የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደርን ጨምሮ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የአሠራር ሥነ ሥርዓት በሚመለከት፣ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የቀረበው ረቂቅ የመከላከያ፣ የደኅንነትና የፖሊስ ተቋማትን አይመለከትም መባሉ ቅሬታ አስነሳ፡፡
ረቂቂ አዋጁ በዋናነት የሚመለከተው ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮችና የፌዴራል አስተዳደር ተቋማትን ሲሆን፣ ተቋማቱ በሕግ የተሰጣቸውን አስተዳደራዊ ውሳኔ የመስጠትና መመርያ የማውጣት ሥልጣንና ተግባራት በሥራ ላይ ሲያውሉ በሕግ መመራታቸውን፣ ከተፈቀደላቸው የሥልጣን ክልል አለማለፋቸውን፣ እንዲሁም የዜጎችን የተሳትፎና የመደመጥ መብት ማክበራቸውን ማረጋገጥና ዕርማት የሚደረግበት ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ መሆኑ በስፋት ተገልጿል፡፡
የረቂቅ አዋጁ መቅረብ በአገሪቱ እየታየ ያለውን የመንግሥት ተቋማትን ብልሹ አሠራር በተወሰነ ደረጃ የሚያሻሽልና ተገልጋይ ዜጎችም በአስፈጻሚ ተቋማትና አመራሮች ላይ እስከምን ድረስ መብት እንዳላቸው ግንዛቤ የሚሰጥ ቢሆንም፣ በዋናነት ቁጥጥር ሊደረግባቸው የሚገባው የፖሊስ፣ የመከላከያና የደኅንነት ተቋማት ግን ከአዋጁ ውጪ መደረጋቸው ወይም ‹‹እነሱን አይመለከትም›› መባሉ ተገቢ እንዳልሆነ፣ ስለረቂቅ አዋጁ በተደረገ ውይይት ላይ የተሳተፉ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡
ሦስቱንም ተቋማት ከሕግ በላይ በማድረግ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ ሆነው መኖራቸውን የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ የሕግ የበላይነት በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለ መሣሪያ መሆኑን፣ አዋጁም እነዚህን ተቋማት አደብ የሚያስገዛ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የአስተዳደር ተቋማት ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ከሚያደርሱት በደል ዜጎችን መጠበቅና በደል ሲደርስባቸውም መፍትሔ የሚያገኙበት ሥርዓት መዘርጋት ስለሚያስፈልግ፣ ሦስቱም ተቋማት በዚህ ሥርዓት ውስጥ መካተትና አዋጁ እነሱንም የሚያቅፍ መሆን እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል የአስተዳደር ተቋሞች የአሠራር ሥነ ሥርዓትን አዋጅ አስፈላጊነት ተቋማት የውሳኔ አሰጣጥና የመመርያ አወጣጥ መርሆዎችንና ሥነ ሥርዓት፣ እንዲሁም በአስተዳደራዊ ውሳኔዎችና መመርያዎች ቅር የተሰኘ ሰው የውሳኔዎቹንና የመመርያዎቹን ሕጋዊነት በፍርድ ቤት የሚያስመረምርበት ሥርዓት በመደንገግ፣ የግልጽነትና ተጠያቂነት ባህል በማዳበር አስተዳደራዊ ፍትሕን ማስፈጸም ስለሚያስፈልግ ሦስቱም ተቋማት በዋናነት በአዋጁ መካተት እንዳለባቸውና ቁጥጥር ሊደረግባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ለበርካታ ዓመታት በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ሳይደረግ የቆየው የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን የሚመለከተውና ለመጀመርያ ጊዜ በጌትፋም ሆቴል ሐምሌ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ለውይይት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ፣ በአራት ንዑስ ክፍሎች፣ 57 አንቀጾችና 67 ንዑስ አንቀጾችን የያዘ ነው፡፡
ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በተገቢው ጊዜ መመርያ ማውጣት እንዳለበት ግዴታ የሚጥለው አዋጁ፣ መመርያ ባያወጣ እንኳን መብቱ ወይም ጥቅሙ የተነካበት ማንኛውም ሰው ተቋሙ ውሳኔ እንዲሰጠው የመጠየቅን መብት ያጎናፅፋል፡፡ ተቋሙ ተገቢውን መመርያ ሳያወጣ ቢቀር እንኳን፣ ማንኛውም ሰው ተገቢውን መመርያ እንዲያወጣ በጽሑፍ ማቅረብ እንደሚችልና የተቋሙ አመራር በ30 የሥራ ቀናት ውስጥ መመርያውን የማውጣት ሒደት መጀመር እንዳለበት፣ ወይም በጽሑፍ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ መስጠት እንዳለበትም ያስረዳል፡፡
የአስተዳደር ተቋማቱ መመርያ ከማውጣታቸው በፊት ስለሚያወጡት መመርያ ረቂቁን በጋዜጣ፣ በተቋሙ ድረ ገጽና በሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ዝርዝር መረጃዎችን ማውጣት እንዳለበትም ረቂቅ አዋጁ ያስረዳል፡፡
የተቋማቱ አስተዳደር ውሳኔ ጥያቄ በጽሑፍ ሆኖ እንደ ሁኔታው በአካል፣ በተመዘገበ ፖስታ ወይም በኤሌክትሮኒክስ ዘዴዎች ሊቀርብ እንደሚችልና ለቀረበው ጥያቄ ወዲያውኑ ውሳኔ የማይሰጥ ከሆነ ለጥያቄ አቅራቢው ደረሰኝ መስጠት፣ ጥያቄው በተገቢው ጊዜ እንዲመዘገብና ለውሳኔ እንዲቀርብ ማድረግና ጉዳዩ የሚታይበትን ቀነ ቀጠሮ ለባለጉዳዩ የማሳወቅ ግዴታ ይጥላል፡፡ ውሳኔ የሚሰጠው የተቋሙ የበላይ ኃላፊ ወይም ሥልጣን የተሰጠው የተቋሙ የሥራ ኃላፊ ብቻ መሆን እንዳለበትም ይደነግጋል፡፡ ውሳኔ የሚሰጠው ኃላፊ ተገልጋዮች ያቀረቡትን ፍሬ ነገርና ማስረጃ መመርመር፣ እንደ ሁኔታው የሦስተኛ ወገን አስተያየት ማዳመጥ እንዳለበትም ግዴታ ይጥላል፡፡
ቅሬታ አቅራቢው ውሳኔ ከሚሰጠው ኃላፊ ጋር በሥጋ ወይም በጋብቻ ዝምድና ካለው ወይም በማንኛውም ሁኔታ ግጭት የሚያስከትልበት ከሆነ ጉዳዩን ማየት እንደሌለበት፣ በዘር፣ በብሔር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት መጠን፣ በትውልድ ሁኔታ፣ ወይም በሌላ ምክንያት ልዩነት ሳያደርግ ማስተናገድ እንዳለበትም አዋጁ ያስጠነቅቃል፡፡
በፌዴራል ተቋማት ውሳኔ ቅር የተሰኘ ተገልጋይ ለአስተዳደር ተቋሙ ቅሬታ ማቅረብ እንደሚችል፣ ተቋሙም የቅሬታ ማስተናገጃ አካል ማቋቋምና ለተገልጋዩም ይፋ ማድረግ እንዳለበት፣ የቀረበው ቅሬታ ተመርምሮ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ እንዳይፈጸምም እንደሚደረግ ረቂቂ አዋጁ ያብራራል፡፡ የአስተዳደር ተቋሙ ውሳኔ ተገቢ አለመሆኑን የተረዳ ሰው፣ ውሳኔው በፍርድ ቤት እንዲከለስ አቤቱታ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚችልና የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የመጨረሻ እንደሚሆንም ደንግጓል፡፡ የክለሳ አቤቱታው መመርያውን በሚመለከት ከሆነ መመርያው ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ በ90 ቀናት ውስጥ መሆኑን፣ የአስተዳደር ውሳኔን ለማስከለስ ከሆነ ደግሞ ውሳኔው ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ መሆን እንዳለበትም አዋጁ ያስረዳል፡፡ ፍርድ ቤቱም ውሳኔው ሊመረመር ይገባዋል ብሎ ሲያምን ቅሬታ የቀረበበት ተቋም በ15 ቀናት ውስጥ የጽሑፍ መልስ እንዲሰጥ ማዘዝ እንዳለበት ይገልጻል፡፡
የአስተዳደር ተቋማቱ በሚያወጡት መመርያ ወይም በሚሰጡት ውሳኔ ጉዳት የደረሰበት ማንኛውም ተገልጋይ፣ የአስተዳደር ተቋሙን (የመንግሥት አስፈጻሚ ተቋማትን) አግባብ ባለው ሕግ መሠረት ካሳ እንዲከፍል መጠየቅ እንደሚችልም ረቂቅ አዋጁ ለተገልጋይ ሕጋዊ መብት ሰጥቷል፡፡