛዝበን? የምሬን ነው!
ኧረ ለመሆኑ መሆንና መምሰል እንዴት እያደረጋችሁ ነው? አደራ ተመሥገን ማለቱን አትርሱ። ምክንያቱማ ለዕድለ ጠማማ መሆንም መምሰልም የሚያቅተን ዘመን ላይ ነው ያለነው። እውነቴን ነው! ይይዙት ይጨብጡትን ማጣት ነው የጊዜው አረማመድ ሥልት እየሆነ የመጣው። እንዲያው ምን እንደሚሻል እንጃ እንጂ። እንኳን ደስ የማይለው ነገር በዝቶ፣ እንዲሁም ይክፋን ካልን ደግሞ ያው ቢጫና ቀይ የሚሰጠን ዳኛ በየፊናው ተሹሞብናል። እናንተ ደግሞ የሹመትን ነገር ሳነሳ አጥብቃችሁ መጠየቅ ትወዳላችሁ። ተነቃቅተናል፡፡ ስለምርጫ እንድንቦጫረቅ ፈልጋችሁ አይደል? ታዲያ አንዱ ምን እንዳለኝ ልንገራችሁ።
ሰሞኑን የአንድ ወዳጃችን ቅድመ አያት ማይክል ጃክሰን ዙርያውን በሳይንሳዊ መንገድ በንፁህ ኦክስጅን ታጥሮ እየኖረ ሊያገኛት የቋመጣትን መቶን አልፈው ጭራሽ ሰባት መርቀውበት አረፉና ሐዘን ሳናበዛ (የአንዳንዶቹ አቀማመጥ ግን ተቆራጭና መዋጮ በበዛበት ዘመን በስንት ዓመቴ እጠራ ይሆን ዓይነት ነው) ተሰብስበናል። እናላችሁ የእራት ሰዓት ደርሶ አንሱ ሲባል ወጡ እጅ ያስቆረጥም ስለነበር እኛ ሳንደርስበት አለቀ። ተራችን ደርሶ ተነስተን ስናይ ከቀረበው አራት ዓይነት ወጥ ተሟጦ የቀረለት አንደኛው ድስት ብቻ ነው። ይኼኔ ወዳጄ፣ ‹‹ኤድያ! አሁንስ በዛ!›› ብሎ ደነፋ። ‹‹ምን ሆንክ?›› እለዋለሁ? ‹‹ምርጫው ካለቀና ካለፈ በኋላ ምኑን ሊያስመርጡን ከሞቀ መቀመጫችን ያስነሱናል?›› ብሎኝ ሳህኑን ወርውሮ ሄዶ ተቀመጠ። ‹‹በለቅሶ ቤት ወጥ እንዲህ ከሆንክ በሠርግ ቤትማ እንዴት ልትሆን ነው?›› ብል ደግሞ እኔ እንደመጣልኝ ሌላኛው ወዳጄ ከት ብሎ ስቆ፣ ‹‹ተው አንበርብር ተው! የሦስተኛውን ዓለም ዴሞክራሲንና የአንደኛውን አታነፃፅር ታብዳለህ!›› አይለኝ መሰላችሁ? ሰው ማስተዛዘንም እንታቀብ እንዴ? እንዴት ነው ነገሩ?!
‹‹አምባሰል ተንዶ ግሸን ገድቦታል፣ የቆመውን ጀግና የተኛው ገድሎታል፣ የቆመውን ጀግና የተኛው መግደሉ፣ ሥፍራ በመያዙ በመደላደሉ. . .›› ያለችው አዝማሪ ትዝ ስትለኝ፣ እንዲያው እንደ ዘራፍ ደርሶ እንደ መወራጨት ያደርገኝና ቀልቤን እንደበተንኩ ተነስቼ እብከነከናለሁ። ውዬ ቤት ስገባ ደግሞ ማንጠግቦሽን በከባዱ አስጠንቅቄያታለሁ። ወላ ቴሌቪዥን ወላ ሬዲዮ የሚባል ነገር እንዳትከፍትብኝ ነዋ። አበጣሪውን ከአጫጁ ምን ይለየዋል? በሉ እስኪ ንገሩኝ? ታዲያ እራት ቀማምሰን ትንሽ እንደቆየን፣ ‹‹ኧረ ቤቱ ሊበላኝ ደረሰ?›› ትለኛለች። ‹‹ስንት ነፍሰ በላ እያየሽ አገርሽ ያውም ቤትሽ ምን ብሎ ይበላሻል?›› ብዬ እደነፋለሁ። ‹‹ባይሆን ድምፁን ቀነስ አድርጌ ልክፈት›› ብላ ትለማመጠኛለች። ቤታችን እኩልነት ስለሌለ አይደለም የምትለማመጠኝ (ደግሞ ነገር እንዳይመጣ ላብራራ እንጂ! አልብራራ፣ አላብራራ እያሉ ነገር በራሳቸው ከሚጠመጥሙት ካልተማርን ከማን እንማር?)። የምትለማመጠኝ ክፉኛ ስላዘንኩና ስሜቴ ስለተጎዳ ብቻ ነው። ሌላ ፆታዊም ሆነ ፖለቲካዊ የበላይነት እኛ ቤት እንደሌለ ልታውቁልኝ እወዳለሁ። በስንት ጭቅጭቅ አጩሃም ሆነ ቀንሳ ስትከፍተው ደግሞ የሰለቸ ወሬ፣ የጠነዛ ቀልድ ፊታችን ድቅን። መጥኔ!
