በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተማ በፀጥታ አካላትና በውጭ አገር ዜጎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባትና ግጭት ምክንያት በቁጥጥር ሥር የሚገኙ 150 ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ዓርብ ነሐሴ 3 ቀን 2011 ለጋዜጠኞች በሰጡት መደበኛ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት፣ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ የከተማው የንግድ ማዕከል ከሚገኙ ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከሕግ አስከባሪዎች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ለእስር የተዳረጉ ዜጎች መኖራቸውን በመግለጽ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፕሪቶሪያ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
‹‹በግጭቱ ሳቢያ 600 የሚሆኑ የተለያዩ አገር ዜግት ያላቸው ሰዎች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 150 የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው፤›› ያሉት ቃል አቀባዩ፣ በእስር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን መካከል በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱትን ለማስፈታት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም አክለዋል፡፡
ክስተቱን ተከትሎ በፕሪቶሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኢትዮጵያ ዜጎች ጉዳይን አስመልክቶ ባደረገው ክትትል ኢትዮጵያውያኑ የት ቦታ እንደታሰሩና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ማወቁን የገለጹት አቶ ነቢያት፣ ኢትዮጵያውያኑን ለማስፈታትም ከደቡብ አፍሪካ ፖሊስ፣ ከአገሪቱ የገዥው ፓርቲ (ኤኤንሲ) የቀድሞ አመራሮች፣ እንዲሁም ስቲቭ ቢኮ ፋውንዴሽን ከተሰኘ መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በጋራ በመሥራት ላይ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤምባሲ በዋነኛነት ከደቡብ አፍሪካ የሕግ አስከባሪ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ እንደሆነ የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ በውይይቱም በዋነኛነት በቁጥጥር ሥር የሚገኙት ዜጎች የሕግ አካሄድ እንዲከበር፣ በማጣራት ሒደቱም አላስፈላጊ የመብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙና የተጀመረውን የፍርድ ሒደት የሚከታተል ጠበቃ በማቆም እየሠራ እንደሚገኝም አክለው ገልጸዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ሰነድ አልባ ያላቸውን የውጭ ዜጎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቆ፣ የወንጀል ሪከርዳቸውንና ወደ አገር የገቡበትን ሁኔታ እንደሚመረምር ገልጿል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ ሦስት ሚሊዮን የሚገመቱ የውጭ ዜጎች ሲኖሩ፣ የኢትዮጵያዊያን ቁጥር በመቶ ሺዎች ይገመታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ቃል አቀባዩ ስለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ ስደተኞችን ወደ አገራቸው የመመለስ ሥራ፣ በጉዲፈቻ ወደተለያዩ አገሮች የሄዱ ሕፃናትና ወጣቶች ትውልድ አገራቸውን መጎብኘታቸውን፣ የሱዳን ወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤትና የነፃነትና ለውጥ ኃይሎች ስለፈረሙት ስምምነት፣ እንዲሁም ስምምነቱ እንዲፈጸም ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት የኢትዮጵያ መንግሥትና የአፍሪካ ኅብረት የምሥጋናና የሽልማት ሁነት መርሐ ግብር መከናወኑን የተመለከቱ ጉዳዮችን አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል፡፡