Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሪፎርም ስም ሱፐርቫይዘሮችን ከቦታቸው ማንሳት በአስቸኳይ እንዲቆም ትምህርት ሚኒስቴር አዘዘ

በሪፎርም ስም ሱፐርቫይዘሮችን ከቦታቸው ማንሳት በአስቸኳይ እንዲቆም ትምህርት ሚኒስቴር አዘዘ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ እያከናወነው ባለው ሪፎርም ምክንያት ‹‹ከፍተኛ›› የሥልጠና ወጪ ወጥቶባቸዋል የተባሉ ሱፐርቫይዘሮችን ከሥራ ምድባቸው በማንሳት ወደ ተለያዩ ትምህርት ቤቶች መመደቡን “በአስቸኳይ” እንዲያቆም፣ የትምህርት ሚኒስቴር ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

በቅርቡ ከቦታቸው ተነስተው በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በዳይሬክተርነትና በምክትል ዳይሬክተርነት የመደባቸውን ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመለስ ሲል፣ ሚኒስቴሩ ለቢሮው በጻፈው ደብዳቤ ማሳወቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣነ መንበሩን ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ መንግሥት በአገር አቀፍ ደረጃ ሪፎርም መጀመሩ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮም በከተማ ደረጃ ባካሄደው ሪፎርም፣ ባዘጋጃቸው የሥራ መደቦች የሠራተኛ ድልድል ማድረጉ ይታወቃል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይሁን እንጂ በዚህ የሥራ ድልድል የሱፐርቫይዘርነት የሥራ መደብን ለሁሉም የትምህርት ባለሙያዎች ክፍት በማድረጉና በድልድሉ በሥራ ላይ የሚገኙትን ቅር እንዳሰኛቸው፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ከሥራ መደቡ የተነሱና በቅርቡ እንደሚነሱ ሥጋት ያደረባቸው በሥራ ላይ ያሉ ሱፐርቫይዘሮች አስረድተዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ እነዚህ ሱፐርቫይዘሮች ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ሱፐርቫይዘሮች በርካታ ሥልጠናዎችን የወሰዱ፣ የረዥም ዓመት ልምድ ያላቸውና በትምህርት ዝግጅታቸውም የተሻሉ ሆነው የተመደቡ ናቸው፡፡

የሥራ ምደባቸውም እንደ መደበኛ የትምህርት ባለሙያዎች በደረጃ የሚመደቡ አለመሆናቸው እየታወቀ፣ ቢሮው ከአሠራርና ከደንብ ውጪ ባለሙያ ካልሆኑት ጋር እንዲወዳደሩ ማድረጉ አግባብ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሱፐርቫይዘሮች በዋነኛነት በአስተዳደሩ ሥር ያሉ ትምህርት ቤቶችን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራ የሚያከናውኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች ሲሆኑ፣ ተጠሪነታቸውም በቀጥታ ለትምህርት ቢሮው ነው፡፡

የደመወዝ ስኬላቸውም ሆነ የደረጃ ዕድገት አወሳሰን ከመደበኛ የትምህርት ባለሙያዎች የሚለይ ሆኖ፣ በትምህርት ሚኒስቴር በተዘጋጀ የራሱ መመርያና ስታንዳርድ መሠረት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

በሲቪል ሰርቪስ መመርያ መሠረት የ‘ኬሪር ስትራክቸር’ ያላቸው ሱፐርቫይዘሮች በመደብ ከሚታዩ የትምህርት ባለሙያዎች ጋር እኩል በሥራ ድልድሉ ተወዳደሩ በመባላቸው፣ ቅሬታቸውን ለትምህርት ሚኒስቴር ለማሰማት መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡

በዚሁ በተጠቀሰው የሪፎርም ሥራ የተነሱትና በቀጣይ የመነሳት ዕርምጃ ይጠብቀናል ያሉት ሱፐርቫይዘሮቹ፣ በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም. ለትምህርት ሚኒስቴር በጽሑፍ አመልክተዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በቁጥር 2/2-1188/90701(2) በጻፈው ደብዳቤ የትምህርት ቢሮው የሪፎርም ዕርምጃ አሠራርን የጣሰ ነው ሲል ኮንኖታል፡፡

በሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ፅዮን ተክሉ ስም ተፈርሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ግልባጭ ከተደገ በኋላ ለትምህርት ቢሮው የተላከው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ በቅሬታ አቅራቢዎች ማመልከቻ መሠረት ሚኒስቴሩ አጣሪ ኮሚቴ ልኮ ባደረገው ምርመራ ችግሩን መረዳት መቻሉን አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ከራሱ ከሚኒስቴሩ፣ ከፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና ከኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር በማዋቀር የደረሰበትን ግኝት በደብዳቤ ገልጿል፡፡