በሉ እንሰነባበት። የሰሞኑን ብርድና ዝናብ አልስማማ ብሎኛል። ድምፄ እንደታፈነ ቢሆንም ሰውነቴን ትንሽ ለቀቅ ስላደረገኝ አሁን አሁን ወጣ ማለት ጀምሬያለሁ። ታዲያ አንድ ባልደረባዬ ደንበኞቼን ሲሸኝልኝ ሰነበተ። ትናንትናና ዛሬ ግን ዘግቶኝ መቅረቱ ከንክኖኛል። ስደውልለት ‹‹ኔትወርኩ’ አይሰማኝም፣ ቆይ መልሼ ልደውል. . .›› ይልና ስልኩን ያጠፋል። ጠቀም ያለ ኮሚሽን እንዳገኘበትና ሊያካፍለኝ እንዳልወደደ ገባኝ። አንዳንዴ ይኼውላችሁ ማን ጠላታችሁ ማን እውነተኛ ወዳጃችሁ እንደሆነ እንድታዩ አልጋ ትይዛላችሁ። ከባሻዬ ልጅ ጋር የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ተሰይመን ስናወራ ይኼንኑ ብነግረው ያውቀው ነበርና በጣም ደነቀው። ‹‹ሲያዩት እኮ እንዲህ ዓይነት ሰው አይመስልም፤›› አለኝ።
‹‹ቢመስልማ ኖሮ ይሁዳን አስቀድመው እነ ጴጥሮስ አይነቁበትም ነበር። መምሰሉን ትቶ መሆኑን የሚያውቀው አምላክ ግን እውነተኛ ጠላት አብሮ በልቶ አብሮ ጠጥቶ፣ ከጉያ እንደሚነሳ ሊያስተምረን ሲያስከትለው ኖረ. . .›› ብዬ ባሻዬ ሊያፅናኑኝ የነገሩኝ ወንጌል ነገርኩት። ‘ዋና ዋናችንን’ ጨርሰን ወደ ቤታችን ስንጓዝ ቅስሜ እጅግ ተሰብሮ ነበርና በአዕምሮዬ የማወጣ የማወርደው ነገር ብዙ ነው። ከጥንት እንዲህ ነበር? ወይስ ዛሬ ነው ገንዘብ እንዲህ የሚጫወትብን? የታለ ታማኝነት? የታለ አብሮ ማደግ? የታለ አብሮ መብላት? ለምንድነው አንዲት ጎጆ ከማቅናት አንስቶ አገር እስከ መገንባት አብረን አፈር ፈጭተን ጭቃ አቡክተን ባደግንባት ምድር ላይ የሚከብደን? ለምን ከጥምረት ለመለያየት፣ ከኅብረት ለመበተን ጎዳናው ሁሉ አልጋ በአልጋ እየሆነ ይጠብቀናል? ለምን? ለምን? ለምን? ተሽሎኝ የነበረው ራስ ምታት ሲብስብኝ ጥያቄዎቼን ሳልመልስ እንቅልፍ አዳፋኝ። ደግሞ ዘር፣ ቋንቋ፣ ባህልና እምነት ሲጨማመርበት አስቡት። አንዳንዴማ ካልጠበበ ቦታ እግር መዘርጊያ ሊያሳጡን የሚከጅሉትን ሳይ ህሊናዬ ይበጠበጣል፡፡ ሰፊው አዳራሽ እያለ ጠባብ ጉረኖ ውስጥ ለምን እንደምንታገል ይደንቀኛል፡፡ ስሜት ህሊናን ሲሟገት፣ ህሊና ታዛቢ ሆኖ ሲደመም ይገርመኛል፡፡ እንቅልፍ እየተጫጫነኝ ሰፊው ቦታ ሲጠበኝ ስንብት አማረኝ፡፡ መልካም ሰንበት!