Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ስድስት የውጭ ሰፋፊ እርሻዎች ኃላፊነት የጎደለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ማከናወናቸው በጥናት ተረጋገጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሁሉም እርሻዎች የዕቅዳቸውን 30 በመቶ እንኳ ማሳካት ሳይችሉ ቀርተዋል

አራት የህንድ፣ አንድ የሳዑዲና አንድ የቱርክ ሰፋፊ እርሻዎች የተካተቱበት አዲስ ጥናት ይፋ እንዳደረገው፣ ሳዑዲ ስታርን ጨምሮ ስድስት ኩባንያዎች ለአካባቢ፣ ለማኅበረሰቦችና ለድህነት ቅነሳ ተስማሚነት የጎደለው የኢንቨስትመንት እቅስቃሴ ሲያካሄዱ መቆየታቸውን ይፋ አደረገ፡፡ ሁሉም ኩባንያዎች ስለሰፋፊ እርሻ ዕውቀቱም ክህሎቱም አልነበራቸውም ተብሏል፡፡

ጥናቱን ያካሄዱትና የጥናት ውጤቶቻቸውን በመጽሐፍ አሳትመው በቅርቡ ለንባብ ያበቁት አጥቅየለሽ ጂ.ኤም. ፕርሰን (ዶ/ር) የተባሉ ኢትዮጵያዊ ምሁር በተለይ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ይፋ እንዳደረጉት፣ በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በምግብ ሰብል ምርት ብሎም በባዮፊውል ተክሎች ልማት ለመሠማራት ፈቃድ ካወጡበት ሂደት ጀምሮ እስከ ትግበራ በነበራቸው እንቅስቃሴ ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ ውኃ ገብ መሬቶችን፣ ጥብቅ ደን መሬቶችንና በእርሻዎቹ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ህልውና አደጋ በሚጥል ሁኔታ የእርሻ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡

ይህም ሆኖ አንዳቸውም በአካባቢና በሰዎች ላይ ካደረሱት ጉዳት በቀር ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳያስገኙ የአገሩን ሀብት ለኪሳራ ዳርገዋል ያሉት አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፣ ያለ በቂ ዕውቀትና ክህሎት ወደ እርሻ ሥራው መግባታቸውም በአገሪቱ ላይ የደረሰውን ጉዳት እንዳባባሰው አብራርተዋል፡፡

ከኢንቨስትመንት አኳያ ከ70 በመቶ ካፒታል ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተበድረው ሥራ መጀመራቸው የተነገረላቸው ኩባንያዎች፣ ከሁለት እስከ አራት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የኦፕሬሽን ሥራዎቻቸውን በማሳካት ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ቢያቅዱም፣ አንዳቸውም 30 በመቶ እንኳ ማሳካት እንዳልቻሉ አጥቅየለሽ (ዶ/ር) በመጽሐፋቸው አመላክተዋል፡፡

የሼክ መሐመድ አል አሙዲ ንብረት የሆነው ሳዑዲ ስታር፣ እንዲሁም የህንዳዊው ሳይ ራማክሪሽና ካሩቱሪ ኩባንያ የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን ከፊል ይዞታ ቆርሶ የሚወስድ ሰፊ መሬት ወስደዋል፡፡ ሳዑዲ ስታር ከአሥር ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት በመውሰድ በአብዛኛው ሩዝ ለማምረት እንቅስቃሴ ቢጀምርም አልሆነለትም፡፡ ካሩቱሪ አግሮ ፕሮዳክት የተሰኘው ኩባንያም፣ በ100 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የፓልም ዘይት ተክል፣ ሸንኮራ አገዳ፣ ሩዝ፣ በቆሎና ጥጥ ለማምረት በሰፊው እንደሚገባ ሲጠበቅ በእንጭጩ ቀርቷል፡፡ ሌሎቹም በተመሳሳይ ሁኔታ ከመንገድ መቅረታቸውን አጥኚዋ አብራርተዋል፡፡