አጣሪ ኮሚቴውም ወደ ትምህርት ቢሮ በመሄድ የሚመለከታቸውን ኃላፊዎችና የትምህርት ባለሙያዎች በማነጋገር፣ የተፈጠረውን ቅሬታና አገራዊ አሠራሮችን መሠረት በማድረግ ክፍተቱን በግልጽ እንዳስቀመጠ በሚኒስቴሩ ደብዳቤ ተገልጿል፡፡

‹‹ስለሆነም ለኢፌዴሪ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሰው ሀብት አስተዳደር መመርያ በመደብና በኬሪር ስትራክቸር መካከል ግልጽ ልዩነቶችን ያስቀመጠ ሆኖ እያለ፣ የከተማ አስተዳደሩ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ሰኔ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በቁጥር 11/ከ11-24081-1066 ለአሥሩ ክፍለ ከተሞች ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤቶች በተጻፈ ደብዳቤ ላይ እንደተጠቀሰው፣ ከትምህርት ቢሮ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በተደረገው ውይይትና ስምምነት ለሱፐርቫይዘሮችና ለትምህርት ባለሙያዎች እኩል ዕድል ተሰጥቶ ለሱፐርቫይዘር የሥራ መደብ እንዲወዳደሩ፣ ከፕሳ ወደ ሱፐርቫይዘር የሚመደቡ ባለሙያዎች በተባባሪ ሱፐርቫይዘርነት እንዲሁም በውድድር የማይቀጥሉ ሱፐርቫይዘሮች ሌላ ሥራ እንዲሰጣቸው ይላል፡፡ ይህ ሁኔታ በመደብና በኬሪር ስትራክቸር በኩል ያለውን አሠራር የጣሰ መሆኑን ያሳያል፤›› ይላል የሚኒስቴር ደብዳቤ፡፡

‹‹በሌላ በኩል በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር በመምህራንና በትምህርት አመራሮች ገዥ መመርያ (ብሉ ፕሪንት) በግልጽ እንደተገለጸው፣ በተለያየ ጊዜ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተዘጋጀው የደረጃ ዕድገት መመርያ የትምህርት ቤቶች ስታንዳርድ ሰነድ እንደገለጸው፣ ሱፐርቫይዘር የሥራ መደብ የትምህርት አስተዳደራዊ ሥራን ለማሳለጥ በጥናት ላይ ተመሥርቶ የተቀመጠ የሥራ ዘርፍ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የሱፐርቫይዘር ፕሮፋይልና ፑል ተመላክቷል፤›› ሲል ይኸው የሚኒስቴሩ ደብዳቤ ያክላል፡፡

‹‹ይሁንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮና የትምህርት ቢሮ ከፍተኛ አመራሮች ማንኛውም የትምህርት ባለሙያ በሱፐርቫይዘር የሥራ መደብ ክፍት ሆኖ እንዲወዳደር ማድረጋቸው መዋቅራዊ አሠራርን የጣሰ ከመሆኑም በላይ፣ ለሥልጠና እየፈሰሰ ያለውን የአገር ሀብትና የሠለጠነ የሰው ኃይል ዋጋ አለመስጠት ብቻም ሳይሆን፣ የሚኒስቴር መሥርያ ቤቱን የትምህርት ስታንዳርድና ፑሉን ጭምር የጣሰ አሠራር እንደሆነ ማየት ተችሏል፤›› ይላል፡፡

ስለሆነም የአዲስ አበባ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በሱፐርቫይዘሮች ላይ ያደረገው ምደባ የትምህርት ሥርዓቱን ያልተከተለና አገራዊ አሠራሩን የጣሰ በመሆኑ፣ ምደባው በአስቸኳይ እንዲቆምና በዚህ ምደባ ሥርዓት ከሥራቸው የተፈናቀሉ ሱፐርቫይዘሮች ወደነበሩበት የሥራ መደባቸው እንዲመለሱ ሚኒስቴሩ በጥብቅ አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ ዘለዓለም ሙላቱ ቢሮው የሪፎርም ሥራውን አላቆምም ማለቱን በተመለከተ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የትምህርት ሚኒስቴርን ትዕዛዝ ሥራ ላይ ለማዋል ገና አልተወሰነም፡፡ በከተማ ቻርተሩ መሠረትና ባለው ስታንዳርድ እየሠራን ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለጊዜው ዝርዝር መረጃ አልሰጥም፤›› ብለዋል፡፡

በቢሮው ሥር 160 ያህሉ ሱፐርቫይዘሮች ያሉ ሲሆን፣ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ከ50 እስከ 60 የሚደርሱት በአዲሱ ሪፎርም ወደ ተለያዩ ትምህርት ቤቶች መመደባቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...