Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሜቴክ ተመርተው ገዥ ያጡ ከአሥር ሺሕ በላይ ትራክተሮችና መለዋወጫዎች በርካሽ ዋጋ እንዲሸጡ...

በሜቴክ ተመርተው ገዥ ያጡ ከአሥር ሺሕ በላይ ትራክተሮችና መለዋወጫዎች በርካሽ ዋጋ እንዲሸጡ ወይም በስጦታ እንዲበረከቱ ተወሰነ

ቀን:

ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የተሰየመው አዲሱ የሥራ አመራር ቦርድ፣ በኮርፖሬሽኑ ያለ ገበያ ጥናት ተመርተው ገዥ ማግኘት ባለመቻላቸው በአዳማ የእርሻ መሣሪያዎች ኢንዱስትሪ ከስድስት ዓመታት በላይ ተከማችተው የሚገኙ ከአሥር ሺሕ በላይ የሚሆኑ ትራክተሮችና መለዋወጫዎች፣ ከተቻለ በርካሽ ዋጋ እንዲሸጡ ካልሆነም ለክልሎች በስጦታ እንዲበረከቱ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ሜቴክን ከገባበት የኢኮኖሚ ውድቀት የማንሳት ተልዕኮ ተሰጥቶት የተሰየመው አዲሱ የተቋሙ ሥራ አመራር ቦርድ፣ ከሰኔ ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ከተቋሙ አስተዳደር ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተደጋጋሚ ስብሰባዎችን ማድረጉን ሪፖርተር ያገኘው የሰነድ ማስረጃ ያመለክታል፡፡

አገሪቱን ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር መደላድል እንዲሆንና የአገር ውስጥ የኢንጂነሪንግ አቅም የመፍጠር ተልዕኮ በመንግሥት ተሰጥቶት በ2002 ዓ.ም. የተቋቋመው ሜቴክ፣ ዓላማውን ስቶና በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቆ በአሁኑ ወቀት በካዝናው ውስጥ የሥራ መንቀሳቀሻ ቤሳቤስቲን እንደሌለው ማኔጅመንቱና የሥራ አመራር ቦርድ መረዳቱ ታውቋል፡፡ ተቋሙን ከአዘቅት ውስጥ ለማውጣት ከተወሰኑት ጉዳዮች አንዱ በተቋሙ ያለ ገበያ ጥናት ተመርተው ከስድስት ዓመታት በላይ ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቁባቸው የከረሙ ትራክተሮችና መለዋወጫዎቻቸውን፣ እንዲሁም ሌሎች ተመርተው የተከማቹ የኢንዱስትሪ መሣሪያዎችን በመሸጥ ተቋሙ የገጠመውን መንቀሳቀሻ መቅረፍ ነው፡፡ የተከማቹትን ትራክተሮችና መለዋወጫዎች ወደ ገንዘብ መለወጥን በተመለከተ፣ የሜቴክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሦስት አማራጮችን ለቦርዱ ማቅረባቸውን ሪፖርተር ያገኘው ማስረጃ ያመለክታል፡፡

 የመጀመሪያው አማራጭ ዋጋቸው ተቀንሶ ለግብርና ሚኒስቴርና ለስኳር ኮርፖሬሽን እንዲሸጡ፣ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ በከተማ ውስጥ ቆሻሻ ለማንሳት  ወይም ለሌላ ተመሳሳይ ሥራ እንዲውሉ በአነስተኛ ዋጋ እንዲሸጡ፣ በሦስተኛነት የቀረበው አማራጭ ቆራርጦ በመሸጥ የተቋሙን ጥቅም ማስከበር እንደሚቻል የሚያስረዱ ናቸው፡፡ ሦስቱም አማራጮች ካልተሳኩ ደግሞ ለክልሎች በስጦታ መልክ ቢበረከቱ የተቋሙን ገጽታ ከመገንባት አንፃር ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ አማራጮችን፣ የሥራ ኃላፊዎቹ ለቦርዱ ለውሳኔ ማቅረባቸውን መረጃው ያስረዳል፡፡

ይሁን እንጂ ቦርዱ በቀረቡት አማራጮች በተለይም በመጀመሪያው አማራጭ ላይ ባነሳቸው የማብራሪያ ጥያቄዎች፣ በአዳማ የእርሻ መሣሪያዎች ኢንዱስትሪ የተከማቹት ትራክተሮች ከገቡ የቆዩ መሆናቸውና ለሽያጭ የወጣላቸው ዋጋም ከፍተኛ በመሆኑ ገዥ ማግኘት እንደማይቻል፣ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ባስቀመጠው የሥራ ዕድል ፈጠራ ስትራቴጂ ውስጥ የተካተተውን በረሃማ አካባቢዎችን የማልማት ፕሮጀክት ለማሳካት ግብርና ሚኒስቴር ትራክተሮችን ከታክስ ውጪ እንዲያስገባ የተፈቀደለት በመሆኑ፣ አሁን ካለው ገበያ ሁኔታ ጋር ተወዳድሮ ለመሸጥ ከባድ እንደሚሆን ግንዛቤ መወሰዱን መረጃው ያመለክታል፡፡

 ይህንን መሠረት በማድረግም ቦርዱ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ የመጀመሪያው የመፍትሔ አቅጣጫ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ትራክተሮችንና መለዋጫዎችን የግብርና ሚኒስቴር በዝቅተኛ ዋጋ ቢገዛ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ማዳን እንደሚቻል ተደራድሮ በማሳመን እንዲሸጡ ማድረግ ለተቋሙ ጥቅም ማስገኘት የሚል ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በክልሎችና በከተሞች የቆሻሻ ማንሳት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ወይም ለመሰል አገልግሎቶች እንዲውሉ በስጦታ መልክ ማበርከት፣ በሕዝብ ዘንድ ያለውን የተቋሙን ገጽታ በመለወጥ ረገድ በገንዘብ የማይገመት ጥቅም እንደሚኖረው በመግለጽ፣ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጡን መረጃው ያመለክታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሜቴክ የያዘው ከ15 ሺሕ በላይ የሰው ኃይል ከፍተኛ መሆኑንና አብዛኛውም አምራች ያልሆነ የሰው ኃይል እንደሆነ፣ ይህ ደግሞ  ትርፋማና በቀጣይ ዕውቀት የሚያሸጋግር፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንት የሚያስፋፋና አገሪቱ በኢንዱስትሪ የበለፀገች እንድትሆን የበኩሉን ሚና እንዲጫወት የተሰጠውን ተልዕኮ እንዳይወጣ የሚያደርገው በመሆኑ፣ እሴት መጨመር የማይችሉትን ማሰናበት እንደሚገባ ቦርዱ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጡን መረጃው ያመለክታል፡፡

ከስድስት ዓመታት በላይ ተከማችተው የከረሙትና ያለ ገበያ ጥናት ከውጭ በገፍ ገብተው የተገጣጠሙት ትራክተሮችና መለዋወጫዎች፣ እንዲሁም ሌሎች የኢንዱስትሪ ማሽነሪዎችና መለዋወጫዎች ወቅታዊ ግምት ዋጋ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን መረጃው ያመለክታል፡፡

መረጃው እንደሚያመለክተው የኮርፖሬሽኑ ተሰብሳቢ ሒሳብ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ነገር ግን የሚሰበሰበውና የማይሰበሰበው ተለይቶ አይታወቅም፡፡ በተጨማሪም እያንዳንዱ ተሰብሳቢም በኮርፖሬሽኑ የሒሳብ መዝገብ ላይ ከመታየቱ ውጪ ከማን ምን እንደሚሰበሰብ የሚያመላክት መረጃ አለመኖሩን፣ ይህም ማለት ኮርፖሬሽኑ ተሰብሳቢ ብሎ ከያዘው ሀብት ውስጥ የማይሰበሰው ሰፊ መሆኑን መረጃው ያስገነዝባል፡፡

የኮርፖሬሽኑን ሀብትና ዕዳ ለማወቅ በ2011 ዓ.ም. ትኩረት ተሰጥቶ የተሠራበትና በተወሰነ ደረጃ ማወቅ የተቻለበት ሁኔታ ቢኖርም፣ እስካሁን አስተማማኝ የሆነ መረጃ ማግኘት አለመቻሉንና ይህም ደግሞ የፋይናንስ አያያዝ ችግሩ ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያመለክት ያስረዳል፡፡

ሜቴክ ሲቋቋም አሥር ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታልና 3.17 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የነበረው ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ጠቅላላ ሀብቱ 53.2 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ካፒታሉ ደግሞ 16.5 ቢሊዮን ብር እንደሆነ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ይሁን እንጂ ቀድሞ በነበረው የተቋሙ የአሠራር ዝርክርነትና ሥርዓትን ያለ መሥራት ምክንያት፣ በአሁኑ ጊዜ 70.3 ቢሊዮን ብር ዕዳ አለበት ተብሏል፡፡

ይህ ዕዳ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ለወሰዳቸው ሥራዎች ቅድመ ክፍያ ወስዶ፣ ነገር ግን ሥራውን ባለመሥራቱ ምክንያት የመጣውን ዕዳ የሚጨምር ነው፡፡ መፍትሔ ካልተቀመጠለት በስተቀር ሜቴክ ወደፊት የማያንቀሳቅሰውና እንደታሰበለት ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ያላቸውን ተግባራት ከመፈጸም የተበላሸ ጉዳይ በመፍታት ላይ እንዲጠመድ የሚያደርገው በመሆኑ፣ መንግሥት ዕዳውን እንዲከልስለት መጠየቁን መረጃው ያስረዳል፡፡

ሰሞኑን ከመንግሥታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክትር ብርጋዴር ጀኔራል አህመድ ሐምዛ፣ መንግሥት ኮርፖሬሽኑ ካለበት ዕዳ ውስጥ 57 ቢሊዮን ብሩን እንዲሰርዝና የተወሰነውን ካፒታል አድርጎ እንዲመዘግብ መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...