ሳዑዲ ስታር በአራት ዓመታት ውስጥ መቶ በመቶ የሰብል ምርት በአራት ዓመታት ውስጥ እንደሚያሳካ ቢወጥንም፣ ከአምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ያከናወነው የዕቅዱን 3.5 በመቶ ብቻ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ካሩቱሪ በበኩሉ ሥራ በጀመረ በሁለት ዓመታት ውስጥ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ እንደሚተገብር ቢያስታውቅም፣ በአምስት ዓመታት ውስጥ ሊያሳካ የቻለው ግን 30 በመቶ ብቻ ሆኗል፡፡

ቶረን አግሮ ኢንዱስትሪ የተሰኘ ኩባንያም በሦስት ዓመታት 28 በመቶ የዕቅዱን ሲያከናውን፣ ኤስ ኤንዴ ፒ ኢነርጂ ሶሉሽንስ የዕቅዱን ሰባት በመቶ በአራት ዓመታት ውስጥ አከናውኗል፡፡ ሩኪ አግሪ እንዲሁም ቢኤችኦ ባዮ ፕሮዳክትስ የተሰኘው ኩባንያም በአራት ዓመታት ውስጥ ለማሳካት ያቀደውን የግብርና ሥራ ትልም፣ በሦስት ዓመታት ውስጥ ከ22 በመቶ በላይ ሊገፋበት ሳይችል በኪሳራ ወጥቷል፡፡ 

እንዲህ ያለውን የወረደ አፈጻጸም ያስመዘገቡት የውጭ ኩባንያዎች ብቻም ሳይሆኑ፣ የመንግሥት ተቋማትም ከፍተኛ የአቅም ችግርና የክትትል ድክመት ስለነበረባቸው፣ በክልልና በፌዴራል መንግሥት መካከል በነበሩ የአሠራር ክፍተቶች፣ በመሠረተ ልማት እጥረትና በሌሎችም ችግሮች ሳቢያ የሰፋፊ እርሻዎች ውጥን ከግብ ሳይደርስ በመንገድ መቅረቱን አጥኚዋ አስረድተዋል፡፡

ኩባንያዎቹ በሚገቡበት ወቅት የእርሻ ሥራቸውን በሚያከናውኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ማኅበረሰቦች ስለኩባንያዎቹ መግባት እንዲያውቁና እንዲመክሩበት፣ ሐሳባቸውንም እንዲያካፍሉ አለመደረጉ ለእርሻዎቹ መውደቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አጥቅየለሽ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የማኅበረሰቦቹን ፍላጎትና ሐሳብ የመንግሥት ተቋማትም ሆኑ ባለሀብቶቹ ቸል በማለታቸው ሳቢያ በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን፣ በተለይም እንደ ካሩቱሪ ያሉ ኩባንያዎች በዘረጉት የተሳሳተ የመስኖ እርሻ መሠረተ ልማት በእርሻው ከሚገኙ መካከል የሦስት ቀበሌ መንደሮች ሙሉ ለሙሉ በጎርፍ እንዲጥለቀለቁ መንስዔ መሆኑን አውስተዋል፡፡

መንግሥት በሰፋፊ እርሻዎች ላይ ፍላጎት ካለው እንዲህ ያሉ ችግሮችን በማጤን ለወደፊቱ እንዲያስተካክላቸው የጠየቁት አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፣ ጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉምዝ ካላቸው ተፈጥሯዊ መስህብና አረንጓዴያማነት አኳያ ከእርሻ ይልቅ የኢኮ ቱሪዝም ሥራ ትኩረት ቢሰጠውና አዋጭነቱም ቢጠና በማለት ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

በመደበኛ ሥራቸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የፕሮግራም ኦፊሰር የሆኑት አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፣ የ20 ዓመታት የጥናትና ምርምር ተሞክሮ አካል የሆነውና ‹‹ፎሬን ዳይሬክት ኢንቨስትመንት ኢን ላርጅ ስኬል አግሪካልቸር ኢን አፍሪካ›› በሚል ርዕስ ያሳተሙት መጽሐፍ፣ ስድስት የተመረጡ እርሻዎች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና አካባቢያዊ ዘላቂነት ላይ ያሳደሩትን ጫና በትንታኔ አቅርበውበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች